ለምለም መንግሥቱ
ይህች ምድር ዜማ ስትጠማ፣ ሙዚቃ ስትራብ በ1940ዎቹ ብቅ ያለ ሙዚቃን እንኳን በዜማ በንግግር ውስጥ የሚቀምር የሚመስል ታላቅ የጥበብ ሰው ድሬደዋ ገንደቆሬ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ተወለደ።
ጎምቱው የጥበብ ሰው ሲነሳ ስለ ድሬዳዋ የማያወሳ የለም። በሙዚቃ ሥራው አላነሳውም የሚባል ነገር ባይኖርም አካባቢውን ዳስሶ አስዳሶናል፤ ፍትህን ናፍቆ አስናፍቆናል፤ ስለ ዕውነት ቆርጦ አስቆርጦናል፤ ውበትን ከወፍ በተቀዳ ዜማ አሞካሽቷል።
ሙዚቃ የተፈጥሮው ልክፍቱ ነውና በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ቋንቋ የተዜሙ ሙዚቃዎችን ሳይመርጥ ያዳምጣል። ያዳመጠውንና ቀልቡ የወደደውን ሙዚቃ ደግሞ መልሶ ለቤተሰቡና ለአብሮ አደግ ጓደኞቹ በመዝፈን ያዝናናቸዋል። ነፍሱ ለሙዚቃ ስሱ፤ ለጥበብ ቀልቧን የሰጠች ናት፤ ለብቻውም ሲሆን ያንጎራጉራል።
በፊት በለጋ ዕድሜው ነው ስለሙዚቃ የጠለቀ ዕውቀት ሳያካብት በሙዚቃ ፍቅር የተያዘው። ኧረ እንዲያውም ማዜም የጀመረው በ14 ዓመት ዕድሜው ነው። የሙዚቃ ጥማቱን ለመወጣትም መሰሎቹን ፈልጎ ዘርፉን የተቀላቀለው ገና በዚሁ የዕድሜው ምዕራፍ የመጀመሪያው ክፍል ነው።
በወቅቱም የኦሮምኛን የሙዚቃ ሥራ በዘመናዊ የአዘፋፈን ስልት ለማስተዋወቅ ዓላማ አድርጎ በተቋቋመው ‹‹አፍረን ቀሎ›› የተባለ የወጣቶች የሙዚቃ ቡድንን ተቀላቀለ። ጉዞው በዚህ አላበቃም ከትውልድ ቀዬው ድሬዳዋ ወደ አዲስ አበባ ከተማ መጥቶ ክቡር ዘበኛ ተብሎ በሚጠራው የሙዚቃ ቡድን ተቀላቅሎ በዚያ ጊዜ የመጀመሪያ ሥራውን በሸክላ አሳተመ።
ቀጥሎም ከክቡር ዘበኛ ለቅቆ በወቅቱ ዝነኛ ከነበሩት አይቤክስና ኢትዮ ስታር ባንዶች ጋር ተጫውቷል።
ይህ ሰው ታላቁ የጥበብ አባት የክቡር ዶክተር ዓሊ ቢራ መሆኑን አታጡትምና ነው ሥሙን ሳናነሳ ወደ ሕይወት ታሪኩ የተንደረደርነው። በኢትዮጵያ በዘመኑ ታላላቅ ባንዶች ጋር ሲሠራ የቆየው ዓሊ በ1980ዎቹ ወደ ባህር ማዶ የመሰደድ ዕጣም ገጥሞት ነበር፤ ሆኖም ከዓመታት ቆይታ በኋላ ዛሬ እትብቱ በተቀበረበት ኢትዮጵያ ኑሮውን አድርጓል።
ይህ የጥበብ ሰው እትብቱ ከተቀበረባት ድሬዳዋ ተነስቶ አዲስ አበባ ባሉ ባንዶች አቀንቅኖ በውጭ ሀገር ቆይቶ እስኪመለስ ከሙዚቃ ሥራ አልተለየም። በሙዚቃ የሕይወት መንገድ ውስጥ የአንድ አዛውንት ዕድሜ አስቆጥሯል፤ ለስድስት አሥርተ ዓመታት።
አሁንም እንኳን በሽምግልና ዕድሜው ሆኖ በቅርቡ ከተለያዩ የዚህ ዘመንና የቀደመው ዘመን አንጋፋና ወጣት ሥመጥር ሙዚቀኞች ጋር የተለያዩ ዜማዎችን አዚሟል። ከማሕሙድ አሕመድ፣ ጎሳዬ ተስፋዬ፣ አብርሐም በላይነህ፣ ሄለን በረሔ፣ ሙክታር አደም እና በርካታ ሙዚቀኞች ጋር በመዝፈን በዘመናችን የሙዚቃ መወደድ በሚለካበት ዩቲዩብ ዕይታ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ተመልካች ያገኘ ሥራን ሠርቷል።
ሌሎች በርካታ የሙዚቃ ተጫዋቾችም የሱን ሥራ አፍ መፍቻቸው አድርገው ተጫውተዋል። ይህ የጥበብ ሰው ለተለያዩ አንጋፋ ድምፃውያን ዜማ ቀምሮ በመስጠትም ይታወቃል።
ዓሊ ቢራ በሙያው ለሀገሩ ላበረከተው አስተዋፅዖ በቅርቡ ከሐሮማያ ዩኒቨርስቲ የክብር ዶክትሬት ተበርክቶለታል። ስለዚህ ታላቅ ባለታሪክ በዘመናዊ የሙዚቃ ሥራው ዕውቅናንና ተወዳጅነትን ያተረፈው ክቡር ዶክተር አርቲስት ዓሊ ቢራ በተለያየ ጊዜ በመገናኛ ብዙሃን እንደተዘገበውና ምሥክርነት እንደተሰጠው ዓሊ ከሙዚቃ ሥራው ባለፈ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ነው።
እርሱም በአንድ ወቅት ተጠይቆ ‹‹እራሴን የምፈርጀው የሀቅ ታጋይ ብዬ ነው›› ብሏል። በቻለው ሁሉ በሙዚቃ ሥራው ጭቆናን በመቃወም፣ ስለሰዎች እኩልነት መልዕክት በማስተላለፍ መልካም ስብዕና ያለው የሙዚቃ ባለሙያ ነው። ተተኪ ለማፍራት አቅም ያላቸው በርካታ የሙዚቃ ሥራዎችን አበርክቷል።
አርቲስት ዓሊ ቢራ በአፋን ኦሮሞ ዘመናዊ የሙዚቃ ሥራው በእጅጉ ይታወቅ እንጂ በበርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ቋንቋዎች ሙዚቃዎችን ተጫውቷል። አማርኛ፣ ሶማሊኛ፣ አረብኛና ጨምሮ በተለያዩ ሰባት ቋንቋዎች በተወዳጅ ድምጹ ከጉሮሮው በሚቃኝ ተስረቅራቂ ድምፁ አቀንቅኗል።
በሀገራችን ዕንቁ ለሆኑ ድምጻውያን የዘፈን ግጥም በመስጠት የሙያ አጋርነቱን አስመስክሯል። በአማርኛ ሙዚቃ ከሚጫወቱ ጋርም አብሮ በመጫወት ሁለገብ ባለሙያ ነው።
ዓሊ ቢራ የሚለው መጠሪያ ሥሙን ያገኘው በሙዚቃ ሥራው እንጂ እናት አባቱ ያወጡለት አይደለም። ‹‹አፍረን ቀሎ›› የወጣቶች የሙዚቃ ቡድንን ሲቀላቀል ሞክሼዎች ስለነበሩ አንዱን ከሌላው ለመለየት ሲባል ዓሊ ቢራ ‹‹ብራን በርኤ›› በሚለው የሙዚቃ ሥራው እንደተጠራና ሥሙ ሆኖም እንደፀደቀ ይነገራል።
ስለ ዓሊ ቢራ ‹‹አባይን በጭልፋ›› እንደሚባለው ከብዙ በጥቂቱ ለማንሳት የወደድነው የኦሮሚያ ክልል ያዘጋጀለትን የምሥጋና እና የዕውቅና ፕሮግራም እንዲሁም ግለታሪኩን የያዘውን የመጽሐፍ ምረቃ ምክንያት በማድረግ ነው።
ክልሉ በተለያየ ዝግጅት ሲያስበው እኛም ልናወድሰው ወደናል። ለመሆኑ ዓሊ ቢራን በተለያየ አጋጣሚ የሚያውቁትና በሙዚቃ ሙያ ውስጥ የሚገኙት ስለእርሱ ምን ይላሉ?
ለ47 ዓመት ዓሊ ቢራን የሚያውቁትና ስለሙዚቃም ብዙ ዕውቀት ከእርሱ መቅሰማቸውንና ሙዚቃንም እንዲወዱ ምክንያት እንደሆናቸው የነገሩኝ በኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት የባህልና የሚዲያ ጉዳዮች አማካሪ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ መሐመድ አህመድ ናቸው።
‹‹አርቲስትና ጋዜጠኛ ነኝ። በልጅነት ያለኝን ተሰጥኦ እንዳሳድግ የረዳኝ መምህሬ ዓሊ ቢራ ነው፤ አሊ ሸቦም ጭምር። ሁለቱ የማይነጣጠሉ በመሆናቸው ነው የማነሳቸው።
በአጠቃላይ ስለግጥም አጻጻፍና ዜማ ማውጣት ከእርሱ ነው የተማርኩት። አሊ ቢራ ከፍተኛ ችሎታ አለው። ከእርሱ ጋር መኖር ትምህርት ቤት እንደመኖር ነው። በሙዚቀኛ ብቻ ሳይሆን ኮሜዲያንም ነው፤ ያዝናናል።›› በማለት ዓሊ ቢራ የሙዚቃው ንጉሥ እንደሆነ በአድናቆት ይገልጻሉ።
ከአቶ መሐመድ ጋር ደስታን ብቻም ሳይሆን ችግርንም አብረው አሳልፈዋል። በአንድ ወቅት ደረቅ እንጀራ አጥተው ማባያውን ወጥ ለረሀብ ማስታገሻ እንደተጠቀሙ ያስታውሳሉ። ሰው ችግርን ሳያልፍ ትልቅ ቦታ እንደማይደርስም ከእርሱ ተምረዋል። በሙዚቃ ሥራው ዛሬ ክብር ያገኘው ብዙ ፈተናዎችን አልፎ እንደሆነ ይናገራሉ።
እርሳቸው እንዳሉት ዓሊ በተለያየ ጊዜ ታስሯል። በዘመኑ ፖለቲካው ያን ያህል አልነበረም። ግን በኦሮምኛ መዝፈን እንደወንጀል ይታይ ስለነበር እርሱ በቋንቋው መዝፈኑ ባለመወደዱ ነው የታሰረው። በተለይም ለሙዚቃ ሥራ ወደ ጅቡቲ ሄዶ በነበረበት ወቅት ያለፈቃድ ሄዷል ተብሎ ለስድስት ወር ታስሯል።
ከእስር ቢለቀቅም ለአንድ ዓመት ከድሬዳዋ እንዳይወጣ በየቀኑ ፖሊስ ጣቢያ እየሄደ መኖሩን በፊርማ እንዲያረጋግጥ ተደርጎ ግዞተኛ ሆኗል። የልጃቸው ስቃይ አዕምሮአቸውን ዕረፍት የነሳቸው አባቱ የሚለብሰው አንድ ብርድ ልብስና 20 ብር አስይዘው ወደ አዲስ አበባ ይልኩታል።
ዓሊ ቢራ የደረሰበት ችግር ከሙዚቃ ሥራው ወደ ኋላ አላስቀረውም። በወቅቱ ታዋቂ ከሆኑ ጥላሁን ገሠሠና ከሌሎችም ጋር በክቡር ዘበኛ የሙዚቃ ቡድን ውስጥ ተቀላቅሎ ሥራውን ቀጠለ።
‹‹የኔነሽ እያልኩ አድርጌሽ የግሌ ነው ከልብሽ ከሌላ…›› የሚለውን የዘፍን ግጥም ለአርቲስት ጥላሁን ገሠሠ፤ ‹‹ትዝ ትዝ እያለኝ…›› የሚለውን የዘፈን ግጥም ደግሞ ለአርቲስት መሐሙድ አሕመድ መስጠቱን ከራሱ አልፎ ለሙያ አጋሮቹም በማበርከት እራሱን ለሙያው የሰጠ እንደሆነ የተከበሩ አቶ መሐመድ ተናግረዋል።
ጋሼ ዓሊ ብሎ የሙያ አባቱን በአክብሮት በመጥራት ሀሳቡን ያካፈለን የመልቲ ሚዲያ ሥራ አስኪያጅ አርቲስት ኃይሌ ሩት ‹‹ኢትዮጵያዊ እና የዘመናዊ ሙዚቃ መጀመሪያ ነው። ቋንቋን ለማያውቀው እንኳን በሙዚቃው ሀሴት እንዲያደርግ ጉልበት ያለው ሙዚቃ በማቅረብ የሚታወቅ የሀገራችን መለያ ነው ብዬ የማደንቀው የሙዚቃ ሰው ነው። ለእኔ በሙዚቃ ሥራው ሁላችንንም ያሸነፈ ሰው ነው።›› በማለት አክብሮቱን ገልጾለታል።
በአሜሪካን ሀገር ሚኒሶታ የተመቻቸ የሙዚቃ መድረክ ላይ አብሮ የሙዚቃ ሥራ ለማቅረብ ዕድሉን አግኝቶ በተለያየ ምክንያት ዝግጅቱ ባይሳካም በወቅቱ ከእርሱ ጋር መድረክ ላይ ለመውጣት ዕድሉን ማግኘቱ አስደስቶታል።
የዘፈን ግጥም በማዘጋጀትና በማቀናበር፣ በሙዚቃ መሳሪያዎች በመጫወት በአጠቃላይ ሙዚቃን ያሟላ በመሆኑ በግሌ ትምህርት አግኝቼበታለሁ የሚለው አርቲስት ኃይሌ አርቲስቱ የሚገባውን ያህል ክብር አግኝቷል ብሎ አያምንም። ዓሊ ቢራ ለሀገር ካበረከተው አስተዋጽኦ አንጻር ትልቅ ነገር ሊደረግለት ይገባል ሲል ይናገራል። በሕይወት እያለ ግለታሪኩ መጻፉና ምሥጋናም መዘጋጀቱን አድንቋል ።
የዓሊን ግለታሪክ የጻፉት ዶክተር ሱራፌል ገልገሎ እንደገለጹት የመጽሐፉ ዋና ዓላማ ታማኝ ባለሙያ ሆኖ በሥራው ውስጥ ለቆየ፤ በሙዚቃው ከማዝናናት ባለፈ ሕዝቦችን በማንቃት፤ በአርቱ ውስጥ የሀገርና ያለፉ መሪዎችን ማሳየት የሚችል ሆኖ የተገኘን ትልቅ የሀገር ኩራት፤ ለትውልድ ለማሸጋገርና ክብር ለሚገባው ክብር ለመስጠት ነው።
መጽሐፉን ለየት የሚያደርገው አርቲስት ዓሊ እኔ ብሎ የሚገልጸውን ብቻ የያዘ ሳይሆን ስለእርሱ ያለውን ዕውነታ የፈተሸና ለማስተማር አቅም እንዲኖረው ተደርጎ የተሰነደ ነው። በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች መዘጋጀቱም በተደራሽነቱ ለየት ያደርገዋል።
ሁሉንም የሚገድበው ዕድሜ ላይ በመሆኑ ክቡር ዶክተር ዓሊ ቢራን ከዚህ በኋላ በሥፋት በመድረክ ልናገኘው የምንችልበት አጋጣሚ ጠባብ ነው። ነገር ግን ግለታሪኩን የያዘ መጽሐፍ መኖሩ ሁሌም ሲታወስ መኖር እንዲችል ያደርጋል።
ክቡር ዶክተር አርቲስት ዓሊ ቢራ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ የነበረው የጥበብ ጉዞ አልጋ በአልጋ አልነበረም። እንዲያውም በፅናት የደረሰበትን ሁሉ ተጋፍጦ በማለፍ ለትውልዶች ሁሉ ተምሳሌት መሆን የቻለ የጥበብ ሰው ነው።
ዓሊ በአርቱ ዙሪያ ያሉ ሰዎች ከሙያ ተምሣሌትነቱና ፅናቱ ከሚወስዱት ትምህርት ባሻገር የሀገሩ ልጆችና በዓለም ላይ ያሉ የጥበብ አድናቂዎች ሲያወድሱት የሚኖሩ ታላቅ ጀግና ነው።
አርቲስቱ በሀገራችን የአንድነት ትዕምርት ለመሆን ከተለያዬ ብሄር ተወላጅ አርቲስቶች ጋር ከመዝፈኑም ባሻገር ጥበብ ሰዎች ከሚሠሩት መከፋፈያ ድንበር ባሻገር ታደርሳለችና ከሀገሩ ውጪ ባሉ ቋንቋዎችም ሙዚቃዎችን አቀንቅኗል።
ዓሊ ቢራ የጎሳ ቋንቋ የማይገድበው፤ የክልል ወሰንን ከመጤፍ የማይቆጥር ጥበብን ከእስትንፋሱ ያልነጠለ የዘመን ጥበብ ትዕምርት ነው። ከሙያው ባለፈ ለሃቅ እና ለሰብዓዊ መብት መከበር ተሟጋች የሆነ ዕንቁ ባለሙያ ነው።
አዲስ ዘመን ጥር 30/2013