ወንድወሰን ሽመልስ
* እንደ መግቢያ
ሰው የአስተሳሰቡ ውጤት ነው፤ አስተሳሰቡ የቀጣይ እርምጃና መዳረሻውን ይወስንለታል። ይህ ግማሽ ውሃ ሞልቶ የተቀመጠን አንድ ብርጭቆ በምንገልጽበትን እይታ ይመሰላል። ዋናው ጉዳይ የብርጭቆው ውሃ ሙላቱ ወይም ጉድለቱ መነገሩ ሳይሆን፤ “አለ” እና “የለም” የሚሉ እሳቤዎችን በውስጣችን ማኖሩ ነው።
ምክንያቱም አለን ብለን ስናስብ እና የለንም ብለን ስናስብ ስለ ነጋችን የሚኖረን ምልከታ፣ ያሰብነውን ለማሳካት ስለሚጠይቀን ጉልበትና ሀብት በአግባቡ አስበን በመስራት ላይ የሚያሳድርብን ተጽዕኖ ይኖረዋል። ይህ በግለሰብ፣ በቤተሰብ፣ በማህበረሰብ፣ በህዝብ ወይም በአገር ደረጃ ሊገለጽ ይችላል።
በኢትዮጵያም ሲሆን የቆየውና አሁን እየሆነ ያለው ይሄው ነው። በአንድ በኩል ያለንን አቅምና ሀብት ሳይገነዘቡ በትልቁ በማሰብ ከአንዱም ሳይሆኑ መሃል ላይ ሲንገታገቱ ጊዜን ማሳለፍ፤ በሌላ በኩል ጉድለቱን እያሰቡ ሳይጀምሩት ታክቶ መተው ለዘመናት አብረውን ቆይተዋል። ከዚህ ሁሉ በኋላ ግን በኢትዮጵያ ብቅ ያለው የለውጥ አስተሳሰብ፤ ሙላትንም ጉድለትንም በእኩል ተገንዝቦ ሙላቱን ይዞ ጉድለቱን መሙላት ላይ ማተኮር ነው።
ለዚህ ደግሞ መንገድ በአንድ እርምጃ እንደሚጀመር ሁሉ፤ ጉድለትን የመሙላት ስራዎችን ከትንሽ ወደ ትልቅ የሚጓዙ ናቸው። ኢትዮጵያን መለወጥና ማበልጸግ፤ ቤትን፣ አከባቢንና ከተማን ከመለወጥና ከማበልጽ የሚጀምር መሆኑን በመገንዘብም ከሀሳብ እስከ ተግባር የተሰናሰነ እንቅስቃሴ ተጀመረ። መኖራቸው ሳይታወቅ ባክነው የነበሩ ሀብቶችን በመመልከት የማልማት ስራውም በቤተ መንግስት ተጀምሮ፣ በሸገር የተደገመው ተግባር ወደ አገር እንዲያድግ ሆነ።
በ“ገበታ ለሸገር” ከተተገበሩት የአንድነት፣ የወዳጅነት እና እንጦጦ ፓርኮች መገባደድ ማግስትም፤ የፕሮጀክቶቹን ሥኬታማ ተሞክሮ በአገር ደረጃ ለማሳደግ እሳቤው ወደ “ገበታ ለሀገር” ተሸጋገረ። የገበታ ለሀገር ዓላማ ደግሞ የተለያየ ባለድርሻዎች እውቀታቸውን፣ ገንዘብቻውን እና ጉልበታቸውን አዋጥተው ከአዲስ አበባ ባሻገር በክልል ከተሞች የቱሪስት መስህብ የሚሆን፤ የስራ እድል የሚፈጥር፣ የህብረተሰቡን የኑሮ ዘይቤ የሚያዘምንና የሚያሻሽል አዳዲስ ስራዎችን ተፈጥሮን ሳያዛቡና ሳይረብሹ መስራት ነው።
በዚህ ረገድ በየክልሉ የተመረጡ በርካታ ቦታዎች ቢኖሩም፤ እንደ ቀደመው ሁሉን ጀምሮ ሁሉን ሳይጨርሱ ላለመተው ሲባል ካለው ውስጥ ሀብትና የማድረግ አቅምን ባገናዘበ መልኩ ሶስት ፕሮጀክቶች ተለይተው እንዲተገበሩ አቅጣጫ ተቀምጧል። በዚህም መሰረት ጎርጎራ፣ ወንጪ እና ኮይሻ ተመርጠዋል።
* ጎርጎራ
ታላቁን የጣና ሐይቅ ተንተርሶ የሚገኘው የጎርጎራ ፕሮጀክት፤ የታሪክ፣ ባህል፣ እምነትና ተፈጥሮ ከብዙ በጥቂቱ ተጣምረው የተከሰቱበት ድንቅ ከባቢ ነው። ጎርጎራ ጥንታዊቷ ደብረሲና ገዳምን ጨምሮ በርካታ ሃይማኖታዊና ታሪካዊ መዳረሻዎች በዙሪያዋ ይገኛሉ። በጎርጎራና አከባቢዋ በሚገኙ ቀደምት ገዳማት እና አብያተ ክርስቲያናት በተለያዩ ጊዜያት የስልጣንን በትር የጨበጡ የነገስታትን አጽም፤ በርካታ ቁሳቁሶችና ውድ የታሪክ ቅርሶችን በጉያዋ ይዛለች።
በተራራማና ሜዳማ መልከዓ ምድር የታጀበችው እና የበርካታ ብዝሃ ህይወት ባለቤት የሆነውን ጣና ሐይቅ በበረከትነት የታደለችው ጎርጎራ፤ በዙሪያዋ የሚገኙ ደሴቶችም የምስጢራት መገለጫ ሆነው እልፍ ዘመን ኖረዋል። ይህ ገጽታዋ ደግሞ ለበርካታ የኢንቨስትመንት አማራጮች ምቹ ያደርጋታል። ለሆቴልና ቱሪዝም፣ ለዓሳ ሃብት፣ ለመዝናኛና መሰል ዘርፎች ምቹ የሚያደርጋት መልከዓ ምድር ባለቤትም ናት።
ይህ ሥፍራ ምንም እንኳን ታሪክና ባህል፤ እምነትና ተፈጥሮን ለዘመናት አስተሳስሮ የያዘ፤ የዘመናዊነትና ሥልጣኔ ማዕከልነቱ የገዘፈ ሥፍራ ቢሆንም፤ በዘመነ ኢህአዴግ ጎርጎራ ጎርጎራነቱ እንዲዘነጋ፤ የነበረው እንዳልነበረ እንዲታይ ተደርጎ የታሪክ አሻራዋን አጉልተው የሚያሳዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ርቀዋት ቆይተዋል።
አሁን ግን ጎርጎራ ዳግም በታሪክ ምዕራፍ ራሷን ልታድስ በገበታ ለሀገር ታቅፋ ፀጋዋን ልታጎላ እየተሰናዳች ናት። ታዲያ ታሪካዊቷ ጎርጎራ ገና ከጅምሩ የብዙዎችን ቀልብ መሳብ ችላለች፤ ሳትሞሸር ገና በመሰናዳቷ ምዕራፍም 120 ባለሀብቶች በጎርጎራ ከተማ በተለያየ የልማት ዘርፍ ለመሰማራት የፕሮጀክት ንድፈ ሀሳብ ማስገባታቸው ተሰምቷል። እናም ጎርጎሯ ፀጋዎቿን ልትጠቀም፤ አከባቢውንም አገርንም ልትጠቅም ጉዞ ጀምራለች።
* ወንጪ
የወንጪ ፕሮጀክት በምዕራብ እና በደቡብ ምዕራብ ሸዋ መካከል የሚገኝና በሳተ ገሞራ የተፈጠሩትን የወንጪ እና ደንዲ ሐይቆች አጣምሮ የያዘ ነው። ወንጪ ሲነሳ ቀድሞ የሚጠቀሰው የወንጪ ሐይቅ ከአዲስ አበባ ከ150 ባለበለጠ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በደቡብም ምዕራብ ሸዋ ዞን ውስጥ ያለ ሲሆን፤ ከባህር ጠለል በላይ እስከ 3ሺ350 ሜትር ከፍታ ላይ በደን እና በተራሮች ተከብቦ የሚገኝ ቦታ ነው።
ሐይቁ በውስጡ ታሪክ የሚናገሩና ዘመን ያስቆጠሩ ሶስት ደሴቶች እና ገዳማት አሉት። ካርበን የተባለ ማዕድን የያዘ የምንጭ ውሃ፤ እንዲሁም ፈዋሽነቱ የሚነገርለት ተፈጥሯዊ ፋፋቴ በአከባቢው የሚገኙ ሀብቶች ናቸው። የወንጪ ሐይቅ ከውብ ተፈጥሯዊ ገጽታው ባለፈ፤ በዓሳ ሀብቱ እና በማር ምርቱም ለአከባቢው የኢኮቱሪዝም የጎላ ድርሻ ያለው ነው።
ይሁን እንጂ ይህ ሥፍራለአገር ቀርቶ ለአከባቢው ይህ ነው የሚባል ጥቅም ሳይሰጥ ዘመናትን አሳልፏል። ዛሬ ላይ ግን ይህ ስፍራ ለአከባቢው ቀርቶ ለአገር የሚተርፍ ስፍራ መሆኑን የተረዱ፤ ሥፍራውን ለማልማት፣ የቱሪዝምም የኢኮኖሚም ማዕከል ለማድረግ ውጥን ይዘዋል። ውጥኑም ሊተገበር ጉዞ ተጀምሯል።
* ኮይሻ
የጨበራ ጩርጪራ ብሔራቢ ፓርክን በውስጡ አካትቶ የያዘው ይህ ፕሮጀክት፤ ባህልና ተፈጥሯዊ ውበትን አጣምሮ የያዘ ድንቅ አከባቢ ነው። ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ወደ አከባቢው ተጉዘው ከኮንታ እና አከባቢው ህዝብ ጋር ውይይት ባደረጉበት አንድ ወቅት “ኮንታ በጣም የሚያስደንቅ፤ እንደዚህ አይነት ምድር ኢትዮጵያ አላት ወይ? እንድንል እና በአገራችን እንድንኮራ፤ በአገራችን ተስፋ እንድናደርግ፤… የሚደንቅ የፈጣሪ ሥራ የታየበት፤…” ሲሉ ስለአከባቢው ድንቅ የተፈጥሮ ችሮታ ገልጸው ነበር።
ይህ ሥፍራ ጅማ፣ ከፋ፣ ዳውሮ፣ ኮንታን በጥቅሉ ደቡብ ምዕራብ የኢትዮጵያ አከባቢዎችን ፀጋዎች አስተሳስሮ የያዘ ሲሆን፤ ከአዲስ አበባ ወደ ስፍራው ለማቅናት የፈለገም አንድም በሶዶ፣ አልያም በጅማ በኩል ጉዞውን ማሳለጥ ይችላል። የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክን ሞገስ አድርጎ የሚገለጸው ኮይሻ፤ ጥንታዊው የሃላላ ኬላ፣ ጊቤ ሶስት ሰው ሰራሽ ሃይቅ፣ የኮይሻ ሃይድሮ ፓወር ከአከባቢው ፀጋዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
ከከፍተኛ እስከ ዝቅተኛ የመልከዓ ምድር አቀማመጥ፤ ከቆላ እስከ ደጋ የዓይር ፀባይ የሚንጸባረቅበት እና በዚሁ ሊኖሩ የሚችሉ ብዝሃ ህይቶች የያዘው ይህ ከባቢ፤ ወደ 58 አጥቢ እንስሳት፣ 137 ያህል አዕዋፍት፣ ብርቅዬ ዓሣዎችና ድንቅ ተፈጥሯዊ አቀማመጥ ያለው መልከዓ ምድር ባለቤትም ነው።
እናም ይሄን ድንቅ የተፈጥሮ ስጦታ ትንሽ ነገር ጨምሮ ለሰዎች የላቀ የተዝናኖትና ሀሴት ምንጭ ማድረግ እንደሚቻል በመገንዘብም፤ ይሄንኑ እውን ለማድረግ የሚያስችል አገራዊ ፕሮጀክቶች ተነድፈው ወደተግባር ለመግባት ከተዘጋጁ ሶስት ፕሮጀክቶች መካከል የዚሁ አከባቢ በረከት የሆነውን ኮይሻ አንዱ ሆነ።
* ከሀሳብ እስከ ተግባር
እአአ በ2050 ኢትዮጵያ በወታደራዊም ሆነ በኢኮኖሚ አቅሟ በአፍሪካ ውስጥ ካሉ ሁለት ኃያላን አገራት አንዷ መሆን አለባት የሚል ትልም ተይዟል። ይህ ትልም ወደ ተጨባጭ እውነት ሊለወጥ የሚችልበት እድል ደግሞ በእጅጉ ከፍ ያለ፤ በሰው ሃብቱም፣ በፋይናንሱም፣ በእውቀቱም፣ በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያ በታደለቻቸው የተፈጥሮ ፀጋዎቿ ሊመዘን የሚችልም ነው።
ይሄን ታሳቢ በማድረግም ነው በ30 ዓመታት ውስጥ በአፍሪካ ካሉ ሁለት ኃያላን ብቻ ሳይሆን፤ በዓለም ደረጃ ካሉ 20 ኃያላን አገራት መካከል (ምናልባትም ከሃያ ባነሰ) አንዷ ማድረግ እንችላለን የሚል ነው ትልም ተይዞ ዜጎችን ባሳተፈ መልኩ እየተሰራ ያለው።
ይሁን እንጂ ይሄን የማሳካት እና የአገር ብልጽግናን የማረጋገጥ ጉዞው አሻራ ማስቀመጥን እንጂ አቧራ ማስነሳትን አይሻም። አሻራ ደግሞ አጥብቆ መያዝን፤ ተግቶ መስራትን፤ በአስተውሎትና በጥንቃቄ መራመድን ይጠይቃል። አሻራ እንደ አቧራ የሆነ ነገርን አራግቦ አከባቢን አውኮ ማለፍ አይደለም፤ ይልቁንም በቻሉት አቅም ተግቶ በመስራት በቀላሉ የማይፋቅና የሚታይ ነገርን አስቀምጦ ማለፍን ይጠይቃል።
በዚህ ረገድ እነዚህ ፕሮጀክቶች በሰው ልጅ ልብና አዕምሮ ተጠንስሰው፣ በወረቀት ላይ ጎልብተው በመሬት ላይ ሊተገበሩ ተወልደው የሚያድጉ ናቸው። በአንድ ወይም በሁለት ሰው አእምሮ የተጸነሰ ሀሳብ ከሀሳብ አልፎ ፍሬ እንዲያፈራ በብዞዎች ክንድ መሰረት ሊይዝ ይገባል።
በዚህ ረገድ የሸገር ፕሮጀክቶች ትልቁን አብነት ይዘው ዘልቀዋል። አሁንም የገበታ ለአገር ስር በተያዙ ሶስት ፕሮጀክቶች የሚታይ አፈጻጸም፣ የሚፈጠር ልምድና አቅም ደግሞ፤ በቀጣይ ተጨማሪ መሰል ፕሮጀክቶችን እውን ለማድረግ የሚያግዝ ይሆናል።
ይህ ሲሆን ስፍራዎቹን ማዘመን ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ የሚሰራ ሰውም የሚሰራ ሥራም መፍጠር ይቻላል። ለዚህ ደግሞ እነዚህን ሶስት ፕሮጀክቶች መጀመር ብቻ ሳይሆን ፍጻሜያቸውን ለማሳደግ ሀሳብ ያለቸው ሀሳብ እንዲያመነጩ፤ ገንዘብ ያላቸው ገንዘብ እንዲያዋጡ፤ ጉልበት ያላቸውም በጉልበታቸው እንዲያግዙ የሚያስችል አቅጣጫ ተቀምጧል።
የየትኛውም አገር ልምድ እንደሚያሳየውም ዜጎች ያልተሳተፉበት እድገት አልመጣም፤ ኢትዮጵያን ለማዘመን፣ ለማበልጸግና ከድህነት አረንቋ ለማውጣት የሚደረገው ጥረትም እንዲሁ ዜጎቿን በሙላት ያሳተፈ ሊሆን ይገባልና ነው። ምክንያቱም በተለመደው አሰራርና በመንግስት በጀት ብቻ ኢትዮጵያን ማሳደግም፤ መለወጥም፤ ማበልጸግም አይቻልም።
የሁሉንም ተሳትፎ ለሚጠይቀው ገበታ ለአገር ፕሮጀክቶችም የ10 ሚሊዬን ብር የቪ.ቪ.አይ.ፒ እንዲሁም የ5 ሚሊዬን ብር የቪ.አይ.ፒ እራት ያለው ሲሆን፤ ይሄም በኢትዮጵያ ብልጽግና ጉዞ ውስጥ የራሱን አሻራ ማበርከት የሚሻ ግለሰብ፣ ቤተሰብ ወይም ድርጅት የበኩሉን እንዲያበረክት የሚያስችለው ነው።
አስርና አምስት ሚሊዬን ብር ማውጣት ለማይችሉ፤ ነገር ግን በኢትዮጵያ ብልጽግና ውስጥ የድርሻቸውን ለማበርክት ለሚፈልጉ ዜጎችም በአጭር የጽሑፍ መልዕክት አምስትና አስር ብር የሚያበረክቱበት እድልም ተፈጥሮላቸዋል። የዳያስፖራው ማህበረሰብም የባንክ አካውንት ተከፍቶ የሚችሉትን እንዲያበረክቱ እየተደረገ ሲሆን፤ የሀሳብ፣ የሙያ እና የጉልበት ድጋፎች እንዲደረጉም በየፈርጁ እድል ተፈጥሯል።
ምክንያቱም ኢትዮጵያን ከፍ የማድረግ ጉዞው፤ ተደማሪ ገንዘብ፣ ተደማሪ ሀሳብ፣ ተደማሪ ጉልበትና ጊዜ የሚፈልግ፤ ይሄንኑ ማድረግ የሚሻ ነው። የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ ለማፋጠን፤ የከፍታዋን ጉዞ በአጠረ ጊዜ ለማሳካት የሚሻ ማንኛውም ዜጋ እና ወዳጅ በዚህ ላይ ተሳታፊ ሊሆን ያስፈልጋል። ይህ ሲሆን የሚታይም የሚጨበጥም ውጤት ማምጣት ስለሚቻል ኢትዮጵያ ትበለጽጋለች፤ ወደሚገባት ከፍታም ትወጣለች።
* እንደ መውጫ
በኢትዮጵያ ተፈጥሮ ያደላት አገር እንደመሆኗ ትንሽ ተሰርቶባቸው ከፍ ብለው አገርና ህዝብንም ከፍ የሚያደርጉ በርካታ ሀብቶች አሏት። እነዚህን ሀብቶች ለማልማት ደግሞ በአንድ ጊዜ መጀመረም ይቻል ይሆናል። ይህ ግን ጀመርን የሚል አቧራ ከማስነሳት ባለፈ፤ የመጨረስ አቅምን ማሳየትና አሻራን ለማስቀመጥ የሚያበቃ አይሆንም። ምክንያቱም ምንም እንኳን ሊሰራ የሚችል ነገር ቢኖርም፤ መስራት የሚያስችል አቅም እና ይሄን መምራት የሚያስችል ብቃት ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ መግባቱ አይቀሬ ነው።
ዋናው ነገር ሁሉንም ጀምሮ ሁሉንም ሳያሳኩ ከመቅረት፤ ያለውን ሀብት ለይቶ፣ የማድረግ አቅምን ተገንዝቦ መስራትና መፈጸም በሚቻለን ልክ እየሰራን ልንጓዝ፤ ሥራውንም በጋራ ለጋራ ብልጽግናችን ልናከናውን፤ ማድረግ እችላለሁ ከሚል የአፍ ዲስኩር ወጥተን የሚታይና የሚጨበጥ ውጤት ልናሳይ ይጠበቅብናል።
የገበታው ፋይዳም ይሄው ነው። ምክንያቱም ገበታ የሞላ ነገር ነው፤ በሙላቱም ሰዎች በልተው ይጠግባሉ። ገበታው ሙላትም ሆነ የሰዎች ከገበታው በልቶ መጥገብ ግን እንደመጨረሻው አምሮ ተበጅቶ የተገኘ አይደለም። ይልቁንም ገበታው ሙሉ እንዲሆን ከማሳ እስከ ማጀት ባሉ የሥራ መስኮች አያሌ ውጣ ውረዶች ታልፈውበታል፤ የሰዎች ብቻ ሳይሆን የበሬ እና የገበሬ ጥምረትም ተፈጥሮበታል። እርፍና ሞፈር ተዋድደው መሬት ምሰውበታል፤ አያሌ የትብብርና ቅንጅት ጥምረቶች ተፈትነው፣ የፈጠራ ጥበቦች ተቀምረው ያገዘፉት ነው – ገበታ።
እናም እነዚህ ፕሮጀክቶች “ገበታ ለሀገር” በሚል የንቅናቄ አውድ ሲፈጠርላቸው እራት ጋብዞ ገንዘብ ለመሰብሰብ ብቻ አይደለም። ይልቁንም ቅንጅቱ፣ ተዋህዶ መስራቱ፣ ጥበብና ብልሃቱ፣ መውጣትና መውረዱ፣ ወድቆ መነሳቱ፣ ለስራው ተሰጥቶ በመትጋት ኃላፊነትን መወጣቱ አስፈላጊ መሆኑን ለማጠየቅ ነው።
እናም ገበታው ለፍሬ እንዲበቃ ሁላችንም አሻራችንን በቦታውና በጊዜው ልናኖር ይጠበቅብናል። ይሄን ካላደረግን እና በኢትዮጵያችን ብልጽግናን ማረጋገጥ ካልቻልን፤ እንደ ትናንቱ አንዳችን የአንዳችን ብቻ ሳይሆን ለዓለም ሸክም መሆናቸን አይቀርም። ስለዚህ ከ100 ሚሊዬን የላቁ ጭንቅላቶች የሌላው ሸክም የሚሆኑ ሳይሆን ከራሳቸው አልፈው ለሌላው የሚተርፍ የብልጽግናን መንገድ መጥረግ የሚችሉ መሆን አለባቸው።
ለትልቁ ስኬት ትልቅ ሀሳብ መያዝ፤ በሀሳቡ ልክም ተልቆ መገኘት ከሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚጠበቅ ኃላፊነትም፤ ግዴታም ነው። ትልቅነት ደግሞ በቁጥር ብቻ ሳይሆን፤ በሀሳብም፣ በተግባርም ሊሆን፤ በቡድን ጉዞ አቧራን የማንሳት ሳይሆን በደንብ ረግጦ አሻራን ለማኖር ይሁን። ቸር ሰንብቱ፤ ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ፤ ይጠብቅም!!!
አዲስ ዘመን ጥር 30/2013