አሊሴሮ
ስጥ። ስትሰጥ ይሰጥሃል። በተለይም ለሀገርህ፤ ለወገንህ የምትሰጠው መልሶ ይከፍልሃል። ልክ እንደሀገር መከላከያ ሰራዊት ሕይወትህን ጭምር ለሀገርህ ስጥ። መከላከያ ሰራዊት ሕይወቱን ሲሰጥ በምትኩ አንዳች ጥቅምን ፈልጎ አይደለም።
ይልቁንም ሕይወቱን ሳይሰስት የሚሰጠው ለሀገር ሉዓላዊነትና ለወገን ክብር ሲል ነው። ስለዚህም አንተ ቢያንስ ገንዘብህን፤ ዕውቀትህንና ጊዜህን ለሀገርህና ለወገንህ ለመስጠት ወደ ኋላ አትበል።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት አንዱ ክንፍ የሆነው የሰሜን ዕዝ ይህ ደረሰበት። ጥቅምት 23/2013 በትግራይ ክልል የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ሲከላከልና የደረሱ ሰብሎችን ሲያጫድ ውሏል።
ሰራዊቱ ከ21 ዓመት በላይ ከትግራይ ሕዝብ ጋር ኖሯል። ሕዝቡ የደከመበት ሰብል በአንበጣ ሲበላ ዝም ብሎ የማየት አቅም የለውምና ‹‹ደከመኝ፣ ሰለቸኝ ሳይል የአንበጣ መንጋ ሲያባርር ውሏል። ዕለቱን አካሉ በድካም ዝሎ ወደመኖሪያ ካምፑ በሰላም ተመልሷል።
የሰራዊት አባላቱ አመሻሹ ላይ በድካም የዛለ አካላቸውን ለማሳረፍ ጋደም አሉ። ምሽቱ እንደቀድሞው ሰላማዊ አልሆነም። ያልታሰበ ግርግርና ሁከት ተፈጠረ። ባልጠበቁትና ባልገመቱት መልኩ የራሳቸው ጓደኞች ብሔር ለይተው፣ ጥቃት ፈጸሙባቸው።
‹‹በሬ ካራጁ›› እንዲሉ ቀን ጠብቀው ስል ቢላቸውን በአንገታቸው አሳረፉ። በሕይወት የተረፉትን በግፍ አንገላቷቸው፤ በርሃብ ቀጧቸው፤ በጭካኔ ገድለው በሬሳቸው ላይ ዘፈኑ፤ ተሳለቁ። ልብሳቸውን አስወልቀው በራቁት ሰደዷቸው፤ ሴቶቹን ደፈሩ፤ ጡታቸውን ቆረጡ።
የሰሜን ዕዝ ሠራዊት ‹‹ሀገሬ ወገኔ›› ብሎ በሰላም ባለበት የራሴ ወገን እንዲህ ዓይነት አረመኔያዊ ድርጊት ይፈጽምብኛል ብሎ ቅንጣት አልጠረጠረም። በከተማ ጦር ሰፈሩ በየበረሃው፣ በያዘው የመከላከያ ይዞታው ላይ እያለ በከሀዲው የጁንታው ኃይል የተፈጸመበት ዘግናኝ አረመኔያዊ ወንጀልና ጥቃት በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የተፈጸመ ወንጀልና ጥቃት ነው።
መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዳር እስከዳር አስገምግሞ የተነሳው በጁንታው ጭካኔ በልጆቹ ላይ የተፈጸመው ግፍ፣ በደልና ጭፍጨፋ ቢያስቆጣው ነው። ይህ ጥቁር አሻራም በአስከፊ ታሪክነቱ ከትውልድ ትውልድ ይተላለፋል።
ስግብግቡ ጁንታ የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰላም የዘረጋውን እጅ በንቀት ገፍቶ ነክሶታል። የሃይማኖት አባቶችን፣ የእናቶችን፣ ልመና ንቆ የሽምግልና ጥሪውን በእብሪት ሲረግጥ ቆይቷል። ለሰላም የተሰጠውን ቀነ ገደብ ረግጦም ጊዜውን ጦርነት ለማወጅ ተጠቅሞበታል።
ጁንታዎቹና ጀሌዎቻቸው ከ2 ዓመታት በላይ ይበጃል ያሉትን ወታደራዊ ሥልጠና በመስጠት በመላው ትግራይ ሊያዋጉን ይችላሉ ባሏቸው ገዢ ቦታዎች ላይ ስውር ምሽጎች ሰርተዋል። የቀላልና ከባድ መሣሪያ ጥይቶችን፤ ከመንግሥት የዘረፉትን የሕክምና መድኃኒቶችና አስፈላጊ የሚባሉትን ሁሉ አጋብሰው፣ ተራሮችን በመፈልፈል ሲያከማቹ ቆይተዋል።
ነዳጁን ከመሬት ቆፍረው በታንከር በመቅበር ሀገርን ለማውደም ሲዘጋጁ ነበር። እነሆ ዛሬ ይህ ሁሉ የተንኮል ደባ በጀግናው ሠራዊታችን ከፍተኛ ተጋድሎ ‹‹ነበር›› ተብሎ ታሪክ ሆኗል። በአገር የሸመቁ በርካቶች ጊዜ ተፋርዷቸዋል።
ወገናቸውን የካዱ መሪዎች እጅ ሰጥተው ተማርከዋል። የተቀሩት የትም አይሄዱም። የቀናት ጉዳይ ሆኖ መጨረሻቸው ይታያል።
የዛሬን አያድርገውና አስቀድሞ በተጠናና በተደራጀ ዕቅድ ብዙ ሲታሰብ ቆይቷል። በቂ ዝግጅት ተደርጎም ቀላልና ከባድ ተሽከርካሪዎችን፤ አውዳሚ መሣሪያዎችን ከሠራዊታን ላይ በድንገት በመዝረፍ ጦሩን በማገት፣ እሺ ያለውን ከጎን በማሰለፍና ያልተስማማውን በመግደል እቅዳቸውን ለማሳካት ተንቀሳቅሰዋል።
የጁንታው ኃይል በመላው ትግራይ በነበሩ እግረኛ ክፍለጦሮች፤ ታንከኛና ሜካናይዝድ ኃይሎች፤ የሚሳኤል ምድብተኞች፤ የሕክምና ትጥቅና ስንቅ ክፍሎች በሌሎችም ላይ የውስጥ ከሀዲዎችንና ባንዳዎችን በመጠቀም ወረራ ፈጽሞ ሠራዊቱን በተኛበት ረሽኗል።
ትናንት አብሮት የነበረን የትግል ጓዱን ልብስና ጫማውን አስወልቆ በመቀሌ ጎዳናዎች በባዶ እግሩ እያስሮጠ ተመልካች እንዲሳለቅበት ፈቅዷል።
ሠራዊታችን ያለውን እያካፈለ እየቆረሰ ችግረኞችን እየረዳና እያስተማረ እያበላና እያጠጣ፣ ሳይተርፈው ሳይደላው ወገኖቼ ብሎ ያለውን ሲያካፍል ነበር። ለኖረበት አካባቢ ከኪሱ እያወጣ ትምህርት ቤቶችን ገንብቷል፤ ሰብል ሲደርስ ጉልበቱን ሳይሰስት ከፍሏል፣ አንበጣን ተከላክሎ ሕዝቡን ከስጋት ታድጓል፣ ሆኖም ለዚህ ታላቅ ሕዝባዊ ተግባር በከሀዲው ቡድን የተሰጠው ምላሽ በሞት መቀጣትና መዋረድ ሆነ።
አዎ! ይህን ታሪክ ትውልድ አይረሳውም። የሀገር መከታውን ገድለው በሬሳው ላይ ተሳለቁ። ጨፈሩበት። በሥርዓቱ እንዳይቀበር አደረጉ። በሴት ወታደሮች ብልት ቢላ ከተቱ። ጡታቸውን ቆረጡ። አረዷቸው። የሚገርመው የጁንታው ድንቁርና ማሳያ ምን ይመጣብኛል፤ ምንስ ይከተላል ብሎ አለማሰቡ ነው።
ሠራዊቱ ታላቅ ወገን፤ ታላቅ ደጀን፤ ጥቃቱን የሚወጣለት ታላቅና ጀግና ሕዝብ እንዳለውና ጠላቱን መልሶ አፈር እንደሚያስግጠው የታወቀ ነበር። እናም የታሰበው ሁሉ በስኬት ተደመደመ።
የጁንታውን ከበባ ጥሰው የወጡት ታማኝ ወታደሮች የተከዜን ወንዝ ተሻግረው ኤርትራ ምድር ገቡ። የኤርትራ ሠራዊት በክብር ተቀብሎ አብልቶ አጠጥቶ የተራቆተ ገላቸውን አለበሰ። ተበታትነው ወደ ኤርትራ የተሻገሩት ተደራጅተው የወያኔን ጁንታ ለመዋጋት እሳት ለብሰው እሳት ጎርሰው በእልህ በቁጭትና በወኔ ገሰገሱ።
መደፈራቸው እያንገበገባቸው ወደ ትግራይ መሬት ተመልሰው የጁንታውን ወታደራዊ ኃይል በአስገራሚ ፍጥነትና ብቃት በየቦታው እየደመሰሱ በድል ተመለሱ። ቀድሞ 17 ዓመታት የፈጀውን ጦርነት ጀግናው የመከላከያ ሰራዊት በ17 ቀናት በአንጸባራቂ ድል አጠናቀቀው።
የጁንታውን አባላት ከተደበቁበት የቀበሮ ጉዷጓድ ለቅሞ ያዛቸው። ከተሰቀሉበት የዝንጅሮ ገደል ጎትቶ በእጁ አስገባቸው። ከተወተፉበት ቱቦ ፈልፍሎ አወጣቸው። ወትሮም ምኞቱና ትልሙ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት መጠበቅና የሕዝቦቿንም ሰላምና ደህነት ማስከበር የሆነው ጀግናው ሰራዊት ሀገር ለማፈራረስ የተነሱትን ላይመለሱ ድባቅ መታቸው።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እንዳሉትም ‹‹ጀግና አይፎክርም›› እንደተባለውም የመከላከያ ሰራዊት አባላት ሀገር አፍራሾችን በእጃው ሲያደርጉ አንዳች የታየባቸው የመኩራራትና የመጀነን ስሜት የለም።
ይልቁንም የገደሏቸውን፤ ያስራቧቸውን፤ ገድለው በሬሳቸው ላይ የጨፈሩትን፤ ልብሳቸውን አውልቀው የሰደዷቸውን፡ ጡታቸውን የቆረጧቸውን ጁንታዎች የተራበ ሆዳቸውን ሞልተው፣ ጠኔያቸውን አስታገሱ። የደከመ አካላቸውን አሸተው፤ ለሱሳቸው ሲጋራና ቡና ጋበዙ። እውነተኛ ማንነታቸውን አሳይተው ሰብዓዊነታቸውን መሰከሩ።
መስጠት ማለት ይሄ ነው። እንኳን ለሀገርና ለወገን አዙሮ ለወጋ ጠላትም እንዲህ በጎ እንደሚደረግ ከመከላከያ ሰራዊት አይተናል። ተምረናል፤ መለስ ብለንም እራሳችንን ወቅሰናል፤ ‹‹እኔ ለሀገሬ ምን አድርጌያለሁ በሚል እራሳችንን ጠይቀናል። እናም ዛሬ ምኞታችን፤ ቁጭታችን፤ ወቀሳችን በተግባር የሚገለጽበት ወቅት ላይ ነን።
ዛሬ በትግራይና በመተከል በርካታ እርዳታ የሚሹ ወገኖች አሉ። አለሁ የሚላቸው፤ ወገኖቼ ብሎ የሚቆረቆርላቸው፤ ከጎናቸው የሚሆንላቸው፤ ያለውን የሚያካፍላቸው፤ እርሃብ ጥማቸውን የሚጋራቸው፤ የችግርና መከራ ቀንን የሚካፈላቸው ኢትዮጵያውያንን ይሻሉ።
እነሆ እኔም በመልዕክቴ ለወገኔ እንዲህ እላለሁ ‹‹መከላከያ ሰራዊት በሄደበት መንገድ ሁሉ እርጥብ እጆችህ አይለዩ ያለህን ስጥ። ለሀገርና ለወገንህ መኖር ጀምር። ይህ ሲሆን ከእራስ አልፎ የምትኖርለት አላማ ይኖርሃል።
አዲስ ዘመን ጥር 30/2013