ታምራት ተስፋዬ
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣኑ ከቀናት በፊት የስድስት ወር አፈፃፀሙን ይፋ አድርጓል፡፡ በግማሽ ዓመት ውስጥ 492 ኪሎ ሜትር ልዩ ልዩ የግንባታና የጥገና ሥራዎችን ለመስራት አቅዶ 435 ኪሎ ሜትር በማከናወን የእቅዱን 88 በመቶ ማሳካቱንም አሳውቋል፡፡
ባለስልጣኑ ላለፉት ስድስት ወራት ካከናወናቸው አጠቃላይ 74 ኪሎ ሜትር የግንባታ ሥራዎች መካከል 13 ኪሎ ሜትር የአስፋልት 15 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር የጠጠር፣ 7ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር የጋራ መኖሪያ ቤቶች የውስጥ ለውስጥ መንገዶች፣ 15ነጥብ1 ኪሎ ሜትር የጥርብ ድንጋይ ንጣፍ፣ 22 ኪሎ ሜትር የእግረኛ መንገዶች መልሶ ግንባታ፣ 0 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የድሬኔጅ መስመር እና 0 ነጥብ 14 ኪሎሜትር የድጋፍ ግንብ ሥራዎች ይገኙበታል፡፡
በሌላ በኩል 34 ነጥብ 1 ኪሎ ሜትር የአስፋልት፣ 18ነጥብ3 ኪሎ ሜትር የጠጠር፣ 303 ኪሎ ሜትር የድሬኔጅ መስመር ፅዳትና ጥገና፣ 5ነጥብ6 ኪሎ ሜትር የእግረኛ መንገድ በድምሩ በ6 ወራት ውስጥ 361 ኪሎ ሜትር ኪሎ ሜትር የጥገና ሥራዎች አከናውኗል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን የ2013 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የእቅድ አፈፃፀምና የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ቅዳሜ ጥር 8 ቀን 2013 ዓ.ም በግሎባል ሆቴል ውይይት አካሂዶ ነበር፡፡ በዚህ መድረክም የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሞገስ ጥበቡ ባለስልጣኑ ባለፉት ስድስት ወራት ያከናወናቸው ሥራዎች አበረታች መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
ባለስልጣኑ በአሁኑ ወቅት የተለያዩ መንገዶች ፕሮጀክቶችን እያስገነባ ይገኛል፡፡ ከእነዚህ ፕሮጀክቶች መካከልም ከቁስቋም- እንጦጦ ማርያም የሚያገናኘው አዲስ የመንገድ ግንባታ ይገኝበታል፡፡ በኅዳር ወር 2013 ዓ.ም የተጀመረው ይህ ፕሮጀክት አጠቃላይ ርዝመቱ ሦስት ነጥብ ስድስት ኪሎ ሜትር ነው፡፡ የጎን ስፋቱ እግረኛ መንገድን ጨምሮ 12 ስፋት እየተገነባ የሚገኝ ነው፡፡
አዲስ ዘመን ጋዜጣም ከቁስቋም-እንጦጦ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት አፈፃፀም በምን ተክለ ቁመና ላይ ይገኛል የሚል ጥያቄ በማንሳት የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ እያሱ ሰለሞን አነጋግሯል፡፡
ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ እንደገለፁትም፣ ከቁስቋም እንጦጦ ማርያም የሚያገናኘው አዲስ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ዋነኛ አላማ በቅርቡ ሥራ የጀመረውና ለአዲስ አበባ ከተማም ይሁን ለእንግዶች ትልቅ የሕዝብ መዝናኛ ስፍራ የሆነው የእንጦጦ ፓርክና መዳረሻ ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡
በአካባቢው አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው ነባሩ መንገድ ጠባብና በጣም ዳገታማ በመሆኑ ለእንቅስቃሴ አስቸጋሪ እንደነበር ያስታወሱት አቶ እያሱ፣ ይህ ችግርም መንገዱ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ መገንባቱን አስፈላጊ እንዳደረገው ይናገራሉ፡፡
‹‹በአሁኑ ወቅት የዚህ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት፣ የአፈር ቆረጣ ሥራ የገረጋንቲና የአፈር ሙሌትና የድጋፍ ግንብ ሥራዎች በፍጥነት እየተከናወነ ይገኛል›› ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ ፕሮጀከልቱም የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣንም በልዩ ትኩረትና ፍጥነት እየገነባቸው የሚገኙ መካከል ግንባር ቀደም ስለመሆኑ አፅእኖት ሰጥተውታል፡፡
ቀደም ሲል ከኮንትራት ጋር በተያያዘ ችግሮች ይነሱ እንደነበር ያስታወሱት አቶ እያሱ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣንም ችግሩን ለማስወገድ ወደ ሽሮ ሜዳ መዳረሻ የሚሆነውን ስድስት መቶ ሜትር በራሱ ኃይል በመግባት በኮንትራት ከተሰጠው ጋር በአንድነት እንዲጠናቀቁ ለማድረግ መስራቱን አብራርተዋል፡፡
ይህም ከቁስቋም-እንጦጦ ማርያም የሚዘልቀው የመንገድ ፕሮጀክት በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ካለው ፍላጎት የመጣ ስለመሆኑ የጠቀሱት አቶ እያሱ፣ ‹‹የመንገድ ፕሮጀክቱን በበጀት ዓመቱ ለትራፊክ ክፍት ለማድረግ በሚያስችል ደረጃ ላይ ለማድረስና ለአገልግሎት ለማብቃት በከፍተኛ ርብርብ እየሰራን ነው›› ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ፕሮጀክቱ ላይ ያጋጠሙ ፈተናዎችን በሚመለከት ለቀረበላቸው ጥያቄም ፕሮጀክቱ እንደሌሎች ከወሰን ማስከበር ጋር የተያያዙ ችግሮች እንደሌሉበት ገልጸዋል፡፡ ይሁንና ከግብአት ጋር የተያያዙ ፈተናዎች እንደገጠማቸው ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡
የመንገድ ፕሮጀክቱ ግንባታ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ ለአካባቢው ነዋሪዎችና ወደ እንጦጦ ፓርክ ለመዝናናት ለሚንቀሳቀሱ የከተማዋ ነዋሪዎችና ቱሪስቶች አገልግሎት የሚሰጥ ስለመሆኑ አፅእኖት የሰጡት አቶ እያሱ፣ ፕሮጀክቱም የጊዜው ተገቢው ክትትልና በባለስልጣኑ የሥራ መሪዎችም የመስክ ምልከታ እንደሚደረግበት አስታውቀዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 29/2013