ኢያሱ መሰለ
ሰው ኑሮውን ለማሸነፍ በሚያደርገው መፍጨርጨር በርካታ ውጣ ውረዶችን ሊያልፍ ይችላል። አባጣ ጎርባጣውን እያስተካከለ ጥርጊያውን ለማደላደል ይጥራል። ዛሬ ተሳክቶላቸው የምናያቸው አብዛኛዎቹ ባለጸጋዎች ያለፉበትን መንገድ ወደ ኋላ ዞር ብለን ብንመለከት አልጋ ባልጋ እንዳልነበር መገመት አያስቸግርም።
በሕይወት ጉዞ ብዙ ከፍታና ዝቅታዎች ይኖራሉ። ከፍታውም ዝቅታውም የየራሳቸው ምክንያቶች ሊኖራቸው ይችላል። በአንድ ወቅት የተሻለ ሕይወት የሚመራ ሰው በሌላ ጊዜ ወድቆ ሊታይ ይችላል፤ ወድቆ የነበረውም ሊነሳ የሚችልበት አጋጣሚ አለ። ማግኘትና ማጣት ይፈራረቃሉ፤ ዋናው ነገር ሰው ሁል ጊዜ እራሱን ለመለወጥ የሚያደረገው ጥረት ነው።
በርካታ ሰዎች በጥረታቸው ራሳቸውን ለውጠዋል። ኑሯቸውን ለማሸነፍ ሲሉ በአስገራሚ የስራ መስኮች ላይ ሲሰማሩ አይተናል፤ እንዲህም አይነት ስራ ሰርቶ መኖር ይቻላል እንዴ? አስብለውናል።
የዛሬው እንግዳችንም ለሰዎች ችግር ጊዜያዊ መፍትሄ በመስጠት /የአካባቢውን ንጽህና በማስጠበቅ/ በሚያገኘው ገቢ ኑሮውን ለማሸነፍ እየጣረ ያለ ነው። ግለሰቡ የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ ይኖር እንደነበር ይናገራል።
በአንድ ወቅት ባጋጠመው ችግር ምክንያት ከስራ ውጭ ሆኖ ለጎዳና ህይወት ተጋልጧል። የጎዳና ህይወትን በሚመራበት ሜክሲኮ አደባባይ አካባቢ የሰው እጅ ላለመጠበቅ ብሎ የጀመረው ስራ አካባቢን ከብክለት ታድጓል። እርሱም የቀን ጉርሱን እንዲያገኝ ረድቶታል።
ወደ ጉዳዩ እንግባ፤ በአዲስ አበባ ከተማ የሰዎች እንቅስቃሴ ከሚበዛባቸው አካባቢዎች አንዱ ሜክሲኮ አደባባይ ነው። በአደባባዩ አቅራቢያ የሚገኙት ትልልቅ ጎዳናዎች የታክሲዎች መነሻና መዳረሻ በመሆናቸው ይመስላል ሜክሲኮ አደባባይ ትርምስ ይበዛበታል።ከየአቅጣጫው ተሰባስበው መተላለፊያውን ከሚያጨናንቁት ሰዎች በተጨማሪ የጎዳና ላይ ግብይቱ ለሰው ቁጥር መጨመር ሌላ ምክንያት ሆኗል።
የዚህ ሁሉ ሰው መናኽሪያ በሆነው ስፍራ እድሜ ጠገብ ከሆነው የዋቤ ሸበሌ ሆቴል እና ጥቂት ካፌዎች በስተቀር በቂ ሆቴሎችና ማረፊያ ቦታዎች አለመኖራቸው ወይም ርቀው መገኘታቸው ሰዎች የሚፈልጉትን የመጸዳጃ አገልግሎት እንዳያገኙ ሆነዋል። በዚህም የተነሳ አላፊ አግዳሚው በአካባቢው በግንባታ ስም ታጥረው የተቀመጡ ቦታዎችን የመጸዳጃ ቦታ አድርጓቸዋል።
በተለይም ከታክሲ የሚወርዱና ታክሲ ለመሳፈር ለረዥም ጊዜ ተሰልፈው የሚቆሙ ሰዎች በየአጥሩ ጥግ ሲጸዳዱ ማየት የተለመደ ነው።በስፍራው አንድ መጸዳጃ ቤት ተገንብቶ አገልግሎት እንዲሰጥ ቢደረግም ችግሩን መቅረፍ አላስቻለም።
በተለይም ከሜክሲኮ አደባባይ ወደ ተክለ ሃይማኖት በሚወስደው መንገድ በስተቀኝ 200 ሜትር ከፍ ብሎ የሚገኘው ቦታ ቋሚ የሽንት መሽኛ ሆኖ ሲያገለግል እንደነበር ነዋሪዎች ይናገራሉ። ይህም የአካባቢውን ገጽታ ክፉኛ ያበላሸና ሰዎችን እንደጉንፋን ለመሳሰሉ የጤና ችግሮች ያጋልጥ እንደነበር ያስታውሳሉ።
እዚህ አካባቢ በቀን ስራ ተሰማርቶ የሚኖር አንድ ሰው ታዲያ የአካባቢውን ንጽህና እያስጠበቀ እራሱንም እየጠቀመ መኖር የሚችልበትን ሁኔታ አመቻችቷል። ግለሰቡ በስራ እጦት ምክንያት ሲፈተን ኖሯል። የቤት ኪራይ መክፈል አቅቶት ጎዳና ላይ ለመኖር ተገዷል። የሚበላው የሚጠጣው እስከማጣት ደርሷል።
የከተማውን ገጽታ ሲያበላሽ የተመለከተውን ቆሻሻ እንደ አልባሌ ነገር አይቶ ከማለፍ ይልቅ ጊዜያዊ መፍትሄ መስጠት ችሏል። መፍትሄው የአካባቢውን ንጽህና ከማስጠበቅ ባለፈ ለግለሰቡም የገቢ ምንጭ ሆኗል። ድርጊቱ በአካባቢው ለታየው የንጽህና ችግር ትክክለኛ መፍትሄ ነው ማለት ባያስደፍርም ሰው ስራን ሳይንቅ ዝቅ ብሎ ከሰራ አካባቢውንም እራሱንም መለወጥ እንደሚችል አሳይቷል።
ከሁሉ በላይ በኑሮው ወደ ኋላ የተመለሰ ሰው እንደገና ከዜሮ ጀምሮ ህይወቱን መምራት እንደሚችል እና ስራን ሳይንቁ መስራትና መኖር እንደሚያስችል የባለታሪኩ ህይወት ያስረዳል።
በየአካባቢያችን ወደ ገቢ ምንጭ ያልቀየርናቸው እና እንደዋዛ የምናያቸው በርካታ ሁነቶች እንዳሉም ከዚህ ታሪክ መማር እንችላለን። ባለታሪኩ ችግርን አሸንፎ ለመኖር በርካታ ጥረቶችን አድርጓል። የተለያዩ የስራ አይነቶችንም ሞክሯል። የታክሲ ረዳት፣ ግንበኛ፣ የቀን ሰራተኛ፣ ሊስትሮ ሆኖ ሰርቷል። በመጨረሻም ብዙዎች የማያስቡትን ስራ እየሰራ መኖር ችሏል። ይህ ስራ ጊዜያዊ ቢሆንም ወደ ሌላ ስራ ለመሸጋገር አቅም ፈጥሮለታል። የግለሰቡ ህይወት ውጣ ውረድና የግል ጥረት አስተማሪ በመሆኑ ለዚህ አምድ መርጠነዋል።
ኤሊያስ መለስ ይባላል። ቤተሰቦቹ አቅመ ደካሞች ስለነበሩ የቀን ስራ እየሠራ ሊረዳቸው በማሰብ ከትውልድ አካባቢው ወደ አዲስ አበባ ይመጣል። ከዚያም ለጥቂት ወራት የቀን ስራ እየሰራ ህይወቱን ይገፋል። የከተማዋን መዳረሻዎች በቅጡ የማያውቀው እንግዳ ሰው ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የታክሲ ረዳት በመሆን ተቀጥሮ መስራት ይጀምራል።
የማያውቀውን አካባቢ እየተጣራ ጠዋት ወጥቶ ማታ ይገባል። በቀን የሚከፈለው ጥቂት ገንዘብ ከቤት ኪራይ፣ ከልብስና ከምግብ ተርፎ ቤተሰቦቹን መርዳት የሚያስችለው አልሆነም። የታክሲ ረዳትነቱ የሚፈልገውን ገቢ ባያስገኝለትም የአዲስ አበባን የተለያዩ ቦታዎች ለማወቅ እድል እንደፈጠረለት ይናገራል።
ከዚህ በኋላ ኤሊያስ ህይወቱን ለመምራትና ቤተሰቦቹንም ለመርዳት የሚያስችለውን የተሻለ የስራ አማራጭ ማፈላለግ ይጀምራል። የአንድ ሙያ ባለቤት ለመሆን በማሰብ የታክሲ ስራውን ትቶ ረዳት ግንበኛ በመሆን ይቀጠራል። ኤሊያስ የቀን ተከፋይ ከመሆን ወደ ወር ተከፋይነት ይሸጋገራል።
የነገ ተስፋውንና እድገቱን በማሰብ የግንበኝነት ሙያውን ያጠናክራል። በወር የሚሰጠውን ክፍያ በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋል የተረጋጋ ህይወትን መምራት ይቀጥላል። ከታክሲ ረዳትነት ወደ ረዳት ግንበኝነት ባደረገው ሽግግርም ደስተኛ ይሆናል። ቤተሰቦቹን ለመርዳት የሚያስችል አቅም ላይ ባይደርስም ሙያውን እያሳደገ ሲሄድ ነገ ተፈላጊ ሰው የመሆን ተስፋ እንዳለው በማሰብ ስራውን በፍቅር መስራቱን ይያያዛል። እንዲህ እንዲህ እያለ ወራትን ያስቆጥራል።
በአንድ ወቅት ኤሊያስን አሳዛኝ ነገር ይገጥመዋል። ጉዳዩ እንዲህ ነው፤ ረዳት ግንበኛ ሆኖ መስራት ከጀመረ ወዲህ የሰራበትን ደመወዝ የሚቀበለው በወር መጨረሻ ነው። አሰሪው ስራዎችን ከተቋራጮች ላይ እየተረከበ ሰራተኞችን ቀጥሮ የሚያሰራ ነው።በዚሁ መሰረት ኤሊያስ ለበርካታ ወራት ክፍያ ተፈጽሞለታል።
አንድ ቀን ታዲያ እንደተለመደው የደመወዝ ወቅት ደርሶ ለመቀበል ወደ አሰሪው ቢሮ ሲሄድ አሰሪውን ያጣዋል። ሁለት ሶስት ቀን አሳልፎ ሲሄድም ሰውየው ሳይመጣ ይቀራል። ስልክ ሲደወልለት ጉዳይ ገጥሞት እንደቀረ ይናገራል። ከ20 ቀን በላይ አለፈው። በመጨረሻም ስልኩን አጠፋው።
ኤሊያስ ያላሰበው ችግር ገጠመው፤ ግራ ተጋባ፤ ተደነጋገጠ፤ የቤት ኪራይ የሚከፍለው ቀርቶ የሚበላው አጣ። አስፋልት ዳር እየዞረ አንዳንድ የጉልበት ስራዎችን ለመስራት ቢሞክርም የእለት ጉርሱን እንኳን መቻል አቃተው። የቤት ኪራይ መክፈል ባለመቻሉም ጎዳና ላይ ወጣ። ኤሊያስ በጎዳና ህይወት ውስጥ ሆኖ ከገባበት ማጥ ውስጥ ለመውጣት ብዙ ጥረቶችን እንዳደረገ ይገልጻል።
አንድ ቀን ሜክሲኮ አደባባይ አካባቢ ቁጭ ብሎ አላፊ አግዳሚው የሚሸናበትን ቦታ በትኩረት እየተመለከተ ቦታው ላይ ሽንት እንዳይሸናበት በማድረግ የአካባቢውን ንጽህና ማስጠበቅና እራሱንም መጥቀም እንዳለበት አሰበ። ቦታው የአካባቢውን ገጽታ ያበላሸ ከመሆኑም በላይ እዚያ አካባቢ ቁጭ ብለው እቃዎችን የሚሸጡ ነጋዴዎችን ያማረረ ነው። ኤሊያስ በአካባቢው ያሉ ነጋዴዎች ገንዘብ እንዲሰጡትና ባልዲዎችን ገዝቶ መንገደኞች እንዲጠቀሙባቸው ማድረግ ለተማረሩበት መጥፎ ሽታ ጊዜያዊ መፍትሄ እንደሚሆን ይነግራቸዋል።
በዚሁ መሰረት ሃሳቡን በመደገፍ አንድ ሰው ሁለት መቶ ሃምሳ ብር ይሰጠውና ስምንት ባልዲዎችን ገዝቶ መንገደኞች የሚጸዳዱበት ቦታ ላይ ያስቀምጣል። ያም ቦታውን መሸፈን ሳይችል ይቀርና ተጨማሪ ስምንት ባልዲዎችን ገዝቶ በተለያዩ ቦታዎች ያስቀምጣል። ከዚያም ተጠቃሚዎች ከተጠቀሙ በኋላ አንዳንድ ብር እንዲከፍሉ ያደርጋል።
ቀን አገልግሎት ሲሰጡ የዋሉትን ባልዲዎች ማታ እያንጠለጠለ ፍሳሽ ማስወገጃ ውስጥ ይደፋል። ባልዲዎቹን በላርጎና በኦሞ እያጸዳ ጠዋት በቦታቸው ያስቀምጣቸዋል። ኤሊያስ የእለት ገቢ ማግኘት ይጀምራል። ያ አስቀያሚ ገጽታ የነበረው አካባቢ እየተቀየረና መልካም ገጽታ እየተላበሰ ይሄዳል። በአካባቢው የተሰማሩ ነጋዴዎች፣ አሽከርካሪዎችና እግረኞች እፎይታን ያገኛሉ።
የቀበሌ መስተዳድሮችና ደምብ አስከባሪዎችም ያደረገውን መልካም ስራ እያዩ ያበረታቱታል። የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሆኑ አንዳንድ ሰዎችም አማራጭ በሌለበት ቦታ እንዲህ አይነት አገልግሎት ማግኘታቸውን እንደ ትልቅ እድል እያዩ ከሚፈለግባቸው ክፍያ አስበልጠው እንደሚሰጡት ይገልጻል። በተለይም የኩላሊት ህመም ያለባቸው ሰዎች የኤሊያስን ስራ እያዩ ምስጋና ያቀርቡለታል።
የአካባቢው ንጽህና መለወጡን እያዩ የሚያበረታቱት ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ይሄዳል። ከእርሱ ተሞክሮ በመነሳት ሌሎችም የተለያዩ ቦታዎች ላይ ባልዲዎችን በማድረግ የአካባቢያቸውን ንጽህና እየጠበቁ እራሳቸውንም እየጠቀሙ መሆናቸውን ኤሊያስ ይናገራል።
ኤሊያስ በአካባቢው ያስተዋለውን የንጽህና ችግር ለመፍታት የፈጠረው ጊዜያዊ መፍትሄ ነው። ቀጣይነት እንደማይኖረው ያውቃል። በተለይም አካባቢው ላይ የተጀመሩት ግንባታዎች ሲጠናቀቁና ከተሞች እየዘመኑ ሲሄዱ የመጸዳጃ ችግር ጥያቄዎችም መልስ እንደሚያገኙ ያምናል። ሰዎች ከመጸዳጃ ቤት ውጭ ባይሸኑ ይመረጣል የሚለው ኤሊያስ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሰዎች መንገድ ላይ ከመሽናት ይልቅ በተዘጋጁ እቃዎች ላይ ቢጠቀሙ ይመረጣል ይላል።
ለጊዜው የሚታየውን ችግር ለመፍታት በማሰብ የፈጠረው ስራ ጊዜያዊ መፍትሄ ከመስጠት አያልፍም። ጎዳና ላይ መጸዳጃ እቃዎችን ማስቀመጥ በራሱ የከተማዋን ውበት ማበላሸት በመሆኑ ቀጣይነት እንደማይኖረው የገለጸው ኤሊያስ ለጊዜው ግን የራሱንም አካባቢውንም ችግር ፈትቶበታል። ለቀጣይ ህይወቱም በቀን ከሚያገኘው ገቢ እያጠራቀመ ራሱን ወደ ሌላ ስራ ለማሸጋገር ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ይናገራል።
ከጎዳና ህይወት ወጥቶ ቤት ተከራይቶ ወደሚኖርበት ሁኔታ ለመመለስ ተግቶ እየሰራ ነው። የቀበሌው መስተዳድር በአካባቢው ንጽህና ላይ ያበረከተውን አስተዋጽኦ በመመልከት እና ጥረቱን ለማገዝ የስራ ቦታ እንደሚሰጠው ቃል የገባለትን ተስፋ ይዞ ለተሻለ ነገር እየሰራ ነው።
በአካባቢው በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ ሰዎችም ኤሊያስ የአካባቢውን ንጽህና በማስጠበቁ በስራቸው ላይ የነበረውን ጫና እንዳስወገደላቸው ይናገራሉ። ወጣት ገበየሁ አድማሱ በሜክሲኮ አደባባይ አካባቢ ህጋዊ ፈቃድ ወስዶ ጎዳና ላይ በመሸጥ የሚተዳደር ነው።
እርሱ እንደሚያስረዳው ከስራ ቦታው አቅራቢያ ሰዎች ስለሚጸዳዱ የሽንት ሽታ ያስቸግረው ነበር፤ ሰዎችም ቆመው እቃ የመግዛት ፍላጎት አልነበራቸውም። አሁን አካባቢው በመጽዳቱ ምቹ የስራ ሁኔታ እንደተፈጠረለት ይናገራል። ማናችንም በአካባቢው የምንገኝ ነጋዴዎች መንገደኞች ሲጸዳዱ ከመጣላት በስተቀር እንዲህ አይነት አማራጭ አልታየንም ነበር ያለው ገበየሁ የኤሊያስ ተግባር ጊዜያዊ ችግራቸውን የፈታላቸው መሆኑን ይናገራል።
የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የችግሩን ደረጃ ተገንዝበው በአካባቢው ደረጃቸውን የጠበቁ መጸዳጃ ቤቶችን መገንባት እንዳለባቸው ወጣት ገበየሁ በሰጠው አስተያዬት ተሰናበትን። ሳምንት ከሌላ ባለታሪክ ጋር በሌላ ርዕስ እስከምንገናኝ ቸር ይግጠመን።
አዲስ ዘመን ጥር 29/2013