(ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
ነገረ ኅብር ቅኔ፤
ኅብር ቅኔ በአንድ ሥነ ግጥም ውስጥ ወርቅና ሠሙን አስተባብሮ የያዘ ቃል ወይንም ሐረግ ነው። የቅኔ ጠበብት “ሠምና ወርቅ” ይሉት ይትባህልን የወረሱት ከወርቅ አንጥረኞች ሙያ በመዋስ ይመስላል።
የከበሩ ማዕድናት አንጥረኛ ባለ እጅ የጣት ቀለበት ወይንም የአንገት ሃብል ቅርጽ የሚያወጣው በቅድሚያ ሠም አቅልጦ ቅርጹንና መጠኑን ካበጀ በኋላ ነው። ቀጥሎ በነደፈው የሠም ቅርጽ ላይ የነጠረውን ወርቅ ወይንም ማንኛውንም የከበረ ማዕድን ያፈስበታል። ከዚያም የተፈለገው ጌጥ በተፈለገ ቅርጽና መጠን ተዘጋጅቶ ለተፈለገው ጉዳይ ይውላል።
በነባርቹ የግጥሞቻችን ስልቶች ውስጥ ሠምና ወርቅ ባህርያት ያላቸው ግጥሞች በእጅጉ የተለመዱ ናቸው። እንደነዚህ ዓይነት ግጥሞች በተለይም የቋንቋ ተማሪዎችን አእምሮ በሚገባ ያሰላሉ ተብሎ ስለሚታመን ባለፉት ዘመናት በትምህርት ሥርዓታችን ውስጥ በስፋት ሲሰጥ ኖሯል።
በብሔራዊ ፈተናዎች ውስጥም ሳይቀር “ሠሙንና ወርቁን ለዩ?” በሚል ትእዛዝ መሰል ግጥሞች ሳይካተቱ አይቀሩም ነበር። ስለዛሬው እንዴታ እርግጠኛ አይደለሁም።
በሠም የተሸፈነና በወርቅ የተለበጠ ኅብር ቅኔ አምቆ የሚይዘው መልእክት እጅግ የረቀቀና በአእምሮ ውስጥ ተቀርጾ የሚቀር ትርጉም ያለው ነው። እንዳለመታደል ሆኖ ግን ገፍተን ወደ ዳር እንደወረወርናቸው በርካታ ነባር ሀገራዊ ትሩፋቶቻችን “ኅብር ቅኔ” ባህርያት ያላቸው ግጥሞችን በስፋትና በጥልቀት ልጆቻችን በመደበኛ ትምህርቶቻቸው ውስጥ እንዲማሩ ማበረታታቱን ቸል ያልን ይመስላል።
ኢትዮጵያ “ኅብር ቅኔ ነች”
አበው የቅኔ ጥበብን የሚመስሉት ተቀድቶ በማያልቅ የባህር ውሃ ተምሳሌትነት ነው። በቅኔ አማካይነት ታሪካዊ ክስተቶች እየተመሳጠሩ ይገለጻሉ። ከተፈጥሮ ምሥጢራት ጋር እየተሰላሰለም ይተረካል። የቅዱሳት መጻሕፍት ታሪኮች እየተመዘዙ ረቂቅ መልዕክቶች ይተላለፉበታል።
የሠም ለበስ ቅኔን ምሥጢር ለመፍታት አእምሮን አንቅቶ፣ ልቦናን አስፍቶ መመርመርን ግድ ይሏል። ስለዚሀም ቅኔ ከረቂቅነቱ ባህርያት ጎን ለጎን በእውቀት የበለጸገ፣ በታሪክ የደመቀ የሰዋሰው ዘርፍ ነው የሚባለው።
“ሀገር ቅኔ ነች!” የሚለው ኃይለ ቃል “ለማለት ብቻ የሚባል፤ ለማድነቅ ስለተፈለገ ብቻ የሚጋነን” ወትሯዊ መግባቢያ አይደለም። ኢትዮጵያ ረቂቅ ቅኔ ነች የሚባለው “ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ” እንዲሉ “ግለ ትምክህትን” ለማንጸባረቅም ስለተፈለገ አይደለም። “በሠም እውቀት የተለበጡ” እና በጆሮ ጠገብ ተረክ የሰከሩ አንዳንድ ቡድኖችና ግለሰቦች የሀገርን ቅኔያዊ ባህርይ ሲያክፋፉ፣ የረቂቅነት ምሥጢሯንም ሲያኪያኪሱ ያወቁና የበቁ ይመስላቸዋል።
የአለማወቃቸውን ነውርም እንደ ክብር እየቆጠሩ ይኩራሩበታል። ዓይናቸው በርቶ፣ ኅሊናቸው የገሰጻቸውና እውነቱ የተገለጸላቸው ዕለት እንዴት እንደሚያፍሩና እንደሚሸማቀቁ ጊዜው ሲደርስ ማየቱ ይበጃል።
“ኢትዮጵያ ኅብር ቅኔ” የመሆኗ ምሥጢር የሚገለጸው በራሷ ልጆች አንደበትና የታሪክ ሰነዶች ብቻ እየተመሳከረ አይደለም። በቅዱሳት መጻሕፍትና በጥንታዊ ባዕዳን አንደበትና ብዕር ጭምር በተሰጠ ማስረጃነት ማረጋገጥ ስለሚቻልም እንጂ። ማንም ግለሰብ በሕጋዊ አግባብ የወሰን ችካል ቆሞለት የተሰጠው ርስት እንዲከበርለት ይፈልጋል፤ በጉልበተኞች ሲደፈርበትም እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ድረስ ጨክኖ ወደረኛውን ለመፋለም ራሱን ያዘጋጃል።
በዓለም አቀፍ ሕግ የተረጋገጠ የሉዓላዊ ሀገራት ድንበርም እንዳይደፈርና እንዳይገሰስ ሁሌም በጦር ሠራዊት አጥር ይከበባል፤ ይጠበቃልም። በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ በግልጽ እንደተመለከተው “የኢትዮጵያ ምድር የተከበበው በታላቁ የግዮን (አባይ) ወንዝ ድንበርነት ነው። “የሁለተኛውም ወንዝ ስም ግዮን ነው። እርሱም የኢትዮጵያን ምድር ሁሉ ይከብባል” (ዘፍጥረት ምዕ. 2 ቁጥር 13) እንዲል ቅዱስ መጽሐፍ።
በዚህም ምክንያት ፈጣሪ በግዮን ወንዝ ድንበርነት ያሰመረውና በዘላለማዊ ኪዳን ያጸናው ቃል በቀላሉ ይደፈራል፣ በእብሪተኞችም ይዋረዳል ብሎ ማሰብ ለድካምና ለውርደት መዳረጉ ብቻም ሳይሆን የየዋህነት ድርጊት መገለጫ ጭምር ነው። የሀገራችን ምሥጢራዊ ቅኔ የሚጀምረው ከዚህ የዘፍጥረት ታሪክ ነው የሚባለውም ንግግር ለማሳመር ስለታሰበ ብቻም ሳይሆን የፈጣሪ ጣት ስላለበትም ጭምር ነው።
አንዳንዶች ይህንን የፀና እውነት ቢገዳደሩ “የባዶነታቸውና ያለማወቃቸው” ውጤት እንደሆነ አስምሮ ከማለፍ ውጭ ለጉንጭ አልፋ ክርክር ራስን ማዘጋጀት በራሱ ስንፍና ነው። ደፍረን እንከራከር ካሉም ትንፋሻቸው እንደ “ቀላጭ ሠም” ይቆጠር ካልሆነ በስተቀር “ወርቅ” ነው ተብሎ ዋጋ ሊተመንለት አይገባም።
የኢትዮጵያ ታሪክ በርግጥም ኅብር ቅኔ ነው። ሁለተኛ ማስረጃችንም የራሳችን ቀደምት ታሪኮች ናቸው። በዘመናዊ የጦር ትጥቅ የተኩራሩ ባዕዳን ወራሪዎች ሀገራችንን ያልተነኮሷትና ያልተዳፈሩት ጊዜ አልነበረም።
ከጥንት እስከ በቀደም ያለው የጦርነቶቻችንን ታሪኮች እየመዘዝን ብንፈትሽ ማረጋገጫውን በቀላሉ ማግኘት ይቻላል። ጦርና ጎራዴ በመድፍና በታንክ ላይ በመሰልጠን ወራሪዎች ተዋርደውና ተንበርክከው በዚህቺው ምሥጢራዊት ሀገር ጀግኖች አርበኞች ልጆቿ አማካይነት ደጋግመው ኢትዮጵያዊነት ምን እንደሆነ ተምረዋል።
ወድቃለች ስትባል ደምቃ የምትነሳው፣ እንደ ወርቅ በእሳት ስትፈተን ውበቷ የሚፈካው ይህቺ “ተዓምረኛ” ሀገር ረቂቅ ነች። የህልውናዋ እስትንፋስም ምጡቅ ስለሆነ ምሥጢሯ በቀላሉ “ከሠም” ውስጥ ተፈልቅቆ አንደሚወጣ ተራ የወርቅ ጌጥ አይቀልም።
ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች በሙሉ የአርነት ተምሳሌት ተደርጋ የምትታየው በምርጫ ሳይሆን “በተፈጥሯዊ ሥሪቷ” ባህርያት ጭምር ነው። የጀግኖች ልጆቿ ገድል ለዚህ እውነታ ጥሩ ማረጋገጫ ሊሆን ይቻላል የሚባልውም ስለዚሁ ነው።
አንዳንዶች በድፍርስ የፖለቲካ ርዕዮት ነፋስ ግራና ቀኝ እየተላተሙ በመወዛወዝ ይህቺን ኅብር ቅኔ ሀገር ሲያጣጥሉና ሲያዋርዱ ማየትና መስማት ለስሜት ህመም ይዳርጋል። በኢትዮጵያዊነታቸው የሚያፍሩት ደግሞ ጭርሱኑ በመታወር በሽታ የተጠቁ ስለሆነ ለአተካሮ ዕድል መስጠቱ ተገቢነት የለውም።
ኢትዮጵያዊነት ያኮራ ካልሆነ በስተቀር የሚያሳፍር አይደለም። እንኳን ከዚህች ምሥጢራዊት ሀገር አፈር መገኘት ቀርቶ የባዕድ ፓስፖርት መያዝ አንኳን “የኩራት ምንጭ” ሊሆን እንደሚችል እያስተዋልን ነው። የተወለዱበትን ጓዳ ጎድጓዳ ለማክፋፋት አደባባይ መዋል የአስተሳሰብ ድኩምነት እንጂ የአሸናፊነት መገለጫ ሊሆን አይችልም። ምናልባትም በአሳፋሪነቱ ቢገለጽ ተገቢ ሊሆን ይችላል።
ማንም ሰው የተወለደበት ወይንም ያደገበት ብሔር፣ ቋንቋና ባህል አለው። ሊኮራበትና እኔነቱን አድምቆ ቢያስተዋውቅ አግባብም ተገቢም ነው። ነገር ግን የግሉን መለያ አጥር እንደ ዋና ድንበር ቆጥሮና ትልቋን ኢትዮጵያ አሳንሶ ቢከራከርና ቢፎክር ይናቅ ካልሆነ በስተቀር አበጀህ ተብሎ አይከበርም።
በዚህ ጸሐፊ እምነት “ሂያጅና መጭ” የፖለቲካ ርዕዮቶች የሚመሰሉት “በቀላጭ የላይ ላይ ሠም” እንጂ የነጠረ የወርቅ ባህርይ ተሰጥቷቸው በዘላለማዊ ይሁንታ ሊወደሱ አይገባም። ፖለቲካ ለሀገር ህልውና ጊዜያዊ ማማለያ እንጂ ዘላቂ መገለጫ ሊሆን በፍጹም አይችልም።
በወርቅ የምትመሰለው ሀገር ግን በእሳት ብትፈተንም ውበቷ እየደመቀ ይፈካል እንጂ ከስሎ ወደ አመድነት አይለወጥም። አንዳንድ ኅሊና ሙት ቡድኖችና ግለሰቦች የእውር ድንብራቸውን የሚተረማመሱት ይህ እውነት ስላልገባቸው ሊሆን ይችላል።
በሀገራችን ውስጥ ያልተስተናገደ የርዕዮተ ዓለም ዓይነት አልነበረም። ረጂም እድሜ ያስቆጠረው ዘመነ ፊውዳሊዝም “ዘውዱ ተሰባብሮ የተንኮታኮተው” የእብሪቱን ዋንጫ ተጎንጭቶ ነው። የዘመነ ደርጉ ግራ ገብ ሶሻሊዝምም እንዲሁ ታሪክ ሆኖ ያለፈው እንክትክቱ ወጥቶ ነው። የኢህአዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲም ግባ መሬቱ ተፈጽሞ ቀን የጨለመበት በአሳፋሪ መደምደሚያ ነው።
የዛሬ ጀንበር የጠባላቸው፣ “የፀሐይን ብርሃን በእጃቸው ሰብስበው የጨበጡ” የመሰላቸውና “ጊዜ የፈቀደላቸው ጀግኖችም” ከትምክህታቸው ሰብሰብ ካላሉ አወዳደቃቸው እንደማያምር ከጠዋቱ ቢገባቸው ያተርፋሉ እንጂ አይከስሩም። የሚያዋጣው “በሠም” የሚመሰለው የፖለቲካ ጊዜያዊ ትርፍ ሳይሆን “በወርቅ የሚመሰለው” የኢትዮጵያዊነት ኩራት ነው።
ይህ ማለት ግን የራስ ቋንቋ፣ የራስ ብሔር፣ የራስ ባህልና ታሪክ ተጨፍልቆ ህልውናው ይጥፋ ማለት አይደለም። ኢትዮጵያ በኅብር ቅኔነት እንድትመሰል ያደረገው ይህንን መሰሉ ብዙኅነት ስለሆነ ልዩነቱ ውበትም ነው።
ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ፣ ከመሃል እስከ ዳር በተዘረጋው ድንበሯ ውስጥ ተዘልለው የሚኖሩት ብሔረሰቦቿ ለኢትዮጵያ ድምቀቷና ውበቷ ናቸው። እውነታው ይህ ሆኖ እያለ አንድን ብሔር ብቻ መዞ ከፍታ ላይ ለማቆም መሞከር አወዳደቅን ያከፋ ካልሆነ በስተቀር የኩራት መገለጫ ሊሆን አይችልም።
ዛሬ ዛሬ እየተደመጡ ያሉ አንዳንድ ጫጫታዎች ይህንን “ኅብር ቅኔ ኢትዮጵያዊነት” ለጊዜው ያሳደፉ ይምሰል እንጂ ዘላቂነት የላቸውም። ከቆሸሸ ኅሊና የሚወጡ ቆሻሻ ድምጾች በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ሲያስተጋቡ ማድመጥ እንግዳችን ባይሆንም ከጊዜያዊ ቅዠት የሚዘሉ እንዳይደሉ ግን የኢትዮጵያዊነት አቅም በራሱ ምስክር ነው።
ኢትዮጵያ እንድትፈራርስ የሚፈልጉ “ንዑስ ሰብዓዊያን” ወደ ቀልባቸው የተመለሱ ዕለት በፀፀት መቀጣታቸው ስለማይቀር ያንን የውርደት ዋዜማቸውን በትዕግሥት መጠበቅ ጥበብና ማስተዋል ነው።
ግፈኞች ግፍ የጨለጡበትን “ባዶ ዋንጫ” ከፍ አድርገው ውርደትን እንደ ክብር እየዘመሩ “ዋንጫ ኖር! Cheers!” እየተባባሉ ከበሮ መደለቃቸው የዕለት እብደታቸውን ለመግለጽ የተጠቀሙበት ዘዴ መሆኑን መረዳት አይከብድም። በኅሊና ስውርነት ይህንን የሚያደርጉት አወዳደቃቸውና ፍጻሜያቸው እንደማያምር በራሳቸው ድርጊት ማረጋገጣቸው ስለሆነም ለግርምት አይዳርግም።
ኢትዮጵያ ለከት በሌለው የከንቱዎች የአንደበት ጅራፍ ለመገረፍ ጀርባዋን የምታዞር በደለኛ አይደለችም። ኢትዮጵያ ቅኔ ነች። ያውም የረቀቀች ምሥጢር። ኢትዮጵያ በፈጣሪ ጣቶች የተቀረጸች እንቁ ነች የሚባለውም “ንግግር ለማሳመር፤ ጽሑፍ ለማድመቅ” ስለተፈለገ ሳይሆን የተፈተነና የተረጋገጠ እውነት ስለሆነ ነው። ሰላም ይሁን!
አዲስ ዘመን ጥር 29/2013