ፍቅሬ አለምነህ
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሀገርና ሕዝብን ከማንኛውም አይነት የውጭና የውስጥ ጸረ ሰላም አሸባሪና ከሀዲ ኃይሎች ጥቃት የሕይወት መስዋዕትነት እየከፈለ የሚጠብቅ አለኝታ የሆነ ብሔራዊ ኃይል ነው። የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከአራቱም የሀገሪቱ ማዕዘናት በተውጣጡ የኢትዮጵያ ልጆች የተገነባ በኢትዮጵያ አምሳል የተቀረጸ የኢትዮጵያ ብርቱ ክንድ ነው።
መከላከያ ሠራዊታችን በሕዝብ ልጆች የተገነባ፤ ለዳር ድንበሩ መከበር በቁርጠኝነት ተሰልፎ የቆመ በሀገርና በሕዝብ ላይ የተቃጣውን ማንኛውም አይነት ጥቃት በተፈለገው ግዜ ሰዓትና ቦታ በየትኛውም የአየርና የመሬት ገጽ ተንቀሳቅሶ የሚያመክን በብዙ መስኮች የዘመኑን የቴክኖሎጂ መሣሪያዎችን የታጠቀ ኃይል ነው።
በሀገር ብሔራዊ ጥቅምና በሕዝብ ሰላም ላይ የተነሳና የዘመተን የትኛውንም በእብሪት የተወጠረ ኃይል ተገቢውን እርምጃ በመውሰድ ልኩን እንደሚያሳየው ከቀድሞ ጀምሮ በታሪካችን ውስጥ የታየ ነው።
ጁንታው ራሱን የቻለ ከኢትዮጵያ ውጭ ያለ መንግስት እስኪመስል ድረስ ጠዋት ማታ የጦርነት ነጋሪት እየጎሰመ እጅግ የገዘፈ ወታደራዊ ዝግጅት አድርጎ ኑና ግጠሙኝ እስከማለት ደርሶ ነበር።
ትግራይ መቀበሪያችሁ ትሆናለች ሲል ነበር። በራሱ ትንኮሳ የተጀመረው ጦርነት ትግራይን የጁንታው መቀበሪያ አደረጋት።የጁንታው ኃይል የደረሰበት በታሪክ ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ ውድቀትና ውርደት ለዚህ አባባል ጥሩ ማሳያ ነው።
የሰሜን እዝ ሠራዊት ሀገሬ ወገኔ ብሎ በሰላም ባለበት የራሴ ወገን እንዲህ አይነት አረመኔያዊ ድርጊት ይፈጽምብኛል ብሎ ቅንጣት አልተጠራጠረም።በከተማ ጦር ሰፈሩ በየበረሀውም በያዘው የመከላከያ ይዞታ ላይ እያለ በከሀዲው የጁንታው ኃይል የተፈጸመበት ዘግናኝ አረመኔያዊ ወንጀልና ጥቃት በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የተፈጸመ ወንጀልና ጥቃት ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብም ዳር እስከዳር አስገምግሞ የተነሳው በጁንታው አማካኝነት በልጆቹ ላይ የተፈጸመው ግፍ በደል ጭፍጨፋ አስቆጥቶት ነው። በአስከፊ ታሪክነቱ ለትውልድም ገና ይተላለፋል።
ጁንታው የኢትዮጵያ መንግስት በሰፊው ለሰላም የዘረጋውን እጅ በንቀት ተሞልቶ ነክሶታል። የሀይማኖት አባቶችን የእናቶችን የአዛውንቶችን ሽምግልና በእብሪት ረግጦታል። ለሰላም በተሰጣቸው ግዜ እነሱ ለሰፊ ጦርነት ተዘጋጅተውበታል።
አስቀድሞ በተጠና በተደራጀ በታቀደ በቂ ዝግጅት በተደረገበት ሁኔታ ቀላልና ከባድ ተሽከርካሪዎችን፤ ከባድ መሳሪያዎችን በድንገት ከሠራዊታን ላይ በመዝረፍ ሰራዊቱን በማገት እሺ ያለውን ከጎናቸው በማሰለፍ እምቢ ያለውን በመግደል እቅዳቸውን ለማሳካት ተንቀሳቅሰዋል።
ጁንታው በመላው ትግራይ በነበሩ እግረኛ ክፍለጦሮች፤ ታንከኛና ሜካናይዝድ ኃይሎች፤ የሚሳኤል ምድብተኞች፤ የሕክምና ትጥቅና ስንቅ ክፍሎች በሌሎችም ላይ የውስጥ ከሀዲዎችንና ባንዳዎችን በመጠቀም ወረራ አድርጎ ሠራዊታችንን በተኛበት ረሽኖታል;። ልብስና ጫማውን አስወልቀው በባዶ እግሩ በመቀሌ ከተማ ሕዝብ እያየ እየተሳለቀባቸው እንዲሄዱ አድርጓል።
ሠራዊታችን ያለውን እያካፈለ እየቆረሰ ችግረኞችን እየረዳና እያስተማረ እያበላና እያጠጣ ሳይተርፈው ሳይደላው ወገኖቼ ብሎ ያለውን ሲያካፍል ለኖረበት ትምህርት ቤቶችን እያዋጣ ለገነባበት፤ ሰብል ስብሰባ ወጥቶ ለሰበሰበበት፤ አምበጣ ሲመጣ ለተከላከለበት ታላቅ ሕዝባዊ ስራው በከሀዲ ጁንታዎቹ የተሰጠው ምላሽ በሞት መቀጣት መረሸንና መዋረድ ሆነ። ገድለውት በሬሳው ላይ ተሳለቁ።
ጨፈሩበት። በሥርዓቱ እንዳይቀበር አደረጉት። በሴት ወታደሮች ብልት ውስጥ ቢላ ከተቱ።ጡታቸውን ቆረጡ። አረዷቸው። የጁንታው ድንቁርና ማሳያ ምን ይመጣብኛል፤ ምንስ ይከተላል ብሎ አለማሰቡ ነው። ሠራዊቱ ታላቅ ወገን፤ ታላቅ ደጀን፤ጥቃቱን የሚወጣለት ታላቅና ጀግና ሕዝብ እንዳለው ጁንታውን መልሶ አፈር እንደሚያስግጠው የታወቀ ነበር። እናም ሆነ።
እንደነሱማ ቢሆን ኖሮ ያንን ሁሉ ከባድና ቀላል መሳሪያ ነጥቀው ሜካናይዝድና ሞተራይዝዱን፤ አየር መቃወሚያውን፤ ታንክና መድፉን ቢኤሙን ዘርፈው ከታጠቁ በኃላ አዲስ አበባ በ3 ወር ውስጥ እንገባለን ብለው ነበር የተዘጋጁት።
ኢትዮጵያ በታሪኳ ጁንታውን የመሰለ ከሀዲ ባንዳ አረመኔ የዘር ጭፍጨፋ ያካሄደ አይታም ሰምታም አታውቅም። ወድቃችሁ ተነሱ የሚላቸው ስለሌለ ነው ሀገረ ትግራይን እንመሰርታለን ፤ራሳችንን ችለን እንቆማለን ሲሉ የነበሩት። ጉራ መቸም አይገድምና። በቁጥር አነስተኛ መሆናቸውን ስለሚያውቁ እኛ ኢትዮጵያን ካልመራን ካላስተዳደርን ቀጥቅጥን ካልገዛን ኢትዮጵያ ትውደም፤ ትጥፋ ትበታተን የሚለውን አቋማቸውን ከጥንት እስከዛሬ
ገፍተውበታል። በዚሁ እኩይና ለዘመናት ባራመዱት መሰሪ ሴራና አላማቸው የተነሳ ተቀብረውበታል። ልካቸውን ካለማወቅና ከተስገበገበ የኢኮኖሚ ፍላጎታቸው የተነሳ የመጣ ችግር ነው ይዞአቸው የጠፋው።
እንግዲያውማ ተከባብሮ ተቻችሎ መኖሩ ነበር የሚበጀው። በባዶ የተገነባው ጀግኖች ነን፤ ከእኛ በላይ ወንድና ጀግና በኢትዮጵያ የለም አይፈጠርም የሚለው ትዕቢታቸው በጀግናው መከላከያ ሠራዊታችን ብርቱና ፈርጣማ ክንድ ወደ ትቢያነት ተለውጦአል።ለውድቀት በቅተዋል።
ሲያንቀዠቅዣቸው ዘለው የሰሜን እዝን ደፈሩ። አጠቁ። በየትም ዓለም በዚህ መልኩ ተሞክሮም ሆነ ተከስቶ አያውቅም። ሠራዊቱን በዘር ከፋፍሎ ለማፋጀት ያደረጉት ሰፊ ጥረትም መከነ። የእነሱኑ ሞት አፋጠነው። በዚህም እኩይ ስራቸው በኢትዮጵያና በዓለም ሕዝብ ፊት ተዋርደዋል።
ከከፍተኛ መንግስታዊ ስልጣን በአንዴ ወርደው ወደተራ የመንደር ሽፍታነት ተለውጠው ያገኙትን ሁሉ ዘርፈው ተራራ ውስጥ ቆፍረው ቀብረው እነሱም እንደ ጦጦና ዝንጀሮ በየገደላገደሉ ተንጠልጥለው መሽገው ነበር።
እየታደኑ እየተለቀሙ ተይዘዋል። ታሪካቸው በውርደት ተደምድሞአል።እንዲህ አይነቱ ነገር በዘራችሁ በትውልዳችሁ አይድረስ የሚባለው አይነት መዋረድ ውስጥ ነው የወደቁት። ክፉዎች በስራቸው ይዋረዳሉ የሚባለው ቃል ይሄ ነው።
የዘረፉት አልበቃ ብሎአቸው እኛ ካልመራን ኢትዮጵያ እናጠፋታለን እስከማለት ደርሰው ነበር። ደግነቱ በራሳቸው ስራ ጠፉ። ግፋቸው አጋልጦ ሰጣቸው። እብሪታቸው አዋረዳቸው። እንበትናታለን ያሏት ኢትዮጵያ እነሱ ሲበተኑና ሲጠፉ ሲዋረዱ ቆማ አየች። ጁንታዎቹ የሰሩት ግፍና የግፍ ግፍ ገና ለትውልዳቸው የሚያልፍ እርግማን የተሸከመ መሆኑን ያወቁት አይመስልም።
በዚያ ሁሉ የሰሜን እዝ ሠራዊት ላይ የተፈጸመው ወሰንና ድንበር የሌለው ግፍ ገና በመጽሐፍ ታትሞ በፊልም ተቀርጾ ለአደባባይ ይበቃል። ሠራዊት የሀገር ክብር ነው። ሕይወቱን አሳልፎ እየሰጠ ሀገርና ሕዝብ የሚጠብቅ ነው።
አይነካም። አይደፈርምም። የጁንታውን እብሪትና ድንፋታ ሰባብሮ በመጣልና በመደምሰስ ረገድ ሠራዊታችን ዘመን ተሻጋሪ የጀግንነት ስራ ሰርቶአል። ሀገራችንን ከተደቀነባት የመፈራረስ አደጋ ታድጓታል። ልናከብረው ልናወድሰው ይገባል።
አዲስ ዘመን ጥር 29/2013