ይበል ካሳ
ባለፉት ሦስት አስርተ ዓመታት ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ስለመግባት፤ ስለ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር አብዝቶ ተወርቷል። ኢኮኖሚያዊ ሽግግሩን ዕውን ለማድረግ ደግሞ የግብርናውን ዘርፍ ማዘመን ዓይነተኛው መንገድ መሆኑም ተገልጿል።
የግብርና መር ኢንዱስትሪያዊ የኢኮኖሚ ሞዴልም ፖሊሲ አድርጎ ከማውጣት በቀር ሊተገብረው አልቻለም። በመሆኑም ባለፉት 27 ዓመታት ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል ቢባልም ግብርናን ለማዘመን የተደረገው ጥረት የሚፈለገውን ያህል ለውጥ ማምጣት ሳይችል ቀርቷል።
ለዚህም በርካታ ነጥቦችን በምክንያትነት ማቅረብ ቢቻልም የሚሰሩት ሥራዎች የጉዳዩ ዋነኛ ባለቤት የሆነውን አርሶ አደሩን በበቂ ሁኔታ ያሳተፉ አለመሆናቸው እና ለዘርፉ ትኩረት ተሰጥቷል ቢባልም ግብርናው የሃገሪቱ ኢኮኖሚ ተሸካሚ ምሰሶ ከመሆኑና መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግሩን ለማምጣት ዋነኛው ሞተር ከመሆኑ አኳያ የተሰጠው ትኩረት እጅግ አናሳ ነው የሚለው ብዙዎችን ያስማማል።
ትኩረት መስጠት ሲባል ደግሞ በዋነኝነት ለዘርፉ የሚመደበው በጀትና በቂ ፋይናንሲንግ መሆኑንም የኢኮኖሚና የፋይናንስ ጠበብት ይመሰክራሉ። ለአርባ አምስት ዓመታት ያህል በማስተማር፣ በኢኮኖሚ አማካሪነትና በልዩ ልዩ ኃላፊነቶች የቆዩት የኢኮኖሚ ምሁሩ ፕሮፌሰር ፍስሐጽዮን መንግስቱ ግብርናን ጨምሮ ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል ተብለው የተለዩ ዘርፎች የሚጠይቁትን የፋይናንስ አቅርቦት በማሟላት ረገድ ችግር መኖሩን ጠቁመው የግብርናው ዘርፍ ግን ከሁሉም የከፋ መሆኑን ያመለክታሉ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአገልግሎት ዘርፉ እየበለጠ ቢመጣም አሁንም ድረስ ከሃገሪቱ ጠቅላላ ኢኮኖሚ እስከ 35 በመቶ የሚሆነውን የምርት ድርሻ የሚሸፍነውን፤ ከምንም በላይ ደግሞ እስከ 80 በመቶ የሚሆነውን የአገሪቱን የሠራተኛ ኃይል የተሸከመውን እንዲሁም ደግሞ ከሃገሪቱ የወጪ ገቢ ንግድ እስከ 95 በመቶ የሚሆነውን የሚሸፍነው የግብርናው ዘርፍ ነው።ሆኖም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ለዘርፉ የሚቀርበው የፋይናንስ ድጋፍ በእጅጉ አናሳ መሆኑንና ለአብነትም በብድር መልክ የሚሰጠው ገንዘብ ከአስር በመቶ በታች እንደነበረ የኢኮኖሚና የፋይናንስ ባለሙያው ያስታውሳሉ።
ይሁን እንጅ የሃገሪቱ ኢኮኖሚ ዋልታና ማገር የሆነውን የግብርናውን ዘርፍ በበቂ ሁኔታ በፋይናንስ መደገፍ፣ ማሳደግና ማዘመን ካልተቻለ አሁንም ቢሆን ሃገሪቱ ለረጅም ጊዜ ስታልመው የቆየችው መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር እውን ማድረግ አይቻልም ።
በዚህ ረገድ የለውጡ መንግስት በፕላን ኮሚሽን አማካኝነት ባዘጋጀው የአስር ዓመቱ የልማት ዕቅድ ለግብርና ዘርፍ የሚሰጠውን ብድር እስከ አስራ ሰባት በመቶ ለማድረስ መወሰኑና፣ ዘርፉን ለማዘመን የሚደረገውን ሥራ ስኬታማ ለማድረግ በቂ ፋይናንስ ለማቅረብ ራሱን የቻለ የግብርና ባንክ ለማቋቋም ማቀዱ ይበል የሚያስብል እርምጃ መሆኑን ያመላክታሉ።
በቀጣይም የአስር ዓመቱ የልማት ዕቅድ የታለመለትን ግብ እንዲመታና ሃገሪቱ የያዘችውን መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ዕውን ማድረግ ይቻል ዘንድ መንግስት ከዚህም በላይ ግብርናውን ለማዘመን ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይገባዋል።ለዚህም መንግስት የአገር ውስጥ ብድር አቅርቦትን በተመለከተ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የዘርፉን አካላት እንዲሁም የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴርን፣ ብሔራዊ ባንክ፣ ልማት ባንክ፣ ንግድ ባንክና ሌሎችንም የግል ባንኮች እንዲሁም በጉዳዩ ላይ ጥልቅ ዕውቀት ያላቸውን ምሁራን በማካተት ሁሉንም ባለ ድርሻ አካላት ያሳተፈ የሰለጠነ ውይይት ማድረግ የሚገባው መሆኑን ባለሙያው ይመክራሉ።
በውጭ ምንዛሪ አቅርቦት በኩል ስላለው ጉዳይ ግን “የመንግስትን ችግር መገንዘብ ያለብን ይመስለኛል፤ መንግስት ከአቅሙ በላይ ሊሄድ አይችልም” ይላሉ የኢኮኖሚ ባለሙያው ፕሮፌሰር ፍስሐጽዮን። በእርግጥ ተበድሮም ቢሆን የውጭ ምንዛሪውን ለማቅረብ ቢሞከር እንኳን ለአገሪቱ ቀጣይነት ያለው ዘላቂ ልማት የማምጣቱ ጉዳይ ግን ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ይሆናል።
ልማት ባንክ ለውጭ ኢንቨስተሮች 70 በመቶ ብድር ይሰጥ እንደነበር የሚያስታውሱት ፐሮፌሰር ፍስሐጽዮን “እኛ እኮ የውጭ አገር ኢንቨስተሮችን የምንፈልገው የራሳቸውን የውጭ ምንዛሪ ይዘው እንዲመጡ ነው እንጂ ከእኛ የሚበደሩ ከሆነማ ምን ኢንቨስት አደረጉ ይባላል? እንዲህ ከሆነማ የአገራችን ባለ ሃብቶች ማሳደጉ አይሻልም ወይ” የሚሉ ብዙ ሰዎች መኖራቸውን ይናገራሉ።
በዚህ ረገድ ከውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ጋር ያለውን ችግር ለመፍታት ለውጭ አገር ባለሃብቶችና ኢንቨስተሮች የሚሰጠውን ብድር ማጤን እንደሚያስፈልግም በአስተያየታቸው ጠቅሰዋል። ዘላቂና ቀጣይነት ያለው ልማት ሊመጣ የሚችለው በመንግስት፣ በአገር ወዳድ ባለ ሃብቶችና ምሁራንና በህብረተሰቡ ትብብር መሆኑን የሚያመላክቱት የኢኮኖሚ ባለሙያው በዚህ ረገድ የውጭ ባለ ሃብቶች አያስፈልጉም ማለት ሳይሆን የውጪ ኢንቨስተሮችና የአገር ውስጥ ባለሃብቶች በአንድ ዓይን መታየት የሌለባቸው መሆኑንም ይጠቁማሉ።
በዚህ ረገድ አሁን በሃገሪቱ የመጣውን የፖለቲካ ለውጥ ተከትሎ ከሚያዚያ 2010 ጀምሮ ሃገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በመካሄድ ላይ ይገኛል። የዚሁ ሃገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አካል የሆነውና በፕላን ኮሚሽን የተዘጋጀው የአሥር ዓመቱ የልማት ዕቅድም ከዚህ ቀደም ያልተሞከሩ የኢኮኖሚ ልማት ዕድሎችን ጥቅም ላይ በማዋል አዲስ ራዕይ ሰንቆ የተነሳና ሃገሪቱን ወደ አዲስ የዕድገት ምዕራፍ ለማሸጋገር ያለመ መሆኑንም መንግስት የአሥር ዓመቱ የልማት መሪ ዕቅዱን አስመልክቶ ከልማት አጋሮችና ከለጋሽ አካላት ጋር በተወያየበት ወቅት ገልጿል።
የልማት ዕቅዱ በዋነኝነት ለዘመናት የማይለዋወጠውንና ለውጥም ማምጣት ያልቻለውን የሠራተኛ ኃይል ከግብርናው ዘርፍ እንደ አምራች ኢንዱስትሪውና አገልግሎት የመሳሰሉ ግብርና ወዳልሆኑ ዘርፎች በማሸጋገር መዋቅራዊ ኢኮኖሚያዊ ሽግግር ማምጣትና ሁለንተናዊ ዕድገቱ የተረጋገጠለት የተረጋጋና ሰላማዊ ሕብረተሰብ መፍጠርን ዓላማ መሆኑን የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ፍጹም አሰፋ ለዓለም አቀፍ የልማት አጋሮችና ለጋሾች ተገልጾላቸዋል። ለዚህም ግብርናውን በሂደት በኢንዱስትሪ በመተካትና ኢኮኖሚውን ዓለም ዘመናዊው ዓለም በሚጠቀምበት ኢንዱስትሪ መር ፍልስፍና መምራት የግድ መሆኑን በዘርፉ የተደረጉ በርካታ የጥናት ውጤቶች ያመለክታሉ።
ከዚህ አኳያ በቅድሚያ ሰፊውን የሠራተኛ ኃይል የያዘውንና ዋነኛው የሃገሪቱ የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆነውን የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን መንግስት ከዚህ ቀደሙ በተለየ ለፋይናንስ አቅርቦት ትኩረት አድርጎ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል። በአስር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ ላይ ከዓለም አቀፍ የልማት አጋሮችና ለጋሽ አካላት ጋር የተደረገው ውይይትም የዚሁ ዕቅድ አንድ አካል መሆኑን ኮሚሽነሯ ይገልጻሉ። ውይይቱ ለእቅዱ ማስፈጸሚያ በሚያስፈልገው የፋይናንስ አቅርቦት ላይ የለጋሽ አካላትን ድርሻ ለይቶ ለማወቅና ሊያጋጥሙ የሚችሉ እጥረቶችን ከወዲሁ ታሳቢ አድርጎ በራስ አቅም ላይ ትኩረት አድርጎ ለመሥራት ታስቦ የተካሄደ ነው።
ግብርናን በማዘመንና በኢንዱስትሪ የሚመራ መዋቅራዊ ኢኮኖሚያዊ ሽግግር መፍጠርን ዋነኛ ትኩረቱ ያደረገው የአስር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ የመጨረሻ ግቡ ኢኮኖሚውን ዓለም በደረሰበት የእድገት ደረጃ ማድረስና ብሎም ብቁና ተወዳዳሪ በማድረግ ሁለንተናዊ ዕድገቱ የተረጋገጠ ፣ የተረጋጋና ሰላማዊ ሕብረተሰብ መፍጠር ነው።
አዲስ ዘመን ጥር 28/2013