በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com
(ክፍል ሦስት )
በዚሁ ጋዜጣ ሁለት ተከታታይ መጣጥፎች ስለ ከሀዲውና እፉኝቱ ትህነግ/ህወሓት አመሰራረት ታሪካዊ ዳራ እንዲሁም ለውድቀት ያበቁትን ነጥቦች አንስቻለሁ። በዛሬው የመጨረሻ ሶስተኛ ክፍል ደግሞ ትህነግን ለውድቀትና ፖለቲካዊ ራስን በራስ ማጥፋት የዳረጉትን ተጨማሪ ሶስት ምክንያቶችን አነሳሳለሁ።
ከዚህ በቀደመውና በክፍል ሁለት መጣጥፌ የጠራና ወጥ የፖለቲካ ፕሮግራም አለመቅረጽ እና ትህነግ ከውልደቱ አንስቶ በሕገ ወጥ ተግባር በሽቅጦ መገኘቱ ለውድቀቱ ምክንያት መሆናቸውን አንስቻለሁ።
በዛሬው መጣጥፌ በይደር ያቆየኋቸውን ለውድቀት ያበቁትን ማለትም 1ኛ. የመወዳደሪያ ስትራቴጂ መክሸፍ ፤ 2ኛ . በፓርቲዎች ውስጥ የሚፈጠሩ መከፋፈሎች የሚፈቱበት አግባብ፤ 3ኛ. የፓርቲው የአደረጃጀትና አወቃቀር ድክመት የሚሉትን አነሳና በመጨረሻ የፓርቲውን የ46 አመታት ባተሌ አካሄድ በወፍ በረር እቃኛለሁ ።
1ኛ. የመወዳደሪያ ስትራቴጂ መክሸፍ ፤ ትህነግ/ኢህአዴግ ነጻ ፣ ፍትሐዊ ፣ ዴሞክራሲያዊ ፣ ግልጽና አሳታፊ ምርጫ አካሂዶ አያውቅም ማለት ይቻላል ። የ97ቱ ምርጫም ቅድመ ምርጫ ሒደቱ ከቀደሙት አንጻራዊ ነጻነት የተስተዋለበት የነበረ ቢሆንም ድህረ ምርጫው ኮሮጆ በመገልበጥ ፣ በማጭበርበር፣ አሸንፌያለሁ ያለውን የቅንጅት አመራር ጠራርጎ ዘብጥያ በማውረድ ፣ አዲስ አበባ ላይ ድምጻችን ይከበር ብለው ለሰላማዊ ሰልፍ የወጡ ወጣቶችን በአጋዚ ልዩ ኃይል በአደባባይ ጨፈጨፈ። ታሪክም ትውልድም ይቅር በማይለው በዚህ ጭፍጨፋ በመቶዎች የተቆጠሩ ወጣቶች ህይወት ተቀጠፈ።
በአስር ሺዎች የሚገመቱ ለጅምላ እስርና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተዳረጉ። በኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይ በአዲስ አበባ ነዋሪ ላይ የበቀል መዝገብ ተከፈተ። ዜጎች በልማት ስም ከሰፈራቸው ተነቀሉ። ለለየለት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ ተዳረጉ።
ፖለቲካዊ ምህዳሩ ከቀደሙት አመታት በከፋ ተከረቸመ። ከዚያ በኋላ በተካሄዱት ሁለት መረጣዎች /selection/ መራጭም ፣ ታዛቢም ፣ ምርጫ አስፈጻሚም፣ ተወዳዳሪም፣ ፖሊስም ፣ ዳኛም ፣ አቃቤ ሕግም ሆኖ ተውኗል።
መረጣ እያልሁ የምጠራው አምስቱም ምርጫዎች ዝቅተኛውን የቅድመም ሆነ ድህረ ምርጫ መመዘኛ ስለማያሟሉ ነው። ይህ የሚያሳያው ትህነግ/ኢህአዴግ ከማጭበርበርና ኮሮጆ ከመገልበጥ ውጭ ይህ ነው የሚባል የምርጫ እስትራቴጂ እንዳልነበረው የሚያሳይ ነው።
አለው ከተባለም እንዴት ለብቻው ሩጦ አሸናፊ መሆን እንደሚችል የአፈና መዋቅሮቹን ስምሪት የመስጠት የአፈና ስትራቴጂ ነው። እንግዲህ ይህ የአፈና ስትራቴጂው ነው ትህነግን ዛሬ ለሚገኝበት አሳፋሪ ውድቀት እና ራስን በራስ ማጥፋት የዳረገው።
2ኛ . በፓርቲዎች ውስጥ የሚፈጠሩ መከፋፈሎች የሚፈቱበት አግባብ ፤ በፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ በርዕዮት አለም ፣ በትግል ስትራቴጂና ፖሊሲ ልዩነት ፣ ለስልጣን በሚደረግ ሽኩቻ ፣ ወዘተረፈ መከፋፈልና መሰንጠቅ የተለመደ ነው።
የአሜሪካ ዴሞክራትና ሪፐብሊካን ፓርቲዎች በራሳቸው ውስጥ የግራ አክራሪና ለዘብተኛ እንዲሁም የቀኝ አክራሪና ለዘብተኛ የሚሉ አሰላለፎች ቢኖርም በፓርቲው መሠረታዊ መርሆዎች ላይ ግን ብዙም ልዩነት የላቸውም ። በ2016 እኤአ ዶናልድ ትራምፕን ወደ ስልጣን ያመጣው የኒውት ጊንጊሪች
ቀኝ አክራሪና ዲሞክራቶችን በተፎካካሪነት ሳይሆን በጠላትነት ፈርጆ የሚያሰይጥነው ውጥን ነው። በእነ ማካርቲ የሴራ ኀልዮት ትርክት የተቃኘ። ለነጻ ገብያ፣ ለሕገ መንግስቱና ለዴሞክራሲያዊ ተቋማት ታማኝ የነበረውን የእነ ሬጋንን ሪፐብሊካን ነው ትራምፕ ወደ ቀኝ አክራሪነት ስቦ ስቦ በመዳፉ ያስገባው።
ዛሬ የሪፐብሊካን ፓርቲ በትራምፕ ሳንባ ነው የሚተነፍሰው። እድሜ ለትራምፕ ታፍሮና ተከብሮ የኖረውን የዴሞክራሲ ተቋም ጥያቄ ላይ ወድቋል። ወደ 250 አመታት ለሚጠጋ ጊዜ የተገነባው ዴሞክራሲ ለአደጋ ተጋልጧል። በሀገሪቱ ታሪክ በ150 አመታት ውስጥ ሽንፈቱን አልቀበልም ያለና በአሸናፊው በዓለ ሲመት ያልተገኘው እንዲሁም የምርጫውን ውጤት በማስፈራራትና በኃይል ለመቀልበስ የሞከረው ትራምፕ
ነው። የትራምፕ ደጋፊዎች የካፒቶል ሒሉ ጥቃት አለምን በድንጋጤ ራስ ያስያዘ ታሪካዊ ጠባሳ ነበር። በአንድ በኩል የአሜሪካ ዴሞክራሲ የተፈተነበት፤ በሌላ በኩል በአሸናፊነት የወጣበት በሚል በታሪክ መዝገብ ተከትቧል። የዴሞክራሲ ተቋማት ምንም ያህል በጽኑ መሠረት ላይ የቆሙ ቢሆንም እንደ ትራምፕ ያለ መርህ አልባ ሲገጥማቸው እንዴት እንደሚፈተኑ አለም ታዝቧል።
ትራምፕ የአንድ ጊዜ ፕሬዚዳንትና ለሁለተኛ ጊዜ የተከሰሰ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ቢሆንም አሻራውና ጥላው በቀላሉ ከሪፐብሊካኑ መልካዓ ይጠፋል ተብሎ አይጠበቅም። የማንነት ቀውስ ገጥሞታል። በአሜሪካ የጥቁሮች ፣ የስፓኒኮች፣ የሬድ ኢንዲያንስና የሌሎች ህዳጣን ቁጥርና ስብጥር መጨመር ወይም እየተፈጠረ ባለ ቀጣይና ተከታታይ የዴሞግራፊ ለውጥ የተነሳ ሪፐብሊካኖች በቀላሉ ወደ ስልጣን ይመጣሉ ተብሎ አይጠበቅም። ዩናይትድ ኪንግደም ሌበርና ኮንሰርቫቲቭ ፓርቲዎችም ተመሳሳይ ውስጠ የአሰላለፍ መሳሳብ ይስተዋልባቸዋል።
የዩናይትድ ኪንጊደምን ከሕብረቱ ለመነጠል ሽንጡን ገትሮ ሲከራከር የነበረው ወግ አጥባቂው የኮንሰርቫቲቭ ፓርቲ ወግ አጥባቂ ነበር። ለዘብተኛው ዴቪድ ካሜሩን በአንድ በኩል ወግ አጥባቂው ቦሪስ ጆንሰን በተቃራኒው ተሰልፈው ነው። ከሕብረቱ መነጠልን በመደገፍና በመቃወም።
ወደ ትህነግ ስንመጣ ሕንፍሽፍሽ ፣ መከፋፈል፣ እንደ ግራምጣ መሰንጠቅና በአንጃ መፈልፈል የሚታመሰው በርዕዮት አለም ልዩነት ወይም በግራ አክራሪነት ወይም ለዘብተኝነት አይደለም። በተመሰረተ አመት ሳይሞላው በ1968 ዓ.ም ፣ በ1971 ዓ.ም ፣ በ1977 ዓ.ም፣ በ1980ዎቹ ፣ በ1993 ዓ.ም እና በመጨረሻም በ2010 ዓም በተከታታይና በተደጋጋሚ የተከሰቱ መከፋፈሎች መገፋፋቶች በርካታ ቢሆኑም ዋና ዋናዎቹ ግን ኢ ዴሞክራሲያዊነት ፣ አውራጃዊነት ፣ ሴረኝነትና ሙስና ናቸው። ትህነግ በእንቅርት ላይ ቆረቆር እንዲሉ ከፍ ብለው ለተዘረዘሩት ይፋዊና ሕቡዕ ክፍፍሎች መንስኤ የሆኑ ምክንያቶችን መልሶ ክፍፍሎቹን ለመፍታት መጠቀሙ ነው።
አልበርት አነስታይን ከታላላቅ ግኝቶቹ ከአንጻራዊ እይታ ፣ ለአቶሚክ ቦንብ መገኘት ፈር ቀዳጅ ከሆነው ቀመርና ከሌሎች ፈጠራዎቹ ባልተናነሰ እኩል የሚታወሱለት ድንቃ ድንቅ አባባሎች አሉት። ከእነዚህ ውስጥ በተደጋጋሚ የሚጠቀስለት” ችግሩን በፈጠረው አስተሳሰብ ፤ ችግር መፍታት አይቻልም ።
“ ትህነግ ግማሽ ክፍለ ዘመን ለሚጠጋ ጊዜ ዛሬን ጨምሮ ችግሩን በፈጠሩ አስተሳሰቦች ነው ችግሩን ለመፍታት የሚማስነው። ኢ ሕገ መንግስታዊነት ፣ የፈጠራ ትርክት፣ ፈላጭ ቆራጭነት ፣ ክህደት ፣ ዘረፋ ፣ ሴራ ፣ ስልጣን አምላኪነት ፣ ተቸካይነት ፣ ኢ ቅስማዊነት ፣ ቂም በቀል፣ ጥላቻ ፣ ውሸት ፣ ጎጠኝነት ፣ ወዘተረፈ የፈጠሩትን ቀውስ መልሶ በራሳቸው ሊፈታው የሞከረበት አግባብ የውርደት ከል አከናንቦታል።
የሀፍረት ትቢያ አስነስንሶታል። በትህነግ ውስጥም ሆነ በኢህአዴግ አልያም በብልፅግና ውስጥ የተከሰቱ ክፍፍሎችን ለመፍታት የሞከረው እሾህን በሾህ እንዲሉ ክፍፍሉን በነበሩት ችግሮች መሆኑና ከተደጋጋሚ ጥፋቱና ስህተቱ ለመማር ዝግጁ አለመሆኑ መቀመቅ አውርዶታል። ራሱን በራሱ አጥፍቶታል። ለሀገሪቱ ፖለቲካ ከውድቀት መማሪያ የሚሆን ሌላ ገፅ ጨምሯል።
3ኛ . የፓርቲው የአደረጃጀትና አወቃቀር ድክመት ፤
ትህነግ/ህወሓት የተመሰረተው መሬት በረገጠ ተጨባጭ ሳይንሳዊና ነባራዊ ትንተና አልነበረም። ደደቢት ገብቶ የትጥቅ ትግልን ሲያውጅ ፤ የመጀመሪያውን ጥይት ሲተኩስ ምንም አይነት ፕሮግራም አልነበረውም። አደረጃጀቱና አወቃቀሩ አውራጃዊነትንና ቤተሰባዊነትን መሠረት በማድረግ እንጂ የአባላቱን አቅምና እውቀት ወይም ቁርጠኝነት ከግምት በማስገባት አልነበረም።
አባላቱን ይመለምል የነበረው በማይጨበጥ ተስፋና በማስገደድ ጭምር ነበር። ወደ ድል እየተቃረበ ሲመጣ የተቀላቀሉት አብዛኛዎቹ አባላት እንደ ስራ ዕድል፣ ራስን መጥቀሚያና ከተጠያቂነት ማምለጫ እንጂ በፕሮግራሙ አምነውበት አልነበረም። ብዛት እንጂ ጥራት ጉዳዩ አልነበረም። አባላትን ይመለምል የነበረው በጥቅማ ጥቅም በማባበል እንጂ ርዕዮቱን በማስተዋወቅ አልነበረም።
ወደ አመራርነት ያመጣቸው የነበሩ አባላት የታዘዙትን የሚፈጽሙትን እየመረጠ እንጂ የሚሞግቱትንና የሚገዳደሩትን አልነበረም። ከፍተኛ አመራሩ ለአባሉ አርዓያና ምሳሌ የሚሆን ተክለ ሰብዕና ስላልነበረው ታማኝና ሀቀኛ አባል ማፍራት አለመቻሉ ከውድቀት ሊታደገው አልቻለም።
የፓርቲው መዋቅርም ሆነ አደረጃጀት ስልጣን ላይ መቆየትንና ዘረፋን ግብ ያደረገ እንጂ ሀገርንና ሕዝብን መጥቀም ስላልነበር ለግማሽ ክፍለ ዘመን ለሚጠጋ ጊዜ የገነባው ሁሉ የእምቧይ ካብ ሆኖ ቀርቷል። ነጮች እንደሚሉት የተቀረው ታሪክ ነው። ለዛውም ወራዳና አሳፋሪ ታሪክ።
እንደ መውጫ
በሀገሪቱ የፖለቲካ ፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ መድረክ ያለ ከልካይ በማንአለብኝነትና በማን አህሎኝነት አዛዥና ናዛዥ የነበረው እፉኝቱና ከሀዲው ትህነግ ባለፈው ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን ዕዝ ፣ በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እንዲሁም በሀገርና በሕዝብ ላይ በፈጸመው ክህደት እና ኃይልን መሠረት ባደረገ የአመጻ ተግባር ላይ በመሳተፉ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕጋዊ ሰውነቱን አጥቶ እንዲሰረዝ ተወስኗል።
ከሽምቅ ተዋጊነት ፣ የሀገር መሪነት ፣ ከዚያም ወደ ክልል አስተዳዳሪነት ወደ ማታም ማምሻም እድሜ ነው ብሎ በቃሬዛና በሳንሳ ወደ ዋሻ በመግባት ፖለቲካዊ መናኝነት መረጠ ፤ በመጨረሻም ሕጋዊ ሰውነትን አጥቶ በተለምዶ እንደሚባለው ወደ ታሪክነት ሊቀየር ጉዞውን አሀዱ አለ።
እነዛ ለዴሞክራሲ ፣ ለነጻነትና ለእኩልነት በየሸለቆው ፣ በየገመገሙና በየሸንተረሩ ወድቀው የቀሩ አንድያ ህይወታቸውን የገበሩ 70ሺህ ትግራዋይ ታጋዮች በስሁል መሪነት ከመቃብር ቀና ብለው የሆነውን ሁሉ ቢመለከቱ ምን ይሉ ይሆን … !? ብሎ ላሰበ የትህነግ ስራ የእግር እሳት ሆኖ እንደለበለበው፣ ጥርሱን እያፋጨ እንዳቃተተ፣ ጨርቁን ቀዳዶና አስጥሎ በትዕቢያ ያንከባልላል።
ሆኖም መጽናኛው የትግራዋይን ልቦና በፍቅር ማሸነፍ ፤ የትህነግን ሰንኮፍ መንቀል ፣ አሻራውን ማንሳት ፣ ርዝራዡን አድኖ ለሕግ ማቅረብ እና የፈጠራና የበሬ ወለደ የመረጃ ጦርነትን በድል ማጠናቀቅና መቋጨት ነው። የትህነግ ጦር ቢደመሰስም፣ መዋቅሩና ተቋሙ ቢፈርስም መርዘኛ አመለካከቱን ማርከስ ላይ በቀጣይ ተናቦና ተቀናጅቶ መስራትን ይጠይቃል። ለአፍታ መዘናጋት የከፋ ዋጋ ያስከፍላልና።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በጀግኖችና በሀቀኛ ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር !!!
አሜን።
አዲስ ዘመን ጥር 28/2013