ተገኝ ብሩ
ሁለቱም በብዙ መልኩ ይመሳሰሉብኛል። ሁለቱም ይህችን ታላቅ አገር ያልተረዱ ይህንን ጀግና አይደፈሬ ሕዝብ ጠንቅቀው ያልተረዱ እብሪተኞች መሆናቸው አንድ ይሆኑብኛል።የሱዳኑ ፕሬዚዳንት አብደላ ሀምዶክ እና የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሆኖ ያለፈው ዚያድ ባሬ።
ወደስልጣን የወጡበት ሁኔታ፣ ታላቅዋ ኢትዮጵያን ለመፈተን የሞከሩበት አጋጣሚ መመሳሰልና የሁለቱም በዚህች አገር ላይ የፈፀሙት ታላቅ ክህደት።የዚያድ ባሬ መጨረሻ ታውቋል የመሰሉ አብደላ ሀምዶክም ደግሞ መገመት አያስቸግርም።ምክንያቱም ሊዳፈር የሞከረው ኢትዮጵያን የካደው በነፃነት እልፍ ዘመን የተሻገሩ በሉዓላዊነታቸው የማይደራደሩት ኢትዮጵያውያንን ነውና።
ሶማሊያን መንግስት አልባ የአገሪቱን ሕዝብ ደግሞ ተስፋ ቢስ ሆኖ ከ30 ዓመታት በላይ ስርዓት አልበኝነት እንዲሰፍን ምክንያት የሆነው ዚያድ ባሬ ኢትዮጵያን በእብሪቱ ተዳፍሮ አገሩንም መቀመቅ ከቶ በስደት ሞተ።ሶማሊያን በኢኮኖሚ አድቅቆ፣በአገራት ደረጃ የድህነት የታችኛው ወለል ላይ እንድትገኝ ያደረጋት የሶማሊያው እብሪተኛ ዚያድ ባሬ በመፈንቅለ መንግስት ወደ ስልጣን የመጣ ወታደር ነበር።
ሰውዬው እብሪት ያናወዘው፤ስልጣን የጠማው ነበረና በአገሩ በሕገ ወጥ መንገድ የተቆጣጠረው ስልጣን አልበቃህ አለው። ድንበር ተሻግሮ ጎረቤቱና የአፍሪካ የነፃነት አርማ የሆነችውን ኢትዮጵያን መውረር ተመኘ። ከኔ በላይ ማን አለ ብሎ የማትደፈረዋን ታላቅዋ ኢትዮጵያ ላይ ደባ ለመፈጸም ሞከረ። በ1969 ዓ.ም ኢትዮጵያ ላይ ዘመተ።
በቁም ቅዥቱ የማይደረግን ማድረግ የማይሞ ከረውን ለመሞከር ተነሳ። በማይጨበጥ በህልሙ የሳላትን ታላቅዋ ሶማሊያ ለመመስረት አስቦ፤ የአካባቢውን ልዕልና ለመቆናጠጥ በእብሪት ተነስቶ መሐል ኢትዮጵያ አዋሽ ድረስ በመዝለቅ ግዛቱን ማስፋፋት ተመኘ፤ ለዚህም ጦሩን አዘመተ። ነገር ግን የደፈራት ታላቅ አገር ታሪክ ዘንግቶ ነበር። የሕዝብዋን አትንኩኝ ባይነት ሳያውቀው ቀርቶ ፎከረ፤ሸለለም።
በወቅቱ ልክ እንደዛሬው አብደላህ ሀምዶክ የጀመርከው መንገድ አያዋጣህም ተብሎ ተነገረው። የተዳፈርካትን አገር ታሪክ አልተረዳህም፤ ተው ይቅርብህ አሉት ወዳጆቹ። ልክ ዛሬ የሱዳኑን ሀምዶክ አይዞህ እንዳሉቱ ሁሉ ክፉ መካሪዎችም ክፉ ምክርን ለገሱት። ለዚያድ ባሬም ያኔ ጥቂት የኢትዮጵያ ጠላቶች አለንልህ ግፋ በእብሪትህ አሉት።የእብሪት ልቡን አደነደኑት።
ሁሌም ሰላም ወዳድ በሆነችው ኢትዮጵያ፤ ተው ጉርብትናችን አይበላሽ፤ ሰላም ይሻለናል የሚል ሀሳብ ቀረበለት። እሱ ግን ሊሰማ ፈፅሞ አልፈቀደም። በእብሪት ደነፋ ፤ኢትዮጵያ መሐል ድረስ ደርሼ ግዛቴን አስመልሳለሁ አለ።
እንደሱ የሶማሊያ ግዛት መሀል ኢትዮጵያ አዋሽ ድረስ ነው አለ። ልክ እንደዛሬው የአብደላ ሀምዶክ ጦር መሪ ጄኔራል አልቡርሀን የኢትዮጵያን ሁኔታ አጥንተው በሀይል ድንበርዋን ጥሰው ገብተው ሲያበቁ“ኧረ እንደውም ቤኒሻንጉል ሁላ የሱዳን ናት” እንዳለው ማለት ነው።
ያኔ ዚያድ ባሬ ኢትዮጵያን ሲዳፈር ይህቺ ታላቅ አገር ኢትዮጵያ ልክ እንደዛሬው በውስጥ ጉዳይዋ ፈተና የገጠማት ጊዜ ነበር። የእርስ በርስ የፖለቲካ ሽኩቻ የጦዘበትና የተካረረበት ወቅት ነበር። በሰሜን የአገሪቱ ክፍልም የጠነከረ የሰላም እጦት የነበረበት ጊዜ።ለእብሪተኛው ዚያድ ባሬ ይህ ምቹ አጋጣሚ ሆኖ ታየው።
ኢትዮጵያ ባለፉት ወራት የሕግ ማስከበር እርምጃ ለመውሰድ አብዛኛው ጦርዋን በሰሜናዊው የአገሪቱ ክፍል እንዳሰማራችው ሁሉ ያኔም የደርግ መንግስት በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ህወሓት የፈጠረበት ጫና ለመቋቋም የምስራቁ የአገሪቱ ድንበር ይጠብቅ የነበረው 3ኛው “አንበሳ” ክፍለ ጦር ወደ ሰሜን አንቀሳቅሶም ነበር። ለዚያድ ባሬ ይህ ጥሩ አጋጣሚ ሆኖለት ነበር በቀላሉ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ለመጣስ። ዛሬ ሱዳኖች እንዳደረጉት ማለት ነው።
ዚያድ ባሬ አገሪቱ የነበረችበት የውስጥ ችግር ተጠቅሞ፤ ያዋጣኛል ብሎ አስልቶ፤ ኢትዮጵያ ተዳክማለች ዛሬ ጦሬን ባዘምት በቀላሉ ያሰብኩትን አሳካለሁ በሚል ቀቢፀ ተስፋ ሙከራ የማይሞከረውን ሞከረ። ነገር ግን የተዳፈራት አገር ኢትዮጵያ የነካው በሉዓላዊነቱ የማይደራደር ሕዝብ መጨረሻው ውድቀት ሆነ።ያ ሁሉ እብሪትና ድንፋታ በ4 ወር ውስጥ ኢትዮጵያውያን በጋራ ክንድ ደቁሰውት እንዳይነሳ ሆኖ ተቀበረ። ኢትዮጵያም ዳግም በልጆችዋ ሉዓላዊነትዋን አስከበረች።
ዛሬም ከወደ ምዕራብ አቅጣጫ በጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ የሚመራው የሱዳን መንግስት የኢትዮጵያን የውስጥ ችግር መሰረት አድርጎ ዳር ድንበርዋን ተዳፈረ። ልክ ያ ዚያድ ባሬ የኢትዮጵያን ሁኔታን አይቶ እንዳደረገው አብደላህ ሀምዶክ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ግዛት ተሻግሮ ግዛቴ ነውና አለቅም ካለ ወራት ተቆጥረዋል።
ሰውዬው የወረረው ኢትዮጵያን ነው። የተዳፈረው የአፍሪካ የነፃነት ተምሳሌት የጥቁሮች ኩራት የሆኑትን ሕዝቦችን ነው። ስለ ሰላም ቀድመው የሚዘምሩ ካልነኩዋቸው የማይነኩ እንቢኝ ብሎ ለተነኮሳቸው ግን ነበልባል ሆነው በእሳት የሚጋረፉ ጀግኖችን ነው።
በእርግጥ ዛሬ ላይ በዚህች አገር የፖለቲካ አለመረጋጋትና የእርስ በርስ ግጭት እዚያም እዚህም መኖሩ አይካድም። ነገር ግን ከታሪክ እንደምንረዳው ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ጉዳይ በአንድነት ያብራሉ፤በሉዓላዊነታቸው ተከፋፍለው ለሌላ ባዕድ እጅ የሚሰጡ ሳይሆን አብረው ቆመው ሌላውን የሚመክቱ በጋራ ለአገራቸው የሚዋደቁ ናቸው።
የውስጥ ጉዳያቸው ነገ የሚፈታ ጊዜያዊ ትኩሳት መሆኑን አሳምረው ያውቁታል። አንዲት አገራቸው ግን ዘላለማዊ መሆንዋ ለእርስዋ መፅናት አብረው እንደሚቆሙ፤ ለእርስዋ ክብር መረጋገጥ በአንድነት እንደሚተጉ፤የውጪ ጠላት ሲመጣ ተለያይተው እንደማይቆሙ ታሪክ ደጋግሞ አሳይቷል። ነገም የተለየ ነገር አይፈጠርም።ምክንያቱም ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያ ሆነዋል።ዛሬም ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያን ለማቆም ሁሉም በጋራ ዘብ ይቆማሉ።
ይህቺ ታላቅ አገር ታላቅነትዋ በማይመጥኑ ትንንሽ አሳቢዎች ደጋግማ ተፈትናለች። ነገር ግን የገጠሟት ፈተናዎች ሁሉ በልጆችዋ አልፋ ዛሬ ላይ ደርሳለች። ነገም አንድነትዋን ጠብቃ የገዘፈ ስሟን ያህል ታላቅ ሆና ለልጆችዋ ምቹ ለዜጎችዋ መከታ ሆና ትኖራለች።ትላንት ኢትዮጵያን የተነኮሱ በለኮሱት እሳት ተገርፈዋል። የትላንት ታሪክ ሳያውቅ ዛሬም ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያውያንን በእብሪት እዳፈራለሁ ያለ ነገ እራሱ በሀፍረት የሚያሸማቅቀው ታሪክ ይተርካል። በኢትዮጵያውያን ደግሞ እንደተለመደው የድል ዜና ይደመጣል።
አበቃሁ ቸር ይግጠመን
አዲስ ዘመን ጥር 28/2013