የዛሬ ሶስት ዓመት ገደማ ኢትዮጵያ በመንታ መንገድ ላይ ነበረች።በአንድ በኩል ለ27 ዓመታት ያህል በሕዝብ ጫንቃ ላይ የነበረውን ህወሓት መራሹን መንግስት ለማስወገድ በተቀጣጠለው ሕዝባዊ የተቃውሞ አመጽ ሀገሪቱ ወደለየለት መበታተንና መፈራረስ ታመራለች የሚል ስጋት ነግሶ የነበረ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ሀገሪቱን ሲበዘብዝ የኖረው ገዢ ኃይል ተወግዶ ለኢትዮጵያ በአዲስ ዘመን ይመጣል የሚል ተስፋም የጨበጡ ብሩህ አሳቢዎችም አልታጡም።
ኢትዮጵያ አጣብቂኝ ውስጥ በነበረችበት በዚያን ወቅት በዶክተር አብይ የሚመራው የለውጥ መንግስት ለኢትዮጵያውያን አዲስ የተስፋ ውጋገን ይዞ መጣ። በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም በበዓለ ሲመታቸው ወቅት በፓርላማ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያውያን ከልዩነት ይልቅ አንድነትን፤ ከመከፋፈል ይልቅ ሕብረትን እንዲያስቀድሙ መከሩ።
በሀገር ውስጥ ለዘመናት ተዘግቶ የቆየው የዲሞክራሲ በር እንዲከፈት፤እስረኞች እንዲፈቱ፤በውጭ ሲንቀሳቀሱ የቆዩ ተቃዋሚዎች ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው ሀሳባቸውን በነጻነት እንዲያንሸራሽሩ እና የሴቶችን ተሳትፎ የሚያጎለብቱ ስራዎች እንደሚከናወኑ ቃል ገቡ። የኢትዮጵያውያንም ለዘመናት ሲመኙት የኖሩት መንግስት እንደመጣላቸው ሲያውቁ በደስታ ልባቸው ተሞላ። በየክልሉም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ለለውጡ መንግስት ያላቸውን ድጋፍ በሰልፍ ገለጹ።
ባለፉት ሶስት ዓመታት በዶክተር አብይ የሚመራው የለውጥ መንግስት ከሀገር ውስጥ አልፎ በምስራቅ አፍሪካ ሰላም እንዲሰፍን በርካታ ስራዎችን አከናውኗል።ከ20ዓመታት በላይ በጠላትነት ሲተያዩ የነበሩትን ኢትዮጵያና ኤርትራ ወደ ሰላም እንዲመጡ አድርጓል።በተለያዩ ምክንያቶች የተቃቃሩ የጎረቤት ሀገራትን አቀራርቧል።
ከለውጡ በፊት መንታ መንገድ ላይ የነበረች ኢትዮጵያ ዛሬ ስለብልጽግና ማሰብ ጀምራለች።ወደ መኮላሸት ደርሶ የነበረው የህዳሴ ግድብ ዛሬ ሁለቱ ተርባይኖች አገልግሎት ሊሰጡና ብርሃን ሊፈነጥቁ የወራት ዕድሜ ብቻ ቀርቷቸዋል።ኢትዮጵያ በፍጥነት በማደግ ላይ ካሉ ሀገራት ተርታ ዛሬም ተሰልፋለች።
የኮሮና ወረርሽኝ በአለም ሀገራት ኢኮኖሚ ላይ ባመጣው ተጽዕኖ የብዙዎቹ ሀገራት የዕድገት ምጣኔ ከዜሮ በታች በሆነበት ሁኔታ ውስጥ ኢትዮጵያ ከ6በመቶ የዘለለ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማስመዝገብ ችላለች።ባለፉት ሶስት ዓመታት በተደረገው ርብርብም አጠቃላይ ኢኮኖሚው የሶስት ትሪሊዮን ብር ዕድገት ላይ መድረስ ችሏል።
የሸገር ፕሮጀክት እና የእንጦጦ አስደማሚ የቱሪስት መስህቦች ለኢትዮጵያ ሕዝቦች በገጸበረከትነት ቀርበዋል።የኮይሻ፤ የጎርጎራና የወንጪ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ደግሞ መጪውን ጊዜ ሊያደምቁት ተዘጋጅተዋል።
በግብርናው ዘርፍም ቢሆን በኩታ ገጠም ልማት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ አዝመራው ሰምሯል።ለዘመናት ከውጪ ይገባ የነበረውን ስንዴ ምርት በሀገር ውስጥ ለመተካት የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ተደርሷል።
ከሁሉም በላይ ደግሞ ኢትዮጵያን ለ27 ዓመታት ያህል ሲበዘብዝ የኖረውን የህወሓት ቡድን በማስወገድ የለውጡ መንግስት ታሪክ ሰርቷል።ከኢትዮጵያም አልፎ ለምስራቅ አፍሪካ ባለውለታ ሆኗል።
እነዚህና መሰል የለውጡ መንግስት ትሩፋቶች በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ነዋሪዎችን ለዕውቅናና ለድጋፍ እንዲወጡ አስገድዷቸዋል።ዶክተር አብይና እርሳቸው የሚመሩት የለውጡ የመንግስት በጀመሩት የለውጥ ጎዳና እንዲገሰግሱና የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችም እንዲቀረፉ ነዋሪው በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች በነቂስ በመውጣት መልዕክቱን አስተላልፏል።
ታሪካችን መውቀስን እንጂ ማመስገንን አያበረታታም፤ጉድፍ ማውጣት እንጂ ከጉድፉ ባሻገር ያሉ መልካም ጸጋዎችን አሻግሮ አያይም።ይህ ጎታች ባህል ተወግዶ በምትኩ ለሚሰሩ ዕውቅና፤ ለሚተጉ ሽልማት የሚሰጥበትና የሚመሰገኑበት መልካም ዕሴት ሊያብብ ይገባል።ከሰሞኑ በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች ለለውጡ መንግስት የተደረጉት የድጋፍና የዕውቅና ሰልፎች መልካም ጅምሮች ስለሆኑ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል።
አዲስ ዘመን ጥር 28/2013