(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ) gechoseni@gmail.com
ቅድመ ወግ፤
ከሳምንታት በፊት ከአዲስ አበባ ክፍለ ከተሞች ለተውጣጣ የባህል፣ የኪነ ጥበባትና የቱሪዝም ባለሙያዎች ዘለግ ላሉ ሰዓታት የቆየና ከሙያቸው ጋር የተያያዘ ሥልጠና ለመስጠት ዕድል አግኝቼ ነበር።
በከተማው የዘርፉ ቢሮ አስተባባሪነት የማሰልጠኑን ድርሻ የተወጡትና የተሳታፊያኑ ቁጥርና ስብጥር በርከት ያለ ቢሆንም መርሃ ግብሩ በስኬት እንደተጠናቀቀ የመጨረሻው አስተያየት አረጋግጦልኝ ነበር። ነገር ግን ከስኬቱ ይልቅ በልቤ ውስጥ ጎልቶ የተቀረጸው አንድ ወጣት ሰልጣኝ በሻይ እረፍት መካከል ስንወያይ የሰነዘረው አስተያየት ነው።
ወጣቱ በግልጽነትና የቁጭት ስሜት ውስጥ ሆኖ የሰጠው አስተያየት እንዲህ የሚል ነበር። “የሀገራችን አብዛኛው ወጣት ትውልድ በተለያዩ ምክንያቶች ስልቹ ከሆነ ሰነባብቷል። በዚሁ ስልቹነቱ ላይ ነጋ ጠባ በስብሰባ ብዛት እየተደበደብን ደንዝዘናል።
የሀገራችን የስብሰባ ባህል ከወጤታማነቱ ይልቅ ማደንዘዣነቱ ያይላል። የእንቦጭ አረም ሐይቆቻችንን እየወረሰ እንዳው ሁሉ ተቋማትም እየተወረሩ ያሉት “ስብሰባ” የሚል ስም በተሰጠው ትርጉም አልባ የጊዜ ማባከኛ ክፉ ወረርሽኝ ነው።”
ወጣቱ በንግግሩ ውስጥ ስብሰባን በተመለከተ የእሩምታ ያህል ያዘነበብኝ የቃላት አረር እነዚህ ብቻ አልነበሩም። ለቅድመ ወግ መንደርደሪያ ግን ይበቃ ይመስለኛል። ያ “ስልቹ” ወጣት እውነቱን ነበር። የስብሰባ ባህላችን ከእሥራት አርነት ወጥቶ መቼ እንደሚፈወስ ለመገመት ያዳግት ይመስለኛል። “ለሁሉም ጊዜ አለው” በሚለው የጠቢቡ የመጽናኛ ምክር ካልተጽናናን በስተቀር መፍትሔው እንዲህ በቅርብ ይገኛል ተብሎም አይታመንም።
ትንሽም ይሁን በርከት ያሉ ጉባዔተኞች የሚታደሙበት የሀገራችን ስብሰባዎች በሙሉ “ከተራ አዳራሽ ወደ ቅንጡ ባለ ኮከብ ሆቴሎች” የዕድገት እመርታ ካሳዩ ውለው አድረዋል። ስካርቮች፣ ቲ ሸርቶች፣ የማስታወሻ ደብተሮችና መጻፊያዎች ከታደሉ በኋላ የጊዜ ምጣኔ የሌለው ትውውቅ ይደረጋል።
ቀጥሎ የዕለቱ የክብር እንግዳ “የስብሰባውን መከፈት የሚያበስር” ዘለግ ያለ ዲስኩር ያሰማሉ። በማስከተልም ስብሰባውን የጠራው ተቋም የበላይ ኃላፊ ከስብሰባው ዓላማ ጋር ይገናኝም አይገናኝ ብቻ የፈለጉትን የጊዜ ክፋይ ገምሰው “የተቋሙን ስንክሳር” ለመተረክ መድረኩን ይይዛሉ። በማሰለስም የተቋሙ ባለሙያዎች በሰዓት ያልተገደበ የስኬት ሌክቸር በማድረግ ጉባዔተኛው እያዛጋና እየተንጠራራ እንዲዳከም ምክንያት ይሆናሉ።
ነገር ከማሳጠር ዕድሜያችን ቢያጥር እንመርጣለን። ተደጋጋሚ የሻይ ሰዓት፣ የታሸጉ የውሃ ቅብብሎሹ፣ በተደረደረው የምሣ ቢፌ ላይ ፕሮቶኮል እየተጠበቀ ወረራ ተደርጎ “የዕለቱ ጉባዔ በስኬት መጠናቀቁ” ይበሰራል።
ይህ ሂደት በከፍተኛ ሁኔታ እየተለመደ ብቻ ሳይሆን “ደም ሥራችንን ጨምድዶ ከያዘ ሰነባብቷል። ”ሀገሪቱ ለስብሰባ የምታወጣው ዓመታዊ በጀት ይፋ የተደረገ ዕለት ብዙዎቻችን የቁጭት ህመምተኞች ሆነን አልጋ ላይ መዋላችን የሚቀር አይመስለኝም።
የወጌ ደርሶ መልስ፤
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ዴስትኒ ኢትዮጵያ ኢኒሼቲቭ ከተባለ ሀገር በቀል ተቋምና ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ከጥር 19 – 21/2013 ዓ.ም ለሦስት ተከታታይ ቀናት የቆየ የውይይት ፕሮግራም ተዘጋጅቶ ነበር። የመርሃ ግብሩ ተሳታፊዎች የአዘጋጅ ክፍሎቹን ባለሙያዎች ጨምሮ ከሰባት የእምነት ተቋማት የተወከሉ መሪዎችና ምሁራን ተካፍለውበታል።
የዴስትኒ ኢትዮጵያ ስም በተለየ ሁኔታ ጎልቶና ደምቆ መጠራት የጀመረው ከሰኔ 2011 ዓ.ም እስከ መስከረም 2012 ዓ.ም በነበሩት ወራት ውስጥ ለሦስት ያህል ጊዜያት ከገዢው ፓርቲ፣ ከተፎካካሪዎቹና ከሌሎች የሙያ መስኮች ለተውጣጡ ተሳታፊዎች ያዘጋጀው ውጤታማ ውይይት በስኬት መጠናቀቁ ከተበሰረ በኋላ ነበር። የውይይቱ ተካፋይ ጉባዔተኞች በጋራ የቀረጽዋቸው አራት ሴናሪዮዎች (ሠባራ ወንበር፣ አጼ በጉልበቱ፣ የፉክክር ቤት እና ንጋት) ለሕዝባችን በይፋ በተገለጡበት ወቅት “ምን ማለት ነው?” የሚል ሰፊ ውይይት ጭሮ እንደነበር አይዘነጋም።
ተሰብሳቢዎቹ “ንጋትን መርጠው” የማጠቃለያ መርሃ ግብር ባደረጉ ዕለት በቀጥታ የሚዲያዎች ሥርጭት በውይይቶቹ እንደምን እንደረኩና ቆይታቸውም አስደናቂ እንደነበር ሲመሰክሩ ደጋግመን አድምጠናል። በግሌ ስል ዴስትኒ ኢትዮጵያ የነበረኝ የሩቅ እውቀትና መረዳት በተግባር የተረጋገጠው በበቀደሙ ስብሰባ በራሴ ተሞክሮ ከፈተሽኩት በኋላ ነበር።
የሃይማኖት ቤተሰቦቹ ቆይታ አጭር ቅኝት፤
በግሌ በእስካሁኑ የዕድሜ ዘመኔ የተካፈልኳቸውን ስብሰባዎች ብዛትና ዓይነት ዘርዝር ከምባል የአሸዋ ጭብጥ እንድቆጥር ብታዘዝ ይቀል ይመስለኛል። ስብሰባዎቹ በሙሉ “ፋይዳ ቢስ” ነበሩ ማለት ግን አይደለም።
እርግጥ ነው ከአላባዎቹ ይልቅ ገለባው የሚያይል ይመስለኛል። የተማርኩባቸው፣ የሰለ ጠንኩባቸው፣ ያስተማርኩባቸው፣ ያሰለጠንኩባቸው፣ በንቃት የተሳተፍኩባቸው፣ እያንቀላፋሁ ጊዜዬን የገደልኩባቸው ወዘተ. እያልኩ መዘርዘሩ ራሴን ለትዝብት ስለሚዳርግ “በሆድ ይፍጀው” ማለፉን በመምረጥ ወደተነሳሁበት ጉዳይ አዘግማለሁ።
ዴስትኒ ኢትዮጵያ በዋነኛነት የመራው የሃይማኖት ቤተሰቦቹ የውይይት መርሃ ግብር የተከፈተው በቀዳሚ የየቤተ እምነቶቹ መሪዎች ጸሎት ነበር። ከትውውቅ አስከትሎ ተሳታፊያኑ በሙሉ ይጠብቁ የነበረው በጽሑፍ የሚሰጠውን የቆይታችንን የመወያያ አጀንዳ ቢሆንም አጀማመሩ እንደዚያ አልነበረም።
እንደ እውነቱ ከሆነ ቡዙዎቻችን በጅማሮው ግር ተሰኝተን ነበር። የአጀንዳው አመንጪ፣ የችግሮችና የመፍትሔ ጠቋሚው ራሱ ጉባዔው መሆኑ ሲገለጽልን ይበልጥ ግርታችን ማየሉ አልቀረም። ያልተለመደ የስብሰባ አካሄድ ስለሆነብንም ግራ ቀኝ መጠቃቀሳችንን መሸሸጉ አግባብ አይመስለኝም። የውይይታችን ሂደት የሚመራበትን “ጊዜያዊ የሥነ ሥርዓት ሕገ ደንብ” እንድንወስን ተነግሮንም እየተገረምን ታዘዝን።
እጅግ በሚደንቅ ሁኔታ የሚያደርጉትን ጠንቅቀው የሚያውቁትና በትህትናና በአክብሮታቸው ምሳሌ የሆኑት የዴስትኒ ኢትዮጵያ አስተባባሪዎች (ፋሲሊቴተርስ) ወደሚፈልጉት የውይይት ባህር እንድንሰጥም ያደረጉት እያባበሉና እያዋዙ ነበር። በቅድሚያ ቤተ እምነታቸውን ወክለው የተገኙት ጉባዔተኞች ለየብቻ በቡድን ተካፋፍለው ያለፉት ዘመናት አገልግሎታቸውን በተመለከተ የሚኮሩበትን፣ የሚቆጩበትንና ወደፊት ሊጠቀሙባቸው የሚፈልጉትን መልካም ዕድሎች እየዘረዘሩ እንዲወያዩባቸው አቅጣጫ ብቻ ጠቁመው ዘወር አሉ።
በተወሰነው አጭር ጊዜ ውስጥ እውነትም ቤተ እምነታቸውን የሚወክሉት ቡድኖች ለነገ ይደር ሳይሉ በመንፈሳዊ አገልግሎታቸው፣ በልማትና በተራድኦ አስተዋጽዋቸው፣ በወቅት ወለድ ሀገራዊ የተሳትፏቸው ድርሻ ሳይቀር ቀደም ባሉት ዓመታት ያስመዘገቡትን ስኬትና የተደነቃቀፉባቸውን ቁጭቶችና ችግሮችን በግልጽነት ዘረዘሩ ከማለት ይልቅ ዘረገፉት ማለቱ ይቀላል።
ታላላቅ ስኬቶቻቸውን መዘርዘሩ ለጊዜው ይቆይና በዋናነት ካነሷቸው ችግሮቻቸው መካከል ያለፉበት የውስጥ አመራር ፍትጊያና ጠባሳዎቻቸው፣ የውጭው የፖለቲካ ተጽእኖ ያሳረፈባቸው ክፉ አሻራና የወጣቱን ትውልድ አያያዝ በተመለከተ በአብዛኛው ከቤትኛነቱ ይልቅ ባዕድነቱ እንዲጎላ መደረጉና በዚህም ምክንያት እያንዳንዱ ቤተ እምነት በፀፀት መቀጣቱ ዋናዎቹ አንኳር ትኩረታቸው ነበሩ።
በወቅታዊ የሚዲያ አጠቃቀምና በጋራ እሴቶቻቸው ላይ ተባብሮ ያለመስራታቸውም ሌላው የፀፀታቸው ገጽታ ነበር። ቡድኖቹ በእነዚህ ጉዳዮች ዙሪያ ሪፖርት ካደረጉ በኋላ ተከታዮቹና ተደጋጋሚ የቡድንና የጋራ ስብሰባዎች በዋነኛነት ያተኮሩት “ከዚህ በኋላ ፀፀታችንና ቁጭታችን እንዳይደገም በመንፈሳዊ አገልግሎታችን፣ በወቅታዊና በቀጣይ ሀገራዊ አጣዳፊ ተልዕኳችንና አስተዋጽኦዋችን ላይ ችግሮቻችንን እንዴት እናርቅና እናስወግድ?” በሚል ዋና ርእስ ላይ ነበር።
የቤተ እምነቶቹ ተወካዮች ባለፉት ዘመናት በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በእነርሱ በኩል ለተፈጸሙት አንዳንድ ችግሮችና ስህተቶች ጨክነውና ደፍረው ኃላፊነት መውሰድ እንደሚገባቸው በጋራ ስምምነት ላይ ደርሰዋል። የፖለቲካውን ቀጥተኛና የእጅ አዙር ተጽእኖ መቋቋምም እንደሚገባቸውም በደማቁ አስምረውበታል። ከአደባባይ እስከ ግለሰብና የቤተሰብ ጓዳዎች ድረስ ዘልቀው በመግባት ምዕመኖቻቸውን እንዲያስተምሩ፣ እንዲገስጹና ከጥፋት ሊጠብቋቸው እንደሚገባም መክረዋል።
ባለፉት ረጅም ዘመናት ከመንፈሳዊ አገልግሎቶቻቸው ጎን ለጎን በትምህርት፣ በግብርና፣ በጤና፣ በአጠቃላይ የልማት ስኬቶቻቸውና በተራድኦ ፕሮግራሞቻቸው ያሳኳቸውን ውጤቶች በማስታወስ ለወደፊቱ የተሻሉ ውጤቶችን ለማስመዝገብ እንደሚጥሩም አረጋግጠዋል። በተለይም በጋራ የሚያማክሏቸውን እሴቶች እየዘከሩ የመደናነቅና የመከባበር ባህል ለማዳበር “ንስሃ የመግባት ያህል” በቁጭትና በአሜንታ ተማምነዋል።
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት፣ ከኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን፣ ከኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት፣ ከኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ፣ ከኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያንና ከኢትዮጵያ የሰባተኛው ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን እና ከአስተባባሪ ተቋማቱ የተገኙት 54 ያህል ጉባዔተኞች የተገኙበት ያ ስብሰባ ፍጹም መከባበር፣ ድንቅ መቀባበል፣ አስገራሚ መግባባትና መደማመጥ በተትረፈረፈበት ሁኔታ ተካሂዶ ተጠናቋል። በመጨረሻም ከየቤተ እምነቱ የተውጣጡ መሪዎች ያሉበት አንድ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ በስብሰባዎቹ የተላለፉትን ውሳኔዎች እንዲከታተል አደራ ተጥሎበት እንደሰመረ ተጠናቋል።
የሀገራችን አስልቺና ልብ አድካሚ “ውጤት አልባ” የስብሰባ ባህል መፈወስ አለበት ብለን የምናምን ከሆነ በተግባር የተፈተነ መፍትሔ ሊያመላክት የሚችለው ዴስትኒ ኢትዮጵያ ሊሆን እንደሚችል በግሌ በጽኑ አምናለሁ። ያ “የወጣቱን ስልቹነት” በተሰበረ ስሜት ያወጋኝ ወጣት ምነው ዕድል ገጥሞት በዚህ ጉባዔ ላይ በተገኝ ብዬ ያሰብኩት ያን መሰል የተዋጣለት አስተማሪና ተግባር ተኮር ስብሰባ ከተካፈልኩ በኋላ ነበር።
ማሳረጊያዬ የአደራ ቃል ነው። ቤተ እምነታችሁን የወከላችሁት ተሰብሳቢዎች ሆይ በወቅታዊ ሀገራዊ ችግሮቻችን፣ በየቤተ እምነቶቻችን የአመራር ክፍተቶች፣ ውጭዋዊውን የፖለቲካ ተጽእኖ እንዴት መቋቋም እንደሚቻል፣ የተፈጠረውን የትውልድ ክፍተት ለመሙላትና ወጣቱን ለማገዝ፣ በሚዲያ አጠቃቀምና አተገባበር ዙሪያ የሚስተዋሉትን ስር የሰደዱ ችግሮች ለማረቅ፣ በጋራ እሴቶች ግንባታ ላይ ጠንክሮ ለመስራት የተገቡት ኪዳኖችና መልካም መነሳሳቶች ወደተግባር እንዲለወጡና በጋራ እንድንደምቅ የተሳታፊነት ዕድል ስላገኘሁ ብቻም ሳይሆን በተዘወተረው የብዕሬ አደራ ጭምር እነሆ ይድረስ እላለሁ። ሰላም ይሁን!
አዲስ ዘመን ጥር 27/2013