በአዝማቹ ክፍሌ
ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ሌሊት የህ.ወ.ሓ.ት አጥፊ ቡድን በመቀሌ በሚገኘው የአገር መከላከያ ሰራዊት ሀይል ላይ ቅፅበታዊ እርምጃ ወሰደ።ይህንንም ተከትሎ መንግስት በተደራጀ መንገድ በወሰደው እርምጃ የህ.ወ.ሓ.ት የጥፋት ቡድን ላያዳግም እንዳይነሳ ተደርጎ እንዲወድቅ አድርጎታል።
የህ.ወ.ሓ.ት የጥፋት ቡድን መደምሰስ ተከትሎ በአገሪቱ የሚገኙ የመንግስትም ይሁን የግል መገናኛ ብዙሀን የህ.ወ.ሓ.ት የጥፋት ቡድን ባለፉት 27 ዓመታት የሰራቸውን ግፎች እንዲሁም ከ2010 ዓ.ም በኋላ በትግራይ ክልል ቁጭ ብሎ በሌሎች ክልሎች ውስጥ የሰላም መደፍረስ ሲፈጥርም እንደነበር በሰፊው ሲዘገቡ ሰንብተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በትግራይ ክልል ስለተደረገው የሰላም ማስከበር ዘመቻ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት፤ የህ.ወ.ሓ.ት የጥፋት ቡድን የሰራቸውን ኢፍትሀዊና ሰብዓዊ ጥሰቶች አንስተዋል፡፡
የህ.ወ.ሓ.ት ጥፋት ቡድንን ግፍ ማውራት ከ2010 ዓ.ም በኋላ የተከሰቱትን የጥፋትና ኢፍትሀዊ አሰራሮችን ይሸፍን ይሆን? ብለን እራሳችንን እንጠይቅ።በእራሴ አመለካከት ግን የህ.ወ.ሓ.ት የጥፋት ቡድን እንዲህ አድርጎ ነበር ምናምን እየተባለ መደጋገሙ ፋይዳ ያለው አይመስለኝም።ለምን? ከተባለ የህ.ወ.ሓ.ት የጥፋት ቡድን የሰራቸውን የግፍ ስራዎች ህዝብ ቀድሞ አውቆት ሲቃወም ስለኖረ ነው።
የሚያስገርመው ግን በአሁኑ ወቅት በመንግስት ከፍተኛ የስልጣን እርከን ላይ የሚገኙ ሰዎች የህ.ወ.ሓ.ት የጥፋት ቡድን አገሪቱን እየመራ በነበረበት ጊዜ አጠገቡ ተቀምጠው ምንም ጥፋት አጥፍቶ አያውቅም ብለው ሲከራከሩ እንደነበር መዘንጋታቸው ነው።
ወደ ዋናው ጉዳይ ስንገባ የለውጥ ሀይሉ ስልጣን ተረክቦ አገሪቱን ማስተዳደር ከጀመረ ሶስተኛ ዓመት እየመጣ ይገኛል።በነዚህ ዓመታት የሪፎርም ስራዎች በበርካታ ተቋማት ላይ መከናወኑ ይታወሳል።አብዛኛዎቹ ውጤታማ ቢሆኑም በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ግን የተደረጉት ለውጦች ቀድሞ የነበረውን የህዝብ እንባ ከማበስ ይልቅ ያባባሰ ነበር ማለት ይቻላል።
በተለይ በቤት ግንባታና በህገወጥ መሬት ወረራ በኩል ከቀደመው እኩል የሚሆን ኢፍትሀዊነት ተስተውሏል። ሰሞኑን የአዲስ አበባ መስተዳድር አስጠናሁ ባለው ጥናት በርካታ ጉዶች ተመልክተናል።መንግስት ባለበት አገር እንዲህ አይነት አይን ያወጣ ዘረፋ በህ.ወ.ሓ.ት ወይስ በለውጥ ቡድኑ ተፈፀመ የሚለውን ለናንተ ልተው።
በጥናቱ ግኝት መሰረት አንድ ሺህ 338 ሄክታር መሬት ትወርሯል፣ 322 ህንፃዎች ባለቤት የላቸውም፣ 21 ሺህ 695 የጋራ መኖሪያ ቤቶች በህገወጥ ሁኔታ ተይዘዋል፣ 14 ሺህ 641 መኖሪያና ለንግድ የተከራዩ የቀበሌ ቤቶችን ያለ አግባብና በህገ-ወጥ ይዞታነት ይገኛሉ፣ በህገ-ወጥ ወረራ የተያዘው መሬት በገንዘብ ሲተመን በ14 ቢሊየን ብር ይገመታል፣ በሪል ስቴት አልሚዎች፣ በግለሰቦች፣ በሀይማኖት ተቋማትና በቡድን በመደራጀትና መንደር በመመስረት ጭምር በሚገለፅ መልኩ የመሬት ወረራ ተፈፅሟል፣ 75 በመቶ የሚሆኑት ኮንዶሚኒየሞች የተያዙት ባልተመዘገቡና ባልቆጠቡ ሰዎች ነው፣ 18 ሺህ 423 የኮንዶሚኒየም ቤቶች በህገወጥ መንገድ የተያዙ ናቸው፣ እስከ 842 የሚሆኑ ቤቶች እና 83 የጋራ መጠቀሚያ ህንፃዎች ሳይገነቡ የተገነቡ መስለው የተዘገቡ ናቸው፣ ምንም እንኳን መረጃ ባይገኝም ለግንባታው ክፍያ አልተከፈለም ብሎ መደምደም እንደሚያስቸግር በኦዲት ጥናቱ ላይ ተመላክቷል፣ 10 ሺህ 565 የቀበሌ መኖሪያ ቤቶች በህገወጥ መንገድ የተያዙ ናቸው፣ 234 የቀበሌ ቤቶች የጠፉ ቤቶች ናቸው፣ 537 የቀበሌ ቤቶች በህገወጥ መንገድ ወደ ግል ቤትነት የዞሩ መሆናቸው ተመልክቷል።
የአዲስ አበባ ህዝብ ቤት ለማግኘት ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ ተመዝግቦ ቆጥብ የተባለውን ቆጥቦ ቤት ይደርሰኛል ብሎ ሲጠባበቅ አስራ ስድስት ዓመታት ቢቆጠሩም ከተወሰኑት ውጪ አብዛኛው ሰው ቤቱ ሳይደርሰው ተስፋ ቆርጦ ተቀምጧል።በ2005 ዓ.ም ላይም አዲስ የቤት አማራጮች መጥተዋል ተብሎ ነዋሪው በድጋሚ ቢመዘገብም በተመሳሳይ መልኩ ከተመዘገቡት የተወሰኑት ብቻ ደርሷቸው አብዛኛው ቤት ምን እንደዋጠው እስካሁን አልታወቀም።
የከተማ አስተዳደሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶችን ገንብቻለው ለተጠቃሚውም አስተላልፋለው ቢልም አንድም ቀን በቃሉ ተገኝቶ አያውቅም።ይህ አሰራር ደግሞ ከህ.ወ.ሓ.ት እስከ ለውጥ አመራሩ ድረስ የዘለቀ መሆኑ ደግሞ ልዩ ያደርገዋል፡፡
የህ.ወ.ሓ.ት አጥፊ ቡድን በተደራጀ ሰንሰለት አዲስ አበባን በህገወጥ መሬት ወረራና ዝርፊያ ሲያጣድፋት ከርሞ ወደ ለውጥ አመራሩ ያስተላለፈ ስለመሆኑ ማስረጃ መጥቀስ አያስፈልግም።ምክንያቱም የለውጥ አመራሩ የህ.ወ.ሓ.ት አጥፊ ቡድን የዘረጋቸውን የዘረፋ ሰንሰለቶች በጣጥሻለው ቢልም በተግባር ግን እራሱን ቦታው ላይ ተክቶ ኢፍትሀዊ ስራ መስራቱ የአደባባይ ሀቅ ነው።
ለዚህ ደግሞ የመሬት ወረራና የኮንዶሚኒየም እደላውን ማንሳት በቂ ነው።የለውጥ አመራር ነን ብለው ከተማውን ከተቆጣጠሩ በኋላ እንደ ግል ንብረታቸው የተገነቡ ኮንዶሚኒየሞችን ላሻቸው ሰው ሲሰጡ ህግም መመሪያም አላገዳቸውም። ኮንዶሚኒየሞቹ የተገነቡት በህዝብ ገንዘብ እንደመሆኑ ሊሰጥም የሚገባው ለቆጠበው ህዝብ ነው።በተግባር ግን ለቤተ ዘመድ የሚሰጥ ‹‹የገና ስጦታ›› እስኪመስል ድረስ ሲታደሉ ከርመዋል።‹‹እሽ አትበሉኝ የሹም ዶሮ ነኝ›› በሚል ብሂል እስካሁን የተጠየቀ አመራር አላየንም።
ሌላው ደግሞ በሹመት ከተለያየ ቦታ የሚመጡ አመራሮች እየተሰጣቸው የሚገኘው የቀበሌ ቤት ጉዳይ ነው።አመራሮቹ ከየትም ይምጡ የከተማው ነዋሪ ጉዳይ አይደለም።ነገር ግን የከተማው ነዋሪ ቤት አጥቶ ለነሱ የተቀናጣ መኖሪያና ቀበሌ ቤት መስጠት ግን ኢ-ፍትሀዊ አሰራር መስፈኑ አንዱ ማረጋገጫ ነው።ይህ አሰራር በህ.ወ.ሓ.ት ዘመንም በለውጥ አመራሩ ጊዜም ተጠናክሮ የቀጠለ ጉዳይ ነው።
አንድ አመራር የቀበሌ ቤት ሲሰጠው ቤቱ ግቢ የሆነና በውስጡም የሚከራዩ ቤቶች የያዘ መሆኑ ሊያስገርም ይችላል።ነገር ግን ተሿሚው ስራውን ቢያጠናቅቅ ባያጠናቅቅም ወይም ከአመራርነት ቢባረር ቤቱን አለመነጠቁ ከማስገረም አልፎ ያስደነግጣል።
የለውጥ አመራሩ ስራውን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ አዲስ አበባ ከተማ ያለአግባብ ከኦሮሚያ ክልል መሬት ወስዷል በሚል ከፍተኛ ውዝግቦች እንደነበሩ አይረሳም።በውዝግቡም በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ በሚገኙ ከተሞች በህገወጥ መንገድ ተይዘዋል የተባሉ ቤቶችም ሲፈርሱ ተመልክተናል።
አንድ የሚያስማማን ጉዳይ በህገወጥ መንገድ ወይም በአካባቢው የሚገኘውን አርሶ አደር አፈናቅሎ መኖር አይቻልም።ነገር ግን አርሶ አደሩን በአነስተኛ ገንዘብ ከቦታው እንዲለቅ በማድረግ በከፍተኛ ገንዘብ መሬቱን የቸበቸቡት አመራሮች በድሎትና በከፍተኛ ስልጣን መንበር ላይ ሲቀመጡ መሬቱን በከፍተኛ ገንዘብ የገዛው ነዋሪ ግን ከቤት ንብረቱ በድጋሚ በሸጡለት አመራሮች ሲፈናቀል ማየት የአንድ ወቅት ለቅሶ ሆኖ አልፏል።
እንደማጠቃለያ የህ.ወ.ሓ.ት ግፍ ታሪክም ትውልድም የሚረሳው አይደለም።በህ.ወ.ሓ.ት ዘመን የነበረው ሰብዓዊ ጥሰት፣ ኢፍትሀዊነት፣ ዝርፊያና ህገወጥነት አሁን ባለው የለውጥ አመራር ይደገማሉ ብሎ ማሰብ ማንም ሰው አይፈልግም።
ነገር ግን የተወሰኑ ጭላንጭሎች እየተስተዋሉ ነው።የህ.ወ.ሓ.ትን ግፍ ደጋግሞ ማውራት አሁን ያለውን ኢ-ፍትሀዊነት የሚያስረሳ አለመሆኑን አመራሩ ተረድቶ ከገባበት ህገወጥ ተግባር በጊዜ ሊታቀብ ይገባል።
አዲስ ዘመን ጥር 27/2013