ወርቅነሽ ደምሰው
የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ በቅርቡ የዲያስፖራ ፖሊስና ስትራቴጂ ለመከለስ የሚያስችል ጥናት ለማድረግ ከአራት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የስምምነት መግባቢያ ሰነድ መፈራረሙ የሚታወስ ነው።
በዚህ መድረክ የፖሊሲውን ግምገማና ትንተና አስመልክቶ ኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ የዲያስፖራ ማህበረሰብ ልማት ዳይሬክተር ጀኔራል አቶ ተስፋዬ ወልዴ ለውይይት የሚሆን ጽሑፍ ቀርቧል። በዚህ ጽሑፍ የፖሊሲው አጠቃላይ ሁኔታዎችና ለመከለስ የሚያስችሉ አመላካቾች ቀርበዋል።
ዲያስፖራ ፖሊሲ ለምን አስፈለገ
መንግሥት ዲያስፖራው ለሀገር ልማትና ዴሞክራሲ ግንባታ አጋዥ መሆኑን ተረድቶ በፖሊሲ የተደገፈ ተሳትፎ ሊያደርግ ይገባዋል በሚል በመነሻ የዲያስፖራ ፖሊሲ እንዲወጣ ተደርጓል።
ሌላው የዲያስፖራውን ሁለተናዊ ተሳትፎ በተደራጀና ሀገራዊ ልማት በሚያግዝ መልኩ ለመመራት ጭምር ታሰቦ ነው። ዲያስፖራው ሀገርንም ጠቅሞ እራሱም እንዲጠቀም ለማድረግ በተደራጀ ሁኔታ እንዲሳተፍ ለማድረግም ፖሊሲው አስፈላጊ ነው።
በመጀመሪያ ከፖሊሲ ዝግጅት በፊት ጥናቶች የተካሄዱ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ አንደኛው የኢትዮጵያ አጠቃላይ የፍልስት ታሪክ ምንድነው? የፍልስቱ ምንጭ ምንድነው? የሚለውን የሚዳስስ ጥናት አንዱ ነው።
በሁለተኛ ደረጃ የዲያስፖራውን ተሳትፎ ለማሳደግ የሌሎች ሀገራት ዲያስፖራዎች በአገራቸው የልማት ተሳትፎ እንዲያደርጉ ለማድረግ ምን እያደረጉ ነው? እንዴት ነው ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩላቸው የሚለውን የተለያዩ ሀገሮች ተሞክሮ በተለይ የፊሊፒንሲን ፤ የሕንድን፣ የሩዋንዳና የጋና የዲያስፖራ ታሪክ በአካል በመገኘትና እንዲሁም ባለሙያዎችቸውን ወደ ሀገራችን በማምጣት ልምድ እንዲያካፍሉ ተደርጓል። ይህም በተለይ ፖሊሲውን ለመቅረጽ የፊሊፒንሲና የሕንድ ልምድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል።
እንደ አቶ ተስፋዬ ገለጻ፤ ከፖሊሲው ሰነድ ዝግጅት በኋላ ሀገር ውስጥ ካሉ የዲያስፖራ አባላት ጋር፣ በክልልና በፌዴራል ካሉ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትና ለሚሲዮኑ ፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ውይይት ተካሂዷል።
ከዚያ በኋላ ፖሊሲ በሚኒስትሮችም ምክር ቤት አንዳንድ ማሻሻያዎች ተደርገውለት በ2005 ዓ.ም እንዲጸድቅ የተደረገ ሲሆን አሁን የፖሊሲ ጥናት ከተጀመረ ወዲህ አስር ዓመት ሆኖታል።
የፖሊሲው ክፍሎች
የፖሊሲው ሦስት ክፍሎች አሉት። ክፍል አንድ የዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ነባራዊ ሁኔታ ዳሰሳ ትርጉም፣ ዓላማና አስፈላጊነት ላይ የሚያተኩር ነው። ክፍል ሁለት የፖሊሲው መሠረታዊ መርሆችና ዋናዋና ግቦች የያዘ ሲሆን፤ በክፍል ሦስት ፖሊሲውን ለማስፈጸም ምን ዓይነት ስትራቴጂዎች መከተል ይገባል። ፖሊሲውን የሚያስፈጸመው አካል ማነው የሚለው የተካተተበት ነው።
በፖሊሲ ውስጥ ያሉ እያንዳንዱ ግቦች ተግባራዊ እየሆኑ ነው ወይስ የተለያዩ ችግሮች አለባቸው የሚለው መፈተሽ በፖሊሲው ጥናት ሊሻሻሉ ከሚገባቸው ነገሮች ውስጥ መካተት ያለባቸው ሲሆን፤ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መብትና ጥቅም ማስጠበቅ የኤጀንሲው ከሥራዎቹ ውስጥ እንደ ዋና ግብ የሚታይ መሆኑን ነው አቶ ተስፋዬ የሚናገሩት።
ሌላው የኢንቨስትመንት፤ የንግድና የቱሪዝም ተሳትፎን ማጎልበት ግቦች ናቸው። በእነዚህም የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ማሳደግ፤ የውጭ ምንዛሬ ማስገኛ መንገዶችንና ተሳትፎን ማሳደግ፤ ባህላዊ እሴቶች ማዳበርና ለገጽታ ግንባታ ማትጋት፤ በዴሞክራሲያዊ ሂደት የሚኖረውን ተሳትፎ ማሳደግ፣ የግብረሰናይና የልማት ማህበራትን ማትጋት፣ የኢትዮጵያ ገጽታ የሚገነቡ ጉዳዮች ላይ ማሳተፍ የሚሉ ግቦቹ ተቀምጠዋል። ስለሆነም ከዲያስፖራው የሚጠበቀው እነዚህን ሥራዎች መስራት ሲሆን፤ እነዚህን ለማድረግ ምን ዓይነት ስትራቴጂ እንከተላለን የሚለውና እያንዳንዱ ግብ ትኩረት ተደርጎበት ሊከለስ ይገባዋል ሲሉ ገልጸዋል።
የፖሊሲ ስትራቴጂ
የፖሊሲ ስትራቴጂ አንደኛ አስተማማኝ የመረጃ አያያዝና ሥርጭት ሥርዓት መዘርጋት ነው። ስለዲያስፖራ መረጃ ለማግኘት አስቸጋሪ ሁኔታዎች ያጋጥማሉ። እነዚህን ግቦች ለማሳካት ችግሮቹን ፈትቶ በሚስዮኖቻችን ሆነ በተለያየ ቴክኖሎጂ የመረጃ ሥርዓቱን ማዘመን ያስፈልጋል።
ኤጀንሲው ከተቋቋመ በኋላ ኢትዮጵያ ከ60 በላይ የሆኑ ኤጀንሲዎችና ቆንስላ ጽሕፈት ቤቶች አሏት። ዲያስፖራው በሚገኝባቸው አገራት በብዛት የሚኖርባቸውን 38 ቦታዎች በመምረጥ በትኩረት እየተሰራበት ነው። ሌላው ዲያስፖራው በሀገሩ ላይ ለሚያደርገው ተሳትፎ መንግሥት እውቅና መስጠት አለበት። ይህም ሌላው ዲያስፖራ ወደ ሀገር ቤት ገብቶ መስራት ለሚፈልግ መተማመኛ ይሆናል።
በተመሳሳይ የዲያስፖራው የተደራጀ ተሳትፎን ለማትጋት አሁን በውጭ ያለው ዲያስፖራ የፈጠረውን አደረጃጀት እንዲቀጥል ማትጋት ያስፈልጋል። ይህንን ስትራቴጂ በመከተል ዲያስፖራው በአገሩ ልማትና ዴሞክራሲ ግንባታ የተደራጀ እንቅስቃሴ እንዲያደርግ ማገዝ ያስፈልጋል።
ሌላው የትውልደ ኢትዮጵያዊ መታወቂያ ካርድ መስጠት አንዱ ስትራቴጂ ሲሆን፤ ቢጫ ካርድ መስጠቱ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሀገር ውስጥ እንደ ዜጋ ተቆጥረው በሀገር ውስጥ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ላይ መሳተፍ እንዲችሉ ያደርጋል።
ፖሊሲውን ለምን መከለስ አስፈለገ?
እንደ አቶ ተስፋዬ ገለጻ፤ ፖሊሲው በየአምስት ዓመቱ መከለስ አስፈላጊ ቢሆንም፤ በተለያዩ ምክንያቶች ፖሊሲው ሳይከለስ አሁን ላይ አሥር ዓመት ሆኖታል። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ በተመለከተ በሕግም በአደረጃጀትም ብዙ ለውጦች ተከስተዋል። በሕግ የመጣው ለውጥ የዲያስፖራ ኤጀንሲ መቋቋሙ ሲሆን፤ የዲያስፖራ ኤጀንሲ ፖሊሲውን የሚያስፈጸም ከሆነ በፖሊሲ ውስጥ የተገለጸ አስፈጻሚ አካላት ግን ሌሎች በመሆናቸው ነው። በአደረጃጀትም እንደዚሁ የተለያዩ አደረጃጀቶች ተፈጥረዋል።
ፖሊሲውን የዲያስፖራ ማህበራትንና የተለያዩ በሚስዮኖች የሚሰሩ እንቅስቃሴዎችን ጨምሮ ለውጦች አሉት። በአመለካከትም ሲታይ በዲያስፖራው ያለው አመለካከት ለውጦች እየመጡ ነው። በተለይ ከለውጡ በኋላ የዲያስፖራው አመለካከት የፖለቲካ ወገንተኝነት መሆኑ ቀርቶ ሀገሩን እንዲደግፍ የሚያደርጉ ሥራዎችና ለሀገሩ ልማት የሚያደርገው እንቅስቃሴ ይበልጥ ገዥ እየሆነ እየመጣ ነው። በእነዚህ ምክንያቶች የዲያስፖራው ፖሊሲ መከለስ የግድ ያስፈልጋል።
ፖሊሲ በሚዘጋጅበት ወቅት ለውጦችን የሚያስተናግድ መሆን አለበት ያሉት ተስፋዬ፤ ለምሳሌ የቢጫ ካርድ ደንብ ላይ የቢጫ ካርድ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ሌላ የውጭ ዜጋ ቢያገባ ወይም ብታገባ ቢጫ ካርድ የማግኘት መብት አላት (አለው) ይልና። ይህ ኤርትራውያንን አይጨምርም ይላል።
አንድ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ትውልደ ኤርትራዊ ቢያገባ ቢጫ ካርድ የማግኘት መብት የለውም (የለበትም)። ይህ አሁን ላይ ከለውጡ ጋር ተያይዞ አያስኬድም፣ ማንኛውም ፖሊሲ ወደፊት የሚመጡ ለውጦችን (ሁሉን አቀፍ) የሆኑ ነገሮች ያካተተ መሆን አለበት።
እንደ አቶ ተስፋዬ ገለጻ፤ በፖሊሲው ውስጥ መሻሻል የሚገባቸው ጉዳዮች ምንድናቸው የሚለው በጥናት የሚታዩት እንደተጠበቁ ሆነው በክፍል አንድ የታየው የዓለም አቀፍና የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ዳሰሳ እንደገና የሚታይ ይሆናል። ዲያስፖራ የሚለው ትርጉምም ላይ ጥያቄ እያስነሳ ስለሆነ እንደገና ይታያል።
ለምሳሌ ዲያስፖራ የሚለው ውጭ የሚኖረውን ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሲሆን፤ ነገር ግን ሀገር ውስጥ ገብተው የሚኖሩት የዲያስፖራ አባላት ምን መባል እንዳለባቸው አያብራራም።
የፖሊሲው አጠቃላይ አላማ እንደገና በማሻሻያው መታየት አለበት። እነዚህ የፖሊሲው ሁለት ዓላማዎች፤ አንደኛው የኢትዮጵያን ዲያስፖራ ተሳትፎ ማበረታታት ሲሆን፤ ሁለተኛው በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጥቅምና መብት ማስጠበቅ የሚል ነው። ከእነዚህ ሌላ አላማ ካለ ቢታይና በዋናዋና ግቦችና በስትራቴጂ ላይ ያሉት ምንድናቸው የሚለውን መታየት ይገባዋል።
የፖሊሲ አስፈጸሚ አካላት በተመለከተ መሻሻል የሚገባው ጉዳይ አለ ያሉት አቶ ተስፋዬ፤ ፖሊሲው ላይ አስፈጻሚ ብሎ ያስቀመጠው በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስር ሆኖ አማካሪ ተቋም ሊኖረው ይገባል ይላል። አሁን ላይ ባሉት ለውጦች ግን እያስፈጸመ ያለው የዲያስፖራ ኤጀንሲ በመሆኑ በትኩረት ሊታይ ይገባዋል ሲሉ ሀሳባቸውን ቋጭተዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 26/2013