አዲስ አበባ፡- የግብይት ሰንሰለትን በማሳጠር ሸማቹንና አምራቹን እያገናኙ ያሉትን ህብረት ስራ ማህበራት የመጋዘን ችግር የሚያቃልል ስራ መንግስት አለመስራቱን የፌዴራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ የግብይት ዳይሬክተር ገለጹ።የገበያ ማእከላት ግንባታም በበጀት እጥረት ሊሳካ እንዳልቻለ ተጠቁሟል፡፡
ዳይሬክተሯ ወይዘሮ ይርጋዓለም እንየው በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳሉት፤ የህብረት ስራ ማህበራት የህብረተሰቡን ፍላጎት ለማርካት የግብይት ሰንሰለቱን በማሳጠር ሰፊ ስራ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይም አዎንታዊ ሚና እየተጫወቱ ናቸው፡፡
ማህበራቱ እያጋጠማቸው ያለው የመጋዘን ችግር ይህን ኃላፊነታቸውን በሚገባ እንዳይወጡ እያደረጋቸው መሆኑን ዳይሬክሯ ጠቁመው፣ መንግስት ይህ የመጋዘን ችግር እንዲፈታ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚኖርበትም አስገንዝበዋል፡፡
ዳይሬክተሯ እንዳስታወቁት፤ማህበራቱ በአሁኑ ወቅት ከ10 ሚሊየን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ እያሰራጩ ሲሆን፤ የሚያሰራጩት ምርጥ ዘር መጠንም ከግማሽ ሚሊየን ኩንታል በላይ ደርሷል።ይሁንና እነዚህን ግብአቶች ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ማከማቸት የሚችል መጋዘን የላቸውም፡፡ይህን ማዳበሪያና ምርጥ ዘር በመጠቀም አርሶ አደሩ የሚያገኘው ምርት እየጨመረ የመጣ ሲሆን፤ ለዚህም የሚሆን መጋዘን ማግኘት ግን አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል፡፡
አርሶ አደሩ አትክልትና ፍራፍሬዎችን በብዛት እንዲያመርት ድጋፍ እየተደረገለት መሆኑን ጠቅሰው፤ ቀዝቃዛ መጋዘኖች ባለመኖራቸው ሳቢያ ከምርቱ ተጠቃሚ መሆን እንዳልተቻለ ተናግረዋል፡፡ በመጋዘን አለመኖር ሳቢያ ምርቱን ከማምረቻው ዋጋ በታች እንዲሸጥ እየተገደደ መሆኑን አመልክተው፤ ህብረት ስራ ማህበራት ገበያው ላይ ድርሻ እንዲኖራቸው ከተፈለገ በየደረጃውና በየዓይነቱ መጋዘኖችን መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል።
ኤጀንሲው በሁለተኛው የእድገትና ትራንስ ፎርሜሽን እቅድ ካስቀመጣቸው ተግባራት መካከል የህብረት ስራ ማህበራት የግብይት መሰረተ ልማቶችን ማስፋት በዚህም ቀዝቃዛና ደረቅ መጋዘኖችን መገንባትና አምራቹ ምርቱን የሚያከ ፋፍልባቸው መጋዘኖች ሊገነቡ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ መጋዘኖቹ በማህበራቱ የሚመሩ ፣ ደረጃቸውን የጠበቁና የጅምላ ሽያጭ የሚከናወ ንባቸው ሊሆኑ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
መንግስት ምርትና ምርታማነቱ ላይ ኢንቨስት የሚያደርገውን ያህል የግብይት ስርዓቱን ለማዘመን ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚኖርበትም ወይዘሮ ይርጋ አለም ጠቁመዋል።
በህብረት ስራ ማህበራት የሚመሩ አምራቹ ምርቱን አስገብቶ በጅምላ የሚሸጥባቸው ደረጃቸውን የጠበቁ ትላልቅ የገበያ ማዕከላትን በመቀሌ፣ ሀዋሳ ፣ ባህርዳር እና በአዲስ አበባ አራቱም መግቢያዎች ለመገንባት ከግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ጋር እቅድ ተይዞ እንደነበር ጠቅሰው፤ ግንባታው ከፍተኛ በጀት በመጠየቁ እስከ አሁን ወደ ትግበራ እንዳልገባ አስታውቀዋል፡፡ መንግስት ይህንን ስራ ማስፈጸም እንዳለበት ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 28/2011
በእፀገነት አክሊሉ