ውብሸት ሰንደቁ
አቶ አሰፋ መንገሻ ውጭ ሀገር በሚኖሩበት ወቅት የሚያዩት ቴክኖሎጂ ያሳደረባቸው መንፈሳዊ ቅናት ዛሬ ለተሰማሩበት ኢንቨስትመንት መነሻ ሆናቸው። እሳቸው በሙያ አካውንታንት ይሁኑ እንጂ ለቴክኖሎጂ ጥልቅ ፍቅር ነበራቸው፤ አላቸውም።
እስራኤል ሀገር በሙያቸው እያገለገሉ እያለ በሚያዩት ቴክኖሎጂ ይበልጥ ተሳቡ።የሚያዩትን ለየት ያለ ቴክኖሎጂ ሁሉ ይህ ኢትዮጵያ ውስጥ በሆነ ብሎ መመኘት የዘወትር ተግባራቸው ነበር።
በቅንጦት ዕቃዎች ሳይሆን በመሠረታዊ ነገሮች ላይ ቅናታቸው እየጨመረ የመጣው አቶ አሰፋ በተለይ በሀገረ እስራኤል በየቤቱ ተንጠልጥሎ የሚያዩት በፀሐይ ኃይል ውኃን የሚያሞቅ ማሽን በእጅጉ ስቧቸዋል።
እዚያ ሀገር ማንኛውም ሰው ቤት ሠርቶ ከቤቱ እኩል የሚያስገጥመው በፀሐይ ኃይል የሚሠራ የውኃ ማሞቂያ ማሽን ነው። ይህ ለእስራኤላውያን ባህል ሆኗል።
ታዲያ ይህን ቴክኖሎጂ ወደ ሀገር ውስጥ ለማምጣት ሲያስቡ በዘርፉ የሠለጠነ የሰው ኃይል አልነበረምና ገና ከመነሻው መሰናክሎች ብቅ ማለት ጀመሩ።ሆኖም አቶ አሰፋ ከነበራቸው ጥልቅ ፍላጎት ጋር ታግሎ የማሸነፍ ብርታት ያለው እንቅፋት ባለመሆኑ ከሸፈ።
አቶ አሰፋ በተከበሩበት መሥሪያ ቤት ውስጥ የወዝ አደር ልብስ ለብሰው ሁለት ዓመት ለሚሆን ጊዜ እስራኤል ሀገር በሚገኘው ፋብሪካ ውስጥ እየገቡ በመማር በልባቸው ለጎነቆለው ፋብሪካ የመጀመሪያውን መሠረት ጣሉ።የፋብሪካውን የአመራ ረት ሂደትና የግብዓት ጥራት በአግባቡ ከመረዳት ጎን ለጎን ሀገራቸው ሲገቡ የሚጀምሩት ፕሮጀክት ምን እንደሚመስል እዚያው እስራኤል ቁጭ ብለው ነድፈው ጨረሱና ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ።
ይህ ፋብሪካ ዛሬ አፍሮአምክ ሶላርቴክ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ይሰኛል።አፍሮአምክ ሰንዳፋ የሚገኝ በፀሐይ ኃይል ውኃ የሚያሞቅ መሣሪያ የሚያመርት ድርጅት ሲሆን 16 ሚሊዮን ብር አስመዝግቦ ነው ወደ ኢንቨስትመንቱ የገባው።
አጠቃላይ የግቢው ስፋት 3000 ካሬ ሜትር ሲሆን አገልግሎት መስጫ ቢሮዎችን ጨምሮ ፋብሪካው ያረፈው 1000 ካሬ ሜትር ስፋት ገደማ ላይ ነው።25 ያህል ሠራተኞች ቀጥሮ ሥራውን እየሠራ ይገኛል።
የዚህን ፋብሪካ ሠራተኞች እርሳቸው እንደሠ ለጠኑት ሁሉ ማሠልጠን ግድ ነበርና ከእስራኤል ሀገር በሙያው የተካኑ ባለሙያዎችን በማስመጣት እንዲሠለጥኑ አደረጉ። በወቅቱ ምንም እንኳን ከእስ ራኤል ሀገር ያስመጧቸው ባለሙያዎች የሆቴል ክፍያ፣ የቀን ገቢ መሸፈኛ ክፍያና የምግብና የመሳሰሉት ክፍያዎች ከፍተኛ ቢሆንም ኢትዮጵያውያን ሠልጣኞች በአጭር ጊዜ ትምህርቱን መቅሰም መቻላቸው ደግሞ የሚያፅናና ጉዳይ ነበር።16 ዓይነት ዘርፎች ላይ የፋብሪካውን ዕጩ ሠልጣኞች በማሠለጠን ሥራው ተጀመረ፡፡
እናም በፀሐይ ኃይል አማካኝነት ውኃ የሚያሞቀው ማሽን በሀገር ልጅ እጅ፣ ለሀገር ልጅ ተሠርቶ ለገበያ ቀርቦ በተለያዩ ቦታዎች መንጠልጠል ጀመረ።ነገሩ እንዲህ ነው በማሽኑ ውስጥ የሚገጠመው የሶላር ፓኔል ከፍተኛ ሙቀት የመሰብሰብ አቅም ያለው በመሆኑ በውስጡ ውኃ በከፍተኛ ሙቀት መጠን ውስጥ ያልፋል።
በሶላር ፓኔል አማካኝነት ውኃውን ካሞቀ በኋላ እንደ ፔርሙስ ሙቀቱ እንደተጠበቀ የሚያቆየው ክፍል ውስጥ ያስገባዋል።የቀዝቃዛ ውኃ መቀበያ ቱቦ ስላለው ይህ ሂደት እስከተፈለገበት ጊዜ ድረስ ያለማቋረጥ ያገለግላል።
የሞቀ ውኃ በሚያስፈልግበት ጊዜ በሻወር ቤት፣ ለግል ቤቶች፣ ጤና ጣቢያዎች፣ ሆስፒታሎችና ኢንዱስትሪዎች እንዲሁም ለፔኒሲዮኖችና አፓርትመንቶች ተገጥሞ ከፀሐይ በሚመነጭ ኃይል ሙቅ ውኃ መጠቀም የሚያስችል ነው።በተጨማሪም ይህ የመሣሪያው አንድ አካል የሆነው ሶላር ቦይለር ብቻውን በሆስፒታሎች እየተተከሉ ላሉ የካንሰር የጨረር ማሽኖች ላይ እንደ ሙቀት ማስተካከያና መቆጣጠሪያነት ስለሚያገለግል እየተገጠመ ይገኛል።
በዚህም ጥቁር አንበሳና ጳውሎስ ሆስፒታልን ጨምሮ የተለያዩ በክልሎች ጭምር ለሚገኙ ትላልቅ ሆስፒታሎች ላይ መሣሪያው እየተገጠመ ነው።ኢትዮጵያ ውስጥ ማምረት በመጀመሩም ኢትዮጵያ ከውጭ ልታስመጣ የነበረውን ምርት በዚሁ በሀገር ውስጥ በተመረተ ምርት መተካት ችላለች።
ይህ በፀሐይ ኃይል ውኃ የሚያሞቅ መሣሪያ እንደ አስፈላጊነቱ በየመጠኑ የሚዘጋጅ ሲሆን ከ80 ሊትር ጀምሮ ለአፓርትመንቶችና ሆቴሎች ሊያገለግል በሚችል ትላልቅ መጠን መዘጋጀት የሚችል ነው።መሣሪዎቹ በሚሠሩበት ጊዜ እንዳይዝጉ፣ ቀለማቸው እንዳይለቅና ያለጊዜያቸው እንዳይበላሹ በልዩ ጥንቃቄ የተሠሩና ግብዓቶቻቸውም በጥንቃቄ ደረጃቸውን የጠበቁ የአውሮፓ ምርቶች ናቸው።
ዕቃዎቹ ሲመረቱም ታሳቢ ተደርገው የሚመረቱት ከአሥር ዓመት በላይ እንዲያገለግሉ ሆነው ነው።ለምርቶች ገዢዎችም ቢያንስ አምስት ዓመት ዋስትና ይሰጣል።ትላልቅ ሆቴሎች ወስደው ምርቶቹን በመጠቀማቸው ከኤሌክትሪክ ወጪ ድነዋል፤ መብራት ሲቆራረጥ ከሚደርስ የአገልግሎት መቆራረጥ ተርፈዋል።
የጥሬ ዕቃ አቅርቦት እጥረት ከሌለ በቀን እስከ 60 ምርቶችን ማምረት እንደሚችሉ የድርጅቱ መሥራችና ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሰፋ ነግረውናል።
በፀሐይ ኃይል ውኃ የሚያሞቀው መሣሪያ የኤሌክትሪክ እገዛ በሚያስፈልግበት ጊዜ እንዲያገለግል ከሥሩ ለኤሌክትሪክ ዝግጁ የሆነ ቦታ አለው።ይህ እንደኢትዮጵያ ሁልጊዜ ፀሐይ ለማይጠፋባቸው ሀገራት አንገብጋቢ ባይሆንም በኤሌክትሪክ ለመጠቀምም አመቺ እንዲሆን ተደርጎ ነው የሚሠራው።በእርግጥ እንደኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት ፀሐይ ቀኑን ሙሉ ሳትወጣ የምትውልበት አጋጣሚ በጣም ጥቂት ስለሆነ ጉዳዩ አሳሳቢ አይደለም።
ሆኖም መሣሪያው በኤሌክትሪክ እንዲሠራ ተደርጎ ፀሐይ በሚጠፋባቸው ጊዜያት እንኳን እንዲያገለግል ተደርጓል።የሙቅ ውኃ ማጠራቀሚያውም ከ24 ሰዓት በላይ ውኃው እንደሞቀ ይዞ መቆየት የሚችል ነው።ማሽኑ በኢትዮጵያ የአየር ሁኔታ ያለማቋረጥ አገልግሎት የሚሰጥ መሣሪያ ነው።
በኤሌክትሪክ አማካኝነት ውኃ የሚያሞቅ የተሠራ እያንዳንዱ ቦይለር ቢያንስ አምስት ኪሎ ዋት ኤሌክትሪክ ይባላል።ለአብነት አንድን ፎቅ ብንወስድ የኤሌክትሪክ ውኃ ማሞቂያ ቢያንስ በየክፍሉ መኖር የሚጠበቅበት ሲሆን ይህ መሣሪያ አንድ ፎቅ ላይ ለሚገኙ ክፍሎች አንድ ቦይለር ብቻ በማስገጠም መጠቀም መቻሉ አንድ ጥቅም ሆኖ በየክፍሉ የተገጠሙ የኤሌክትሪክ ቦይለሮች በየድርሻቸው ይበሉት የነበረውን ኤሌክትሪክም የሚያስቀር ነው።
ይህም በከተማ ብሎም በሀገር ደረጃ ሲታሰብ በየቀኑ የምናወጣውን የኤሌክትሪክ ወጪ ከመቆጠቡም ባሻገር እንደ ሀገርም መብራት ኃይል የሚሸጠውን የኤሌክትሪክ ኃይል ያለተጨማሪ የኃይል ማመንጫ ግድቦች ግንባታ የኢንዱስትሪዎች መብራት መቆራረጥ እንዲቀር ሊያስደርግ የሚችልና በአገልግሎቱ ላይም የኃይል ጫና እንዳይፈጠር አስቻይ ሁኔታ የሚፈጥር ነው።በተጨማሪም የኤሌክትሪክ ዝርጋታ በሌለባቸው አካባቢዎች በፀሐይ ኃይል የሙቅ ውኃ አገልግሎት ማግኘት ያስችላል፡፡
አቶ አሰፋ ስለምርቱ ጠቀሜታ ሲያስረዱ እንዲህ ይላሉ፤ ይህን በፀሐይ ኃይል የሚሠራ መሣሪያ 10 ሺህ ሰው በየቤቱ ቢያስገጥም እያንዳንዱ ቢያንስ አምስት ኪሎ ዋት ኤሌክትሪክ ኃይል በቀን ያስፈልገው የነበረ ስለሆነ በቀን 50 ሺህ ኪሎ ዋት በወር ደግሞ ከ1500 ሜጋ ዋት በላይ መብራት መታደግ የሚያስችል ሁኔታ ይፈጥራል።ይህ በሕዝብ ደረጃ ሲሰላ የቆቃ ግድበ የሚያመነጨውን የኤሌክትሪክ ኃይል ሁለት ሦስት እጥፍ ከፀሐይ እንደማግኘት የሚቆጠር ነው።
ዜጎች በፀሐይ ኃይል የሚሠራ የውኃ ማሞቂያ እንዲጠቀሙ በማድረግ የኤሌክትሪክ ፍጆታን መቀነስ ይቻላል።በዚህ ዘርፍ ላይ ኢንቨስት ያደረግሁት ለትርፍ ብቻ ሳይሆን የኃይል እጥረት ችግርን ሊቀርፍ የሚችል በመሆኑ ነው።ይህ ሥራ ልክ እንደ አንድ ሀገራዊ ፕሮጀክት መታየት ያለበት ነው።
ጫና በመብዛቱ ምክንያት የሚፈነዳውን የትራንስፎርመር ቁጥርም ይቀንሰዋል።ባለው የኃይል እጥረት ምክንያት መብራት ኃይል ትልቅ ድጋፍ ይፈልጋል።የመብራት ኃይልን ጫና በከፍተኛ ሁኔታ መቅረፍ የሚቻለው በነዚህ ዓይነት ፕሮጀክቶች ነው፡፡
አቶ አሰፋ አክለው እንዳሉት በዚህ ድርጅት የተሠሩ ከ300 በላይ የሚሆኑ በፀሐይ ኃይል ውኃ የሚያፈሉ ማሽኖች በተለያዩ ቦታዎች ተተክለዋል።አሁን በተ ደረገው ዳሰሳ ከሥምንት ሜጋ ዋት በላይ በቀን የኤሌክትሪክ ኃይል መቆጠብ አስችሏል።ይህ በጣም ትንሽ ሊሆን የቻለው የጠየቅነውን የመሥሪያ ብድር በጊዜው ባለማግኘታችን ነው።
ብድሩን በጊዜው ቢያገኙ ከዚህ በላይ ምርቶችን በመሸጥ መብራት ኃይልንም የበለጠ ማገዝ የሚችሉበት ሁኔታ ይፈጠር ነበር።ሆኖም ዳሽን ባንክ ይህን ፋብሪካ ጎብኝቶ ለጊዜው ያለበትን አጣብቂኝ ሁኔታ ሳይሆን ለሀገር የሚያበረክተውን አስተዋፅዖ በማየት የመሥሪያ ብድር ሊያቀርብላቸው በመቻሉ ፋብሪካው አሁን በጥሩ ሁኔታ ውስጥ ይገኛል።አሁን ያለው ጥሬ ዕቃ የሚያስመጡባቸው ሀገራት በኮቪድ 19 ምክንያት በራቸውን የመዝጋት ችግር ብቻ ነው፤ ይህ ሲቀረፍም ወደምርት ለመግባት ዝግጁ ናቸው።
ምርታቸው በገበያ ላይ ስላለው ተወዳዳሪነት የጠየቅናቸው አቶ አሰፋ እንዲህ ብለዋል፤ የሚያስ ፈልገውን ደረጃ ጠብቀን ስለምናመርት ጥሬ ዕቃ የምናስመጣባቸው ሀገራት በራቸውን ክፍት ሲያደርጉ በሚቀጥሉት ቅርብ ጊዜያት በምሥራቅ አፍሪካ ኤክስፖርት ሥራ እንጀምራለን።የምርት ግብዓት ጥራታቸውን የጠበቁ ስለሆኑ ከዚህ በኋላ ማሻሻል ቢጠበቅብን እንኳን ቢኖር አዳዲስ ዲዛይኖችን በመሥራት ምርቶቻችንን ሳቢ ማድረግ ብቻ ነው።ይዘን የገባነው የእስራኤል ቴክኖሎጂ ስለሆነ በጥራትና በተወዳዳሪነት ረገድ ችግሮች አይገጥሙንም።
በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን የኢንቨስትመንት አቀባበል በተመለከተም አቶ አሰፋ ይህን ይላሉ፤ ‹‹ሀገራት ኢንቨስተሮችን በበርካታ ውድድር ነው እየሳቡ ያለው፤ ኢንቨስተሮች መጥተው እናልማ በሚሉበት ጊዜ ምቹ ሁኔታ መፈጠር ካልተቻለ ኢንቨስትመንትን መሳብ አይቻልም።
ሌሎች ሀገራት መሬት በነፃ ያቀርባሉ፤ ብድርም ያለ ወለድ ያበድራሉ።ኢንቨስተሮች ፈቃድ ከወሰዱም በኋላ የት እንደሆኑና ምን እንደሚሠሩ ክትትል መደረግ አለበት።ሀገሪቱን የሚጠቅማት የኢንቨስትመንት ሕግ መውጣቱ ሳይሆን ተግባራዊ መደረጉ ነው።
የባንኮቹ አለመተባበር ለኢንቨስትመንቱ ከፍተኛ ራስ ምታት ነው።ኢንቨስት ለማድረግ ከመጣሁበት ጊዜ ጀምሮ የብድር አቅርቦቱ አስደሳች አልነበረም።ውጭ ሀገር ኖሬ ቴክኖሎጂውን ይዤ መጥቼ ብድር በምጠይቅበት ጊዜ ብዙ ውጣ ውረዶች ገጥመውኛል።የጠየቅሁትን ብድር አሳንሶ ከመስጠት ጀምሮ የተለያዩ ችግሮች ተፈጥሮ ነበር።
አዲስ ቴክኖሎጂ ይዞ ሀገሬን ላልማ ብሎ ለመጣ ሰው ያን ዓይነት አቀባበል መኖር አልነበረበትም።አንዳንዴ በተለይም በቴክኖሎጂ ረገድ የሚገኙ ትርፎች በገንዘብ ብቻ መተመን አይኖርባቸውም።የሚኖረው የቴክኖሎጂ ሽግግርና ጎን ለጎን የሚያስገኛቸው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ከግምት ውስጥ መግባት ያስፈልጋል።ከመጀመሪያው ጊዜ ጀምሮም ብድር ለማግኘት የሚወስደው ረጀም ጊዜ ተገቢ አይደለም፡፡›› ሲሉ ይናገራሉ።
በሚኒስቴር ደረጃ ያሉ ግንዛቤው ያላቸው ተቋማት እንኳን ለመተባበር ያደረጉትን ጥረት ባንኮች አካበቢ ጆሮ መንፈግ ነበር። በባንኮች በኩል ላለመክሰር በመስጋት የሚደረግ ክትትልና ቁጥጥር ቢኖር እንኳን ቁጥጥርና ክትትሉ መደረግ ያለበት ለድጋፍ እንጂ ፋብሪካዎች ላይ እርምጃ ለመውሰድና ውድቀታቸውን ለማፋጠን መሆን አይኖርበትም።
ባለው ቢሮክራሲ ምክንያት ምርት ላይ ስትደርስ የነበረህ የሥራ መነቃቃት ሞቶ፤ አቅምህም ደክሞ ነው የምትደርሰው።ኢንቨስትመንቶችን እየረ ዱና አብረው እየሠሩ ወደፊት የማራመድ ግዴታ በተለይ በመንግሥት ባንኮች ግዴታ መሆን ይገባዋል የሚል መልዕክት አላቸው።
ጋን በጠጠር ይደገፋል እንዲሉ የኃይል ማመንጫ ግድቦቻችንን ጫና በዚህ መሣሪያ ማቃለል ከተቻለ ጣሪያ ላይ የሚንጠለጠል የኃይል ማመንጫ አማራጭ መሆኑ ነውና ይህን ኃይል በመጠቀም ገንዘባችንንና የሀገራችንን የኤሌክትሪክ አቅርቦት ከብክነት እናድን።በመንግሥት በኩል በተለይም በኢንቨስትመንት ረገድ እየወጡ ያሉ የሪፎርም ሥራዎች መሬት ላይ መውረዳቸውን ማረጋገጥ ተገቢ ነው፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 26/2013