ጌትነት ምህረቴ
ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በአማራ ክልል የተከሰተው ጆሮን ጭው የሚያደርግ፣ የሚያስደነግጥና የሚያሳዝን ድርጊት ነው። በወቅቱ በክልሉ የተከሰተው የፀጥታ ችግር ሳይፈታ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ግድያ ያልተጠበቀ፤ ሕዝብን ድንጋጤ ውስጥ የከተተ ነው።
ይህ አሳዛኝ ድርጊት የተፈፀመው ክልሉ በሁለት እግሩ መቆም አቅቶት እዚህም እዚያ ግጭቶች በሚከሰቱበት ወቅት ነበር። በዚሁ ወሳኝ ወቅት ሐምሌ 15 ቀን 2011 ዓ.ም አቶ ተመስገን ጥሩነህ በአማራ ክልል ምክር ቤት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደድር ሆነው ተሹመዋል።
አቶ ተመስገን ከክልል እስከ ፌዴራል በተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በተለያየ የኃላፊነት ደረጃ ቢያገለግሉም በጊዜው የተሰጣቸው ሥልጣን ፈታኝ እንደነበር የተናገሩ ብዙዎች ናቸው።
በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ በመሆን ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ ተመስገን የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት የሆኑበት ጊዜ አስቸጋሪ ጊዜ ላይ ነበር። የክልሉን ፀጥታና ሰላም ለማስጠበቅ ከፊታቸው ብዙ የቤት ሥራዎችና ፈታኝ ችግሮች የተደቀኑባቸው ጊዜ ነበር።
ሆኖም ብልሁ መሪ አቶ ተመስገን ችግሮችን አንድ በአንድ በሰከነ መንገድ እየፈቱ በክልሉ አንፃራዊ ሰላም ያመጡ መሪ ናቸው። ክልሉ ሰላሙ የተረጋገጠበት፤ ለሌሎች ደጀን የሆነና በፀጥታ ችግርና በመሪዎቹ ድንገተኛ ግድያ ምስቅልቅሉ የወጣውን ክልል መስመር እንዲይዝ አድርገዋል።
ብልሁና አስተዋዩ መሪ አቶ ተመስገን ጥሩነህ በአማራ ክልል በፕሬዚዳንትነት በሰሩባቸው ጊዜያቶች ሁሉ ከውጭም ሆነ ከውስጥ የነበሩ ችሮችን በማስተዋልና በጥበብ እየፈቱ እዚህ ደርሰዋል። የኢትዮጵያ ሰላምና ብልጽግና ምቹ ጎዳና በመምራት ረገድም ሳይታክቱ የሠሩ ተራማጅ አመራር ሆነው ተገኘተዋል።
ክልሉ በውስጥና በውጭ ችግሮች ቢተበተብም፤ ትብታቡን በጣጥሰው የወጡ መሪ ናቸው። በአንድ በኩል በቅማንትና በአማራ ግጭትና ሥርዓት በሌላቸው ታጣቂዎች የተፈተኑበት ወቅት ነው።
ከክልሉ በውጭ ደግሞ ህወሓት ጁንታ ቡድን የሀሰት መረጃ እየለቀቀና ፋይናንስ እያደረገ ለዘመናት በአብሮነት የኖረውን የቅማንት እና የአማራ፣ የአማራና የአፋር ሕዝብ፣ የአማራና የኦሮሞ ሕዝብ ወደ ግጭት እንዲያመራ እየሠራ መሆኑ ሌላው ፈተና ነበር።
ምስጋና በተግባር እንዲሉ አቶ ተመስገን ጥሩነህ የሚመሰገኑት በእሳቸው አመራር እነዚህን ሁሉ ፈተናዎችና ሴራዎች አልፈውና አክሽፈው የክልሉን ሰላምና ፀጥታ በሁለት እግሩ በማቆማቸው ነው።
በተለይ በክልሉ የነበረውን ውጥንቅጡ የወጣ የሰላም እጦትና ግጭት በአጭር ጊዜ በሚታይ ለሚጨበጥና ሊሚመዘን በሚችል መልኩ ውጤት ማምጣታቸውን ማንም የሚክደው አይደለም።
የሥራ ውጤታቸውን ያሳዩን በወሬና በአፈ ቀላጤዎቻቸው በኩል ሳይሆን እርሳቸው በፕሬዚዳንትነት በሚመሩት ክልል ውስጥ ሰላምን በማስፈናቸው ነው። በእርቅ የሚፈታው በእርቅ በሃይል የሚፈታው በሃይል ፈትተው ወደ ምቹ ጎዳና የወሰዱ ተራማጅ መሪ ናቸው።
አቶ ተመስገን ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ረጅም ርቀት የሚጓዙም መሪ ናቸው። አቶ ተመስገን የህወሓት ጁንታ ቡድን የአማራ ክልልን የጦርነትና የግጭት ቀጠና ለማድረግ አልሞ ሲንቀሳቀስም እነዚህን ሁሉ ሴራዎች እንዲከሽፉ አመራር የሰጡ፣ በመጨረሻም ጁንታው የአማራን ሕዝብ ለመውረር ያደረገውን ሙከራ ከፀጥታ ሃይሉ ጎን ሆነው ውጤታማ ሥራ እንዲሠራ የበኩላቸውን ከፍተኛ ድርሻ የተወጡ መሪ ናቸው።
በወቅቱም እርሳቸውም በማህበራዊ ገፃቸው ላይ እንዲህ ብለው ነበር። ጁንታው ወራሪ ሃይል የከፈተው ጥቃት ከሽፎ ድል ተመዝግቧል። ድሉ ይቀጥላል። እውነትም ያሉት ነገር ጠብ ሳይል ዛሬ ጁንታው ላይመለስ ተሸኝቷል።
የአማራ ክልል በአንድ ምሽት አራት መሪዎቹን ሲያጣ ክልሉ እንደ ክልል አይቀጥልም፤ የማያባራ የአዙሪት ግጭት ውስጥ ይገባል። ኢትዮጵያዊነትም ይናጋል የሚለው የብዙዎች ሥጋት ነበር።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ተስፋ አስቆራጭ የሆነበት ጊዜ እርሳቸው የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት ሆነው የተሰየሙበት ወቅት ነው። ክልሉን በዛ አስቸጋሪ ወቅት በፕሬዚዳንትነት የተረከቡት አቶ ተመስገን የክልሉን ሰላምና ፀጥታ በአጭር ጊዜ ማረጋገጥ የቻሉ ጠንካራ መሪ ናቸው።
ሰሞኑን በባህር ዳር ከተማ በተካሄደው የአቶ ተመስገን ጥሩነህ የሽኝት ዝግጅት ላይ የተገኙት የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ለአቶ ተመስገን አመራር የሰጡት አድናቆት የምስክርነት ቃል የብቃታቸው ተጨማሪ ማረጋገጫ ይሆናል። አቶ ተመስገን የክልሉ ሰላም እና ፀጥታ እንዲሁም ጁንታውን ለማስወገድ ያደረጉት አስተዋፅኦ የሚደነቅና የሚወደስ መሆኑን ምስክርነት ሰጥተዋል።
በሽኝት ሥነ ሥርዓቱ ለአብነት ያህል የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ሰው በጠፋበት ሰው ሆነው የተገኙ፤ ብልህ፣ አስተዋይና አርቆ አሳቢ የሆኑ መሪ ናቸውም ብለዋል። አቶ ተመስገን አስቸጋሪ በሆነ ወቅት ከጎኔ ሆነው አመራር ሰጥተውኛልም ነው ያሉት። በፈተና ውስጥ ሆነው ከፈተና በኋላ ያለውን ድል የሚመለከቱ እንደሆኑም ምስክርነት ሰጥተውላቸዋል።
ሌላው በሽኝት ፕሮግራሙ ከተገኙት የክልሎች ርዕሰ መስተዳድሮች መካከል አንዱ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሙስጠፌ መሀመድ አንዱ ናቸው። እርሳቸው ስለ አቶ ተመስገን ምስክርነት ሲሰጡ እንዳሉት፤ የሶማሌ ክልል ከፍተኛ ችግር በነበረበት ጊዜ አቶ ተመስገን ድጋፍ ያደረጉልን መሪ ናቸው ።
የሶማሌ ክልል መዋቅር ፈርሶ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሙስጠፌ ክልሉ መዋቅሩ እንዲስተካከል ከፍተኛ ድጋፍ አድርገዋል። እናም አቶ ተመስገን የአማራ ክልልን ብቻ ሳይሆን የሶማሌ ክልልንም አሻግረዋል። አሁንም ከአንድ ፈተና ወደ ሌላ ፈተና የሄዱ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ሙስጠፌ ያሉበትን ተቋም እንደሚያሻግሩትም እምነት አለኝ ሲሉ አድንቀዋቸዋል።
ተጨባጭ ሥራ ለሠራ ሰው እናመሰግናለን ማለት የታላቅነት መገለጫ ነው። ከዚህ አኳያ አቶ ተመስገን ጥሩነህ ብቻ ሳይሆኑ አቶ ሙስጠፌ መሀመድ መመስገን የሚገባቸው የክልል መሪ ናቸው።
አቶ ሙስጠፌም የሶማሌ ክልልና የኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በተፈጠረ ግጭት አንድ ሚሊዮን ያህል ዜጎች በተፈናቀሉበትና ክልሉ የግጭት ቀጠና በሆነበት ወቅት ነው የክልሉ ፕሬዚዳንት የሆኑት።
መንግሥታዊ መዋቅሮች ፈርሰው በሰላም ከቤት ወጥቶ መግባት ብርቅ በሆነበት ጊዜ ነው ወደ አመራርነት የመጡት። እርሳቸው በክልሉ ፕሬዚዳንት በሆኑበት በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰላምን አረጋግጠዋል። የአካባቢውን ፀጥታ ያስጠበቁት የኮንትሮባንዲስቶች ኔትወርክ በጣጥሰው በክልላቸው ሰላም እንዲሰፍን ሕዝቦች እንዳይፈናቀሉ አድርገዋል።
እንደ አቶ ሙስጠፌ የተቃና አመራር ሲገኘ ጊዜያዊ ችግር ከመፍታት ተሻግሮ አገርን ማሻገር የሚችል ይሆናል። ዘላቂና ዘመን ተሻጋሪ የሆነውን የሕዝቦች ግንኙነትና ትስስር በተደላደለና አስተማማኝ በሆነ መሰረት ላይ ማኖር የሚቻልበትን ዕድል መፍጠር የቻሉ መሪ ናቸው ።
በተለይ እንደ አቶ ሙስጠፌ ያሉ መሪዎች ኋላ ቀር ሀሳቦችን አሸንፈው ተራማጅ ሀሳቦችን ይዘው የመጡ በመሆናቸው የሌሎችን ክልሎች አመራሮች ይዞ ለማውጣት ያስችላሉ።
አሁን ሥራ ላይ ያሉ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮችም ከእነ አቶ ተመስገንና አቶ ሙስጠፌ ብዙ ትምህረት መውሰድ አለባቸው። በክልላቸው የሚከሰቱ ግጭቶችን በዘላቂነት ማድረቅ ይኖርባቸዋል።
ባለፈ ታሪክ እርስ በእርስ ከመወቃቀስ ይልቅ ወደፊት የሚያሻግር የጋራ ሥራዎች ላይ ማተኮር አለባቸው። የሕዝቦችን ደህንነት በጋራ በመጠበቅ ኢትዮጵያን በጋራ ለማሻገር መሥራት ያስፈልጋል።
መጪው ጊዜ የሠራ የሚመሰገንበት፤ ጀግና የሚደነ ቅበት፣ ታታሪ የሚበረታታበት በአንፃሩ የሰረቀ በሕግ የሚጠየቅበት፣ ያልሠራ የሚወቀስበት፣ ያጭበረበረና አድር ባይ የምንፀየፍበት ይሁንልን። አሜን!
አዲስ ዘመን ጥር 26/2013