የኢትዮጵያ ፖለቲካና ፖለቲከኛ በዘመናት ሂደት ውስጥ የራሱን ገጽ እያስነበበ፤ በማያቋርጠው የአገረ መንግሥት ግንባታም ሁሉም የየራሱን የፖለቲካ መስመር ቀይሶ አልፏል።
ላለፉት ሶስት አስርተ ዓመታት በቆየው የፖለቲካ ጉዞ ውስጥም በጉልህ በተስተዋለው የመጠላለፍ ፖለቲካ አገርና ሕዝብ የበዛ ዋጋ ከፍለዋል። መልኩን እየቀያየረ በሚገለጸው የሴራ አካሄድም፤ የሰው ሕይወት ጠፍቷል፤ አካል ጎድሏል፤ ዜጎች ተፈናቅለዋል፤ ንብረትም ወድሟል።
ከዚህ ሁሉ በኋላ ከመጣው ለውጥ ማግስትም ቢሆን የጥፋት ኃይሎች ሕዝብን የማሸበርና አገር የማተራመስ ተግባራቸው በመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት እስከመፈጸም አድርሷቸው በቆፈሩት ጉድጓድ እንዲገቡ ሆነዋል። ዛሬም ቢሆን የጥፋት ኃይሉ ርዝራዦች በተለያየ መልኩ አገርን ለማተራመስ፣ ሕዝብንም ሥጋት ውስጥ ለመክተት አላንቀላፉም።
ለዚህ አንድ መንገድ አድርገው የያዙት “የእሳት ፖለቲካ” ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የንግድና የገበያ ማዕከላትን እያወደመ ይገኛል።በዚህም ከመሐል አዲስ አበባ እስከ ዳር አገር፤ ከዋና ከተማ እስከ ቀበሌና መንደር የዘለቀ የእሳት አደጋዎች ታይተዋል፤ በዚህም በብዙ ላብ እና ጥረት የተገኙ ሀብትና ንብረቶች የእሳት እራት ሆኗል።
በኢትዮጵያ ባለፉት ሶስት ወራት (ህዳር፣ ታህሳስና ጥር) ያለውን የእሳት ቃጠሎ ክስተት ስንመለከት ከሕግ ማስከበር እርምጃው ባሉ በእነዚህ ወራት ውስጥ በይፋ ሪፖርት የተደረጉ ከ21 በላይ የእሳት አደጋዎች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተከስተዋል።
ለምሳሌ፣ በህዳር ወር ከተከሰቱት መካከል በአዲስ አበባ የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 በተለምዶ አዋሬ ገበያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የደረሰው የእሳት አደጋ ተጠቃሽ ሲሆን፤ በአደጋው በርካታ ከባድ የንብረት ውድመት ደርሷል።
በተመሳሳይ በታህሳስ ወር 11 ያክል የእሳት አደጋ የተከሰተ ሲሆን፤ እነዚህም በአዲስ አበባ፣ ጅግጅጋ፣ ባህርዳር፣ ደብረማርቆስ፣ ወላይታ ሶዶ፣ ሐሮማያ እና ሌሎችም ቦታዎች ይገኙበታል።
በታህሳስ ወር ከተከሰቱ የእሳት አደጋዎች መካከል ጎላ ብለው ከታዩት መካከል ታኅሣስ 18 እና 19፣ በሀዲያ ዞን በደረሱ የእሳት አደጋዎች ቤቶች ተቃጥለዋል፤ 510 የቤተሰብ አባላትም ተፈናቅለዋል። በደረሰው ጉዳትም ከ23 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ወድሟል። በጥቅሉ በወሩ ውስጥ በዞኑ 15 ሱቆች እና 47 ቤቶች ተቃጥለው 33 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ወድሟል።
በተመሳሳይ ታኅሣስ 19፣ በምዕራብ ኦሞ ዞን ቤሮ ወረዳ ሾላ ቀበሌ በተከሰተ የእሳት አደጋ ከ586 ሚሊዮን ብር በላይ በሚገመት ንብረት ጉዳት የደረሰ ሲሆን፤ 16 ሺህ 709 ነዋሪዎች ከመኖሪያ ቤታቸው ተፈናቅለዋል። እየተጠናቀቀ ባለው ጥር ወርም ቢሆን ከሰባት በላይ የእሳት አደጋዎች በተለያዩ አካባቢዎች ተከስተዋል።
እነዚህ የተጠቀሱት ከብዙ በጥቂቱ የሚነሱ ማሳያዎች እንጂ የችግሩን ሙሉ ገጽታ ወካዮች አይደሉም። በአዲስ አበባ መሰል የእሳት አደጋዎች እየተበራከቱ ነው፤ ብሔራዊ ባንክንና የጉለሌ ዕፅዋት ማዕከልን ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች የተከሰቱ እሳት አደጋዎች ነበሩ።
እነዚህ የእሳት አደጋዎች በምክንያት ሊከሰቱ እንደቻሉ ለመገመት አስቸጋሪ አይደለም። ምክንያቱም የእነዚህ አደጋዎች በተለይም በንግድ ማዕከላት አከባቢ ትኩረታቸውን ማድረጋቸው ከበስተጀርባ አንዳች የተደበቀ ምስጢር ስለመኖሩ ጠቋሚ ነው።
ለምሳሌ፣ ከሰሞኑ በአዲስ አበባ ከተማ ከደረሱ ሁለት የእሳት አደጋዎች በተጓዳኝ ሌላ ሁለት አደጋዎችን ለማድረስ የተደረገን ሙከራ ማክሸፍ ተችሏል። ይህ ደግሞ በከተማው በተለያዩ አካባቢዎች እየታዩ ያሉ የእሳት ቃጠሎዎች ቀደም ሲል የጥፋት ዓላማቸው ያልተሳካላቸው አካላት ሆን ብለው ህብረተሰቡን ለማሸበር እያደረጉት ያለው ተግባር አካል ለመሆናቸው መጠርጠር ተገቢ ነው።
አሁን የደረስንበት ሀገራዊ ፖለቲካ በሰላምና በሃሳብ የበላይነት የሚከወን እንጂ በእሳት የሚጫወቱት ቁማር አይደለም። ነገ አገርና ሕዝብን ከፍ በሚያደርግ ሀሳብ እንጂ፤ ሀብትና ንብረትን የእሳት እራት በማድረግ አገርና ሕዝብን ወደድህነት የሚመልስ መንገድን ሊሆን አይገባም ።
ከዚህ ሀገራዊ ተጨባጭ እውነታ በመነሳት “የእሳት ፖለቲካ” ቁማርተኞችም አደብ ልትይዙ፤ መንግስትም ተገቢውን እርምጃ ሊወስድ ይገባል። የፀጥታና የደህንነት አካሉም እነዚህን መልካቸውን እየቀያየሩ የሚገለጡ የጥፋት ኃይሎችን አድኖ በመያዝ ኃላፊነታችሁን መወጣት ይኖርባችኋል።
ህብረተሰቡም ቢሆን ሳይደናገጥ ተገቢውን ጥንቃቄ እያደረገ፣ ነቅቶ አካባቢውን በመከታተል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ለጋራ ሀገር ደህንነት በቁርጠኝነት ሊንቀሳቀስ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን ጥር 26/2013