ታምራት ተስፋዬ
ፌስቡክ ሰዎች ጓደኛ የሚያፈሩበት፤ ስሜት፣ ሃሳብና እውቀታቸውን የሚለዋወጡበት፣ የሚያሰራጩበትና የሚስተላልፉበት ግዙፉ የማህበራዊ ሚዲያ ገፅ ነው። በመድረኩ መልካምና ገንቢ እሳቤዎች የሚንሸራሽሩበትን ያህል በተለይ በአሁኑ ወቅት ሲመሰረት አላማው ካደረገው ማህበራዊ ሚናው በማፈንገጥ የፖለቲካ መድረክ በመሆን እያገለገለ ይገኛል፡፡
የተለያየ ፍላጎትና ተልዕኮ ያላቸው ግለሰቦች፣ ቡድኖችና ፓርቲዎችም ዓላማቸውን ለማስፋፋት ብሎም ለማሳካት ማህበራዊ ሚዲያውን ተመራጭ አድርገውታል። በርካቶች ጥላቻንና ስሜታዊነትን የሚሰብኩበት፣ ጦርነት የሚቀሰቅሱበት፣ ግለሰብን፣ ሕዝብንና አገርን የሚዘልፉና የሚያፈርሱ መልዕከቶችን የሚያስተላልፉበት መድረክ እየሆነም መጥቷል። «ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት» በሚል ሽፋን የራሳቸውን ፖለቲካዊ ዓላማ ባነገቡና መርዛም ብዕር በመጨበጥ ፍርሃትንና ስጋትን በማሰራጨት ሕዝብን ምቾትና እንቅልፍ ማሳጣት በሚፈልጉ የመንደሩ ፀሐፍት የጥፋት ተግባርም ከአገር እስከ ግለሰብ በርካቶች ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ኪሳራ ደርሶባቸዋል፡፡
በመላው ዓለም የሚገኙ የመድረኩ ተዋናዮችም፣ እውነትን በውሸት ለውሰው አንድን ክስተት በርዝውና ከልሰው እንዳልሆነ በሚያስተላልፉ፣ ማሰብ መጨነቅን፣ ማበጠርንና ማጣራትን በማያውቁ ግዴለሽ እና ልበ ደንዳኖች ተግባር በተደጋጋሚ ሲማረርና ይህን ስሜቱንም በተለያዩ መንገዶች ሲገልፅ ቆይቷል፡፡
ካምፓኒው በአንፃሩ መሰል ቅሬታዎችን ሰምቶ አፋጣኝ ምላሽ በመስጠትም ሆነ ከፖለቲካዊ ውዝግቦች ጋራ ተያይዞ የጠለሸው ስሙን በማደስ ረገድ ፈጣን ሆኖ አልተስተዋለም፡፡ ከቀናት በፊት ግን ከእንቅልፉእንደነቃ የሚያስታውቅ ውሳኔን ይፋ አድርጓል። ‹‹ከፖለቲካ ጋራ የተገናኙ ግሩፕ ወይም ቡድኖችን ለተጠቃሚዎቹ ሪኮመንድ ማድረግ እንደሚያቆም እወቁልን›› ብሏል።
የፌስቡክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ማርክ ዙከንበርግም፣ ‹‹በአሁኑ ወቅት ከማህበረሰባችን በኩል ተደጋግሞ ከሚቀርቡ ዋነኛ አስተያየቶች መረዳት የቻልነው፣ የፖለቲካ ጉዳይ ምቾት እንዳልሰጣቸውና ጡዘቱም ወደ ማህበራዊ ትስስር ገፁ እንዳይገቡ፣ ከገቡም ብዙም ሳይቆዩ ለመውጣት እያስገደዳቸው መሆኑን ነው›› ብሏል።
የዩናይትድ እስቴትስን የምርጫ መርሃ ግብር ተከትሎ ፌስ ቡክ ከፖለቲካ ጋራ የተገናኙ የሲቪክና ፖለቲካ ቡድኖችን ለተጠቃሚዎቹ ሪኮመንድ ማድረግ ማቋረጡ ያስታወሰው ዋና ሥራ አስፈፃሚው፣ ይህ ውሳኔም በመላ ዓለም ተፈፃሚ እንደሚሆን አስታውቋል። በተጨማሪም ከፋፋይ ውይይቶችን ለመገደብና ግለቱን ለመቀነስ በማሰብ ፖለቲካ ነክ ፖስቶች ያላቸውን ተደራሽነት እንደሚቀንስም አሳውቋል፡፡
እርምጃው ፌስቡክ ካለበት እንደ ነውጥ እና የተሳሳተ መረጃ ማዕከል ተደርጎ የመታየት ችግር ለመውጣት ታልሞ የተወሰደ ነው፡፡
ከሳምንታት በፊትም ተቋሙ የአሜሪካን ምክር ቤቶች የሚገኙበት የካፒታል ሕንፃ ላይ በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች አማካኝነት ነውጥ መነሳቱን ተከትሎ የፕሬዚዳንቱን አካውንት ማገዱ ይታወሳል፡፡ ከቀናት በፊትም እገዳው ይዝለቅ ወይስ ይቁም የሚለው ላይ የሚወስን ገለልተኛ ተቆጣጣሪ ኮሚቴ አዋቅሮ ነበር።
የኮሚቴው አባላት አብዛኞቹ ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ ናቸው፡፡ የቀድሞው የዴንማርክ ጠቅላይ ሚኒስትርና የኖቬል የሰላም ሽልማት አሸናፊ እንዲሁም የተለያዩ የሕግ ባለሙያ፣ ጋዜጠኛ፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን ጨምሮ 20 ግለሰቦችን ያሰባሰበ ነው፡፡
ፕሬዚዳንቱ ላይ የተላለፈውን እገዳ ተከትሎም ሁለት ዓይነት አስተያየቶች ተስተጋብተዋል፡፡ ‹‹አብዛኞቹ መሰል ውሳኔ ቀደም ብሎ መተግበር ነበረበት ሲሉ፣ አንዳንዶች በአንፃሩ ውሳኔው የፕሬዚዳንቱን ነፃነት የሚያፍን ነው በሚል ተቃውመውታል፡፡
ፖለቲካ ነክ ጉዳዮች ላይ የተላለፈው ተደራሽነትን የመገደብ ውሳኔን በሚመለከት፣ የካምፓኒው የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ኒክ ክሌግ፣ ‹‹ውሳኔያችን አስፈላጊና ትክክለኛ እንደነበረ አምናለሁ›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የሲ ኤን ኤን የቢዝነስና ቴክኖሎጂ አምድ ፀሐፊዋ ካያ ዩሪፍ እንዳስነበበችው፣ ግዙፉ የማህበረሰብ ትስስር ገፅ በባለፈው ዓመት የመጨረሻ ሦስት ወራት በአጠቃላይ 28 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አግኝቷል፡፡
ዓለማችን ኮሮና ቫይረስ ዓለም ይበልጥ በተጨነቀችበት ወቅትም ካምፓኚው፣ ቢሊየኖችን በማገናኘት ማስታወቂያዎቹን ቀጣይ ለማድረግ ባለመቸገሩ 11 ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ትርፍ አግኝታል፡፡
ይህም በ2019 ከነበረው የ50 በመቶ ብልጫ አሳይቷል። ካምፓኒው፣ ኢንስታግራም፣ ሜሰንጀርና፣ ዋትስ አፕ ፌስ ቡክን የሚጠቀሙትን ጨምሮ በመላ ዓለም በየወሩ ከሦስት ነጥብ ሦስት ቢሊዮን በላይ አክቲቭ ተጠቃሚዎች እንዳሉት የጠቆመችው ፀሐፊዋ፣ የተጠቃሚዎቹ መጠንም ከዓመት ዓመት በ14 በመቶ የከፍታ ብልጫ እያስመለከተ ስለመምጣቱ አስረድታለች።
የካምፓኒው ዋና ሥራ አስፈፃሚው ማርክ ዙከምበርግም፣ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ሰዎችም ሆነ የቢዝነስ ተቋማት አገልግሎታቸንን ይበልጥ ተጠቅመውታል›› ብሏል፡፡
ይሁንና በአሁኑ ወቅት ድርጅቱ ላይ የሚነሱ ቅሬታዎች ቀጣይ ስኬቱ ላይ እንቅፋት እንደሚሆኑ የሚገልፁ አልጠፉም፡፡ በኢንቨስቲንግ ዶት ኮም ስመጥር ባለሙያ የሆነችው ጄሲ ኮህን በአንፃሩ፣ የመተዋወቂያና የማስተዋወቂያ መድረክ የሆነውን የዓለማችን ግዙፍ የማህበራዊ ድረ ገፅ ከመራመድ ሊያስቆም የሚችል እንዳችም ኃይል እንደሌለር እወቁት››ብላለች፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 25/2013