ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አቶ አህመድ ሃጂ ዋሴዕ ይባላሉ፡፡ የተወለዱት ዱብቲ ከተማ ነው። ወላጆቻቸው ልጅ አይጠገብም ከሚሉ ቤተሰብ ናቸውና ከወለዷቸው 11 ልጆች መካከል አቶ አህመድ አምስተኛ ልጅ ሆነው በቤተሰብ አባልነት ተቀላቀሉ።
ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስም በተወለዱበት መንደር አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። ከቤታቸው እስከ ትምህርት ቤት ድረስ ያለው ስድስት ኪሎ ሜትር በየቀኑ ሳይሰለቹ በእግራቸው እየተመላለሱ ፡፡
12ተኛ ክፍል እንዳጠናቀቁ 1990 ዓ.ም መቐለ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ገብተው በክሊኒካል ነርሲንግ በዲፕሎማ ተመርቀዋል፡፡ ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ ሄልዝ ኬር ማኔጅመንት ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ሥራ ዓለም ዳግም ተመለሱ፡፡ ከ19 ዓመት በፊት በመንግሥት ተቋም ተቀጥረው በክልሉ ጤና ቢሮ ሠርተዋል፡፡
የክልሉ ጤና ቢሮ የበሽታ መከላከል ኃላፊም ሆነው ለአንድ ዓመት ከሁለት ወር አገልግለዋል፡፡ ሆኖም የወር ደመወዝተኛ ሆኖ መቆየቱ ብዙም አላስደሰታቸውም፡፡ የራሴን ሥራ ልጀምር በማለት ያወጡ ያወርዱ ጀመር፡፡ በርከት ያሉ ሃሳቦች በአዕምሯው ያመላልሳሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ታዲያ በአካባቢው ወደ ንግድ ለመግባት የሚያስችለውን ዘርፍ ከለዩ በኋላ ከመንግሥት ሥራ በፈቃዳቸው ለቀው ወደ ንግድ ዓለም ተቀላቀሉ ፡፡
በእርግጥ ወደ ንግዱ ዓለም ዘው ብለው አልገቡም። ቤተሰባቸው በንግድ ህይወት ውስጥ ነው ያለፉት፡፡ ታላቅ ወንድማቸው ከአሰብ እስከ ጅቡቲ በመንቀሳቀስ ይነግዱ ነበር፡፡ አባታቸውም በተመሣሣይ በአካባቢው ጎበዝ ነጋዴ የሚባሉ ናቸው፡፡
ታዲያ ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ሃሳባቸውን ለማሣካት ወደ ቤተሰቦቻቸው ጠጋ ብለው ሥራውን ጀመሩ፡፡ የተወሰነ መነሻ ገንዘብ ከቤተሰብ አግኝተው ወደ ንግድ ዓለም ገቡ፡፡ በሂደት የጨው ንግድ ጀመሩ፡፡ ይህም ለእርሳቸው አንድ እርምጃ የስኬት መንገድ መቆናጠጥ ነው ብለው አሰቡ። በቆራጥነት፣ ፅናት እና ትዕግስትም መሥራት ጀመሩ፡፡
ጉዞ ወደ እንግሊዝ
ከ18 ዓመት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ የትምህርት ዕድል አግኝተው ወደ እንግሊዝ ሀገር አመሩ፡፡ እንግሊዝ አገርም ዘመዶች ስለነበሯቸው ብዙም አልተቸገሩም። በሂደት ደግሞ የቤተሰቦቻቸውንም መሰረት እንግሊዝ አገር አደረጉ፡፡ ነገር ግን በአውሮፓ ምድር ጠቅልለው መኖር አልፈለጉም፡፡
ምንም እንኳን ጥሩ መደላድል ያለበት ህይወት ቢገጥማቸውም በአገራቸው በተለይም ደግሞ በተወለዱበት አካባቢ ያለው ማህበረሰብ አኗኗር እና ዘርፈ ብዙ ችግሮችን በርቀት በዓይነ ህሊና ብቻ እያቃኙ መኖሩን አልተቀበሉትም፡፡ ይልቁንም አቅማቸው በቀፈደ መጠንና እገዛ ለማድረግና እውቃታቸውን ሀብታቸውን ጭምር ኢንቨስት ማድረግ እንዳለባቸው ራሳቸውን አሳምነው ወደ ኢትዮጵያ መመላለሱን መረጡ፡፡
ማን እንደ ሀገር
አቶ አህመድ ለአገራቸው እጅግ የላቀ ፍቅርና አክብሮት አላቸው፡፡ ምንም እንኳን ነገሮች በአውሮፓ ምድር የተመቻቸላቸው ቢሆንም በዚያው ሰጥመው መቅረቱን አልፈቀዱም፡፡ እርሳቸው እንግሊዝ አገር ሳሉ የኢትዮጵያን ኮሚኒቲ ጨምሮ ከሌሎች ሰዎች ጋር ይነጋገራሉ፤ ይጨዋወታሉ፡፡
ሆኖም ወደ አገር ቤት ገብቶ ማልማት በሚለው ላይ ብዙ አጋዥ አላገኙም፡፡ እርሳቸው ግን በእረፍት ጊዜ ሁለት ልጆቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ ይዘዋቸው ይመጣሉ፡፡ በዚህም ጊዜ ስለአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ እንዲገነዘቡ ረድቷቸዋል፡፡
እንግሊዝ አገር የቀሰሙትን እውቀትና ልምድ ይዘው ወደ አገራቸው ተመልሰው ኢንቨስት ማድረግ ጀምረዋል። በተለይም ደግሞ አፋር የመሰለ ቦታ ላይ ኢንቨስት ማድረግ ዕድል ነው ይላሉ፡፡ በክልሉ የአካባቢው ማህበረሰብ በብዛት ወደ ኢንቨስመንት አልገባም። ማህብረሰቡም ከኋላቀር አኗኗር አልተላቀቀም። በመሆኑም በዚህ አካባቢ መሥራት ዕድል ነው፡፡
እስካሁን ድረስ በየበረሃው በርካታ ዜጎች ፍየል እያረቡ እና እየነገዱ ይኖራሉ። ብዙም በህይወታቸው ላይ የተለየ ለውጥ አይታይም ከድካም ውጭ። እናም ይሄ ያሳዝናል። የገጠሩ ማህበረሰብ ለመለወጥ እጅግ ከፍተኛ ጥረት ይጠይቃል፡፡ ታዲያ ይህን አካባቢ ማልማት የህሊና ዕረፍት ነው ይላሉ። ውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵውያን አገራቸው ላይ ኢንቨስት ማድረግን ሊላመዱት ይገባል የሚል እምነት አላቸው፡፡
‹‹እንግሊዝ ሀገር አምስት ዓመት ከኖርኩ በኋላ ዜጋ ለመሆን ብቁ ነው ብለው ዜግነት ሰጥተውኛል፡፡ እዚህ አገር ግን በጎጥ፣ በመንደርና በመቧደን አንዱ ሌላውን እያገለለ እጅግ አስነዋሪ ነገሮችን እየተስተዋሉ ነው።
ኢትዮጵየዊ ዜጋ ሆኖ በአገሩ በነፃነት የመንቀሳቀስና የመሥራት መብት መኖርና መረጋገጥ አለበት፡፡ በብሄር ፖለቲካም ቢሆን መጠኑ መገደብ አለበት፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ለአገር ውስጥ ሆነ ለውጭ አገር ኢንቨስተሮች አስቸጋሪ ይሆናል፡፡›› ይላሉ በሀገር ውስጥ ያለውን የፖለቲካ ሁኔታና የታዘቡትን ሲናገሩ።
አዲስ ሥራ
አፋር አካባቢ ጨው በብዛት የሚመረትበት ነው፡፡ አቶ አህመድ ሃጂ ዋሴዕ የጨው ንግዷን ሲጀምር ግን በቂ ብር አልነበራቸውም፡፡ በገበያው ላይም ብዙ ችግሮች ነበሩ፡፡ በተለይም ጨው አምራቾች ለጨው ገዥዎች በእምነት ሸጠው ገንዘባቸውን በጊዜ የሚሰጣቸው አያገኙም፡፡
በዚህን ጊዜ ያለበቂ ገንዘብ በእምነት ብቻ ወደ ጨው ንግድ ገቡ፡፡ ከሚያውቋቸው ሻጮች ጨው በዱቤ እየወሰዱ በትርፍ መሸጥ ጀመሩ፡፡ በዚህ ውስጥ ለዓመታት ቆዩበት፡፡ ቤተሰቦቻቸውም በሥራው ውጤታማ እየሆኑ በመሄዳቸው አይዞ ባይ አገኙ፡፡ እያሉ… እያሉ ከጨው አከፋፋዮችና ትልልቅ ባለሃብቶች ጋር መተዋወቅ ጀመሩ፡፡
የገበያ አድማሳቸውና ትርፋቸውም በእጅጉ እየተጠናከረ መጣ፡፡ ይህ ዘርፍ አዋጭ ሲሆን በክልሉ ከሚሰሩ ሥራዎች በየትኛው ዘርፍ ክፍተት አለ ብለው መለስተኛ ጥናት አካሄዱ፡፡ በመጨረሻም የኮንስትራክሽን ዘርፍ ብዙ ሥራ ከመኖሩም በላይ በክልሉ ብዙ ፕሮጀክቶች እንደሚሰሩ አረጋገጡ፡፡
ይህን አጋጣሚ በመጠቀም የኮንስትራክሽን ፈቃድ አወጡ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜም ጨረታ አሸንፈው 148 ሺህ ብር ሥራ ሠሩ፡፡ ይህም ሌሎች ሥራዎችን ለማከናወንና ጨረታዎችን ለማሸነፍ ብሎም በግንባታ ላይ ልምድ ለማካበት መነሻ ሆናቸው፡፡ በወቅቱ በክልሉ ግንባታዎች እንደ ጉድ ተጧጡፎ ነበር፡፡ በተጨማሪም ጨው ንግድ አዋጭ ነበር፡፡ ታዲያ በሁለቱ ዘርፍ ብዙ ማትረፍ ብዙ ማግኘት ጀመሩ፡፡
አሁን
በአሁኑ ወቅት በክልሉ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ኢንቨስት እያደረጉ ነው፡፡ በሠመራ ዲኒ የሚባል ሆቴል ከፍተው ሥራ ጀምረዋል፡፡ አፋር ክልል ቱሪስቶች በብዛት የሚመጡ ሲሆን ለጎብኚዎች የሚመቹ መሰረተ ልማቶች ባለመኖራቸው በከተሞች አካባቢ የሚቆዩት በጣም ለአጭር ቀናት ወይንም ሰዓታት ነው፡፡
ይህንን ቆይታቸውን ለማራዘም በቂ መሰረት ልማትና ደረጃውን የጠበቀ ሆቴል መኖር አስፈላጊ በመሆኑ ጎብኚዎችን ማዕከል ያደረገ ሆቴል እንደገነቡ ይናገራሉ፡፡ በአሁኑ ወቅትም በሆቴል ሥራው ለ78 ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል ፈጥረዋል፡፡ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ደግሞ ለ58 ሰዎች ቋሚ የሥራ ዕድል ፈጥረዋል፡፡
ዕቅድ
በአሁኑ ወቅት በክልሉ ያሉት ሰባት ሆስፒታሎች እና ሁለት ክሊኒኮች ብቻ ናቸው፡፡ ይህ የጤናው ሁኔታ መሻሻል ስላለበት በቂ አይደለም። እናም ገና ብዙ መሥራት አለበት፡፡ በዚህ ላይ እርሳቸውን ጨምሮ ባለሀብቶች መሳተፍ እንዳለባቸው ይናገራሉ።
አሁን ባለው ሁኔታ በክልሉ አንድም ቦታ የግል ሆስፒታል የለም፡፡ በዚህም በጣም ሰፊ ክፍተት መኖሩን በመረዳታቸው የግል ሆስፒታል ግንባታ የመጀመር ውጥን ይዘዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ባለፈው ዓመት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማህፀን ህክምና ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት ባለቤታቸው ሐኪም በመሆናቸው ሥራውን በሚገባ ለመምራትና ሥራውን የተሳካ ለማድረግም ዕድሉን እንደሚኖራቸው ይናገራሉ፡፡
አቶ አህመድ ሃጂ ዋሴዕ በኮንስትራክሽን ዓለም ላይ 10 ዓመት በላይ አሳልፈዋል፡፡ በዚህ ውስጥ ታዲያ ከእርሳቸው ሥር ተቀጥረው ይሰሩ የነበሩ ሰዎች ራሳቸውን ችለው ተመልሰው ፈቃድ አውጥተው ሲሰሩ ማየታቸው እጥፍ ድርብ ደስታን ፈጥሮላቸዋል። በማህበራዊ ሕይወትም የጠነከረ ወዳጅነት አላቸው፡፡
አቅማቸው በፈቀደ መጠን እጅ አነሶችን ማገዝም ነፍሳቸውን በሀሴት ያረሰርሳል፡፡ ቀደም ሲል በአፋር ባህል ዕቃ ማውረድ፣ ጥበቃ መሆን እና የቀን ሥራ መሥራት እንደ ነውር ይታይ ነበር፡፡ ታዲያ ይህ ሁኔታ እያለፉ አሁን ማንኛውንም ሥራ ለመሥራት ዝግጁ ሆነው ማየታቸው ያስደስታቸዋል፡፡ በቀጣይ ዕቅዳቸውም በርካታ ሰዎች እራሳቸውን ችለው እንዲወጡና ጠንካራ የሥራ ባህል እንዲያዳብሩ ማድረግ ነው።
ምክረ ሃሳብ
በክልሉ አሁንም በኋላቀር የአኗኗር ዘይቤ ውስጥ ያሉ ብዙ ዜጎች አሉ፡፡ አርብቶ አደሮችን በአዋሽ ወንዝ ተፋሰስ አካባቢ ማስፈርና ሌላም ሥራ እንዲላመዱ ማድረግ ይገባል፡፡ ጨውን ጨምሮ ከፍተኛ የማዕድን ሀብት ያለበት በመሆኑ በጥናትና በሥርዓት ቢሰራበትም ትልቅ ለውጥና ዕድገት የሚመጣ ብሎም ለኢትዮጵያ የሚተርፍ አካባቢ መሆኑ ታሳቢ ሊደረግ ይገባል ባይ ናቸው፡፡
ውሃን ማዕከል ያደረጉ ሥራዎች ቢሰሩ አርብቶ አደሩ በራሱ ጊዜ እዚህ አካባቢ በቋሚነት ሊሰፍር ይችላል፡፡ በሂደት ደግሞ ኑሮውን ከአርብቶ አደርነት ወደ አርሶ አደርነትና ከፊል አርብቶ አደር መቀየር ይቻላል። በመሆኑም በክልሉ ኢንቨስትመንት እነዚህን ዜጎች ሕይወት ለመቀየርና ለማሻሻል በማሰብ ጭምር መሆን አለበት ይላሉ፡፡
በ21ኛው ክፍለ ዘመን ያልተማረ እና በየበረሃው የሚኳትን ዜጋ ይዞ መበልፀግ አስቸጋሪ ስለሚሆን ባለሀብቶች፣ መንግሥት እና ምሁራን እንደ ዜጋ አስበው በዚህ አካባቢ ሊሰሩ ይገባል የሚል መልዕክት አላቸው፡፡
በአፋር ዳጉ ተብሎ የሚጠራው የተግባቦት ስልት በባህሪው የመረጃ ልውውጥ መንገድ ቢሆንም የደህንነት ሥራንም ያካተተ ነው፡፡ ለአብነት አንድ እንግዳ ሰው በሆነ መንደር ቢገባ ለምን፣ መቼ እና እንዴት እንደመጣ ይታወቃል፡፡ የሆነ ሰው በሌላ አካባቢ ቢሄድ ቢርበውና ቢጠማው ከደረሰበት አካባቢ አብልተውና አጠጥተው መሸኘት የአካባቢው ሰዎች ኃላፊነት ነው፡፡
ታዲያ ይህ የዘመናዊነት ጥግ ሲሆን ይህን ማዳበርና ሌሎችም ሊጠቀሙበት እንደሚገባ ይጠቁማሉ፡፡ እርሳቸውም የባህል ልማት ላይ የሚሰሩ ሰዎች እነዚህን ጉዳዮችን ታሳቢ ያደረጉ ሥራዎችን ቢሰሩም ይመክራሉ፡፡ እርሳቸውም የተቻላቸውን ድጋፍ የማድረግ ፍላጎት አላቸው፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 25/2013