ለምለም መንግሥቱ
በአሁኑ ጊዜ በሰሚንቶና ብረት ዋጋ መናር እና የአቅርቦት ማነስ ምክንያት የኮንስትራክሽን ሥራ መቀዛቀዙ ይነገራል። የኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ከሥራው ለመውጣት ጫፍ ላይ መድረሳቸውን እየተናገሩ ነው። በተለይ የሲሚንቶ ግብአት አቅርቦትን ለማሻሻልና ዋጋውንም ለማረጋጋት መንግሥት ጣልቃ በመግባት ሲሰራ መቆየቱ ይታወሳል።
ይሁን እንጂ ሥራው በሚፈለገው መጠነ ውጤት አላስገኘም። የዋጋ ማረጋጋት እርምጃው እንዲያውም ከነበረው በባሰ የዋጋ ንረቱንና አቅርቦትን የከፋ እንዳደረገው ነው የሚናገሩት። ብረትም እንዲሁ በአንድ ጊዜ የ18 ብር እና ከዚያ በላይ ጭማሪ ማሳየቱ አነጋጋሪ ሆኗል። ለዋጋ ንረቱ ሰው ሰራሽ ችግሮች፣ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ከሚጠቀሱ ተጽዕኖዎች መካከል ይነሳል። ዛሬም ከችግር ላልወጣው የግንባታ ግብአት ጉዳይ የዘርፉ ተዋናዮች ምን ይላሉ? መንግሥትስ ለቅሬታው ምን ምላሽ አለው? ሁሉንም አነጋግረናቸዋል።
በቅድሚያም የሳምኮል ኢንጂነሪንግ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ሳሙኤል ሳህለማርያም የሲሚንቶ እና የብረት የግንባታ ግብአት ዋጋ መናር ለዘርፉ ከፍተኛ ማነቆ እየሆነ መምጣቱን በምሬት ይገልጻሉ። የግብአት አቅርቦት ዋጋ ከዕለት ዕለት የሚቀጥል እንጂ የሚቀንስ ሆኖ አላገኙትም። የዋጋው እየናረ መምጣት ፕሮጀክቶችን እንዳያስቆም ሥጋት ፈጥሮባቸዋል። የብረት ግብአት በአሁኑ ጊዜ በኪሎ ይሸጥ ከነበረበት 38 ብር በኪሎ እስከ 55ብር በመሸጥ ላይ ነው።
ሲሚንቶ ደግሞ ከፋብሪካ ኩንታሉ 260 ብር ወጥቶ ገበያ ላይ 550 ብር ነው የሚሸጠው። ይሄ እርሳቸው ገበያውን ባዩት ጊዜ የገጠማቸው እንጂ ገበያው በፍጥነት ተለዋዋጭ በመሆኑ ከዚያም በላይ ከፍ ይላል ብለው ይገምታሉ። ብረት መጠኑ የተለያየ ቢሆንም በዋጋ ግን ልዩነት አላሳየም። ጭማሪው እጅግ የተጋነነ ነው ሲሉ ይናገራሉ።
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሲሚንቶ በተመረጡ የመሸጫ ሱቆች ውስጥ እንዲቀርቡ በማድረግ የወሰደውን የዋጋ ማረጋጋት ሂደት ኢንጂነር ሳሙኤል እርምጃውን በተቃራኒው ነው የሚያዩት። ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ጣልቃ ከገባ ወዲህ የዋጋ ንረቱ እየተባባሰና እጥረቱ እየከፋ መሄዱን ይናገራሉ።
በፊት ተቋራጩም አልሚውም በቀጥታ ከፋብሪካ የሚያገኝበት አሠራር እንደነበር በማስታወስ፣ ሚኒስቴሩ ይህን በማስቀረት ምንም እሴት ሳይጨምር የልማት ድርጅቶች እንዲያከፋፍሉ ማድረጉ ጉዳት እንጂ ጥቅም ሆኖ እንዳላገኙት ያስረዳሉ። ‹‹መንግሥት ጋር ያለው አመለካከት ፋብሪካ ማምረት እንጂ መቸርቸር የለበትም የሚል ነው። ቸርቻሪው ከፋብሪካው በላይ ዋጋ የሚያገኝ ከሆነ ፋብሪካው ለምን ያመርታል›› ሲሉም የችግሩን ስፋት ያነሳሉ።
ሌላው ኢንጂነሩ ያነሱት በመንግሥት እና በግል አልሚዎች መካከል ስላለው ልዩነት ነው። በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ በመንግሥት የሚከናወነው የመኖሪያቤቶች ሥራ ካልሆነ ሌላው ሥራው ቆሟል በሚባል ደረጃ ላይ ይገኛል። ምክንያቱ ደግሞ ለመንግሥት ፕሮጀክቶች ብረት የሚያቀርበው መንግሥት ራሱ በመሆኑና ክምችትም ስላለው እንደሆነ ይገልጻሉ። ለግል አልሚው ግን ብረትና ሲሚንቶ ለሥራቸው ማነቆ መሆኑ እንዳልታየ ይጠቅሳሉ።
እንደ ኢንጂነር ሳሙኤል ማብራሪያ የግንባታው ዘርፍ ተፈትሾ መፍትሄ ካላገኘ መልሶ ጉዳቱ የመንግሥት ነው። የፕሮጀክት መጓተት የሚያስከትለው ኪሳራ አልሚው ላይ ብቻ ሳይሆን በኅብረተሰቡ ላይም የሚፈጥረው ጫና ከባድ መሆኑን ይናገራሉ። ለመኖሪያም ሆነ ለተለያየ አገልግሎት የሚውሉ ሕንፃዎች በካሬ ሽያጫቸው ይጨምራል። ይሄ ገዥው ላይ ሲጨምር ለኅብረተሰቡ በሚሰጠው የተለያየ አገልግሎት ላይም የኪራይ ዋጋ ይጨምራል።ይህ ደግሞ የዋጋ ግሽበትን በከፍተኛ ሁኔታ ያባብሳል።
በግንባታው ዘርፍ ለ25 ዓመታት የቆዩት ኢንጂነር ሳሙኤል በቆይታቸው የግንባታ ግብአቶች የዋጋ ንረት ጉዳይ በሥርዓት ሲፈታ ለማየት አልታደሉም። በዚህ ችግር ውስጥ ሆነው ነው ለተለያየ የንግድ አገልግሎት የሚውል ሕንፃ በመገንባት እያከራዩ ሥራቸውን የቀጠሉት። በቅርቡ ተክለኃይማኖት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የጀመሩትን ግንባታ ለጊዜው ማቆሙን መርጠዋል። የግብአቶቹ ዋጋ ከተረጋጋ ተጠቃሚ ለመሆን፣ ካልሆነ ደግሞ ባለው ወቅታዊ የግብአት ዋጋ ቢገነቡ ገበያው አዋጭ እንደሆነ ለማጥናት እንዲያስችላቸው ነው ግንባታውን ማዘግየት የፈለጉት።
ከመንግሥት በጨረታ የተረከቧቸውም የብረት ግብአት ዋጋ በ18 ብር ጭማሪ በማሳየቱ ማስተካከያ ጠይቀዋል። ያወጡትን ወጪ ለማካካስ ብቻ ሳይሆን ለግንባታ የወሰዱትን የባንክ ብድር በወቅቱ ለመመለስ እንዲያስችላቸው ቆም ብሎ ማሰቡን መርጠዋል። የሀገር ውስጥ ተቋራጮችን አቅም ከሚፈታተኑት አንዱ በየጊዜው ተለዋዋጭ የሆነው የግብአት ዋጋ መናርና በቂ የሆነ አቅርቦት አለመኖር እንደሆነም ይጠቅሳሉ።
የብረት የግንባታ ግብአት በሀገር ውስጥም የሚቀርብ በመሆኑ የዋጋ መናሩ ለምን እንደተከሰተም አንስተንላቸው ነበር። በምላሻቸው እንዳሉት የዋጋ ልዩነቱ በጣም የተራራቀ ባለመሆኑ አብዛኛው ተጠቃሚ ከውጭ ሀገር የሚገባውን መጠቀም ይመርጣል። ከውጭ የሚገባው ከሀገር ውስጥ ምርት በተሻለ ደረጃውን የጠበቀ በመሆኑ ነው ተመራጭ የሆነው። በሲሚንቶ በኩል ግን ያለው ችግር በእርሳቸው እምነት በመካከል ላይ ሆኖ ገበያውን የሚመራው ደላላ በመሆኑ ነው።
ኢንጂነር ሳሙኤል የግንባታ ግብአት ዋጋ መናር የሚያስከትለውን ጉዳት ሲያስረዱም የግንባታ ግብአት ዋጋ በወረደበት ጊዜ የተገነቡ ሕንፃዎችም ቢሆኑ ዋጋቸው ሲጨምር እንጂ ሲቀንስ አይስተዋልም። ለምን እንደሆነም ኢንጂነር ሳሙኤል ላቀረብኩላቸው ጥያቄ፤ እርሳቸው የተለያየ አገልግሎት ፈልገው ገበያ ሲወጡ አብዛኞቹ አገልግሎቶች ባሉበት ሳይሆን ዋጋቸው ጨምሮ እንደሚያገኙት ሁሉ ሕንፃም ቀደም ሲል ስለተገነባ ዋጋ መጨመር የለበትም የሚል እሳቤ እንደሌለና የንግድ ተሞክሮውም ይህንኑ እንደሚያሳይ ምላሽ ሰጥተዋል።
ሌላው ሀሳባቸውን የሰጡኝ ዶክተር ኢንጂነር ውብሸት ዠቅአለ። በመንገድና በሕንፃ የግንባታ ዘርፍ ከመሰማራታቸው በተጨማሪ በማማከር ሥራ ላይም ይገኛሉ። መሬት ላይ ስላለው ነባራዊ ሁኔታም እንዳስረዱት፤ ከውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር ተያይዞ የዋጋ ንረት መከሰቱ ይታወቃል። ነገር ግን በመንግሥት አሠራር ከ18 ወር በታች ለሆነ ፕሮጀክት የዋጋ ማስተካከያ ማድረግ አይቻልም።
የሲሚንቶና የብረት ዋጋ ደግሞ በየቀኑ እየጨመረ ነው። የኮንትራት ውል ወቅታዊውን የግብአት ዋጋ መሠረት አድርጎ ማስተካከያ እስካልተደረገ ድረስ ችግሩ መፍትሄ አያገኝም። ተቋራጭ ሥራውን ይዞ ይቀመጣል እንጂ ከስሮ ይሰራል ማለት የዋህነት ነው። አሁን 95 በመቶ የግንባታ ሥራ በመንግሥት የሚከናወን በመሆኑ መልሶ ተጎጂ የሚሆነው መንግሥት ነው።
እንደ እርሳቸው እምነት በሀገር ውስጥ በሚቀርቡ ግብአቶች ሥራዎች ቢሰሩ ይመረጣል። ግን ደግሞ የብረት ግብአት በሀገር ውስጥ እየቀረበ አይደለም። ነጋዴው ደግሞ አጋጣሚን መጠቀም ስለሚፈልግ ያለ ርህራሄ ዋጋ ይጨምራል። ይሄ ለምን ሆነ ብሎ መፈተሽና የውጭ ምንዛሪውን ማስተካከል ይጠበቃል።
በተቋራጮች የሚነሳው በሀገር ውስጥ የሚመረተው የሲሚንቶ ጥራት ጉዳይ በክትትልና ቁጥጥር ከተስተካከለ ሊሻሻል ስለሚችል ሥጋት ሊሆን አይገባም። በሲሚንቶ በኩል የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታትም የአምራች ኢንዱስትሪዎቹን አቅም ማሳደግ ይገባል። አሁን ያለው የግንባታ ሥራ እንቅስቃሴ በኢንጂነር ውብሸት ምልከታ እያዘገመ እንጂ ቆሟል የሚባል ደረጃ ላይ አይደለም።
በተነሱት ጉዳዮች ላይ በንግድ ሚኒስቴር የብረታብረትና ኬሚካል ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ አቶ ዱጋሳ ዱንፋ ምላሽ አላቸው። የማምረት አቅም ሲፈጠር ገበያውም ስለሚረጋጋ መንግሥት ቅድሚያ ሰጥቶ የሰራው አሠራሩን መፈተሽ ነበር።
ሲሚንቶ ከማምረቻ ኢንዱስትሪ ወደ ተጠቃሚው በምን ዓይነት የገበያ ሰንሰለት እየተፈጸመ እንደሆነና ስላለው ነባራዊ ሁኔታ ለማጣራት ጣልቃ ገብቶ ባከናወነው ሥራም የሲሚንቶ ንግዱ በብዙ እጆች ውስጥ የሚያልፍና የተበላሸ አሠራር እንደነበር ደርሶበታል። የፋብሪካዎች በቀን የማምረት አቅማቸው ታይቷል።
በመለዋወጫ እጥረትና በተለያየ ምክንያት ለጊዜው ማምረት ያቆሙ ፋብሪካዎችም መኖራቸው ተለይቷል። የጥገናና የመለዋወጫ ችግር ቀጥታ ከውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ጋር ስለሚያያዝ መንግሥት ችግሩን ለመፍታት ከመጠባበቂያ ላይ ወደ 85ሚሊዮን ዶላር ሥራ ላይ እንዲውል አድርጓል። ከዚህ ውስጥም ወደ 65 ሚሊዮን ዶላር ጥቅም ላይ ውሏል። ድጋፉ ሥራ ያቆሙ ፋብሪካዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ ከማድረጉ በተጨማሪ ተከታታይ ምርት እንዲኖር ያግዛል።
በቀን በአማካይ 250 ሺ ኩንታል የማምረት አቅም ተፈጥሯል። የየቀኑ የምርት መጠንም ለሚኒስቴሩ መረጃ እንዲደርስ አሠራር በመዘርጋቱ ተመርቶ ለገበያ የሚቀርበውን ማወቅ ተችሏል። ኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ እንደተከሰተ ፋብሪካዎች አምርተውና የተለያዩ ወጪዎችን አካተው ለገበያ የሚያቀርቡበትን ዋጋ መሠረት በማድረግ የመሸጫ ዋጋ ለመተመን ጥረት ተደርጎ ነበር። ዓላማው የገበያውን ሁኔታ ለማየት እንጂ የነፃ ገበያውን የአሠራር ሥርዓት ለመጋፋት አይደለም።
እንደ አቶ ዱጋሣ ማብራሪያ ዘርፉ በትልቅ ማነቆ ውስጥ እንደነበርም በተሰራው ሥራ ለመረዳት ተችሏል። ላለፉት 15 ዓመታት ኢንቨስት ማድረግም ሆነ ማስፋፊያ ለመሥራት በመከላከሉ እንቅስቃሴው ተዳክሞ ነው የቆየው። በዚህ ላይም ማሻሻያ ተደርጓል።
ለአብነትም ዳንጎቴ ሲሚንቶ በሥራ ላይ ያለውን ያህል ፋብሪካ ገንብቶ ተጨማሪ አቅም እንዲፈጥር ፋብሪካው በደብዳቤ እንዲያውቀው ተደርጎ ከፋብሪካው ተቀባይነት አግኝቷል። በመሆኑም ጉዳዩ መሥመር ይዟል። ፋብሪካው በአሁኑ ጊዜ በቀን እስከ 80ሺ ኩንታል ሲሚንቶ ያመርታል። ተጨማሪ አቅም ቢገነባ ደግሞ እስከ 110 ሺ ኩንታል ማምረት ይችላል። አዲስ በመቋቋም ላይ ካሉት ደግሞ አባይ ሲሚንቶ ይጠቀሳል።
ፋብሪካው ወደ ሥራ ለመግባት የሚያስችለው ከኢንቨስትመንት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በማጠናቀቅ ላይ ይገኛል። ለፋብሪካው የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች ከውጭ እንዲያስገባ ወደ 20ሚሊዮን ዶላር ተፈቅዶለታል። መንግሥት በተጨማሪ የሲሚንቶ የአቅርቦት ችግርን ለመፍታት በጊዜያዊነት የገንዘብ አቅሙ ወይንም ዲያስፖራ አካውንት ያላቸው ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲያስገቡ ፈቅዷል።
በዚህ ረገድ ቀርቦ ሚኒስቴር መሥሪያቤቱን ያነጋገረ አካል የለም። በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሥር የተዋቀረ አመቻችና ቴክኒካል የተባለ ቡድን መኖሩናን ሁሉም ዘርፉን በማገዝ ሚናቸውን በመወጣት ላይ እንደሆኑ የጠቀሱት አቶ ዱጋሣ፤ የክትትልና ቁጥጥር ሥራውም መጠናከሩን ያመለክታሉ።
በግንባታ ዘርፉ ላይ የተሰማራው ቀጥታ ከፋብሪካዎች እንዳይገዛ የተደረገበትን ዋና ምክንያት እንዲያስረዱ አቶ ዱጋሣ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ ‹‹ለመሆኑ ስንቶቹ ናቸው ትክክለኛ ቅሬታ ያላቸው ብለን ስንወስድ በጣም ጥቂት ናቸው። ቀጥታ ከፋብሪካ ገዝተው ለግንባታ ለማዋል ነው የሚለው ያነጋግራል። ቀደም ባለው አሠራር ቀጥታ ከፋብሪካ የሚገዙበት ሁኔታ ነበር።
ይህን ዕድል በመጠቀም ለ18 ሚሊዮን ብር ለሚያወጣ ፕሮጀክት 60 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ፕሮጀክት የተጠየቅንበት ጊዜ ነበር። ይሄ ከሥነምግባር ውጪ የሆነ አካሄድ ነው። የተወሰደው እርምጃ በመንግሥት የሚገነቡ ትላልቅ የሆኑና ሕዝብ የሚፈልጋቸውን ፕሮጀክቶች በመምረጥ ቀጥታ ከፋብሪካ ግዥ እንዲፈጸም ነው የተደረገው።
ሌላው መታሰብ ያለበት መንግሥት ጣልቃ ገብቶ ዋጋውን ባያረጋጋው የሲሚንቶ ዋጋ አሁን ካለበትም በላይ ይሆን ነበር። መንግሥት ሳይወድ በግድ ነው ወደዚህ አሠራር ውስጥ የገባው። እንዲያውም በተቃራኒው ለቀጣይ እርምጃዎች የሚረዱ ትምህርት ተገኝቶበታል። የውጭ ምንዛሪ ግኝቱ በመንግሥት እጅ በመሆኑ ማን ይሰራል ማን አይሰራም የሚለውን ለመለየት ይረዳል›› ብለዋል።
ለአብነትም ሲያስረዱ በኃይል መቆራረጥ ሥራው የተስተጓጎለበት ፋብሪካ ከሚመለከተው አካል ጋር በመነጋገር ችግሩ እንዲፈታ ተደርጓል። ሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ ከነበሩት ሦስት የመብራት መሥመሮች ሁለቱ ብቻ ነበሩ የሚሰሩት።
ይሰራል የተባለውም አጥጋቢ አልነበረም። አሁን ግን ችግሩ እየተፈታለት ይገኛል። ሌሎችም ፋብሪካዎች በተመሳሳይ ችግሮቻቸው እየተፈቱላቸው ነው። ከጥገና ጋር በተያያዘም ሚኒስቴር መሥሪያቤቱ ሳያውቀው ሥራ የሚያቆም ፋብሪካ የለም።
የብረት ግብአት አቅርቦት ላይም የብረትና ኬሚካል ኢንዱስትሪዎች 85 በመቶ ያህል ግብአት የሚጠቀሙት ከውጭ በማስመጣት በመሆኑ ችግሩ ከውጭ ምንዛሪ ጋር ይያያዛል። ለኢንዱስትሪዎች ቅድሚያ ተሰጥቶ 45 በመቶ እንዲሰጣቸው ውሳኔ ላይ ተደርሷል። ይሁን እንጂ በሀገር ውስጥ ብረት የማምረት አቅም በመኖሩ የሀገር ውስጡን ማጠናከሩ ይመረጣል።
እስካሁን ያለው የማምረት አቅም ከ25 በመቶ የበለጠ አይደለም። ይሄ በግንባታ ዘርፉ ላይ ተጽፅኖ ያሳድራል። በመሆኑም ብረቱን ከውጭ ከማስገባት ለብረት ኢንዱስትሪው የሚውለው ከውጭ የሚገባው ግብአት ላይ እልባት በመስጠት የፋብሪካዎቹን አቅም ማጠናከሩ ይመረጣል። በመንግሥት ደረጃም ውይይት እየተደረገበት መሆኑን ያነሳሉ።
አዲስ ዘመን ጥር 25/2013