
አዳማ፡- የኢትዮጵያ ምግብ፣መድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን በምግብ፣መድኃኒት፣ህክምና መሳሪያዎች፣ኮስሞቲክስ፣ ትንባሆና ፀረ ተባይ ምርቶች ላይ የሚያደርገውን ቁጥጥር እንደሚያጠናክር ተገለፀ፡፡
በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የህግ ባለሙያ አቶ ዳግም አለማየሁ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤ የምግብና የመድኃኒት አስተዳደር አዋጅ በ9 ክፍሎችና በ74 አንቀፆች ተደራጅቶ በምግብ፣ መድኃኒት፣ ህክምና መሳሪያዎች፣ ኮስሞቲክስ ትንባሆና የፀረ ተባይ ምርቶች ላይ ጠንካራ ቁጥጥር ለማድረግ እንዲያስችል ተደርጎ እየተሻሻለ የሚገኘው ይህ አዋጅ ጥሰቶች ሲያጋጥሙም ህጋዊ ርምጃ ለመውሰድ ይጠቅማል፡፡
የቀድሞው አዋጅ ቁጥር 661/2002 በአፈፃፀም ወቅት በርካታ ችግሮች እንደነበሩበት መታወቁን አቶ ዳግም አስታውሰው፣ይህን የአፈፃፀም ክፍተት መነሻ በማድረግ ጥናት መካሄዱንም ተናግረዋል፡፡ በጥናቱም አዋጁ ከተለያዩ አስፈፃሚ የመንግስት አካላት ጋር የስልጣን መጣረስ የሚያመጣ ይዘት እንደነበረው ለማወቅ ተችሏል ያሉት አቶ ዳግም፤ አዋጁ የምግብ፣ መድኃኒት፣ የህክምና መሳሪያዎች፣ ኮስሞቲክስ ትንባሆና ፀረ ተባይ ምርቶችን በዝርዝር ያላካተተ እንዲሁም የወንጀል ድንጋጌዎችን የያዘ እንዳልነበረም ጠቅሰው፣ በምርቶቹ ላይ ቁጥጥር ሲደረግ ጥሰቶች ሲያጋጥሙ በህግ ለመጠየቅ የማያስችል እንደነበርም ተናግረዋል፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በምግብ፣መድኃኒት ህክምና መሳሪያዎች፣ ኮስሞቲክስ ፣ትንባሆና የፀረ ተባይ ምርቶች ላይ በዋናነት ቁጥጥር የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት የጠቀሱት ባለሙያው ፣የአዋጁ መሻሻል ተቋሙ ከበጀትም ሆነ ከሰው ሃይል አኳያ የተሻለ አደረጃጀት እንዲኖቸራው ያስችለዋል ብለዋል፡፡ የተሰራው አደረጃጀትም የሰው ኃይሉን ውጤታማ በሆነ መንገድ በመጠቀም የተሻለ የቁጥጥር ስራ እንዲያከናውንም እንደሚረዳውም ገልጸዋል፡፡ በአዋጁ የወንጀል ቅጣት መካተቱም ህጋዊ እርምጃዎችን በመውሰድ የቁጥጥር አፈፃፀሙን የተሻለ እንዲሆን የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የተቋሙን የቀድሞ አዋጅ ቁጥር 661/2002 ለማሻሻል ሶስት ጊዜ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ የተሻሻለው አዋጅ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቆ ተፈፃሚ መሆን ሲጀምር በምግብ፣ መድኃኒት፣ ህክምና መሳሪያዎች፣ ኮስሞቲክስ፣ ትንባሆና የፀረ ተባይ ምርቶች ላይ የሚደረገውን ቁጥጥር የበለጠ ያጠናክረዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 28/2011
በአስናቀ ፀጋዬ