አብርሃም ተወልደ
ትዳር ለቤተሰብ መሰረት ነው። ይህ የማህበረሰብ የትውልድ መቀጠያው ድልድይ ትዳር የሚመሰረተው ሕግ በሚፈቅደው ጋብቻ ነው። ጠንካራ እና ውጤታማ ልጆች የመልካም ትዳር ወይም ቤተሰብ ውጤቶች ናቸው ተብሎ ይታመናል።
ለዚህም ነው ጋብቻ ብሎም ቤተሰብ በጥሩ ሁኔታ መያዝና መታነፅ አለበት የሚባለው። ቤተሰብ ደግሞ በተራው የጠንካራ ማህበረሰብ እና አገር መሰረት ይሆናል፡፡
የትዳር ውስጥ የሚከሰት ችግር ጠንቅና መዘዙ ብዙ ስለሆነ የአንድ ባል እና ሚስት ተራ ጉዳይ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም። በዚህም ምክንያት በርካታ አገሮች የትዳር ችግሮችን ለመለየት እና መፍትሔ ለመስጠት የተለያዩ ተግባራትን ያከናውናሉ።
ይህም በቤተሰብ በልጅ አስተዳደግ ወዘተ ላይ ጥናት እና ምርምር የሚያደርጉ ተቋሞችን በማቋቋምና ከፍተኛ ገንዘብ በመመደብ ችግሮችን እየለዩ መፍትሔ ያበጃሉ፡፡
በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ እየተደረገ ስላለው በቂ መረጃ ባይኖረኝም በተለያዩ ቢሮዎች ተቋማት የተለያዩ ሥራዎች እንደሚሰሩ እገምታለሁ። ከትዳር ጋር የተያያዙ ችግሮች ዓይነትና ውጤታቸው ፈርጀ ብዙ እና ውስብስብ ስለሆኑ አበክረን ልንሰራባቸው የሚገቡ በእርካታ ጉዳዮች እንዳሉ ግን ጽኑ እምነት አለኝ።
ለምሳሌ ስለፍቺ ምክንያቶች እና የትዳር አለመግባባቶች በግልጽ መነጋገር እና መወያየት አስፈላጊ ነው፡፡
በእኔ እይታ በአብዛኛው ጥንዶች ትዳራቸውን የሚያፈርሱት ከራሳቸው ምቾት አንጻር ነው። ለሚራበው፣ ለሚታረዘውና በየጎዳናው ለሚወጣው ትውልድ ቁብ የላቸውም፤ ማሰብም የሚፈልጉም አይመስለኝም፡፡
ፍቺን በተለመከተ ባለሙያዎች ከተለያዩ ሁኔታዎች ጋር አገናኝተው ማጥናታቸው የተለመደ ነው።ተፋቺዎች እና የፍቺ ውጤቶችን መሰረት አድርገው የሚሰሩ ጥናቶች ተፋቺዎች የሰጧቸውን መረጃዎች መሰረት በማድረግ የሚዘረዝሩትን ላንሳ። ምንያህል ተጋቢዎቹ ራስ ወዳድ እንደሆኑ በምክንያታቸው ለማየት ይረዳል፡፡
ለፍቺ የሚያጋልጡ ምክንያቶች ብለው ከዘረዘሯቸው መካከል በለጋ ዕድሜ ትዳር መመስረት አንዱ ነው። ይህም ተጋቢዎች የብስለት ደረጃ ሳይደርሱ ይጋባሉ። በዚህም ምክንያት ቤታቸውን ማስተዳደር ስለሚሳናቸው ይፋታሉ፤ ይህ አንዱ ምክንያት እንደሆነ ይነገራል፡፡
ሌላኛው የገቢ ዝቅተኛነት ከጋብቻ በፊት አብሮ መኖር፣ ከጋብቻ በፊት ልጅ መውለድ እና እርግዝና ባህሪ፣ ታማኝነት በወሲብ አለመጣጣም …ወዘተ ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል። ይህ ሁሉ ምክንያት በእኔ አተያይ ራስ ወዳድነት ነው። አሊያም ለወለዱት ለቀጣይ ትውልድ አለማሰብ ነው፤ ዋጋ ለመክፈል አለመፈለግ፡፡
የእኔ በእኔ ዘመን ያለን ወላጆቻችን እኮ! ባሎቻቸው ውጪ በልቶ ጠጥቶ በመምጣት ከቃላት ጥቃት እስከ አካላዊ ጥቃት ሲያደርስባቸው ችለው ያለፉት ለልጆቻቸው በማሰብ ነው፤ በእነርሱ ትዕግስት ቤት «ቤት» ሆኖ እንዲጸና ልጆች እንዳይበተኑ ሆኗል፡፡
በዚህ ዘመን በትዳር ዙሪያ የሚነሳው መሠረታዊ ጥያቄ በትዳር ውስጥ ችግር ሲፈጠር ስለችግሩ ለመነጋገር ማን ነው የሚፈልገው? «ማን ነው» የሚለው ጥያቄ ነው? በአንዳንድ የውጭ አገር ጥናቶች ላይ እንደሰፈረው ባልና ሚስት ትዳራቸው ችግር ሲገጥመው በችግሩ ላይ እንነጋገር በማለት ጥያቄ የሚያቀርቡት ከባሎች ይልቅ ሚስቶች ናቸው።
ብዙውን ጊዜ ባሎች በችግሮች ላይ ለመነጋገር ፈቃደኛ ያለመሆን በዝምታ ወይም አድበስብሶ ለማለፍ የመሞከር አዝማሚያ የሚያሳዩ ሲሆኑ፤ ሚስቶች ግን አሉ ባሏቸው የትዳር ችግር ላይ በሚገባ ለመነጋገር እና መፍትሔ ለመፈለግ የመሞከር አዝማሚያ ያሳያሉ፡፡
በአገራችንም ሁኔታው ተመሳሳይ ይመስላል። በትዳር ውስጥ በሚፈጠሩ ችግሮች በብዛት ጎልተው የሚታዩት በወንዶች ላይ ከመሆን አንጻር ሚስቶች የትዳር ችግሮች ላይ ለመነጋገር ጎትጓች እና ተማፅያን ሲሆኑ ወንዱ ግን ዳተኝነት እንደሚያሳይ መታዘብ ይቻላል።
«ለመንኩ፤ አስለመንኩ፤ መከርኩ፤ አስመከርኩ፣ ግን ምንም ለውጥ የለም፤» የሚለው በተደጋጋሚ አንዳንድ ጊዜ እንዲያውም «…ጭራሽ ችግሩን ሰው ሲያውቀው ባሰበት..» በሚል ለውጥ ያመጣል ብለው ያደረጉት «ማስመከር» ችግሩን እንዳባባሰው ይገልጻሉ፡፡
ይህ የሚያስረዳው ምንም እንኳን ሴቶች (ሚስቶች) ትዳራቸው ከባሎች (ከወንዶች) ይልቅ ጸንቶ እንዲቆይ ቢፈልጉም፤ ወይም ችግሮቻቸውን በመፍታት ትዳራቸውን ቀጣይነት እንዲኖረው በማድረግ ረገድ የሚቀራቸው ነገር እንዳለ ነው።
ይህም ለራሳቸው እንደሚደረግላቸው ከሚያስቡት በላይ አርቀው ጐዳና ስለሚወድቀው ወላጆቹን በማጣት በሥነልቦና ስለሚጎዳው ልጆቻቸው አለማሰባቸው ነው።በእርግጥ እዚህ ላይ ሁሉንም እያልኩ አይደለም ይታወቅልኝ።
በመሆኑም የባልና እና የሚስት አለመግባባት እና የፍቺ ምክንያቶች ሰፊና ውስብስብ ናቸው። ከዚህ አንጻር የሚከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት በትዕግስት እና በጥንካሬ መስራት ያስፈልጋል።የቤተሰብ የሚመሰረትበት ዓላማዎች ይበልጥ በተሳካ መጠን ጠንካራ ማህበረሰብ እና አገር መፍጠር ይቻላል።
የምርምር ተቋማት በየጊዜው በቤተሰብ ሁኔታ ላይ ሰፊና ጥልቅ ምርምር ማድረጋቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። እያንዳንዱ ቀን የራሱን የሕይወት ፈተናዎች ይዞ ስለሚመጣ ለማስቀጠል ጥረት ይጠይቃል፡፡
ትዳራችንን ፈተና ውስጥ ሳንከት የመሰረትነውን የቤተሰብ ሕይወት አክብረን፣ ወደምንፈልገው የተሻለ ሕይወት ለመለወጥ በጨዋነትና በትጋት መጣር ይኖርብናል።ትዳር ራሱን የቻለ የግል ጉዳይ ባህሪይ ስላለው ባልና ሚስት ተስማምተው ካልሆነ በስተቀር ሌሎች ሦስተኛ ወገኖች በሕይወታቸው ውስጥ ጣልቃ እንዲገቡ መፍቀድ የለባቸውም፡፡
በአጠቃላይ በዚህ ጽሑፍ ለመጥቀስ እና ለማስገንዘብ የሞከርኩት የጋብቻ መፍረስ ውሳኔ ጠለቅ ተብሎ ሊታሰብበት ይገባል። የተጋቢዎች የወደፊት ሕይወት በልጆች ዕጣ ፈንታ እና በማህበረሰብ ውስጥ በሚኖራቸው ግንኙነት ላይ ሊያስከትሉ የሚችሉ ችግሮች እንዳሉ እንዲያስተውሉ ማድረግ ይገባል። ለትዳራቸው ዋጋ በመክፈል የጀመሩትን ሕይወት የሚከፈለውን መስዋትነት በመክፈል እንዲያጸኑት እንዲገነዘቡ ነው፡፡
ጋብቻቸው እንዲፈርስ የወሰኑ ባለትዳሮች የሚያቀርቡት ምክንያት እና ጋብቻው ከፈረሰ በኋላ የደረሰባቸው ጉዳት በልጆቻቸው ላይ ያስከተለው ቀውስ ወዘተ… ሲመዛዘን የፍቺ ምክንያታቸው እዚህ ግባ የሚባል ላይሆን ይችላል።
ስለዚህ ችግሮችን ማቻቻል እንዲሁም ቅሬታዎች እና ግጭቶችን ሆደ ሰፊ ሆኖ መመልከት ከብዙ መከራና ስቃይ ሊያድን ይችላል።
ለዚህም የሚመለከተው ሕግ አውጪ አካል ፍቺ የሚፈጥረውን ቀውስ አይቶ ፍቺን በሕግ እንዲከለክል ስል እማጻናለሁ!! መልካም መልካሙን ለትውልድ …አበቃሁ!!
አዲስ ዘመን ጥር 25/2013