ከገብረክርስቶስ
እንደምን ሰነበታችሁ! እንኳን በጤና ተገናኘን!
ከሰሞኑ መቼስ የማህበራዊ ሚዲያ አርበኛው ሁሉ ባጭር ታጥቆ፤ የወሬ ጦሩን ሰብቆ፤ የውሸት ዘገሩን ነቅንቆ የሀሰትና የጥላቻ ዘመቻውን ሲያጧጡፈው ሰነባብቷል፡፡
ሳቢ ለጓሚውም የወሬ ፈብራኪውን ፈለግ ተከትሎ በስማ በለው ወሬውን ሲጠርቅ ነበር የከረመው፡፡ እናም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ቢያስተውሉ «እባካችሁ ወሬ አይፍታን» ሲሉ ተማጠኑ፡፡
የሕዝቡ እንዲህ እንደአሁኑ በወሬ የመፈታት ነገር እንደውሃ ፈሳሽ፤ እንደ እንግዳ ደራሽ ሆኖ ከሰሞኑ ብቻ የተከሰተ አይደለም፡፡
ይልቁንም ከ2010 ዓ.ም. ለውጥ ማግስት ማህበራዊ ሚዲያውን ጨምሮ በቴሌቪዥንና በሬዲዮኖችም ጭምር በአግባቡ ተጠንቶ አጀንዳ እየተቀረጸ፤ ዲጂታል አርበኞችም ወሬ ታጥቀው ነበር ሕዝቡን ሲያደናግሩ የከረሙት፡፡
በወጉ ያልጠገገው የወሬ ቁስላችን
ጦርነት ሕዝብ አስጨራሽ፣ አገር አፍራሽ ነው፡፡ ከጦርነት በሚብስ ሁኔታ ደግሞ ወሬ አስከፊ ውጤት ያስከትላል፡፡
በወሬ አርበኞች በተሰራጩ የሐሰትና የጥላቻ መልዕክቶች ምክንያት በምድረ-ኢትዮጵያ ሚሊዮኖች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡
በርካቶች በብሔራቸው ተለይተው ግፍ ተፈጽሞባቸዋል፡፡ ንብረታቸው ወድሟል፤ ተዘርፏልም። አብያተ-ክርስቲያናት እና መስጂዶች ተቃጥለዋል፡፡ የአገልጋዮችና የምዕመናን ደም ፈሷል፡፡
ይህ ሁሉ የሆነው በጦርነት አልነበረም፤ በወሬ እንጂ፡፡ በማህበራዊ የትስስር ገጾችና በሚዲያዎች አንዱ በሌላው ላይ እንዲነሳ የሚያደርጉ፣ ብሔርን፣ ሃይማኖትን ወይም የፖለቲካ አስተሳሰብን መሠረት ያደረጉ ወሬዎች በመሰራጨታቸው ነው አገሪቱ ለዚህ ሁሉ ችግር የተጋለጠችው፡፡
በለውጡ ማግስት ኢትዮጵያን የተጣባት ሾተላይ ስለቱን ሞርዶ አንጋፋ የማሕጸኗን ፍሬዎች ቀጭቷል፡፡
በድንቃድንቅ ዘፈኖቹ በሚሊዮኖች ልብ ውስጥ የትግል ወኔን ያቀጣጠለው ሀጫሉ ሁንዴሳ ተረኛው የሾተላዩ ሰለባ በሆነ ማግስት ምን ተከሰተ?
በርካቶች የጦስ ግብር ሆነው ተቀጠፉ፡፡ በዚህም ምክንያት የማሕጸናቸውን ፍሬ የተነጠቁት እናቶች፤ የአብራካቸውን ክፋይ ያጡት አባቶች የኀዘን ሸማ ተከናንበዋል፡፡ ቅስማቸውም ተሰባብሯል፡፡ የዕንባቸው ጎርፍም ንፍር ሆኖ ምድሪቱን እየተፋረዳት ይገኛል፡፡
ይህ ሁሉ የተከሰተው ታዲያ በወሬ ነው፡፡ ያን ዕለት ማለዳ በኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ፣ በትግራይ ቴሊቪዥንና በድምጸ ወያነ አማካኝነት ይሰራጭ የነበረው የሾተላዩ ግብር አቀባዮች የዕልቂት ጥሪ አሁን ሲታወሰን ይዘገንነናል፡፡
የሾተላይ ነጋሪት ጎሳሚዎች ባስተላለፉት የዕልቂት ጥሪ አማካኝነት ኢትዮጵያ በደም እንድትታጠብ፤ በእንባ ጎርፍ እንድትጥለቀለቅ አድርገዋል፡፡ ምድሪቱንም በሐዘን ቆፈን ተሰቅዛ እንድትሰነብት አድርገዋል፡፡
በዚያች የማክሰኞ ማለዳ በአገር አማን ሰዉ ሁሉ ወደየተግባሩ ሊሰማራ ሲሰናዳ ነበር የአርቲስቱ በሾተላዩ መበላት የተሰማው፡፡ መላ ኢትዮጵያም በታጋዩ ዘፋኝ ሞት በኀዘን ተውጦ አረፈደ፡፡
ብዙም ሳይቆይ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ በቀጥታ የቴሌቪዥን ፕሮግራም የአርቲስቱ አስከሬን ለምርመራ ካደረበት ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ወጥቶ ለቀብር ሥነ-ሥርዓት እትብቱ ወደተቀበረባትና የታጋይነት ችቦውን ወደለኮሰባት የአምቦ ከተማ በማምራት ላይ የነበረበትን የአሸኛኘት ሥርዓት ማስተላለፉን ይቀጥላል። የአርቲስት ሀጫሉ ወዳጅ ዘመዶች እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ አድናቂዎች የተገኙበትን ይህንን በአጀብ የተሞላ የአሸኛኘት ሥነ-ሥርዓት በቀጥታ ማስተላለፉ ለወዲያው በብዙዎች ዘንድ አስመስግኖት ነበር፡፡
ይሁንና እንዲያ ባለ አስደንጋጭና አሳዛኝ ሁኔታ የአርቲስቱ ሕይወት ማለፍ የሚያስቆጣ ቢሆንም ያ ጣቢያ ግን በቀጥታ ሥርጭት ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጭና ዕልቂት የሚጠራ የሾተላዩን ነጋሪት መጎሰሙን ተያያዘው፡፡
የሀጫሉን ግድያ ሰበብ በማድረግ ከአገሪቱ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነውን ቁጥር የያዙትን የአማራና የኦሮሞ ሕዝቦችን እርስ በእርስ የሚያጫርሱ የዕልቂት ጥሪዎችንና መልዕክቶችን በቀጥታ መሰራጨቱን አንዘነጋውም፡፡
የአማራና የኦሮሞ ሕዝቦች ከሌሎች ወንድምና እህቶቻቸው ጋር ትናንት በጋራ ቆመው ይህችን አገር በደግም በክፉ መሀል አሻግረዋል፡፡ ምድሯን በጠላት ሳያስደፍሩ፤ ከአድዋ እስከ ካራማራ፣ ከመተማ እስከ ዶጋሊ የጋራ መስዋዕትነት ከፍለው በአንድ ጉድጓድ ውስጥ ተቀብረዋል፡፡ ተጋብተው ተዋልደው ተጋምደው የቆዩ ወንድማማች ሕዝቦች ናቸው፡፡
ይሁንና ይህንን አሽቀንጥሮ በመጣል ትውልዱ ተምሮባቸው እንዳይደግማቸው ሳይዘነጉ ለታሪክ ብቻ የሚተዉ አሉታዊ ግንኙነቶችንና የ27ቱ ዓመታት የወያኔ ከፋፍለህ ግዛ ሥርዓት የዘራቸውን የተንሻፈፉና የተዛቡ የመቃቃር ትርክቶችን ብቻ ነቅሶ በማውጣት የኦሮሞ ወጣቶች በቁጣና በስሜት ተነሳስተው በወንድሞቻቸው ላይ ጥፋት እንዲያደርሱ ነበር ሲቀሰቅስ ያረፈደው፡፡
ይህ የጥፋት ቅስቀሳውም የርዋንዳውን የዘር ፍጅትና የያኔውን የሚዲያዎች የዕልቂት ጥሪ ነበር የሚያስታውሰው፡፡ ዓላማውም የርዋንዳው ዘግናኝ ግጭት በምሥራቅ አፍሪካ ግዙፍና ታሪካዊ ሕዝቦች በሆኑት በአማራና በኦሮሞ ወንድማማቾች መካከል እንዲደገም ማድረግ ይመስል ነበር፡፡
ይባስ ብሎም እጅግ በሚያሳፍር መልኩ ከኦሮሞ ሕዝብም ሆነ ከአገራችን ሕዝቦች የጋራ ባህል ፍጹም በሚጻረር መልኩ የእናት የአባት እንዲሁም የወዳጅ ዘመድ ስሜትንና ክብርን በሚነካ መልኩ አስከሬኑ ወደ አምቦ መሸኘት እንደሌለበትና አዲስ አበባ ውስጥ እንዲቀበር ተወትውቷል፡፡
የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ በቀጥታ በሚያሰ ራጫቸው በእነዚሁ ፕሮግራምና መልዕክቶቹ የአርቲስት ሀጫሉን ገዳይ «እከሌ ነው» ብሎ በግልጽ በመፈረጅ በመላ አገሪቱ በተለይም በኦሮሚያ ክልል ይበልጡንም በአዲስ አበባ ሁከት እንዲቀሰቀስ ነበር ሲሰብክ ያረፈደው፡፡
ይህንን የቴሌቪዥን ጣቢያውን የዕልቂት ጥሪ ተከትሎ የአስከሬን ሽኝት ሥነ-ሥርዓቱ በሁከት ተበጠበጠ፡፡ መላው የኦሮሚያ ክልልም በሾተላዩ ሰይፍ ተመታ፡፡
ሥርዓት አልበኝነትና መገዳደል ነገሰ፡፡ የሰከረው የሾተላዩ ሰይፍ የበርካቶችን ሕይወት ቀጠፈ፤ የመንግሥትና የግለሰቦች የልፋት ጥሪት የእሳት ራት ሆነ፡፡
አሳፋሪው ነገር ደግሞ ወዲህ ነው – የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ ይህንን የጥፋት ጥሪ ሲያሰራጭ የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጭ ግንባር (ትህነግ/ ህወሓት) ልሳኖች የነበሩት ድምጸ ወያነ እና የትግራይ ቴሌቪዥን በየፊናቸው የጥፋት ጥሪውን በመቀባበል ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጩ ዘገባዎችን በማቅረብ መጠመዳቸው ነበር፡፡
የአርቲስት ሀጫሉ ግድያን ተከትሎ የተፈጸመው የእርስ በእርስ መጠፋፋትና ውድመት ከለውጡ በፊት በነበሩት የዝርፊያና የግርፊያ ዓመታት በወያኔ መራሹ ኢሕአዴግ ሲፈጸም የነበረው መንግሥታዊ የአሸባሪነትና የጎሰኝነት አገዛዝ ውጤት ስለመሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡
አገሪቱ በትህነግ አፈና ውስጥ በነበረችበት ወቅት የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክም ሆነ ባለቤትና መስራቾች በአሸባሪነት ተፈርጀው ተሳዳጆች ነበሩ፡፡ ድምጸ ወያነና የትግራይ ቴሌቪዥንም ከሌሎቹ የኢሕአዴግ ሚዲያዎች ጋር በመሆን የአሳዳጆቹ መሣሪያና አውጋዦች ነበሩ፡፡
የዛሬን አያድርገውና ለውጡ እንደደራሽ ጎርፍ ጠራርጎ መቀሌ የቀረቀረው የህወሓት ቡድን በኦሮምኛ ቋንቋ በኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ የሚተላለፉ የጥፋት ጥሪዎችን ወደትግርኛ እና አማርኛ ቋንቋዎች በመመለስ በሁለቱም ሚዲያዎቹ ሰፊ የዕልቂት ቅስቀሳ አድርጓል፡፡
የትግራይ ቴሌቪዥንና ድምጸ ወያነ ከኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ ጋር ፍጹም በተናበበ መልኩ የጥፋት ነጋሪት ሲጎስሙ የሰነበቱት ታዲያ ተመሳሳይ የሆነ አገር የማፈራረስ እኩይ ዓላማ ስላነገቡ ነበር፡፡
የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የአብሮነት ሀረግ የሚመዘዘው ከዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ዘመን ወዲህ ብቻ እንደሆነ በማስመሰልና ረዥሙን የአማራና የኦሮሞ ጭቁን ሕዝቦች የአብሮነትና የትግል ጎዳና «ጨቋጭ ተጨቋኝ» በሚለው የህወሓት ውስጠ- መርዝ ትርክት ተጠቅሞ ሕዝቦቹን ለማጣላት የመሰሪነት መርዙን ረጭቷል፡፡
ድምጸ ወያነና የትግራይ ቴሌቪዥን በበኩላቸው የሁለቱን ግዙፍ ሕዝቦች ግንኙነት «እሳትና ጭድ» በሚል በሚገልጹት እኩይ የህወሓት ቁንጮዎች እየተመሩ የአርቲስቱን ግድያ ተከትሎ የተፈጠረውን ትኩሳት የመንግሥት መፍረስና የአገሪቱ መበታተን ዋዜማ አድርገው በማቅረብ የሾተላይ ነጋሪታቸውን ጎስመዋል፡፡
ዛሬ ላይ እነርሱ ፈራርሰው አገራችን በጽናት ቆመች እንጂ የትህነግና የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ ወሬ ጎሳሚዎች ኢትዮጵያን ከዩጎዝላቪያ ጋር በማነጻጸር በመፈራረስ ቋፍ ላይ ያለች አድርገው በማቅረብ ሕዝቡን በሀሰት አምሰውታል፡፡
በዓለም ታሪክ ተመዝግቦ እንደምናነበው ዩጎዝላቪያ ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የሶቭዬት ሕብረትን መፈራረስ ተከትሎ ክሮሽያ፣ ሰርቢያ፣ ቦሲኒያን የመሰሉ ስድስት አገሮች የፈጠሯት አገር ነበረች፡፡ ይሁንና ብዙም ሳይቆይ ዩጎዝላቪያ ፈራርሳ በዓለም መድረክ እምብዛም ተጽዕኖ የሌላቸው ትናንሽና ደካማ ስድስት አገሮች ወደመሆን ተቀይራለች፡፡
ኢትዮጵያችን ግን በአምስት ሺህ ዓመታት የመንግሥትነት ታሪክ ውስጥ በክፉም በደግም በጋራ ሆነው አገር አቅንተው፤ ጠላት መክተው በነፃነት የኖሩ የተዋለዱና በማይበጠስ የጋራ የባህልና የታሪክ ተዛምዶ የተሰናሰሉ ከ80 የሚልቁ ብሔር ብሔረሰቦች አገር ናት። በክርስትናም ሆነ በእስልምና ቅዱሳት መጻህፍት ውስጥ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን እንደ ግብጽ በበደል፤ እንደሰዶምና ገሞራ በጥፋት ሳይሆን በጥበበኝነት፣ በደግነት፣ ለፈጣሪ ቅርብ በመሆንና በመሳሰሉት መልኮች ነው የተገለጹት፡፡
የኢትዮጵያውያን የመንግሥት ታሪክና የሕግ አክባሪነት እንዲሁም የጨዋነትና የግብረ ገብነት ተምሳሌትነት በጥንታውያኑ የግሪክ የታሪክ የቀለም ቀንዶች ሳይቀር የተመሰከረ ነው፡፡ የሰው ዘር መገኛ፣ የጥንት የሥልጣኔ ቁንጮ እንዲሁም የድንቃድንቅ ቅርሶች ባለቤትም ናቸው ኢትዮጵያውያን፡፡
እነዚያ የወሬ ፈብራኪዎች ግና ደናቁርት ስለነበሩ ይህንን ዓይነት ነባራዊ ሐቅ ወደጎን ትተው ኢትዮጵያ በህወሓትና አሁን ባለው ሕገ-መንግሥት የተፈጠረች ትናንት የሌላት ሥር-አልባ የ27 ዓመት አገር አስመስለው በማቅረብ የውሸት ትርክታቸውን ደርድረዋል፡፡
በባህልና በታሪክ የተጋመደ ሕብር ያለውን ሕዝብ ንቀው የሺ ዘመናት የአብሮነት ቋጠሮውን እየፈቱ ኮሽ ባለ ቁጥር አገር ልትፈርስ ነው እያሉ በሟርታቸው ሕዝቡን አደንቁረዋል፤ አደናግረዋልም፡፡
የሕዝቡ በተለይም የወጣቱ ድርሻ
እርግጥ የወሬ ነጋሪት ጉሰማው በአገሪቱ የብልጽግና ጉዞ ላይ የራሱን ጥቁር ነጥብ ማሳረፉ አልቀረም፡፡
ከኢትዮጵያ ሕዝብ 60 በመቶው የሚሆነው ወጣት በመሆኑ መልካም ዕድል ቢሆንም ቅሉ፤ ትውልድ ለማጨንገፍ ታስቦ በተተገበረው የህወሓት የትምህርት ሥርዓት መነሻ ግብረ-ገብነት፣ ምክንያታዊነትና ብስለት በቅጡ ስላልሰረጸ ሥራ-አጥነት ታክሎበት የብጥብጥና የሁከት ጎርፍ ከባድ ጥፋትን እያስከተለ አልፏል፡፡
ይሁንና አብዛኛው ሕዝብ ከተለያዩ የመገናኛ አውታሮች የሚያገኘውን መረጃ በመመዘንና በራሱም ያስተዋለውን ነባራዊ ሐቅ ከግምት በማስገባት አስተዋይነት በተሞላበት መልኩ በመንቀሳቀሱ የጥፋት ደጋሾቹ ያቀዱት አገርን የማፍረስ የቅዠት ሴራ ጨንግፎ ቀርቷል፡፡
ነፃ ሀሳብ መያዝ፤ የያዙትንም አስተሳሰብ በነጻነት ማሰራጨት በዓለምም ሆነ በአገራችን ሕጎች የተፈቀደ ነው፡፡ የሥልጡንነት ጠባይ ማሳያም ነው፡፡
ይሁንና ይህ ሃሳብን በነፃነት የመያዝና የመግለጽ መብት ከአገር ሰላምና ከሕዝብ ደህንነት ጋር ሚዛኑን ጠብቆ ሊጓዝ እንደሚገባ ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡
እናም እኩይ ዓላማን ያነገቡ የዛሬዎቹ ወሬ ፈብራኪዎችም እንደትናንቶቹ የግብር አባቶቻቸው አሁንም ሕዝቡን በወሬ ሊፈቱት ይማስናሉ፡፡
የእኩይ ዓላማቸው ማስፈጸሚያ የነበሩት የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎቻቸው የውሃ ሽታ ሲሆኑባቸው ማህበራዊ ሚዲያውን ዋነኛ መሣሪያቸው አድርገዋል፡፡ ይሁንና እነርሱ እንደቁራ ቢጮሁም ሕዝቡ በተለይም ወጣቱ ነገራቸውን ማውጠንጠን፤ ሴራቸውንም አላምጦ መትፋት አለበት፡፡
የእኩይ ግብር አባቶቻቸው እስከመቃብራቸው ይዘውት የወረዱትን የሀሰትና የጥላቻ ወሬ የዛሬዎቹ ውላጆቻቸው ሲያስተጋቡት ቢውሉም ወጣቱ ፊቱን ሊያዞርባቸው ይገባል፡፡
በደህና እንሰንብት!
አዲስ ዘመን ጥር 25/2013