ወንድወሰን መኮንን
ሁሉም ነገር እንዳልሆነ ሆኖ ተገለባብጦ በነበር ቀርቶ የተደመደመው በአጭር ጊዜ ነው፡፡ የእብሪትና የማን አለብኝነት የመጨረሻው ጥግ አሳዛኝና አሳፋሪ ውድቀት ነው፡፡ የሆነው ሁሉ መሆን ስላለበት ሆነ፡፡ የሀገር ውስጥ ችግሮችን መፍታትና ማከም የሚችሉት የሀገሪቷ ባለቤት የሆኑት ኢትዮጵያውያን ብቻ ናቸው፡፡
የማይመለከታቸው የማያገባቸው ገና ለገና እርዳታ ሰፍረናልና አዛዥ ናዛዥ እንሆናለን የሚሉ የውጭ ኃይሎች በሀገር ውስጥ የውስጥ ጉዳይ እየገቡ እንዳሻቸው እንፈንጭ የሚሉበት ዕድል ሊሰጣቸው አይገባም፡፡
በኢትዮጵያ ላይ ተደጋጋሚ ክህደት ሲፈጽሙ የኖሩ ኃይሎች የውጭ ዜግነትን ተሸክመው በእጅ አዙር የሌሎች ፍላጎትና አላማ አስፈጻሚ ሆነው በኢትዮጵያዊነት ስም የሚነግዱ ሸቃዮች የሚበጃቸው እጃቸውን ከኢትዮጵያ ላይ ማንሳት ነው፡፡ የዚያን ሰሞን በመቀሌ የነበረው ሁኔታ ሲጋጋም ዜጎቻችንን ለማውጣት ይፈቀድልን ያሉ የምዕራባውያን መንግሥታት በነዚያው ሰዎች አማካኝነት በሀገራችን ላይ ያሻቸውን ሲሰሩ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
በቀደም ፍርድቤት ቀርበው በእንግሊዝኛ ነው የምናገረው ያሉት አዛውንት ለረዥም ዘመን የእንግሊዝ ዜግነት ያላቸው መሆኑን ምን ያህል ሰው እንደሚያውቅ አይታወቅም፡፡ አሜሪካዊ፣ እንግሊዛዊ፣ ካናዳዊ፣ ወዘተርፈ ሆናችሁ ይህችን ታላቅ ሀገርና ሕዝብ በተላላኪነት ለመግዛት የምትመኙ ሁሉ አንድ ቀን እንደ ወያኔ የኢትዮጵያ መሬቷ እንደሚከዳችሁ ከወዲሁ እውቁት፡፡ አታቆሽሹን፡፡
ዛሬ በዓለም አቀፍ ሚዲዎች በስፋት የተከፈተው ጸረ ኢትዮጵያ ፕሮፓጋንዳና ዘመቻ አንዱም እኛ ያስቀመጥናቸው ዜጎቻችን ተነኩብን ታሰሩ እርምጃ ተወሰደባቸው የሚል ነው፡፡ ጉዳዩ አልጠፋንም፡፡ ከጀርባ ሌሎች መንግሥታትም ታክለውበት ድምጻቸውን እያሰሙ ነው፡፡ ከጀርባ ሆነው በውስጥ ጉዳዮቻችን በመግባት አዛዥና ናዛዥ ለመሆን ይዳዳቸዋል፡፡ በተለይም ምዕራባውያን ሚዲያዎች በገንዘብ እየተገዙ እጅግ የተሳሳቱ የተዛቡ መረጃዎችን በኢትዮጵያ ላይ ማሰራጨት ይዘዋል፡፡
በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት መደፈር መንገላታት ነበረ ብለው በመቃወም ለውጡን የደገፉት የምዕራቡ ዓለም ኃይሎች ዛሬ ጀምበር ሳትጠልቅ የፈለጉትን ስላላገኙ ተመልሰው አሁን እየመራ ባለው መንግሥት ላይ ከፍተኛ ጫና ለማሳደር እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ሚዲያዎቻቸው ይህ ቀረው የማይባል ዘመቻ ከፍተዋል፡፡
አዎ የውጭ ኃይሎቹ ፍላጎት እነሱ ባሰቡትና በተለሙት መንገድ ብቻ የሚጎተት የሚመራ የሚነዳ አስተዳደር ነው የሚፈልጉት፡፡ ያን ማድረግ ካልተቻለ የተለመደውን የጭቃ ጅራፋቸውን ያወርዱበታል፡፡ ስመ ብዙ ዓለም አቀፍ ድርጅቶቻቸው በሰብአዊ መብት፤ በፕሬስ ነፃነት ወዘተ አስከባሪ ስም ተቋቁመው የእነሱኑ ጥቅም የሚያራምዱት በሙሉ የከፋ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ይከፍታሉ፡፡ አሁን እየሆነ ያለውም ይኸው ነው፡፡
በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ በተደራጀ መልኩ አጸፋዊ ተገቢ ምላሽ የሚሰጥ፤ እውነታውን ለማሳወቅ የሚጥር፤ ሸፍጣቸውን በአደባባይ የሚያጋልጥ በተለይ በሀገር ውስጥና በውጭ ላሉትም ተደራሽ የሆነ አሠራር የለም። በመንግሥት በጀትና በሽንጣም መኪና የሚረገረግ የጠላትን ፕሮፓጋንዳ ለመመከትም ሆነ ለማምከን አቅምም እውቀትም አልቦ የሆኑ ሹማምንት ናቸው ሞልተው የተረፉት፡፡ ወግ ጠራቂና አሳማሪ፡፡ ግብር አልቦዎች፡፡
ኢትዮጵያውያን ዲፕሎማቶችና አምባሳደሮች እንዲሁም በዲያስፖራ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተውን ሀገር አፍራሽ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ በአግባቡ መክተው ሊያመክኑት ይገባል፡፡ ሰፊ ርብርብ ማድረግም አለባቸው፡፡ በጅምላ መናገሩ ተገቢ ባይሆንም በተለያየ ሀገራት ያሉ የተወሰኑ የኢትዮጵያ አምባሳደሮችና ምሁራን ብቻ ናቸው አንገት ለአንገት እየተናነቁ የውጭ ኃይሎች የከፈቱትን ሴራ በውጭ ሚዲያ እየቀረቡ እየተዋጉ ያሉት፡፡ ሁሉም ወገን በያለበት ሊያግዛቸው ይገባል፡፡
በተቀናበረ ሁኔታ የተከፈተው ዘመቻ መልከ ብዙና ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ መመከት ብቻ ሳይሆን በላቀ ብቃት መስራትንም ይጠይቃል፡፡ በውጭ ያለው የኢትዮጵያ ዲፕሎማት ዛሬ በሀገራችን ስላለው ተጨባጭ ሁኔታና እውነት ለያለበት ሀገር መንግሥትና ሚዲያ ሳይታክት ማሳወቅ ይጠበቅበታል፡፡ ይሄ አንድ ራሱን የቻለ የጦርነት ግንባር ነው፡፡ መጋፈጥ ግድ ይላል፡፡ ለሀገር ክብር መፋለም፡፡
የኢትዮጵያን መንግሥት ገጽታ ለማጠልሸት የሚሰሩት እነ ማርቲን ፕላውትን የመሰሉ ቅጥረኞችና እንዲሁም ሎቢስቶች የሚታወቀውን ተጨባጭ ሀቅ እያዛቡ በስፋት በማቅረብ ላይ ይገኛሉ፡፡ ያው በኢትዮጵያ በኩል በተደራጀ ሁኔታ እውነቱን ለውጭው ዓለም ለማሳወቅ የሚደረገው ጥረት እጅግ ደካማ ነው፡፡ ሰው ጠፍቶ ሳይሆን ሰው የለምና ነው፡፡
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ወይንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ብቻ የቱንም ያህል ቢደክሙ በሰፊ መሠረት ካልታገዙ ብቻቸውን መማሰናቸው ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ጡረታ ከወጡትም ቢሆን ለዚህ ሥራ ማሳተፍ ያስፈልጋል፡፡ እየሰሩ ላሉት ሥራ ግን ሊመሰገኑ ይገባል፡፡
ለዚህ ሀገርና አመራሩን የማጠልሸት፤ በዓለም አቀፍ መድረክ ተቀባይነት እንዲያጣ ለማድረግ፤ በአንጻሩም ግዙፍ ከሆኑ ዓለም አቀፍ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ተቋማት እገዛና እርዳታ እንዳያገኝ እነ ግብጽና ሌሎችም ሌት ከቀን እየሰሩ ያሉት ሥራ በቸልታ የሚታለፍ አይደለም፡፡ በተቀናጀና በተደራጀ መልኩ የሚመራ ነው፡፡
በሜዳው ላይ ያሉ ተጨባጭ እውነቶችን፤ በኢትዮጵያ ሠራዊት ላይ የተሰሩ አረመኔያዊ ግፎችና ጭፍጨፋዎችን ምንም እንዳልተሰሩና እንዳልተደረጉ አድርጎ ለማቅረብ መሞከር ሀገሬ ብለው ምንም ባላወቁትና ባልተዘጋጁበት በየሜዳው በታረዱት፤ የፊጥኝ ታስረው በተረሸኑት፤ በአስከሬናቸው ላይ በተጨፈረባቸው ልብሳቸውንና ጫማቸውን አውቅለው በባዶ እግራቸው በረሀ እንዲወርዱ በተፈረደባቸው፤ ከግንድ ጋር ታስረው በተረሸኑት የመከላከያ ሠራዊታችን አባላት ደምና መስዋዕትነት መቀለድ ነው የሚሆነው፡፡ በወንድሞቻችን ደምም ሆነ በሀገራችን ጉዳይ አንደራደርም፡፡
ከጦረኝነት ድንፋታም ባለፈ ባሕርዳርና አስመራን ሮኬት አስወንጭፎ በተደጋጋሚ የደበደበው በእብሪት ታውሮ የነበረው ኃይል የዐጸፋ ምላሹ ምን ሊሆን ይችላል ብሎ ለማሰብ እንኳን ሕሊናው ተሸፍኖ ነበር። በየትኛውም ዓለም የሠራዊት ሕግ ራስን ከጥቃት መከላከል ወንጀል አይደለም፡፡
በትግራይ ሥርዓተ አልበኝነት እልቂት ረሀብና ስደት እንዲሰፍን ያደረገው ወያኔ ነው፡፡ የመንግሥትና የሕዝብ አገልግሎት ተቋማትን አክሱም አየር ማረፊያን ጨምሮ አገልግሎት እንዳይሰጥ መሬቱን ያረሰው ያወደመው ወያኔ ነው፡፡ በመከላከያ ሠራዊት አባላት ላይ ይህ ቀረው የማይባል ዘግናኝ ጭፍጨፋ የፈጸመው ወያኔ ነው። በምን መስፈርት ነው ይህን ኃይል ፍትሀዊና ሕጋዊ አድርገው የፕሮፓጋንዳ ሥራ የሚሰሩት ተብሎ ሲጠየቅ ይሄን የሚያደርጉት ከሰብእና ከሰውነት የተፋቱ ሰዎች ብቻ ናቸው ብሎ መደምደም ይቻላል፡፡
ግብጽ በሁለቱም የጸረ ኢትዮጵያ ግንባር ከጀርባ አመጽና ሁከት በማስነሳትም ሆነ አማጽያንን በማደራጀትና በመርዳት የጦር መሳሪያ በማስታጠቅ እንዲሁም በፕሮፓጋንዳው ጦርነት ግንባር ኢትዮጵያን ለማዳከምና ከቻለችም ለመበታተን በብዙ ሚሊዮኖች በጀት በጅታ እንደምትንቀሳቀስ ይታወቃል፡፡
ሀገር የሚያባሉ አክቲቪስቶች እንደገናም በብልጽግና ስም ተጠልለው በሸነና የሚሉ የበግ ለምድ የለበሱ ተኩላዎች፤ በዘረኝነት ልክፍት የምታጓሩ ሁሉ የኢትዮጵያ ጠላቶች ተላላኪና ቅጥረኛ መሆናችሁን ልታውቁት ይገባል፡፡ እናንተም እንደ ውጮቹ ኃይሎች ሁሉ እጃችሁን ከኢትዮጵያ ላይ አንሱ !! ኢትዮጵያ በጠላቶቿ ፕሮፓጋንዳ የምትፈርስ ሀገር አይደለችም !
አዲስ ዘመን ጥር 25/2013