ዘካርያስ ዶቢ
መሥሪያ ቤቴ በአዲስ አበባ ከተማ አንድ ዋና መንገድ ላይ ነው። ሁለተኛ ፎቅ ላይ በስራ ተጠምጃለሁ። ከዋና ጎዳናው ከወትሮው ወጣ ያለ ድምጽ ሰማሁ፤የማስታወቂያ ወይም የጥሪ ድምጽ ነው። በዚያውም ልፍታታ ብዬ ለስራዬ ውል አብጅቼለት በመስኮት ቁልቁል መመልከት ጀመርኩ።
ለወትሮው እንዲህ ያሉ ማስታወቂያዎች በተሽከርካሪ ላይ ትላልቅ ድምጽ ማጉያዎች ተጭነው የሚከናወኑ ናቸውና ተሽከርካሪ መፈለግ ጀመርኩ። ይህን መልዕክት ለማስተላለፍ በሚል የተዘጋጀ አንድም መኪና ማግኘት አልቻልኩም። አሁንም ፍለጋዬን በርቀት ጭምር ወደ ግራም ወደ ቀኝም እያደርግሁ ቀጠልኩ።
በመሀል ያ ድምጽ ተመልሶ መጣ። ድምጹ የሚወጣበትን አካባቢ ለየሁ። አንድ ሰው ድምጽ ማጉያ ይዞ አንዴ ወደኋላ ሌላ ጊዜ ወደፊት ወደጎን እያለ እየተናገረ ነው። ስፒከር ግን አጠገቡ የለም፤ ይህ ድምጽ ያለ ግዙፍ ስፒከር እንዴት እንዲህ ሊሰማ ቻለ ብዬ አሁንም አካባቢውን መቃኘት ውስጥ ገባሁ። ወዲያው አንድ ለየት ያለ ሰው ተመለከትኩ። ያ ሰው በጭንቅላቱ ላይ ትልቅ ስፒከር/ሞንታርቦ/ ተሸክሞ ዋየርለስ መነጋገሪያ የያዘውን ሰው ይከተለዋል።
ይህን ጉድ ተመልከቱ ብዬ አጠገቤ የሚገኙትን ባልደረቦቼ አስነስቼ አሳየኋቸው። ሰዎቹ ማስታወቂያውን መኪና ተከራይተው ማስነገር ለብዙ ወጪ ሊዳርጋቸው እንደሚችል አስበው ሊሆን ይችላል ይህን ያደረጉት። ምናልባትም ይህን አይነቱ መልዕክት የማስተላለፊያ መንገድ ተመራጭና ተደማጭ ያደርገናል ብለውም ይሆናል።
ጎበዝ ለእኛ ለአድማጮቹ ማዘን ከቀረ ቆይቷል። የድምጽ ብክለት እየተባለ ብዙ ቢወራም፣የመጣ ለውጥ ግን የለም። የእነዚህ ሰዎች መልዕክት ማስተላለፊያ መንገድ ደግሞ ወጣ ያለ ነው። ድምጽ ማጉያውን የተሸከመው ሰው ጆሮ የሰው ጆሮ አይደለም እንዴ?
በዚህ ላይ ሌሎች ጎጂ ነገሮች በሰውየው ላይ ሊደርሱ አይችሉም ወይ? የሰውዬውን ሁኔታ ስመለከተው ለእዚህ ሥራ በኪራይ የተገኘም አይደለም፤በቀጥታ ማስታወቂያውን ከሚሰሩት አንዱ ነው፤ቁመናው ያስታውቃል። በኪራይ የተገኘ ሰውስ ቢሆን ለምን በዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ እንዲሰራ ይደረጋል። ይህ በጣም የሚያሳስብ ጉዳይ ነው። ለጆሮው እንኳ አለመታሰቡ ምን ይባላል?
ሞንተርቦ መንፈሳዊው፣ አለማዊው ጥሪ ይተላለፍበታል፤የንግዱ ማስታወቂያ በዓይነት ዓይነት ይነገርበታል፤ሰው ታመመብን ለውጪ ሀገር ህክምና እርዱን ባሉ ድጋፍ ይሰበሰብበታል፤ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ጥሪ ይቀርብበታል። አሁን አሁንማ ባንኮችም ድንኳናቸውን ተክለው ቆጥቡ ይሉበታል። ደም ለግሱ ይባልበታል፤ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ግዙን ይሉበታል። እነዚህ ከብዙ በጥቂቱ አገልግሎቶቹ ናቸው።
ጥሪው ወይም ማስታወቂያ በግልጽ መኪኖች /በፒክ አፕ፣በአይሱዙ /፣ በሚኒባሶች፣ ወዘተ. በየጎዳናው፣ በየአደባባዩ፣በየገበያው ስፍራ ፣ወዘተ ይተላለፋል። ትላልቅ መድረኮች ሳይቀሩ ይካሄዱበታል። የማስታወቂያና መልዕክት ማስተላለፊያ መሳሪያ በመሆን በስፋት እያገለገለ ባለው ሞንታርቦ።
በእርግጥ መልዕክት ለማስተላለፊያ ፣ለማስታወቂያ .ወዘተ አንጀት አርስ ነው። አልሰማም ያለውን ጭምር አንዲሰማ ማድረግ ይቻላል። በሞንታርቦ ጥሪ እየተላለፈ ነው፣ትምህርትና ሰበካ እየተካሄደ ነው ከተባለ ጥሪው ከፍ ያለ ነው።
ሞንታርቦ በራሱ ብቻ ብዙ ወጪን ስለሚጠይቅ። አሁን አሁን ራሱን የቻለ የማስታወቂያ ስራ በመሆን ብዙዎችን እንጀራ በቅጡ እያበላም ይመስለኛል። መልካም ነው።
መልዕክት ወይም ጥሪ በደረቁ ማስተላለፍ የተፈለገውን ያህል ውጤታማ ሊያደርግ አይችልምና ማስታወቂያንና ትምህርትን እያጀቡ በዚህ አይነቱ መንገድ ማስተላለፍ ውጤታማ አያደርግም ተብሎ አይታሰብም።
በሀገራችን ማስታወቂያ ማስነገሪያና መልዕክት ማስተላለፊያ መንገዶች እንደ የዘመኑ ይለያያሉ። ጥሩምባ በማሰማት መልዕክቴን ስሙኝ ሲባል ተኖሯል። ይህ ብዙ ዘመናትን ቢያስቆጥርም ህያው ነው። በአብዛኛው እድሮች ለቀብር ጥሪ ይጠቀሙበታል፤ለስብሰባ እና ለተለያዩ የሥራ ዘመቻዎች ጥሪ ሲደረጉበትም ይስተዋላል።
መልዕክት ማስተላለፊያው ወይም ጥሪ ማድረጊያው መንገድ እየተሻሻለ መጥቶ የድምጽ ማጉያዎች /ሜጋ ፎኖች / ጥቅም ላይ ውለዋል። እነዚህ በባትሪ ድንጋይ የሚሰሩ ሜጋ ፎኖች ማስታወቂያ ለመንገርም ሆነ ጥሪ ለማስተላለፍ ሲያገለግሉ ቆይተዋል፤አሁንም እያገለገሉ ይገኛሉ። በተለይ እየተዘዋወሩ መልእክት ለማስተላለፍ በእጅጉ ጠቅመዋል።
ቴፕ ሪከርደሮች በፈጠሩት ምቹ ሁኔታ ድምጽን በካሴት በመቅረጽ መልዕክት እንዲተላለፍ ሲደረግም ቆይቷል። የቴፕ ሪከርደሮቹ የድምጽ ማጉያ ለእዚህ አይነቱ ስራ ምቹ በመሆኑ ማስታወቂያን በተለያዩ ሙዚቃዎች እያጀቡ ለማቅረብ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።
አሁን ደግሞ ግዙፍ ድምጽ ማጉያዎች ይህን ሥራ ተረክበውታል። ድምጽ ማጉያዎችን ህዝብ በብዛት በሚተላለፍባቸው ቦታዎች፣በስብሰባ አደራሾች፣ጎዳናዎች ወዘተ. ላይ በማስቀመጥ መልዕክት የማስተላለፍ ማስታወቂያ የማስነገር ስራዎች ተለምደዋል። በተሽከርካሪዎች ላይ ግዙፍ ድምጽ ማጉያዎችን/ሞንታርቦ / በመጫን አካባቢዎችን ድብልቅልቅ በማውጣት ያም ያም የሚተላለፈውን መልዕክት በግድ ጭምር እንዲሰማ ማድረግ ውስጥ ተገብቷል።
ድምጽ ማጉያዎቹ ሰዎች እንዲደማመጡ ምንም አይነት እድል አይሰጡም፤ሰዎች ሳይወዱ በግድ ውይይታቸውን ጭውውታቸውን ያቋርጣሉ። በምትኩ ድምጽ ማጉያዎቹ የጎረሱትን መልዕክት ወይም ማስታወቂያ በየሰው ጆሮ ይሰዳሉ። ሳይወዱ በግድ እንዲሰሙ ያደርጋሉ።
ሰዎች በመኪና ላይ ሆነው በተዘጋጀላቸው ድምጽ ማጉያ በመጠቀም ጥሪ ያስተላልፋሉ፤አለዚያም የተቀረጸ መልዕክት በድምጽ ማጉያው በመጠቀም ያስተላልፋሉ። መኪናዎቹ ጀነሬተር ይጫንባቸዋል፤ ትላልቅ ስፒከሮች ይደረጉላቸዋል። ይህም የዘመኑ የተለመደ የማስታወቂያ ማስነገሪያና መልዕክት ማስተላለፊያ መንገድ ሆኗል።
ድምጽ ማጉያዎቹ እንደ አቅም እንዳቅም ተደርገውም ተሰርተዋል። የበረሮ መድኃኒት ሻጭ ነኝ የሚለው የሆነ ጥግ ላይ ሆኖ መድኃኒቱን ግዙኝ ይልባቸዋል። በአንድ ወቅት አንድ የበረሮ መዳህኒት ሻጭ መልዕክቱን ሲያስተላልፍ ከዚህ መኪና ላይ መድኃኒቱን ያገኛሉ ሲል ሰምቼ ዞር ስል ግዙኝ ባዩ ሰውዬና ድምጽ ማጉያው ብቻ ነበሩ በስፍራው ያሉት፤መኪና የለም። መልዕክቱ የተዘጋጀው በመኪና ለሚደረግ ሽያጭ ብቻ ነው።
በመኪና ወይም በተለያየ መንገድ ሰዎችን በሚረብሽ መልኩ በትላልቅ ድምጽ ማጉያዎች በየመንገዱ ማስታወቂያዎች መልቀቅ እንዲሁም መልዕክት ማስተላለፍ በድምጽ ብክለት የሚያስጠይቅ ቢሆንም፣እነ እከሌ ተጠየቁ ሲባል ግን አይሰማም። ይህ ቢሆን ኖሮ እንዲህ ቅጥ ባጣ መልኩ ባልተስፋፉ ነበር። ማስታወቂያዎቹ በህዝብ ፣በተለያዩ መስሪያ ቤቶች ትምህርት ቤቶች ላይ ሊያስከትሉ የሚችሉት ረብሻ ማንም እንደሚረዳው ቢታወቅም እነሱን የደረሰባቸው ግን የለም።
ይሄ ችግር ሄዶ ሄዶ የደረሰበትን ደረጃ እያየን ነው። ግዙፍ ድምጽ ማጉያ ሰው እያሸከሙ ማስታወቂያ እስከ ማስነገር መልዕክት እስከማስተላለፍ የደረሰው ተግባር በሰዎች ጤና ላይ ሊያደርስ የሚችለው አደጋ ለምን ሊታይ አልቻለም። ዛሬ ሰውን ሞንታርቦ አሸክመው ማስታወቂያ ያስነገሩ ሰዎች፣ነገ ለሞንታርቦው ሀይል የሚለግሰውን ጀነሬተር አሸከመው አያስከትሉም ተብሎ አይታሰብና ጉዳዩ ይታሰብበት እላለሁ፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 24/2013