አብርሃም ተወልደ
የቧንቧ ውሃ በአዲስ አበባ ተዘርግቶ አግልግሎት መስጠት የጀመረው በጥር 22 ቀን 1886 ዓመተ ምህረት፤ ከዛሬ 127 ዓመታት በፊት ባሳለፍነው ሳምንት ነበር።
አዲስ አበባ ከተማ ከተመሰረተችበት እና ነዋሪዋ ብዛት እየጨመረ በመሄዱ ምክንያት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የውሃ እጥረት እያስቸገረ ሄደ። ገንቦውን እየተሸከመ በየወንዙ እና በየምንጩ የሚንከራተተው በዛ። በተለይ በሳምንት ሦስት ጊዜ ግብር የሚያበላው ቤተ መንግሥት ለጠላና ጠጅ መጥመቂያ ቀርቶ ለቡኮ ማቡኪያ በመቸገሩ ምንጮችን እየተከተሉ ለቤተ መንግሥት ብቻ እንዲውሉ ተደረገ።
ነገር ግን ምንኙ ውሎ ሲያድር መንጠፍ ጀመረ። የምንጮቹም ሁኔታ እያደር እያነሰ በመሄዱ ለችግሩ ማቃለያ የሚሆን ዘዴ አልተገኘም።
አፄ ምኒልክ የውጭ አገር አማካሪዎቻቸውን ሰብስበው “በእናንተ አገር የውሃ ነገር እንዴት ይሆን” አሏቸው። በፈረንጅ አገር ውሃ እዳይባክን ምንጮች እየተከለሉ ውሃው በቧንቧ እየተጠለፈ እንዴት አድርጎ እቤት ድረስ እንደሚመጣ አስረዷቸው። እኛስ ታዲያ በአገራችን ይሄን ለምን አንሞክርም የሚል ሀሳብ ለተሰብሳቢዎቹ ንጉሱ አቀረቡ። ያ ቧንቧ የተባለው ስራ እንዲሰራ ዋና ሙሴ ኢልግን አዘዙት።
ኢልግ ፕላኑን አወጣ። አሰራሩንም ለአጤ ምኒልክ አሳየ። እዚህ ላይ ኬለር ታሪኩን ሲነግረን እንዲህ ይላል “…. ኢልግም በአካባቢው ካለ ተራራ ስራ ከሚመነጨው ምንጭ ውሃ ቧንቧ ለማምጣት ሃሳብ አቀረበ።
በምኒልክ ችሎት ስር ያሉ ሰዎች አሳቡን ተቃወሙት።የተቃወሙትም ውሃን ከተራራ ወደታች ማምጣት ይቻላል እንጂ ከታች ወደ ተራራ መውጣት አይቻልም ብለው ነው። ምኒልክ ግን ኢልግ አሳብ ተስማምተው እንደ ኢልግ አስተሳሰብና ፕላን ቧንቧዎች ተዘረጉ…”
ምኒልክ ለቧንቧ መግዢያ ሰባት ሺህ ማርትሬዚያ ሰጥተዋል።ይህ ሰባት ሺህ ብር የጨረሰው ቧንቧ የመዘርጋት ስራ በ1886 ዓ.ም በጥር ወር አለቀ።ከላይ ከኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ካለ ምንጭ የተጠለፈ ውሃ ከቤተ መንግሥት ካለው የመጨረሻ ቧንቧ አልደርስ አለ።
ቧንቧው ሲከፈትም ጠብ የምትል ውሃ ታጣች።ውሃው የቀረበበት ምክንያት ይፈለግ ጀመር። ስለወቅቱ ታሪክ በስፋት የሚነግረን ወደ ኬለር መጽሐፍ ስንመለስ “… ኢልግ እንደገና ይፈትሽ ጀመር።በፍተሻው እንደተገኘው ውሃው ሊመጣ ያልቻለው ቧንቧው በጥጥ ፍሬ በመደፈኑ ሆኖ ተገኘ።ጥጥ ፍሬው ተጠርጎ ከወጣ በኋላ ውሃው ከቤተ መንግሥቱ ደረሰ። ስራው ተደነቀ ….” ይላል።
ያ የቧንቧ ውሃ በ1886 ዓ.ም ማለት አዲስ አበባ ከተማ በተመሰረተች በሰባተኛው ዓመት ከቤተ መንግሥቱ ደረሰ። በዘመኑ የነበሩት ጸሐፊ ትዕዛዝ ገብረ ስላሴ ስለቧንቧው ሲገልጡ “… አደባባዩ ላይ ውሃ በመዘውር ገብቶ ይፈስ ነበር።የውሃውም አመጣጥ እንዲህ ነው።አጤ ምኒልክ መሐንዲሱን አዝዘው ከእንጦጦ ደጋ መሐንዲሱ በኖራ እያስገነባ ውሃውን በቦይ አመጣው።
አዲስ አበባም ከሚዳው በደረሰ ጊዜ ጉድጓድ በሰፊው ተቆፍሮ ውስጡ በኖራ ፣በአሸዋ፣በከሰል እንዳይፈርስ ሆኖ አምሮ ተበጀ።ከዚያ ላይ ከፈረንጅ አገር በሰባት ሺህ በር ተገዝቶ የመጣ የውሃ መዘውር ተተከለበት።
መሐንዲሱ መሬቱን በትክክሉ እያስቆፈረ ኖራውን እያስነጠፈ መዘውሩን እያቀጣጠለ ከቅጥሩ ውስጥ አደረሰው።ከቅጥሩም በደረሰ ጊዜ በማለፊያ ወጥ ቤት መካከል እየፈሰሰ መጣ።ደግሞ አዳራሹ ወደ ግራ እያደረገ አደባባዩ ገባ።
“አደባባዩም በደረሰ ጊዜ እንደዚሁ ተቆፍሮ በኖራ በስሚንቶ ተበጅቶ ስራውም እንደ ሰህን እንደ መሶብ ወርቅ ያለ ነው።በአራቱም ማዕዘን እንደ ምንጭ ይፈሳል።ከታች የባህር መቋሚያ አለው።ይኸውም ውሃ በእልፍኙ ደጃፍ ይፈሳል። አትክልቱንም ያጠጣል። ከእልፍኙም ደጃፍ ላይ በኖራ በሲሚንቶ ተሰርቷል።መቅጃው የሸማ ማጠቢያው ለየብቻ ነው።
የአጤ ምኒልክ የእቴጌ ጣይቱም ድርቦች የባለሟሎቹም የእልፍኝ አሽከሮችም ልብስ ማጠቢያ በልዩ ልዩ ተሰርቷል።ይህ ውሃ ከገባ ሸማ ለማጠብ ወደ ወንዝ የወረደ ሰው የለም።
በእልፍኙም በሰገነቱም መሀል ለመሀል ይፈሳል። በግብርም ጊዜ በአደባባዩ ይፈሳል።“ይህንኑም ውሃ ሁለቱ ይጠጡታል፤ የሚጠጡትም እነዚህ ናቸው። ከአዳራሹ ሳይገባ ቀርቶ ጸሐይ የመታው አንድም አዳራሽ ገብቶ ጠጅ እና አረቄ የተኮሰው ከዚያ ወንዝ ሁሉም ይጠጣል።
ያንኑም ውሃ የሚያየው ሰው ሁሉ ከስጋው ከጠጁ ይልቅ ውሃውን ያደንቃል።ከደረቀ መሬት ላይ ስለመገኘቱ።ንጉሠ ነገሥቱም ከአዳራሽ ወደ እልፍኝ ሲመለሱ ውሃውም በመዘውር ተመልሶ ወደ ታዘዘበት ይፈሳል …” ሲሉ ጽፈዋል።
በዘመኑም “እንዲህ ያለ ንጉሥ የንጉሥ ቂናጣ ውሃ በመዘውር ሰገነት አወጣ አሁን ከዚያ ወዲያ ምነ ጥበብ ሊመጣ።” ተብሎ ተገጠመ።ንጉሡ በሰሩት ሥራ ባስገቡት ቧንቧ ተወደሱ።
በቤተ መንግሥት የገባው የቧንቧ ውሃ ሁሉን አስደስቶ ዘዴው ከታወቀና ከተጠና በኋላ ይህ የቧንቧ ውሃ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እንዲዳረስ ምኒልክ የውሃ ቧንቧ አዘዙ። ምኒልክ ትዕዛዝ ከሰጡባቸው ከብዙዎቹ ደብዳቤዎች መሀል አራቱን ደብዳቤዎች እነሆ!
ይድረስ ለልጅ ግዛው
ከድሬዳዋ በልፍ የተነሳ የውሃ የቧንቧ ብረት መጥቷል። እታህሳስ በአቦ ድረስ አንተ ከተማ አጠገብ እመንገድ ዳር ጠቅሎ ይሰብሰብ ብያለሁ።ከወዲህም ይህንኑ የቧንቧ ብረት ለማንሳት ደጃች ውቤንም ሌላም ሰው አዝዣለሁ።
ለታህሳስ ሚካኤል አንተ ዘንድ ይገባል›› እዚያ ድረስ የቧንቧ ብረት ከታች እንደመጣልህ እየተቀበልክ ከመንገድ ዳር ከደህና ስፍራ አቆይተህ የሚያነሳው ሰው ለታህሳስ ሚካኤል አንተ ዘንድ ሲገባ በየሹሙ በየሹሙ እገሌ ይህን ያህል እገሌ ይህን ያህል ያንሳ እያልክ በደብዳቤ እያደረክ እንድትሰጥ ይሁን።
አንተም የአገርህን ሰው ወታደርም ቢሆን አንድ ሳይቀር አዘዝህ የቻልከውን ያክል በብዙ አስነስተህ አንተው ራስህ አሲይዘህ መጥተህ ሎሜ ውስጥ ጠገዴ ማርያም ድረስ እንድታመጣ ይሁን። ከዚያ ወዲህ እኔ ሄጄ አስመጣለሁ።
ህዳር 14 ቀን 1890 ዓመተ ምህረት በአዲስ አበባ ከተማ ተጻፈ።
በንጉሱ በወቅቱ የቧንቧ ሥራ በተመለከተ የተፃፈው ሌላኛው ደብዳቤ ደግሞ በሚከተለው መልኩ ቀርቧል።
ይድረስ ለፊታውራሪ አብተማሪያም
ከታች ከድሬዳዋ የተነሳ የውሃ ማውጫ ቧንቧ ብረት በአሩሲ በኩል ይምጣ ብያለሁ እና ይህንን ለማንሳት እንደዳች ውቤን ከአዋሽ ማዶ ያለውን አገር ሁሉ አዝዣለሁና ምንአልባት ከዚህ ቀደም የተበጀው መንገድ የተበላሸ እንዳለ ካዋሽ ጀምሮ ሎሜ ጠገዴ ማሪያም ድረስ ያለውን ያንተን ግዛት መንገድ የተበላሸ የተበላሸውን እንድታበጅ ይሁን።
ህዳር 20 ቀን 1890 ዓ.ምህረት ከአዲስ አበባ ከተማ ተጻፈ።
ለደጃዝማች ውቤ በንጉሱ ለዚሁ ስራ የተፃፈው ደብዳቤም ይዘት የሚከተለው ነበር።
ይድረስ ለደጃዝማች ውቤ
የውሃ ቧንቧ ብረት ከድሬዳዋ ተነስቶ በጨርጨር በኩል መጥቷል። ይህንኑ ብረት እግዛው ወልደገብርኤል አገር ተሰብስቦ ቆይቶ ከአዋሽ ማዶ ያለው አገር ሁሉ አንስቶ ሎሜ ጠገዴ ማሪያም ድረስ ያምጣ ብዬ አዝዣለሁ እና አንተም የአገርን ሰው ጢስ አዝዘህ እግዛው ወልደገብርኤል አገርድረስ ለታህሳስ ማሪያም አንተው ራስህ ሰውን ይዘህ ሄደህ የቧንቧውን ብረት አስነስተህ ሎሜ ጠገዴ ማሪያም ድረስ እንዲመጣልኝ ይሁን።
ነገር ግን ብረቱ ብዙ ነው። በመጀመሪያ ጨርሳችሁ ሳታነሱ የተረፋችሁ እንደሆነ ሁለተኛ ተመልሳችሁ የምታነሱት እናንተ ናችሁ እና ጠንክራችሁ አንድ ጊዜ እንዲነሳ ማድረግ ነው። መንገዱን ከዚህ ቀደም የተበጀው ተበላሽቶ እንደሆነ ብረቱን ለሚሸከመው ሰው እንዳያስቸግር የተበላሸውን መንገድ ማስበጃጀት ነው።
ህዳር 23 ቀን 1890 ዓ.ም አዲስ አበባ ተጻፈ።
ይድረስ ለፊታውራሪ ሀብተማሪያም
ከሐረርጌ የመጣ የውሃ ማውጫ የቧንቧ ብረት ጉጉ እግዛው ወልደገብርኤል አገር ገብቷል፤ ይህንኑ ለማንሳት ከአዋሽ ማዶ ያለውን ሰው ሁሉ አዠዣለሁ እና እናተም ከአዋሽ ወዲያ ማዶ ያለውን አገርህን ከአዋሽ ወዲህ ያለውን አገርህን ከአዋሽ ወዲህ ማዶ ያለውንም አገር ሳይቀር በጥስ እዝዘህ በቅሎ ፣ጌኛም ፣አህያም ያለው ከብቱን እያያዘ አንተ ዘንድ ጠንካራ ሹም ጨምረህ አገር ገብቶ በከብትም በሰውም ሸክም አስነስቶ ሎሜ ጠገዴ ማሪያም ድረስ እንዲያመጣልኝ ይሁን።
ያንተ ሰው የሚያነሳውም የቧንቧ ብረት ከወፍራም ዓይነት ሺህ ብረት።ከቀጭኑ ዓይነት ሺ ብረት ነውና ይህንን አንድ ጊዜ ጨርሶ እንዲያመጣ አድርግልኝ ።የዚህ የቧንቧ ብረት ነገር የምቸኩልበት ብርቱ ጉዳይ ነውና ይህንን ያዘዝኩህን ሁለቱን ሺህ ብረት ቶሎ ሳታነሳ ቀርተህ ወደ ኋላ የቀረህብኝ እንደሆነ አይሆንም።
ትህሳስ 7 ቀን 1890 ዓመተ ምህረት አዲስ አበባ ተጻፈ
አፄ ምኒልክ ያሰሩት የቧንቧ ውሃ እምብዛም ሳይስፋፋ የኢጣሊያ ፋሽሽት ኢትዮጵያን እስከያዘበት ዘመን ድረስ ቆየ። በዚያ ዘመን የነበረው የቧንቧ ውሃ ላንዳድ ምርጥ መኳንቶች ቤቶች የገባ እንጂ አብዛኛው የአዲስ አበባ ነዋሪ ህዝብ ውሃ የሚቀዳው ከወንዝ ከምንጭ እና ከጉድጓድ ነበር።
ከዘሬ አንድ መቶ ዓመት በፊት በንጉሡ የተጀመረው የቧንቧ ውሀ ዝርጋታና የውሀ አቅርቦት ዛሬ ድረስ የመዲናዋ ነዋሪዎች ፍላጎት ማርካት ተስኖት ይገኛል። በእርግጥ ንጉሡ በዚያን ዘመን የጀመሩት የውሀ ቧንቧ ዝርጋታ ጅማሮ የሚደነቅ ነበር።
አዲስ ዘመን ጥር 23/2013