ለምለም መንግሥቱ
አዳማ ከተማን ካየኋት ትንሽ ስለቆየሁ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ እና እንደሀገር ህግ ለማስከበር እየተወሰደ ባለው እርምጃ ምክንያት እንቅስቃሴዋ ቀዝቀዝ ብሎ የማያት መስሎኝ ነበር። ነገር ግን እንደጠበኩት ሳይሆን የተለያዩ ግንባታዎች ሲከናወኑና በከተማዋ ዋና የአስፓልት ዳር ይዘው የተገነቡት ሆቴል ቤቶችም እንደቀድሞ እንግዶቻቸውን እያስተናግዱ ሞቅ ደመቅ ብላ ነው ያገኘኋት።
የንግድ ኮሪዶር የሆነችው አዳማ ከተማ የተለያዩ ስብሰባዎች የሚካሄዱባት በመሆኗ የቱሪዝም ኮንፈረንስ መዳረሻ ሆናም ሰፊ የህዝብ ቁጥር በማስተናገድ ላይ የምትገኝ ውብና ተመራጭ ከተማ ነች።
አዳማ የተለያዩ ስብሰባዎችን ለማስተናገድ የሚያስችሉ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎችና ሪዞርቶች በውስጧ ያቀፈች ሲሆን፣እነርሱን ተከትለው በየደረጃው በአነሥተኛ ዋጋ የመኝታ አገልግሎት የሚሰጡ እንግዳ ማረፊያና ሆቴሎች እየተስፋፉ መጥተዋል። በሥራው የተበረታቱና ውጤታማ የሆኑ አንዳንድ የሆቴል ባለቤቶች ደረጃቸውን በማሳደግና በማስፋፋት አገልግሎታቸውን ለማሻሻል ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
እነዚህ ሁሉ ሰላማዊ እንቅስቃሴዎች ደግሞ በሆቴል ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶችን ወደ ከተማዋ ለመሳብ መንገድ ከፍተዋል። የማስፋፊያ ሥራ በመስራት ከአንድ ወደ ሁለት ያደገው በአዳማ ከተማ ከሚገኙ ሆቴልቤቶች ድሬ ኢንተርናሽናል ሆቴል ተጠቃሽ ነው።
በድሬ ኢንተርናሽናል ሆቴል በነበረኝ ቆይታ የሆቴልቤቱ አስተናጋጆች እንግዶችን በማስተናገድ ተጠምደው ነበር። አዳራሾቻቸውም በተሰብሳቢዎች ተይዘው ለመታዘብ ችያለሁ። መቸም ኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ እንደተከሰተ ሆቴልቤት ሄዶ ለመዝናናት ቀርቶ ሰው ከቤቱም ለመውጣት የፈራበት ጊዜ እንደነበር አይዘነጋም።
በአጋጣሚው ያነጋገርኳቸው አንዳንድ የሆቴልቤቱ ሰራተኞችና የሆቴሉ ሥራአስኪያጅ ምንይጠ የቃል በሚል አይነት ስሜት ነበር ወረርሽኙ በሥራቸው ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖው የገለጹልኝ።
ለወትሮው እንግዶችን በማስተናገድ እረፍት የሌለው ሆቴል ተቀዛቅዞ እነርሱንም የሥራ ዋስትና የማሳጣት ደረጃ ላይ የደረሰ ሥጋት ፈጥሮባቸው እንደነበር አስታውሰዋል። ሆቴሉ አልፎ ሂያጅ እንግዳ ከማስተናገድ በላይ ለቀናት ቆይተው የምርምር ሥራ የሚያካሂዱ፣ወደተለያዩ የቱሪስት መዳረሻዎች የሚያቀኑ፣ለመሸጋገሪያነት የሚጠቀሙበት እንዲሁም ሥልጠናዎችንና የተለያዩ ስብሰባዎችን የሚያዘጋጁ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትን በስፋት ሲያስተናግዱ ቆይተዋል።
በአብዛኛው የሀገር ውስጥ እንግዳ የሚያስተናግዱ ቢሆንም ለስልጠና የሚጋበዙና በከተማዋና አካባቢዋ በተለያየ ዘርፍ የተሰማሩ ኢንዱስትሪዎች የግንባታ ሥራ የሚያከናውኑ የውጭ ሀገር ዜጎችም ደንበኞቻቸው ናቸው።
አህጉራዊና ዓለምአቀፍ ስብሰባዎችን በማዘጋጀት የአንበሳውን ድርሻ የምትወስደው የኢትዮጵያ ዋና መዲና አዲስ አበባ ከተማ ብትሆንም እንደ አዳማ ከተማ ሁሉ የሐዋሳና የባህርዳር ክልል ከተሞች ስብሰባዎችንና ኮንፈረንሶችን በማዘጋጀት ተጠቃሽ ናቸው። እነዚህ የቱሪስት መዳረሻና ስብሰባን ማዕከል ያደረጉ የክልል ከተሞች በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ መነቃቃት እየታየባቸው ይገኛል።
በሌላ በኩል እንደጎንደር፣ ላልይበላ፣ አክሱም… ያሉ የቱሪስት መዳረሻ ከተሞች ደግሞ ስብሰባዎች በስፋት ሲካሄድባቸው አይታይም። ይልቁንም እነዚህ ከተሞች ገቢ ለማግኘት ትኩረት አድርገው የሚንቀሳቀሱት ታሪካዊ ቦታዎችን ለመጎብኘት ወደ አካባቢው የሚሄደውን ቱሪስት እና በዓመት አንዴ የሚካሄድን ክብረ በዓል ላይ የሚታደመውን እንግዳ በመጠበቅ ነው።ይህም ቢሆን ከውጭ የሚመጣውን እንግዳ በማስተናገድ ላይ ትኩረት ያደረገ እንጂ በዓልን ለመታደምም ሆነ በተለያየ ምክንያት ወደ አካባቢው የሚሄደውን የሀገር ውስጥ ዕንግዳ ለመያዝ ደጋግሞ ወደ ስፍራው እንዲመጣ ለማበረታታት የሚደረገው እንቅስቃሴ ጠንካራ አይደለም።
በአንድ አቅጣጫ ላይ ትኩረት ያደረገ የቱሪዝም መሳቢያና ከዘርፉ የመጠቀም አካሄድ ኮቪድ 19 ቫይረስ ሲከሰት ጉዳቱ ጎልቶ ታይቷል። ለዚህ ደግሞ የጎንደር ከተማ አንዷ ማሳያ ናት። የጎንደር ከተማ የሆቴሎች ማህበር ፕሬዚዳንትና የጎሀ ሆቴል ሥራ አስኪያጅ አቶ አማረ አጥናፉ እንደገለጹት እንደ ሌሎች ከተሞች ቱሪዝም ኮንፈረንስ በከተማዋ ቢለመድ የገቢ ማካካሻ አድርጎ መጠቀም ይቻል ነበር።
በበሽታው ምክንያት ሥራቸው ተዳክሞ ለችግር የተዳረጉት የአካባቢው አስጎብኝዎችና የሆቴል ቤቶች ቀድመው በሀገር ውስጥ ትኩረት ያደረገ ሥራ አዳብረው ቢሆን ኖሮ በሽታው ካደረሰባቸው ጉዳት ለማገገም ዕድሉን ያገኙ እንደነበር አንስተዋል ። የኮሮና ወረርሽኝ አሁንም መፍትሄ ያልተገኘለት በመሆኑ የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት የከተማ አስተዳደሩ ቱሪዝም ኮንፈረንስን ታሳቢ አደርጎ እንዲሰራ ጥረት በማድረግ ላይ ነው ሲሉ ተናግረዋል ።
በስብሰባና ኮንፈረንስ ላይ የተመሰረተ ቱሪዝም ‹‹meeting incetiv conference exhibitions›› ወይም ባጭሩ ‹MICE› ‹ማይስ› በሚባለው የሚገኘው ገቢ እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ ከድረገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። በነባሩ አሰራር በትርፍ ጊዜያቸው ኢትዮጵያን ለመጎብኘት በሚመጡ ጎብኝዎች ላይ የተመሠረተ ሲሆን፣በአስጎብኝዎች በኩል ከሚገቡት ውስን ቁጥር ካላቸው ጎብኝዎች የሚገኘው በማይስ ቱሪዝም ከሚመጡት ጋር ሲነፃፀር የሚገኘው ገቢ ዝቅተኛ ነው።
ማይስ ቱሪዝምን በስፋት እየተጠቀሙ ያሉት ያደጉ ሀገራት ሲሆኑ ከፍተኛ ገቢ እያገኙበት እንደሆነም መረጃዎች ይጠቁማሉ። እ.ኤ.አ በ2017 በሰሜን አሜሪካን 329ነጥብ 7 ሚሊየን የማይስ እንግዶች የተገለገሉ ሲሆን እያንዳንዳቸው በአማካይ አንድ ሺ156 ዶላር ወጪ አድርገዋል።
መደበኛ በሚባለው በአስጎብኚ ድርጅቶች አማካኝነት በሚከናወነው የቱሪዝም ሥራ አንድ ቱሪስት በአማካይ የሚያጠፋው አንድ መቶ ዶላር ሲሆን፣በማይስ የሚመጣው ሰው ደግሞ እስከ አምስት መቶ ዶላር ያጠፋል። ልዩነቱን በዚህ መልኩ ያሳየው የድረገጽ መረጃው እንዳመለከተው በማይስ ቱሪዝም ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱ በሥራ ምክንያት ስለሚዘዋወሩና ወጪያቸውን የሚሸፍኑላቸው ትላልቅ ኩባንያዎች በመሆናቸው እንደፈለጋቸው ተዝናንተው ጥሩ ጊዜ አሳልፈው ወደ መጡበት የሚመለሱ ሲሆን የኢኮኖሚ አቅም ጉዳይ የሚያሳስባቸው አይደሉም።
በተጨማሪ የእንግዶቹ መዳረሻ ቦታዎች ሳቢ ስለመሆናቸውና አለመሆናቸው ብዙም አይጨነቁም። የሚፈልጉት ያረፉበት አካባቢ ደህንነት፣ ምቹነቱ፣ መስተንግዶው የተሟላና ጥራት ያለው መሆኑን ነው የሚያስደስታቸው።
ማይስ በቀላሉ ስብሰባና ኤግዚቢሽን ፕሮግራሞችን ከሚያዘጋጁ ግለሰቦች ጋር በመደራደር በአንድ ጊዜ ከፍተኛ ገቢ የሚገኝበት በመሆኑ ብዙ ሀገሮች ፊታቸውን ወደ ማይስ ቱሪዝም እንዲያዞሩ መንገድ ከፍቶላቸዋል።
በዚህ ረገድ ምዕራባዊያን ያላቸውን መልካም አጋጣሚ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ። ለማይስ መዳበር እንደ ትራንስፖርት፣ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት፣በአጠቃላይ የተሟላ መሠረተ ልማትና አስፈላጊው ነገር መሟላት አለበት።
ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዋን ልታሳድግበት የምትችልበት መልካም አጋጣሚዎች ቢኖሩዋትም ዘርፉ በሚጠይቀው መጠን በሠለጠነ የሰው ኃይል ስብጥር፣በመወዳደር፣በቱሪስት አገልግሎት ብዙ ማሟላት የሚጠበቅባት የቤት ሥራዎች አሉ። በእነዚህ ጉድለቶች ምክንያትም በማይስ ቱሪዝም ኢንደስትሪ ኢትዮጵያ ከ140 ሀገሮች 122ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
ሌላው የቱሪዝም የገቢ ምንጭ ሆኖ የሚያገለግለው ‹‹ስቶፕ ኦቨር›› ቱሪዝም የሚባለው ዘርፍ ሲሆን፣ይህም በትራንዚት ወቅት በትርፍ ጊዜያቸው ያረፉባቸውን ሀገራት የመጎብኘት ፍላጎት ያላቸውን የማስተናገድ ስራ ነው።
‹‹ስቶፕ ኦቨር ቱሪዝም›› እኤአ በ1950ዎቹ እንደተጀመረ መረጃዎች የሚያሳዩ ሲሆን ዘርፉ በርካታ ሀገራትንም ተጠቃሚ አደርጓል ። የተለያዩ ሀገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየውም ለአንድ ቀን አርፎ ለመሄድ ያስበ መንገደኛን እስከ አምስት ቀናት እንዲቆይ በማድረግ ተጠቃሚ መሆን ይቻላል።
ኢትዮጵያም እንዲህ ያለውን አጋጣሚ አጠናክራ መቀጠል እንዳለባት የዘርፉ ባለሙያዎች ይመክራሉ። ከአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ያገኘነውም መረጃ እንደሚያመለክተው ከትራንስፖርትና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመሆን ለአንድ ቀን አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ቆይታ ለማድረግ የመጣ የውጭ ሀገር
ዕንግዳ የጉዞ ሰነዱ ለቀናት ተራዝሞለት በከተማዋ የሚገኙ መዳረሻዎችን እንዲጎበኝ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በመሰራት ላይ ይገኛሉ። ለዚህም ማዕከል በሆኑ ቦታዎች የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማስታወቂያ ሰሌዳ በመለጠፍ የማስተዋወቅ ሥራዎችን በመሰራት ላይ ነው።
በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የዓለምአቀፍ ቱሪዝም ፋሲሊቴሽን ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ደርበው ሀሳቡን በማጠናከር የጎረቤት ሀገሮችን ተሞክሮ መሰረት አድርገው እንዳብራሩት የኬኒያ፣ዩጋንዳ፣ደቡብ አፍሪካ ከተሞች የኮንፈረንስ የማይስ ቱሪዝም ከተሞች እየሆኑ ነው። በቢሊየን ዶላር የሚንቀሳቀስበት ዘርፍ በመሆኑ ለኢኮኖሚ ምንጭና የደም ሥር ተደርጎ ይወሰዳል።
በኢትዮጵያ በተለይም አዲስ አበባ ከተማ የዲፕሎማቲክ ከተማ እንደመሆኗ የኮንፈረንስ ቱሪዝምን ለማካሄድ ከፍ ያለ አቅም አላት። ወደ ክልል ከተሞች የመስፋፋቱ ዕድልም እየተፈጠረ ነው።
በሀገር ውስጥ ባሉ ኩነቶችም ሰዎች ከተለመደው የሥራ ሁኔታ ወጣ ብለው ስብሰባዎችን የማካሄዱ ተግባር እየተለመደ መጥቷል። በመሆኑም በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኙት አዳማና ቢሾፍቱ ብዙ ኩነቶች ይካሄዳል። በተለይ አዳማ ትላልቅ ስብሰባዎች የሚካሄዱባት ከተማ ለመሆን በመቻሏ ይህን ተከትሎ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች እየተስፋፉ ይገኛሉ። መጠጥ፣ ምግብና መኝታ አገልግሎት ለመሥጠት ብቻ ሆቴል መገንባት የማይስ ቱሪዝምን ዓላማ አያሳካም።
ስብሰባ የሚካሄድባቸው ሰፋፊ አዳራሾች በግንባታ ወቅት ታሳቢ መሆን አለባቸው። ብዙዎችም ግንባታቸው ይህን ማዕከል ያደረገ ነው። የቱንም ያህል ባህላዊ፣የተፈጥሮ ቅርሶችና የቱሪስት መዳረሻዎች ቢኖሩም የበለጠ መስህብ የሚሆኑት የተለያየ አገልግሎት የሚሰጡ ሆቴል ቤቶች ሲኖሩ በመሆኑ ዘርፉን ማጠናከሩ አስፈላጊ ነው።
እንደ አቶ ቴዎድሮስ ማብራሪያ በማይስ ቱሪዝም አንድ ሰው ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ሲንቀሳቀስ በአማካይ አራት ሺ አምሥት መቶ ዶላር ያወጣል። ስብሰባና ኮንፈረንስ ላይ የሚካፈሉ እንግዶች በእረፍት ጊዜያቸው የመዝናናትና የጉብኝት ፕሮግራም ጎን ለጎን በማቀድ የከተማዋን የቱሪስት መዳረሻዎች ይጎበኛሉ። የተለያዩ የገጸበረከት ዕቃዎች ይገዛሉ። ይዝናናሉ።
ይህ ደግሞ ስብሰባውን የሚያዘጋጀው ሀገር በገቢ ተጠቃሚ ያደርጋል። ኢትዮጵያ በየዓመቱ አህጉር አቀፍና ዓለምአቀፍ ስብሰባዎችን በማስተናገድ አቅም ብትፈጥርም ማይስ ቱሪዝምን ብዙ ያልሰራችበት ዘርፍ ነው።
የተፈጥሮ፣ሰው ሰራሽና የተለያዩ ቅርሶች ያሉበትን የቱሪስት መዳረሻዎች ማስጎብኘት ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ኩነቶችን በማከናወን በተቀናጀ አሰራር ማህበራዊ ልማትን ለማፋጠንና ለዜጎችም የሥራ ዕድል በመፍጠር ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን ማግኘት ይቻላል።
ይህ መልካም አጋጣሚ ያለው ዘርፍ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት መጎዳቱን ያስታወሱት አቶ ቴዎድሮስ፤ወረርሽኙን ለመከላከል የሚረዱ የንጽህና መጠበቂያዎችን እንዲያሟሉ እንዲሁም የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ) መጠቀም ባህል እንዲሆን በማድረግ ሥራዎች እንዲከናወኑ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያስችሉ ስትራቴጂዎችን በመደገፍና በመተግበር ዘርፉ መልሶ እንዲያገግም የመቀልበስ ሥራ ተሰርቷል። ዘርፉን የበለጠ አጠናክሮ ተጠቃሚ ለመሆን ግን የራሱ የሆነ አደረጃጀት ሊኖረው ይገባል ብለዋል።
ኮቪድ ባስከተለው ተጽዕኖ ብዙዎቹ ከተሞች ገና አላገገሙም። አዳማ ከተማ ግን ከሌሎቹ የተሻለ እንቅስቃሴ ላይ ትገኛለች። በአጠቃላይ ዘርፉ እንደ አንድ የቱሪዝም መስህብና መወዳደሪያም እንዲሆን ለኮንፍረንስ ቱሪዝም ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ክፍል ለማደራጀት ሥራዎች መጀመራቸውንም አቶ ቴዎድሮስ ጠቁመዋል።
ኮንፈረንስ ወይንም ማይስ ቱሪዝም ለማካሄድ የሚያስችል የሆቴልቤቶች ባለቤቶች የሚያከናውኑት የአዳራሽ ግንባታ በክልል ከተሞች ቀርቶ በአዲስ አበባም የተሟላ ነው ለማለት አያስደፍርም። በክልል ከተማ ደረጃ ባህርዳር ከተማ ላይ በየዓመቱ የሚካሄደው አህጉር አቀፍ የጣና ፎረም ስብሰባ መልካም ተሞክሮ ለአብነት በመጥቀስ፣ ከሌሎች ሀገሮች ልምድ አንጻር የተጠናከረ ሥራ እንደሚጠበቅ አቶ ቴዎድሮስ ተናግረዋል። ያለፉት ዓመታት የኢትዮጵያ የቱሪዝም መረጃዎች ተሞክሮ የኮንፍረንስ ቱሪዝም ድርሻ 30 በመቶ መሆኑና ውጤቱም የሚያበረታታ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 23/2013