አክበረት ታደለ (ሄዋን)
በዚህ ጉዳይ ላይ ለመፃፍ ያነሳሳኝን አጋጣሚ ላስቀድም አንድ በዲኤስቲቪ የሚተላለፍ የሴቶች የንጸሕና መጠበቂያ ሞዴስ ማስታወቂያ ነው። ማስታወቂያው የተሠራው አውሮፕላን ውስጥ ሲሆን አንዲት ሴት ወደ መታጠቢያ ቤት ስትሄድ ያሳያል። እንደ አጋጣሚ ሁሉም ክፍል ተይዟልና ቆማ ብዙ ጠበቀች።
ነገር ግን የተለቀቀ ክፍል አልነበረምና ከነበረችበት ሁኔታ አንፃር ከዚያ በላይ ቆማ መጠበቅ አልቻለችም። ከአቅሟ በላይ ስለሆነባትም እዚያው የቆመችበት ንጽሕና መጠበቂያዋን መቀየር ግድ ይሆንባታል። ከዚያም የቀየረችውን ሞዴስ በመስኮት ስትወረውረው የገባው ባህር ውስጥ ነበር ወዲያው የባህሩ ውሃ በሙሉ ይደርቃል።
የወረወረችው ሞዴስ የባህሩን ውሃ በሙሉ መጠጠው ማለት ነው። የሞዴሱን ምርት ምን ያህል ፈሳሹን መጥጦ የማስቀረት አቅም እንዳለው ለማሳየት የተጠቀሙበት የፈጠራ ሥራ ነው። የበዛ ግነት ቢጠቀሙም ለማስተላለፍ ከፈለጉት መልዕክት ጋር በቀጥታ የሚሄድና ዘና የሚያደርግም ማስታወቂያ መሥራት ችለዋል።
ደግነቱም የሚያሳቅቅ አይደለም ማስተላለፍ የፈለጉት ምርታቸውን ፈሳሽን የመያዝ አቅሙ በጣም ከፍተኛ ስለሆነ ለሴቶች ምቾት የሚሰጥና በራስ መተማመን እንዲሰማቸው የሚያደርግ መሆኑን ነው። ይህን ደግሞ በሚገባና በማይረሳ መልኩ ማስተላለፍ ችለዋል።
ማስታወቂያ እንደዚህ በሚገባና በማይረሳ መልኩ የሰውን ቀልብ መያዝ ከቻለ ትልቅ ስኬት ነው የፈጠራ ሃሳብ ደግሞ ትልቅ ግብዐቱ ነው። ይህን በማስታከክ የሀገራችን የቴሌቪዥን ማስታወቂያዎች ላይ ያለኝን ትዝብት ልቀጥል።
እውነቱን ለመናገር አብዛኞቹ የሀገራችን ማስታወቂያዎች የምርቶች ማስታወቂያ ሳይሆን የቆንጆ ሴቶች ትርዒት ነው የሚመስለው ምርቱን ከመግለጽ ይልቅ ማስታወቂያውን የሚሠሩት ሴቶች ውበት፣ አለባበስ፣ ሜክአፕ፣ ዝነኝነት ያጎለብታል ብል ማጋነን አይሆንም።
በጣም ብዙ ማስታወቂያዎች ላይ የታዘብኩትና አንዳቸው ከሌላቸው አይተው ማስተካከል ያልቻሉት እንደውም እንደ ማስታወቂያ ጥሩ ጎን እየተቆጠረ ያለውን ጉዳይ ላንሳ። አንዲት ሴት አርቲስት ወይም ሞዴል አልያም የማስታወቂያ ባለሙያ ልትሆን ትችላለች፣ የፈርኒቸር ማስታወቂያ ላይ የማዕድ ቤት ዕቃዎችን ማስታወቂያ ስትሠራ ማዕድ ቤት ውስጥ እያበሰለች ነው የሚሆነው፣ አለባበሷ ፀጉሯ ሜካፑዋ ግን የእራት ግብዣ ላይ ያለች ነው የሚመስለው። ሌላም የዘይት፣የተለያዩ የምግብ ግብዓቶች ማስታወቂያ ሲሠራ ቀረፃው ኪችን ውስጥ ነው የሚሆነው።
ነገር ግን ማስታወቂያውን የምትሠራው ሴት አለባበስ፣ የፀጉሯ ሁኔታና የምትቀባው ሜክአፕ ሲመለከቱት ምግብ የምታበስል ሴት ሳይሆን ወደ አንድ ትልቅ የግብዣ ፕሮግራም ለመሄድ የተዘጋጀች ነው የምትመስለው። ልብ ሊባል የሚገባው የማወራው ስለ አንድ ማስታወቂያ አይደለም። አብዛኛዎቹ ማስታወቂያዎች ላይ ስለታዘብኩት ነገር ነው።
እውነታውን ስንነጋገር ምግብ ለማብሰል ማዕድ ቤት ስንገባ ፀጉራችንን ተሠርተን፣ ሜካፕ ተቀብተን ነው። ውጪ ስንወጣ የምንሠራውን አድርገንስ ማዕድ ቤት እንገባለን። ይሄ ፈፅሞ ስህተትና ከእውነታው ጋር የማይገናኝ ነገር ነው ከእውነት የራቀ ጉዳይም ነው ይህ ማለት ሙሉ ልብስ ለብሶ ኳስ ሜዳ እንደመሄድ አልያም የራት ቀሚስ አድርጐ ቤተክርስቲያን እንደመግባት ማለት ነው ምንም ነገር ካለቦታውና ካለጊዜው ውበት አይኖረውም። የማስታወቂያ ባለሙያዎቻችን ይህን ነገር መገንዘብ ለምን እንዳቃታቸው አይገባኝም፤ ይህንን የሚያስተውል አንድም ባለሙያ አለመኖሩም በጣም ያስገርመኛል።
ትክክለኛው ነገር ሴት ልጅ ማዕድ ቤት ገብታ ስታዘጋጅ ከቻለች ፀጉሯን መሸፈን ካልሆነም ቢያንስ እንኳን ሰብሰብ አድርጋ ታስረዋለች እንጂ ፀጉር ተለቆ ምግብ መሠራት አይመችም። አንድም ለመሥራት አይመቻትም፤ ሌላም ከንፅሕና አንፃር ወደ ምግብ ፀጉር የመግባት አጋጣሚ ሊኖረው ይችላልና ሌላውና ሊዘናጋ የማይገባው ነገር ሜክአፕ ተቀብቶ ወደ እሳትና እንፋሎት መጠጋት የራሱ የሆነ ትልቅ የጤና ችግር የሚያመጣ መሆኑ ነው።
ይሄን ጉዳይ ከዚህ አንፃር የሚመለከተው ሰው እንዴት ይጠፋል ሜክአፕ ሰው ሠራሽ ነገር ነው የተለያዩ ኬሚካሎች አሉበት ያን ሁሉ ነገር ተቀብቶ ወደ እሳት መቅረብ ደግሞ የፊት ቆዳ ላይ ችግር ያመጣል ሜክአፕ አድርጐ አይደለም ወደ እሳት ብዙ ፀሐይ ፊትን እንዲነካው እንኳን እንደማይፈቀድ የዘርፉ ባለሙያዎች ደጋግመው የሚመክሩት ጉዳይ ነው።
ታዲያ ምን ለማስተላለፍ ተፈልጐ ነው ምግብ የምታበስል ሴት የቀለም መዓት ተቀብታ እንድትቀረፅ የሚደረገው? ወይስ ማስታወቂያውን የሚሠሩት ሴቶች ቤታቸውም ያንን ነው የሚያደርጉት? እሱ ሊሆን አይችልም ምክንያቱም ለጤናቸውም ያስባሉና። ደግሞም ምቾት አይሰጣቸውም ለትንሽ ደቂቃዎች ቀረፃ ስለሆነ ነው ብለው የሚያደርጉት ከሆነ ይሄ ከእውነታው ይርቃል። እንደዚያ ከሆነ የማዕድ ቤት ማስታወቂያን መታጠቢያ ቤት መሥራት አግባብ ነው ማለት ነው፤ ተጠቅመነዋል እያሉ አይደለ የሚያስተዋውቁት እንደሱ ከሆነ ወደ እውነታው መቅረብ አለባቸው ሆነው መሥራት ባይችሉ ቢያንስ መምሰል ይጠበቅባቸዋልና።
እውነቱን ለመናገር እነዚህን ዓይነቶቹን ማስታወቂያዎች በምመለከትበት ጊዜ የአርተፊሻል ጸጉር ወይም የሂዩማን ሄር አልያም ደግሞ የጐበዝ ሜክአፕ ባለሙያ ማስታወቂያ ቢሆን ይሻል ነበር እላለሁ እናም እጠይቃለሁ የሀገራችን የማስታወቂያ ሕግ ወይስ ሴቶቹ ያለሜካፕ የመታየት በራስ መተማመን ስለሌላቸው ይሆን? መልሱን ለባለሙያዎቹ እተወዋለሁ ግን ደግሜ እላለሁ ምንም ነገር ቢሆን ያለቦታው ከተቀመጠ ውበት አይኖረውም።
በቅርብ ቀን ወደተመለከትኩት የልብስ ሳሙና ማስታወቂያ ልለፍ በዚህ ማስታወቂያ ላይ ሦስት ሴቶች ተደርድረው ልብስ እያጠቡ ነው የሚታየው። ሦስቱም ፀጉራቸውን በሻሽ ሸፍነውት ቀለል ያለ የቤት ልበስ ነው የለበሱት። ነገርግን በጣም የሚያምር ሜክአፕ ተሠርተዋል ሊያውም በጣም ደማቅ Occasional የምንለውን ዓይነት ሜክአፕ።
ይህ ደግሞ ከአለባበሳቸውና ከሚሠሩት ሥራ ጋር ፈፅሞ የማይገናኝ ነበርና በጉዳዩ በጣም ነው የተገረምኩት፤ ከዚያም ሦስቱም በየተራ ስለ ሳሙናው ጥራት በመደነቅ የሚናገሩበት ክፍል አለ ሁለተኛዋ ሴት ስትናገር ዓይኗ ላይ ያደረገችው ሠው ሠራሽ ሽፋሽፍት ዓይኗን እየወጋት በጣም ተቸግራ ነበር የሠራችው፤ ላስተዋለው ብቻ ሳይሆን በደምብ በሚታወቅ መልኩ ማለት ነው ይህም ምንም ጥሩ ነገር ያለቦታው ምንም ነው የሚለውን ነገር ያስታውሰናል።
ሌላው የታዘብኩት ነገር ፈጠራ አልባነት ነው የተመልካቹን ቀል ብ በመሳብ ምርቱን እንዲጠቀመው የሚገፋፋ የፈጠራ ሃሳብ የላቸውም ተደግመው እንኳን ቢታዩ ይሰለቻሉ። ተመሳሳይ ምርት የሚያመርቱ የተለያዩ ካምፓኒዎች ባሉበት ሁኔታ ተወዳድረው ማሸነፍ ብልጫን ማግኘት፣ ትኩረትን መሳብ ሲገባቸው አንዱ የሠራውን ሌላኛው ይደግመዋል ምናልባት ምናልባት የሚቀየረው ማስታወቂያው ላይ የሚሠራው ሰው ብቻ ይሆናል።
ሌላው የማስታወቂያዎቻችን ባህሪ እየሆነ የመጣው ጉዳይ ከእውነታው መራቅ፣ ከርዕሰ ጉዳዩ መውጣት፣ ማስተላለፍ የተፈለገው ጉዳይ ሌላ ሆኖ እያለ የትኩረት አቅጣጫቸው ደግሞ ሌላ መሆን ነው።
በጽሑፌ መጀመሪያ አካባቢ ካነሳሁት ጋር የሚያያዝ ቢሆንም ግን ራሱን የቻለ ሌላ ድክመት ነው አንድ የወተት ማስታወቂያ ሊሆን ይችላል ወይ? ደግሞ የሆቴል አልያም ደግሞ የሪል ስቴት ከማስታወቂያው በላይ አጉልተው የሚያሳዩን ስለ ወተቱ፣ ሆቴሉና ስለሪል ስቴቱ ሳይሆን ማስታወቂያውን ስለሚሠራው ወንድ ወይም ሴት ነው ወንድ ከሆነ ስለ ቁመናውና አረማመዱ፤ ሴት ከሆነች ስለሰውነት ቅርፅ ስላደረገችው ጫማ ልብስ ሂዩማንሄር ብቻ!
ከርዕሰ ጉዳዬ ሳልወጣ አንድ ማስታወቂያ ላይ የታዘብኩትን ደግሞ ላካፍላችሁ ማስታወቂያው የሪል ስቴት ነው። ለተመልካች ማሳየት የሚገባው ነገር ግልፅ ነው። ሁላችንም የምንጠብቀው የቤቱን የተለያዩ ክፍሎች ማየት አካባቢውንና የቤቱን አቀማመጥ… ወዘተ… ነው በዚህ ማስታወቂያ ላይ ግን ያለማጋነን ነው የምናገረው ሙሉ ደቂቃውን ሲታይ የነበረው የልጅቷ የሰውነት ቅርፅ፣ ጫማዋ ያደረገችው ሂዩማን ሄር፣ ሜክአፕ፣ ጥፍሯ ነበር። በአጠቃላይ የሚመስለው የውበት ሳሎት ማስታወቂያ እንጂ የመኖሪያ ቤት አልነበረም አልያም የጂምናዝየም ወይም የሰው ሠራሽ ፀጉር ማስታወቂያ።
እርግጥ ነው የሚያምር ነገር ማየት ማንም አይጠላም ነገር ግን ይሄ የውበት ማሳያ ሳይሆን የቤት ማስታወቂያ ነው። ስለዚህ ትኩረቱ መሆን ያለበት የቤቱ ሁኔታ እንጂ የልጅቷ ውበት አይደለም። የዚህን ያህል ትዝብት ውስጥ እስኪገባ ድረስ ዓላማውን መርሳትም ተገቢ አይደለም ምክንያቱም ባለቤቶቹ ሰው እንዲገዛላቸው የሚፈልጉት ቤቱን እንጂ ልጅቷን አይደለምና።
ትዝብቴን ቀጥያለሁ ሁላችንም እንደምናውቀው ተመሳሳይ አገልግሎት የሚሰጡ ነገሮችን ግን ደግሞ የተለያዩ ካምፓኒዎች ያመርታል ለምሳሌ ሎሽኖች፣ የፀጉር ቅባት፣ ሳሙና፣ ዘይት፣ ውሃ… ብዙ ነገሮች አሉ። ስለዚህ አንደኛው ካምፓኒ ከሌላው የተሻለ ተጠቃሚ እንዲኖረው የሚያሠራቸው ማስታቂያዎች የተሻሉ መሆን ይኖርባቸዋል አንድ ጊዜ እንደዚህ ተፈጠረ ፤ የጥበብ ባለሙያዎች አካባቢ የመገኘት አጋጣሚ አለኝና አንድ የታሸገ ውሃ ማስታወቂያ በሚሠራበት ወቅት እዚያው ነበርኩ።
እንደአጋጣሚ ማስታወቂያውን ከምትሠራው ልጅ ጋር ትውውቅ አለን። ከዚህ በፊት የሠራችው አንድ ዝነኛ የታሸገ ውሃ ማስታወቂያ አላትና በዚያ ማስታወቂያ ሰው ያውቅሻል። ተመራጭ ነው ብለሽ እንደዚያ አስተዋውቀሽ አሁን ደግሞ ከዚህኛው ውጪ ውሃ የለም ስትይ ሁለቱ አይጋጭም አልኳት።
ነይ ሥሪ አሉኝ። የኔ ኃላፊነት መሥራት ነውና እስከከፈሉኝ ድረስ አይመለከተኝም አለችኝ ይህ ምላሽ ትንሽ ግራ አጋባኝ ይህን ነገር ሌሎች ማስታወቂያዎችም ላይ አስተውዬዋለሁ የሆነን ዳይፐር የመጨረሻ ምርጥ ነው ብሎ ሲያስተዋውቅ የነበረ የማስታወቂያ ባለሙያ በዚያው ምላሱ ዓለም አቀፍ ጥራቱን የጠበቀ ብሎ ሌላ ዳይፐር ያስተዋውቃል የምንጊዜም ምርጫዬ ብላ ያስተዋወቀችውን የልብስ ኮሌክሽን የትም የማይገኝ ብላ ሌላ የልብስ መሸጫ ብራንድ ታስተዋውቃለች ቢያንስ እንኳን ለተወሰነ ጊዜ ወይም የሠራው ማስታወቂያ እይታው እስኪያበቃ ድረስ ሌላ ተመሳሳይ ምርት ማስተዋወቅ እንደማይቻል የሚገልጽ ውል ቢፈራረሙ ጥሩ ይመስለኛል።
ምክንያቱም ይህን ሥራ የሚሠሩት ታዋቂ ሰዎች ናቸው ተጽዕኖ ፈጣሪ ናቸው የምንላቸው ማለት ነው ስለዚህ ትላንት ሌላ ብለውን ዛሬ ሌላ እያሉ ተመልካቹንም ባያወዛግቡት ጥሩ ነውና ይሄ ተመልካችን ካለማክበርና ክብር ካለመስጠት ጋር ሊያያዝም ይችላል ለኔ በፍጹም የማይገባኝ ነገርም ነው። እንዲህ የሚደረገውም ሰው አያስተውለውም ተብሎ ስለሚታሰብ ነው? ወይስ የማስታወቂያ ባለሙያ እጥረት ስላለ?! የባለሙያ እጥረት እንዳንል እኛ ሀገር የማስታወቂያ ባለሙያ በተለየ መመዘኛ ተሰጥቶት የሚሠራ ሥራ አይደለም አንድ ታዋቂ ሰው በየትኛውም ዘርፍ ይሁን ብቻ ሰው የሚያውቀው ሰው ነው የሚሠራው።
እርግጥ ነው በውጪውም ዓለም ዝነኛ ሰዎችን ማሠራት የተለመደ ነው ብራንድ አምባሳደር በማድረግ ፕሮፌሽናል በሆነ መልኩ ማለት ነው ታዲያ ምንድነው ችግሩ የትወና ባለሙያ፣ ሞዴሎች፣ ሙዚቀኞች በገፍ አሉን ለአንደኛው ካምፓኒ የሠሩት ምናለ ደግመው ባያሠሯቸውና ለሌላ ዕድል ቢሰጡ በጣም የሚገርመው ምስሉን የሚሠሩት ብቻ ሳይሆኑ ድምፁን የሚሠሩትም እነሱ ናቸው እያወራሁ ያለሁት ተመሳሳይ ምርት ስለሚያመርቱ የተለያዩ ካምፓኒዎች መሆኑ ይሠመርበት።
ትላንት ይህ ይሻላችኋል ሲሉን ከርመው ዛሬ ይሄ ይበልጣል ይሉንና ነገ ደግሞ ማን እንደዚህኛው ማለታቸውን ይቀጥላሉ በሌላ ዓለም ለማስታወቂያ ሥራ የሚሰጠው ቦታና ዝግጅት በጣም አስገራሚ ነውና ፍጹም አድርገው ነው የሚሠሩት። የሚያሠሯቸውን ሰዎች እንኳን በሚመጡበት ጊዜ ከሰዎቹ ሕይወት ጋር የሚያያዝ ነገር እንዲኖረው አድርገው ነው በውጭው ዓለም ለምሳሌ አንድ የቅባት ካምፓኒ ማስታወቂያውን የሚሠሩለት የራሱ ሞዴሎች ይኖሩታል።
ሪል ስቴት፣ ሆቴል ፣ ምግብ ነክ ነግሮችን የሚያመርቱ ሁሉ እያንዳንዱ ካምፓኒ የራሱ ባለሙያዎች አሉት እነዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ ገና ብንሆንም ግን ቢያንስ ከላይ እንደገለጽኩት በጣም በተቀራራቢ ጊዜ ተመሳሳይ ምርት አንድ ሰው ማስተዋወቅ ቢቀር መልካም ነው እላለሁ ማስታወቂያዎቻችን ላይ የተመለከትኩትን ከብዙው በጥቂቲ ለማየት የሞከርኩበትን ሐተታዬን በዚሁ አበቃሁ ሻሎም!
አዲስ ዘመን ጥር 23/2013