ወንድወሰን መኮንን
ዘመናትና ወቅቶች ይፈራረቃሉ። መንግሥታዊ ስርዓትም እንዲሁ። አሮጌው ሲያልፍ አዲሱ ሲመጣ አንድ በቋሚነት ጸንቶ በየትውልዱ ተራ የሚሸጋገር የሚኖር የሚዘልቅ ሕያውነቱ የማያቋርጥ ትልቅ ጉዳይ አለ።
ሀገር። የሁሉም መሰብሰቢያ መጠጊያ በደስታ ቀንም መፈንጠዣ በኀዘን ቀንም ኀዘንን መወጫ የሁሉም የጋራ ቤት እናት ሀገር። ሀገር ከማንም ከምንም በላይ ነች። አቻ ተወዳዳሪ ተፎካካሪ የላትም። ሊኖራትም አይችልም።
ሀገር ከፖለቲካ ስልጣን፤ ከፖለቲካ ድርጅቶችና ከብሔር ድርጅቶችና ስመ ብዙ ሰልፈኞቻቸው፤ ጊዜ ከወለዳቸው በስልጣን ጥም አብደው ሀገር ለማፍረስ ከሚማስኑ ወፈፌዎች እጅግ በላይ ነች። ሀገር የመኖር የሕልውና የማንነት መለያ ታላቅ ክብር ነች። እደግመዋለሁ።
ገዢዎች መሪዎች እንደ ወቅት ሁሉ ይመጣሉ። ይሄዳሉ። ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ጥንታዊ የመንግሥትነት የገዘፈ ታሪክ ያላት ሀገር ነች። ዛሬ ኃያላን መንግሥታት ነን ከሚሉት አንዳንዶቹም ከመፈጠራቸው ከመኖራቸው በፊት ኢትዮጵያ ተብላ የምትጠራ የጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤት የነበረች ሕግና መንግሥት የነበራት ሀገር ነበረች። ዘመኑና መሪዎቹ ቢለዋወጡም በትውልድ ቅብብሎሽ ዛሬ ድረስ ደርሳ የተረከብናት ሀገር አለች። ኢትዮጵያ ። ትኖራለችም።
ጥንታዊ ታሪካዊ ኩሩ ጀግና የጀግናም ጀግና የሆነ ሕዝብ ነው ያለን። እስከዛሬም አስደናቂው ወደፊትም ዝንተ ዓለም ሲያስደንቅና ሲያስደምም የሚኖረው አቻና ወደር የማይገኝለት የነደደ የሀገር ፍቅር ጥልቅ ስሜታችን ነው። ሀገር ተነካች ተደፈረች ከተባለ ቀፎው እንደተነካ ንብ እያስገመገመ በአራቱም ማእዘናት ሴት ወንድ አሮጊት ወጣት ሽማግሌ ሕጻናት ጭምር እየፈከሩ እየሸለሉ ሀገሬን ለሰው አልሰጥም እያሉ ሆ ብለው የሚወጡባት ድንቅ ሀገር።
በሞቀ ደምና በሚንተገተግ ወኔ ለመሞት ቁርጠኝነታቸውን የሚገልጹባት ብቸኛዋ ሀገር ነች ኢትዮጵያ ። ይሄንን መግለጽ ከሚቻለው በላይ የሆነውን ጥልቅ የሀገር ፍቅር ስሜት ሊያጠፉት ሊቀብሩት ብዙ ቢደክሙም ማኮላሸትም ሆነ ማጥፋት አልተቻላቸውም። ቀደመት አባቶች እንዳሉት ሀገርህ እናትህ ፤ ሚስትህ ፤ ልጆችህም ነች።
ሀገርህ አባትህ ወገኖችህ ዘመዶችህ ናቸው። ሀገርህ እምነትህ ሃይማኖትህ ነች። ሀገርህ ክብርህ ገበናህ መጠጊያና ማኩረፊያ የክፉ ቀንም መሸሸጊያህ ነች። መድመቂያ ጌጥህም ነች። ሀገርህ ወልደህ ከብደህ በነጻነት ተከብርህ የምትኖርባት የጉልምስና ጊዜህ ሲያበቃ በልጅ ልጆችህ ተከበህ በስተእርጅናህ የምትጦርባት ስታልፍም መቀበሪያህ ነች። እውነት ነው ስትኖርም ኢትዮጵያዊ ነበርክና ስትሞትም ኢትዮጵያዊነትህ ተከብሮ ከጥቁር አፈሯ ጉያ ትገባለህ።
ወዳጄ ሀገር እምዬ እንዲህ ነች። ከአንተም በፊት በአባቶችህ በአያቶችህ በቅድመ አያቶችህ ሩቅ የኋላ ዘመን ሁሉ በየትውልዱ ፈረቃና ፍርርቆሽም የሀገር ነገር እንዲሁ ነበር። አቻና ምትክ የላትም። ሀገር እንደ እናት አንድ ነች። በምንም የማትተካ በማንም የማትለወጥ ብቸኛ። ብዙ ነገር ሊኖርህ ይችላል። ሀገር ግን አንድና አንድ ብቻ ናት። ከሀገር በላይ ምንም የለም።
ለዚህም ነው ልትጠብቃት ልትቆምላት ሕይወትህንም ገብረህ ልታጸናት የሚገባህ። በሀገር ነጻነት በሀገር ክብር ጉዳይ ከማንም ጋር ድርድር ብሎ ነገር አይታሰብም። በእናቱ የሚደራደር ማንም የለም።
ሁሉም ነገር ከሀገር በታች እንጂ በላይ አይደለም። በየዘመኑ የሚቀያየረው እስስታዊው የፖለቲከኞች ፖለቲካና ቅብጥርጥሮሽ የስልጣን ጥምና እራሮት አብሮአቸው እንደ ጉምና ዳመና እንደ ጤዛም የማለዳ ጸሐይ ብርሃን ሲወጣ በኖ የሚጠፋ ወይንም አንድ ሰሞን አንዣቦ የሚያልፍ እንጂ እንደ ሀገር ቋሚና ሕያው ሁኖ አይቀጥልም።
ለዚህ ነው በፖለቲካ ስካር ውስጥ ተዘፍቀው ፖለቲካዊ እብደት ካበዱ ሀገር ትጥፋ፤ ትገንጥል፤ ትበተን፤እያሉ በባእዳን ኃይሎች ግብጽና ሌሎችም ጭምር ተገዝተው በሀገራቸውና በገዛ ወገናቸው ላይ ከዘመቱት ከሀዲዎችና የታሪክ እንግዴ ልጆች ጋር መቼም ሰልፋችን አይገጥምም። አብረንም አንቆምም።
ኢትዮጵያውያን ኩሩ፤ የአርበኝነት ስሜታቸው የነደደ፤ በሀገራቸው ሕልውናና ክብር ከመጡባቸው ለማንም ለምንም የማይመለሱ፤ ግንባራቸው የማይታጠፍ ሞቴን ከሀገሬ በፊት ያድርገው የሚሉ ለሀገራቸው ሲሉ ሞትን የናቁ ሞት አይፈሬዎች መሆናቸውን ዓለም የመሰከረው እውነት ነው።
የእኛ አያቶች አባቶች እኛም ኢትዮጵያውያን ልጆቻቸው ማን ይፈራል ሞት ማን ይፈራል——ለእናት ሀገር ሲባል ብለን የምንዘምር የምንፈክር ለሀገር መሞትን መውደቅን መሰዋትን ታላቅ ክብርና ኩራት አድርገን የምንወስድ ነን። ማንም መጣ ማንም ሄደ ከሀገር በላይ ማንም የለም። አይኖርምም።
በተንቀለቀለና በተጋጋመ የጦርነት እሳትና በሞት መሀል እየተረማመዱ ሞት ለምኔ ብለው ለሀገራቸው የወደቁ እልፍ አእላፍ ጀግኖች የነበሯት ዛሬም ያሏት ሀገር ነች ኢትዮጵያ። በሀገር ድርድር የለም። ከሀገር በላይም ማንም የለም። መቼም አይኖርም።
ይኸው እውነት ምንም እንኳን የውስጥ ጦርነት ቢሆንም በሚያስደንቅ ሁኔታ በቅርቡ በሰሜን ኢትዮጵያ አውደ ግንባር በተካሄደው ፍልሚያ ላይ በአስገራሚና አስደናቂ ሁኔታ ታይቷል። በገዛ ወገኑና ወንድሞቹ የተከዳው በተኛበት የታረደው በጥይት የተደበደበው የሰሜን እዝ ሠራዊት ዳግም እራሱን አሰባብሶ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለምን ተነካሁ በሚል ታላቅ ቁጭትና እልህ ተነስቶ እንደ እሳተ ገሞራ የሚንቀለቀል የሚንተገተግ የማይበርድ የፋመ ወኔ ተላብሶ እንዴት አድርጎ ጠላቶቹን በመደምሰስ ድል እንዳስመዘገበ የሰማውና ያየነው ነው።
ሀገር አውድማና ጎራው፤ ጋራና ሸንተረሩ፤ ምንጭና ፏፏቴው፤ ጫካና ዱሩ፤ ለጥ ያለው ሜዳና ዋልቃ አፈሩ፤ ጭው ያለው በረሀ፤ ዱርና ጫካው ብቻ አይደለም። በዋናነት ሕዝቡ ነው። የተለያየ ባሕል፤ መልክአ ምድር፤ እምነት፤ ቋንቋ ፤ ስነልቦና ፤አለባበስ፤ አመጋገብ፤ የነበራቸውና ያላቸው ግን ደግሞ ተዋልደው ተጋብተው ተወራርሰው፤ በአብሮነት ዘመናትን ተሻግረው፤በክፉና በደግ ጊዜ አብረው አሳልፈው ወልደው ከብደው የኖሩት ሕዝቦች። የልጅ ልጅ አይተው የኖሩባት የሚኖሩባት ተረኛው ትውልድ ደግሞ በተራው ጠብቆ የሚያኖራት ታላቅ ጸጋ ነች ሀገር። ከሀገር በላይ ማንም ምንም የለም ።
የሀገር ፍቅር እያደር ይጎመራል። ይፈካል። ይደምቃል። ደከመ ሲሉት የሚበረታ ፤ ሞተ ሲሉት አፈርና አቧራውን አራግፎ የሚነሳ ፤ ቢከፋም ቢደላም ቢመችም ባይመችም በምንም የማይለወጥ የማይተካ ነው የሀገር ፍቅር። በሀገር ሕልውናና ክብር መቼም ድርድር የለም።
የኢትዮጵያ ሕዝብ በሀገሩ ሕልውና የመጣን ጠላት ሁሉ እየመከተ እየደመሰሰ ታሪኩን በደመቀ የደም ቀለም ጽፎ አስከብሮ የኖረ ነው። እንደ ዛሬው ጎጠኞችና መንደርተኞች ከፋፋዮች እንደ አሸን ሳይፈሉና ሳይቀፈቀፉ ፤ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ተላላኪና መሳሪያ ሁነው በገንዘብ ተገዝተው ሀገራቸውን ለባእዳን ፍላጎት አሳልፈው ለመስጠት ሳይጣደፉ በፊት ትልቁ ክብር ለሀገር በታማኝነት እስከ መስዋእትነት ድረስ መቆም ነበር።
ከሀዲዎችና ባንዳዎች እኛ ያልመራናት፤ እኛ የማንፈነጭባት፤ እኛ እንዳሻን የማንሆንባት ኢትዮጵያ ትፍረስ ትውደም ትበታተን ብለው ቢንፈራገጡም እጣው ተቀያይሮ ሞትም መፍረስም መበተንም ውርደትም ለእነሱው ሆኗል። ጠላቶቻችን ምን ቢያሴሩ ለባእዳን አሽከርነት ገብተው በገንዘብ ተገዝተው ሊከፋፍሉን ቢከጅሉ የቁርጡ ቀን ሲመጣ ኢትዮጵያውያን እንዴት በአንድነት ቆመው ጠላትን መመከትና ማደባየት እንደሚችሉ እንደ ጥንቱ ሁሉ ዛሬም አሳይተዋል። ኢትዮጵያን ማጥፋት አይቻልም። ከሀገር በላይ ሰማይ ካልሆነ በስተቀር ማንም የለም። አይኖርምም።
ተተኪው ትውልድ የቀደምት አባቶቹንና እናቶቹን ጥልቅ የሀገር ፍቅርና መውደድ ከፍ አድርጎ አርማውን ያውለበልባል። ከፍ ወደ ላይ ከፍ — አሁንም ወደ ላይ ከፍ ያደርገዋል። አዎን እንደ ጥንቱ ሁሉ ዛሬም ወደፊትም ከሀገር በላይ ምንም የለም !! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም በጀግኖች ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘለዓለም ትኑር !!
አዲስ ዘመን ጥር 23/2013