ጌትነት ተስፋማርያም
ስድስት ሰዎች በአንዴ ቢስተናገዱባት ልትጨናነቅ የምትችለው አነስተኛ የመኖሪያ ቤታቸው በርካታ አገልግሎቶችን ትሰጣለች። አራት በአራት በሆነችው ጠባብ ቤት አንዱ ጥግ ላይ መኝታቸውን ሲያሳርፉ በሌላኛው ጥግ ደግሞ ለማብሰያ የሚሆኑ ምድጃዎች ተቀምጠዋል።
መኖሪያ ቤቷ አብዛኛውን ጊዜ ቀን ላይ ተከርችማ ትውላለች፤ ምክንያቱም ኗሪዎቿ ማልደው ለሥራ ወጥተው አመሻሹን ነው ወደቤታቸው የሚመለሱት። የቤቷ ጊዜያዊ ባለቤቶች ደግሞ በትዳር የተቆራኙት አቶ ማየት አለማየሁ እና ወይዘሮ ህይወት በትሩ ናቸው። አቶ ማየት የተወለደው ጎንደር ከተማ አራዳ በተሰኘው አካባቢ ነው። ቤተሰቦቹ ወደ ደብረማርቆስ በመሄዳቸው እርሱም የትምህርት ጊዜውን ያሳለፈው በንጉስ ተክለሃይማኖት መናገሻ በሆነችው በትናንቷ መንቆረር በአሁኗ ደብረ ማርቆስ ከተማ ነው።
አቶ ማየት ሥራ የጀመረው ገና የአምስተኛ ክፍል ተማሪ እያለ መሆኑን ያስታውሳል። በወቅቱ ከቤተሰብ ተደብቆ የቀለም ቅብ ፣ የኤሌክትሪክ ጥገና እና የግንባታ ፌሮ እና ስታፋ ሥራ ይከውን ነበር። በዚህ ምክንያት ግን ከቤተሰብ ጋር ሁል ጊዜ ይጣላ እንደነበር አይዘነጋውም። ምክንያቱም ወላጆቹ ትምህርቱ ላይ እንዲያተኩር እንጂ ወደሥራው እንዲያዘነብል አይፈልጉምና ነጋ ጠባ ምክርና ተግሳጽ አይለየውም።እሱ ግን ወይ ፍንክች ።
እንዲህ እንዲያ እያለ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቆ የቴክኒክና ሙያ ትምህርቱንም ከተከታተለ በኋላ ወደ ኮብልስቶን ንጣፍ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ሥራ ላይ መሳተፍ ጀመረ። የኮብልስቶን ንጣፍ ሥራውን ሙያ በሚገባ እንደለመደ ግን ሥራው ተቀዛቀዘ። በዚህ ወቅት የፖሊስነት ቅጥር ማስታወቂያ አዲስ አበባ ከተማ መውጣቱን በመስማቱ ወደመዲናይቱ መጥቶ ተመዘገበ። አስፈላጊውን የፖሊስነት ስልጠና ከወሰደ በኋላ ወደሥራ ተሰማራ።
ለአንድ ዓመት ያክል ካገለገለ በኋላ ግን መልቀቅ እንዳለበት መወሰኑን አቶ ማየት ይናገራል። ምክንያቱ ደግሞ በርካታ ሥራዎችን በማየቱ እና ገንዘብ ማግኘትንም በልጅነቱ በመልመዱ በፖሊስነት ሥራው ወር እስከ ወር ጠብቆ ደመወዝ መቀበሉን አዕምሮው ሊቀበለው አለመቻሉ ነው። እናም በስተመጨረሻ አዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ አካባቢዎች ዳግም ወደሚያውቀው የኮብልስቶን ንጣፍ ሥራ ተሰማራ።
ማንም ዘመድ አዝማድ በሌለበት ቤት ተከራይቶ እራሱን እያስተዳደረ ሙያውን ገፋበት። ይሄ ሙያ ነገ ወደተሻለ ደረጃ ሊያደርሰው ይችላልና እራሱን አሳምኖና ጠንክሮ ሥራውን መስራት ቀጠለ። በኮብል ነጠፋ ሥራው ብቁ ሙያተኛ ተብሎ በመመረጡ በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የፎርማንነት ስልጠና በነጻ ተሰጠው። በፎርማንነት ለስምንት ወራት ከሰራ በኋላ ግን የኮብልስቶን ሥራውም ገበያ ጠፋ።
ለጥቂት ወራት ያለሥራ ወጪ እንጂ ገቢ በሌለበት ሁኔታ ማሳለፉ ግድ ሆነ። በእነዚያ ወራት ችግር በችግር ላይ ተደራርቦ የቤት ኪራይ በመጣበት ወቅት ከየትም ብሎ እያሟላ ችግርን ቀምሶ ማሳለፉን አይዘነጋውም። ይሁን እንጂ በጥንካሬ ወደፊት ከማለት ውጪ አንድም ቀን ተስፋ መቁረጥ አይታይበትም።
ሥራው በመቀዛቀዙ ችግሩ ሲበዛ ግን ወደቤተሰቦቹ መንደር ተመልሶ ወደ ደብረ ማርቆስ አቀና። የኮብልስቶን ንጣፍ ሥራውን በከተማዋ ቀጠለ። ጥቂት ገንዘብ ሲያገኝ ወደኳታር መሄድ የሚያስችለውን የቪዛ ፕሮሰስ በህጋዊ መንገድ ጀመረ። ጉዞው ተሳካና ኳታር የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ስር የእቃ ማንሻ ክሬን ተሽከርካሪ ረዳት ሆኖ ለመስራት ተቀጠረ ። ይሁንና የጠበቀውን ያክል ክፍያ አላገኘም።ኑሮውንም በአጭር ጊዜ ለመለወጥ የነበረው ሀሳብ አልተሳካም ።
ይባሱንም የሚያገኘው ገቢና እና የሚያወጣው ገንዘብ ተቀራራቢ ሆነበት። ኑሮው ከእጅ ወደ አፍ ከመሆን አልዘለለም። ሆኖም ለአንድ ዓመት ያክል ከሰራ በኋላ ለእረፍት ወደ አዲስ አበባ ሲመጣ ከአሁኗ ባለቤቱ ወይዘሮ ሂሩት በትሩ ጋር በአጋጣሚ ተዋወቁ። ጓደኝነታቸውም እየጠነከረ ሄዶ አብረው ስለመኖር ማሰብ ጀምረው እንደነበር ጥንዶቹ ያስታውሳሉ። ይሁንና አቶ ማየት የእረፍት ቆይታውን አጠናቆ ወደኳታር ተመለሰ።
ባህር ተሻግሮ ቢሄድም ግን በስልክ እየተደዋወሉ ስለፍቅራቸው እናጤንነታቸው ማውጋታቸውን አላስታጎሉም። አቶ ማየትም በኳታር ከኮንስትራክሽን ሥራው በተጨማሪ በድብቅም የወንዶች ጸጉር ሥራ እያከናወነ ተጨማሪ ገንዘብ በማግኘት ጥቂት እራሱን ለመደጎም ሞከረ።
በኋላም በአጠቃላይ ከሁለት ዓመት ከሰባት ወር ከቆየባት ኳታር በቃኝ ብሎ አዲስ አበባ ሲመጣ ቤት ተከራይቶ መኖር ጀመረ። በዚህ ወቅት ከወይዘሮ ህይወት ጋር አብረው መኖር እንዳለባቸው ቢወያዩም አልወሰኑም ነበርና ኑሯቸውን ለየግል ቀጠሉ። ወይዘሮ ህይወት አልባሶ እና ቁጥርጥር የተባሉ እንዲሁም በርካታ የሴቶች የጸጉር ሥራዎች ሙያ ባለቤት ነችና አብዛኛዋን ጊዜ የምታሳልፈው ተቀጥራ በምትሰራበት የሴቶች የውበት ሳሎን ነው።
በተለይ ሐሙስ ቀን በሚውለው የእረፍት ቀኗ በአካል እየተገናኙ የሆድ የሆዳቸውን ማውጋታቸው አልቀረም። ከዚያ መልስ በስልክ እና በኢንተርኔት አማራጮች ነበር የሚገናኙት። የብቻ ኑሯቸውን ማሸነፍ እንዳለባቸው የወሰነው አቶ ማየት 64 ካሬ የሆነ ሰፊ የኮንዶሚኒየም ቤት በሶስት ሺህ ብር ከተከራየ በኋላ ያለችውን አልጋ እና ጥቂት እቃዎች አስገብቶ ወይዘሮ ህይወትን አብረው እንዲኖሩ ጥሪ አቀረበላት። ወይዘሮ ህይወት ከስድስት ዓመታት በፊት በአንድ ጎጆ ስር የሚሆኑበትን እድል ወደ ዕውነታነት እንዲቀየር እሺታዋን ሰጠች።
ጥንዶቹ በወቅቱ የቤቱ ስፋት እና የቤት እቃቸው ካለመመጣጠኑ የተነሳ እንዱን መቀመጫ ከሌላኛው መቀመጫ ጋር በሁለት እና ሶስት ሜትር ጭምር አራርቀው የሚያስቀምጡበት እንደነበር አይዘነጉትም። ከእለት እለት ግን ያ ሰፊው ቤታቸው የኪራይ ዋጋው እየናረ ሲመጣ ምንም እንኳን የቤት እቃዎቻቸውን እያሟሉ ጓዛቸውን እያበዙ ቢመጡም አነስ ያለ ቤት እየፈለጉ መቀያየራቸው አልቀረም።
በመኖሪያ ቤት ኪራይ ውድነት የተነሳ ሶስት እና አራት ቤቶችን እያቀያየሩ አሁን ላይ አራት በአራት የሆነች ጎጆ ውስጥ አርፈዋል። ያኔ ከስድስት ዓመታት በፊት እቃቸው አንሶ ቤቱ እንዳልሰፋቸው በዚያው የኪራይ ክፍያ አሁን ላይ ደግሞ እቃቸው በዝቶ ቤቷ ጠባቸው ኑሯቸውን እየገፉ ይገኛል።
በጠባቧ እና ዘርፈ ብዙ ግልጋሎት ባላት ጎጇቸው ቦታ ያጣውን እቃቸውን በኬሻ አሳስረው አንድ ጥግ አስይዘው በፍቅር እየኖሩ በመሆናቸው ደስተኛ ናቸው። ወይዘሮ ህይወት ከምትሰራበት የጸጉር ቤት በሚኖራት የእረፍት ቀን ሙያዋን በሚፈልጉት ሴቶች ቤት እየሄደች የተለያዩ ቁንዳላ አይነቶችን እየሰራች ታሰማምራቸዋል።
በምላሹም ለኑሯቸው መደጎሚያ የሚሆን ገቢ ታገኛለች። በእረፍት ጊዜዋ ደግሞ የበይነመረብ አማራጮችን በመጠቀም አዳዲስ የጸጉር ሥራ ዲዛይኖችን ልምድ መቅሰሙን አታስታጉልም።
አቶ ማየት በበኩሉ ቀን ሴራሚክስ፣ ጂብሰም እና የተለያዩ የእንጨት ሥራዎችን እየከወነ ሌሊት ላይ ደግሞ አትክልት ተራ አካባቢ እየሄደ ከአከፋፋዮች ላይ የሚገዛቸውን ምርቶች በጉሊት መልክ አስቀምጦ በመነገድ ማልደው ለሚመጡ ደንበኞች ያቀርባል።
አሁን እንኳን የአትክልት ተራው ጉሊት ሥራ ቢቀርም ቀድሞ ግን በሚሰራበት ጊዜ ከደንብ አስከባሪዎች እና ከሌቦች ጋር የነበረው ድብብቆሽ እና በአይነቁራኛ የመተያየት ሁኔታ ከባድ እንደነበር ያስታውሳል። በኋላ ላይ ሥራአጥ መሆኑን አስመስክሮ ከቀበሌ አንዲት ተለጣፊ የኮንቴይነር ሱቅ ፒያሳ ካቴድራል አካባቢ ተሰጠው።
በሱቋ የተለያዩ ምግቦችን እያቀረበ ደንበኞቹን ያስተናግድባታል። በተለይ ከኮሮና በፊት ከንጋት 12 ሰዓት ጀምሮ እራሱ ምግብ እያበሰለ እና እያስተናገደ በርካታ ደንበኞችን ይሸኛል። አሁን ላይ ምንም እንኳን በኮሮና በሽታ ምክንያት የምግብ ሥራው ገበያ ቢቀዛቀዝም ለጎጇቸው የሚሆን መጠነኛ ገቢ ግን አላጣም።
የእኔ የእሷ የሚሉት ገንዘብ ሳይኖራቸው በየፊናቸው እየሰሩ በጋራ እያዋጡ በሚኖሩባት ቤታቸው ህይወትን እያጣጣሟት ይገኛሉ። የጎጆ ችግራቸውን ለመቅረፍ በየፊናቸው ሲውተረተሩ ውለው ወደቤት ሲመለሱ እርሷ ቀድማ ከገባች ምግብ ታበስላለች ፤ባለቤቷ ቀድሞ ከገባ ደግሞ ተራው የእርሱ ይሆናል። እንዲህ እንዲያ እያሉ እርስ በእርስ እየተደጋገፉ የሚኖሩት ጥንዶች የዛሬው የጎጆ መጥበብና የግላቸው መኖሪያ አለመኖር
ቢያሳስባቸውም ነገ ግን የግላቸውን ጎጆ ቀልሰው በደስታ ህይወታቸውን እንደሚመሩ ያስባሉ። ይሄንኑ ሀሳበ በአእምሯቸውና በእቅዶቻቸው ሰንቀው ነው ኑሮን በትጋት በፍቅር እየተወጡ ያሉት። ቸር እን ሰንብት!!
አዲስ ዘመን ጥር 22/2013