(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
ቁጥሮች እንዴት ቀለሉብን!?
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ መደበኛዎቹ የሀገር ውስጥ ሚዲያዎቻችን እያቀበሉን ያሉት በቁጥር የታጀቡ አስፈሪና አስደንጋጭ ዜናዎችንና መረጃዎችን ስለመሆኑ ይጠፋናል ብዬ አልገምትም፡፡ ማህበራዊ ሚዲያዎችም ቁጥሮቹን በመቶ፣ በሺህ፣ ካሻም በሚሊዮን እያጋነኑ ናላችንን በማዞር ግራ እንዳጋቡን ነግቶ መምሸቱ እውነት ነው፡፡ ጥቂትም ቢሆን እረፍት የምናገኘው መባነኑ ቢበረታብንም እንቅልፍ በሚሉት ተፈጥሯዊ ፀጋ ስንረታ ብቻ ነው፡፡
በፈረጠሙ ቁጥሮች የታጀቡት ዜናዎች የተገነቡ መንገዶችን ኪሎ ሜትሮች ወይንም ከልማት ስኬታችን ጋር የተያያዙ መሠረተ ልማቶችን ብቻ የሚተርኩ ቢሆኑ ኖሮ ባልጠላን ነበር፡፡ በማን እድል፡፡ ለክፋቱ ቁጥሮቹ ገዝፈው የሚገልጹልን የሀገራዊ መከራችንንና አሳራችንን ለማሳየት መሆኑ ላይ ነው፡፡ አዚማሞቹ ቁጥሮች አንዳንዴ ኡ!ኡ! አሰኝተው በማስጮኽ መንፈሳችንን ሊያውኩ እንደሚችሉ መረዳቱ አይከብድም፡፡
የዕለት ኑሯችን ውድነት ማሻቀብ በቁጥሮች እየተሰላ እንደ ቅሪላ ሲያጦዘን ችለናል፡፡ ቁጥራቸው እንደ “ጅብ ጥላ የተፈለፈለ” የፖለቲካ ቡድኖች ግራ እያጋቡ ሲያንቀረቅቡንም የነገውን ምፅዓተ “ዴሞክራሲ” እየናፈቅን በትዕግስት እንጠብቃለን፡፡ ኢኮኖሚው ሲያዳሽቀን “ግዴለም የችግራችን ዕድሜው አጭር ነው” የሚለውን የመሪዎቻችንን ሚሊዮን ተስፋዎች እያመንን እንጽናናለን፡፡
ባታካች ቁጥር የሚገለጸውን የኮረና “የጅራፍ” ግርፋት ታግሰንም ቢሆን ላለመንፈራገጥ እየተጋን “በቆይ ብቻ” መጽናናት የህመምተኞችንና የሟቾችን ሪፖርቶች ለማዳመጥ አልታከተንም፡፡ ተፈጥሮ በጎርፍና በአንበጣ ቁጣ ስትዘምትብንም ለምህረት ልመና ከልደታ እስከ ባለእግዚሃር በየቤተ እምነታችን ደጀ ሰላም ውለን እያደርን ከፈጣሪ ጋር ለመሟገቱ አልሰነፍንም፡፡
እብሪተኞችና ጨካኞች በነፍሳችን ተወራርደው ቁጥሩን መገመት እስኪያዳግት ድረስ እስትንፋሳችንን ሲነጥቁንና ከኖርንበት ቀዬ ሲያፈናቅሉን ኀዘናችን ቢበረታም “የኢትዮጵያዊ ጨዋነት ባህሉ” ስለሚበረታብን ከመበቃቀል ተጠብቀን በእርቅና ተሃድሶ እንደገና አብሮ ለመኖር እንጨክናለን፡፡ ስንቱን አሳር ችለናል ጎበዝ! ቢሆንስ እስከ መቼ መከራችንን እንኮኮ እንደተሸከምን እንዘልቀዋለን? ይህም አነሰ ተብሎ በሹማምንቱና በሚዲያ የቁጥር ወረራ ነጋ ጠባ መጠቃታችንን ሪፖርት አድራጊዎቹ አልተረዱት ይሆን?
የሀገራዊው ችግራችን አስኳል ምን ቢሆን ነው ችግር እየተቀፈቀፈ መከራችን ሊበዛ የቻለው? ምነው የቁጥሮች ዱላ በረታብን? ለደስታ ማብሰሪያ ሳይሆን ለኀዘን መግለጫነት፣ ለልማት ሳይሆን ለጥፋት ማስታወቂያነት እኮ ምነው መጠን በሌለው የቁጥር ናዳ መወገራችን? በግልጽነት ተወያይተን፣ በቅንነት ተነጋግረን እርስ በርስ ለመደማመጥና ቋንቋ ለቋንቋ ለመግባባት እስካልቻልን ድረስ እየዳከርንባቸው ካሉት የችግር አረንቋዎቻችን ማጥ ውስጥ በቀላሉ ለመውጣት የሚያዳግት ይመስለኛል። መምሰል ብቻም ሳይሆን በርግጥኝነት ሥር ነቀል መፍትሔው ይሄው ብቻ ይመስለኛል፡፡
በዘመናችን ዐውድ በቁጥሮች ስሌት የምንገልጻቸውን ዘርፈ ብዙ ሀገራዊ ችግሮች ቀንሰን የመጪውን ትውልድ ጎዳና በተሻሉ መገለጫዎች እስካልደለደልንላቸው ድረስ በወራሾቻችን አንደበት ብቻም ሳይሆን በታሪክ ገጾች ጭምር መናቅና ጥዩፍነት እንደሚገጥመን መጠርጠሩ አይከፋም፡፡ ሰሞኑን በተከታታይ የምናደምጣቸውን በአሃዞች የታጀቡ ሀገራዊ ረፖርቶችን ጥቂቶቹን ብቻ በማስታወስ የችግራችን ግዝፈት ምን ያህል ያበጥ እንደሆነ ለመገንዘብ እንሞክራለን፡፡
አንድ፤
“የፍትሕ ፍላጎት እና የመሟላታቸው ሁኔታ በሚል ርዕስ እና በኢትዮጵያ የወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ላይ በተዘጋጁ ጥናታዊ ሰነዶች ዙሪያ ውይይት ለማድረግ” እንደ መጫኛ በተዘረጋው በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የዐውደ ጥናት መድረክ ተዘጋጅቶ እንደነበር ዜናው የተገለጸልን የእለቱ እለት ጥር 16 ቀን 2013 ዓ.ም ከሸራተን አዲስ በቀጥታ በተላለፈ የብዙኃን መገናኛዎች ሪፖርት ነበር፡፡
ከሪፖርቱ የሰማሁት በቁጥር የታጀበው መግለጫ በግሌ አስደንግጦ እጄን በአፌ ላይ መጫኔ አልቀረም። ወዴት እየገሰገስን ነው በሚል ፍርሃት ጭምር፡፡ በዜናውና በኃላፊዎች አንደበት የተነገረን መርዶ ይዘት የሚከተለውን ይመስል ነበር፡፡ “በስድስት ክልሎች ትኩረት አድርጎና ከ5400 በላይ ግለሰቦችን አሳትፎ ጥናት የተደረገበት ጉዳይ” በሚል መንደርደሪያ የቀረበው ሪፖርት የተገለጸው በሚከተሉት የቁጥሮች ውጤት ነበር። በአንድ ዓመት ውስጥ 7.4 ሚሊዮን ጉዳዮች ፍርድ ቤት ይቀርባሉ፡፡
ከአነዚህ ጉዳዮች መካከል ውሳኔ የሚያገኙት 2.2 ሚሊዮኖቹ ወይንም 40 ከመቶዎቹ ብቻ ናቸው። 5.2 ሚሊዮኖቹ ጉዳዮች የፍርድ ቤቶችን እንዳጣበቡ ሌሎች ጉዳዮች “ይደረትባቸዋል፡፡” ከሙያው ውጪ እንዳለ አንድ ዜጋ ይህ ቁጥር በእጅጉ የሚያሳስብ እንጂ በቁጥሮች ስለተገለጸ ብቻ “እህ ነው እንዴ!?” አሰኝቶ ብቻ በአግራሞት የሚታለፍ አይደለም፡፡
ሪፖርቱን በቀላል የሂሳብ ስሌት እንተንትነው፡፡ ከ7.4 ሚሊዮን የፍርድ ቤት ጉዳዮች ጋር የሚገናኘው ምን ያህል ህዝብና የከሳሽና ተከሳሽ ቁጥሩ ብዛት ምን ያህል ሚሊዮን ሊሆን እንደሚችል ቤቱ ይቁጠረው፡፡ ምን ያህሉስ ምስክር ለእነዚህ ፋይሎች ፍርድ ቤት እንዲውል ይገደዳል? ህግን የማስከበሩ ሃላፊነት በጫንቃቸው ላይ የወደቀው ዳኞችና ድጋፍ ሰጪ ባለሙያዎች፣ የጸጥታ ሠራተኞች፣ የፍርድ ሂደቶቹን ለመከታተል የፍትሕ ተቋማቱን የሚያጣብቡ የከሳሽና የተከሳሽ ቤተሰቦችና ወዳጆችን ቁጥር በምን ያህል ሚሊዮን ልናሰላው እንችላለን? በአጭሩ ቢያንስ በዐሠርት ሚሊዮኖች፤ ደፈር ካልንም የህዝባችንን ቁጥር ሩብና ግማሽ ያህል ዜጎች በየቀኑ ውሏቸው ፍርድ ቤት ሳይሆን ይቀራልን? ግምት ነው፡፡ አሳማኝ ማስተባበያ የሚቀርብ ከሆነ ለመማር ዝግጁ ነኝ፡፡
ከሪፖርቱ ጋር የተያያዘውና የገዘፈው ችግር የተገለጸው “ፋይሎቹ ከመሬትና ከቤተሰብ ጋር የተያያዙ” መሆናቸው ነው፡፡ ለመሆኑ የአንድ አማካይ የኢትዮጵያ ቤተሰብ ቁጥር ምን ያህል ነው? ግምታዊ ቁጥሮችን ከፋይሎቹ ጋር በማስላት ምን ያህል ዜጋ “የፍትህ ያለህ!” የሚል ጩኸት ላይ እንዳለ ለመገንዘብ አያዳግትም፡፡ በሀገሪቱ ምክትል አቃቤ ሕግ የፍትሕ ሥርዓቱ አካሄድ “ቀርፋፋ፣ አድሏዊና ዘለቄታዊ መፍትሔ የማይሰጥ” ተብሎ የተገለጸውን ድምዳሜ መስማት እንደምን ስሜትንና ተስፋን እንደሚያጨፈግግ ለመገመት አይከብድም፡፡
ለመሆኑ የሀገራችን “እመቤት ሆይ ፍትህ” (Lady Justice) ዓይኗን በእራፊ ጨርቅ እንደሸፈነች፣ እኛም ዜጎች ፈጣንና አርኪ ፍትሕ እንደተጠማን “በቀርፋፋው” የፍትሕ ሥርዓት እንዳለቀስንና እንደተንተከተክን እድሜያችንንና ዘመናችንን የምንገፋው እስከ መቼ ይሆን? ይህ የቁጥር ሪፖርት እንደ ሀገር መከንከን ብቻም ሳይሆን ቁርጠኝነትን የሚጠይቅ እርምጃ መወሰድ የሚገባበት የሀገራዊ አሳራችን አንዱ ገጽታ ነው፡፡
ጉዳዩን በአጭሩ ለመጠቅለል ያህል ሳይገለጡ የቀሩት የፍርድ ቤት ፋይሎች ብቻ አይመስሉኝም፡፡ በእያንዳንዱ ዜጋ ልብ ውስጥ እጅጉን የታመቁና ምላሽ የሚጠይቁ ሚሊዮን ፋይሎችም ስለሚኖሩ “የሀገሪቱን አቅም ያህል” ትጋት ካልታየ በስተቀር ዜጎች የተረጋጋ ሕይወት ይመራሉ ብሎ መጠበቅ አዳጋች መሆኑ አይቀርም፡፡ ከላይ የጠቀስኩት ጉባዔ የተሰበሰበው ለመፍትሔ ፍለጋ ቢሆን ደግ በሆነ ነበር፡፡
ከመድረኩ ጀርባ ግድግዳ ላይ የተሰቀለው ባነር እንዳረጋገጠው ጉባዔው የተጠራው “ለውይይት” ብቻ መሆኑ ትንሽም ቢሆን ተስፋን ማቅጠኑ አይቀርም፡፡ ለውይይት ለውይይትማ ሀገራዊ ተቋሞቻችን በባለ ኮከብ ሆቴሎች የሚያዘጋጇቸውን አሰልቺ ውይይቶች መች አነሱን?
ሁለት፤
“በመተከል ዞን ከ 15 ሺህ በላይ የጉሙዝ ማህበረሰብ ተወላጆች ችግሩን ሸሽተው ከገቡበት ጫካ ወጥተው ወደ መኖሪያቸው ተመለሱ፡፡ በዳንጉር ወረዳ ብቻ ከሰባት ቀበሌዎች 8 ሺህ የጉሙዝ ተወላጆች ወደ ቀዬአቸው ተመልሰዋል፡፡” የሚለው የጥር 16 ቀን 2013 ዓ.ም የፕሬስ ድርጅት ዜናም መንፈስን ማወኩ አሌ አይባልም፡፡ ከአንድ ዞን ይህንን ያህል ቁጥር ያለው ሕዝብ ጫካ የሸሸው ለምን ነበር? ቁጥሩ ያልተገለጠውና በየጊዜው የምንሰማቸው የሌሎች ብሔረሰቦች ተፈናቃዮች ቁጥርስ ድምሩ ምን ያህል ይሆናል? ጫካ ከርመው የተመለሱት ዜጎች ለመሆኑ ምን ሲመክሩ ሰነበቱ? ከተመለሱስ በኋላ ምን ሊያደርጉ አሰቡ? በዚሁ መፈናቀልና ሽሽት ምክንያትስ የምን ያህሉ ዜጋችን ደም “ደመ ከልብ” ሆኖ “በምድራዊ መዝገባችንና በፈጣሪ ፋይል ውስጥ” ተመዘገበ? እነዚህን ጥያቄዎች ከቁጥሮቹ ጋር እያመሳከርን ስናስተያይ የመከራችን ክብደት ምን ያህል የገዘፈ እንደሆነ ጥሩ ማሳያ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
ሦስት፤
ክብርት የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ጥር 18 ቀን 2013 ዓ.ም በቁጥር የደለበ የመሬትና የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ወረራ አስመልክቶ ሪፖርት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ የሪፖርቱን ዝርዝር ደግሜ አልከልስም፡፡ ምክንያቱም ሪፖርቱ ከተለቀቀ ጊዜ ጀምሮ የሀገሬ ህዝብ እንዴት ቁጭትና ትካዜ እንደወረረው በራሳችን ስሜት መዝነን ፍርዱን ልንሰጥ እንችላለን፡፡ ለማናኛውም 322 ባለቤት አልባ ቤቶችና ህንጻዎች በአፍሪካ መዲና በአዲስ አበባችን ተገንብቶ መገኘቱ “የአድባሬ ተረት ያህል” ካልሆነ በስተቀር በውን ስለመፈጸሙ ግርምት ላይ ይጥላል፡፡ 1338 ሄክታር የሚገመተው የተዘረፈውና የተወረረው መሬት በካሬ ሜትር ሲመነዘር 13 ሚሊዮን 338 ሺህ ገደማ ማለት እንደሆነ በሪፖርቱ ውስጥ ቁልጭ ብሎ ተገልጿል፡፡
“የመኖሪያ ቤት ያለህ!?” እያለ ቀን ከሌት ፈጣሪውን በጸሎት፤ መንግሥትን በመማጠን ለሚያለቅሰው የከተማችን ነዋሪ ቢያንስ አንገቱን ብቻ የሚያስገባበትን ጎጆ እንዲቀልስበት ተሸንሽኖ ቢከፋፈለው ኖሮ ምን ያህል ሺህ ዜጎች ከተማዋን በዕልልታ እንደሚያናውጡ ማሰቡ ምናባዊ አያሰኝም፡፡ እንደ ቀዳማዊት የሀገራችን ሳተላይት ወደ ሰማየ ሰማያት በመጠቀው የመሬት ዋጋ በጨረታ አሽሞንሙን ለአልሚዎች እናስተላልፍ ከተባለም የሚገኘው ሀብት ያለምንም ጥርጥር የሀገሪቱን ኢኮኖሚ አስፈንጥሮ ወደ ላይ እንደሚያጎን አይታበልም፡፡
21 ሺህ 695 የጋራ መኖሪያ ቤቶች በሕገ ወጥ መንገድ የመያዛቸው መርዶም “ኡኡታ!” ሲያንስበት ነው፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት ዕጣ ወጥቶለት በተስፋና በምሬት፣ በጾምና በጸሎት ፈጣሪንም መንግሥትንም ፋታ የነሳው አዲስ አቤቤ ይህ መርዶ ጆሮው በደረሰ ምሽት ሌሊቱን የሰላም እንቅልፍ ተኝቶ ያድራል ማለት ዘበት ነው፡፡
ብቻም ሳይሆን ለደም ብዛትና ለስኳር ህመም ጭምር መዳረጉ አይቀሬ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ሆስፒታሎቻችን የተቀበሏቸውን አዳዲስ ህሙማን ቁጥር ቢያሳውቁን አይከፋም፡፡ “የጉድ ሀገር ገንፎ እያደር ይፋጃል” ይሏል ይሄን ጊዜ ነው፡፡
አራት፤
ታኅሣሥ 5 ቀን 2013 ዓ.ም ከጆሯችን የደረሰው ዜናም ከአጀብም አልፎ ግራ አጋብቶናል፡፡ በዘርፉ ሚኒስትር የተገለጸው ዜና ይዘት በሚከተሉት ቁጥሮች ታጭቆ የቀረበ ነበር፡፡ “ባለፉት አምስት ወራቶች ህግን ባላከበሩ የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ መወሰዱን የንግድ ሚኒስትሩ አስታወቁ፡፡” ይልና፤ ውጤቱ በቁጥሮች አሸንዳ አማካይነት እንደሚከተለው ይጎርፋል፡፡ 812 የንግድ ፈቃዳቸው እንደተሰረዘ፡፡
58 ሺህ 423 የንግድ ድርጅቶች ላይ ማስጠንቀቂያ መጻፉ፡፡ 40 ሺህ 823 ተቋማት ላይ ክስ መከፈቱ፡፡ በ90 ተቋማት ላይ ደግሞ የእገዳ እርምጃ መወሰዱ በሚኒስትሩ አንደበት ይፋ ሆኗል፡፡ መቼም ህግ አይከበር ብሎ መከራከር ህጉን ራሱ መዳፈር ይሆናል። ቢሆንም ግን የኮቪዱ፣ የሀገራዊው ወቅታዊ ሁኔታ ተጋግሎ ዜጎች በዚያም ሆነ በዚህ መንፈሳቸውም ሆነ ሥጋቸው እየቃተተ ባለበት ክፉ ጊዜ ይህንን ሪፖርት ለሕዝብ ተሽቀዳድሞ መግለጹ ፋይዳው ምንድን ነው? ያስተምራል? ያንጻል? ወደ ህጋዊነት ለመመለስስ ያበረታታል? በእነዚህ የንግድ ድርጅቶች ምክንያት የዕለት እንጀራቸውን ተስፋ የሚያደርጉትን ሺህ ምንተ ሺህ የጉዳተኛ ቤተሰብ አባላት “እልል!” ያሰኛል?
የሪፖርቱ በዚህ ወቅት መገለጥስ አስፈላጊነቱ ምኑ ላይ ነው፡፡ የጎንዮሽ ጉዳቱ ተፈትሾ በይደር ሊታለፍ አይችልም ነበር? እንደ ባለጠጋዎቹ ሀገራት “የኮቪድ ማገገሚያ” ዳረጎት ባይገባን እንኳን በሪፖርት ጋጋታ የንግድ ተቋማትን ብቻም ሳይሆን የዜጎችን የመኖር ተስፋ ማጨለሙ ፋይዳው ምኑ ላይ ነው? “መንግሥት ይህንን ያህል የንግድ ድርጅቶች ጨክኖ የሚዘጋ ከሆነ እኔም ስለማይቀርልኝ ወዘተ.” የሚል ትምህርት እንዲሰጥ ታስቦ ወይንስ ምን ትርጉም ይሰጣል? እንዲያው ለነገሩ ከከፍተኛ እስከ ዝቅተኛ ደረጃ ያሉት የንግድ ተቋማት በኮቪድና በሀገራዊ ችግሮች ተጽእኖ እየተዘጉ ገቢዎች ሚኒስቴር በፈቃድ መላሾች እየተጥለቀለቀ እንደሆነ ክቡር ሚኒስትሩ ሪፖርቱ አልደረሳቸው ይሆን? ይህ ጸሐፊ በኮቪድ ተጽእኖ ምክንያት የንግድ ድርጅቱን ከዘጉት መካከል አንዱና “የታክስ አምባሳደር የሚል” ሥራ ላይ የማይውል አደራ የተቀበለ ዜጋ ስለሆነ በቂ መረጃ እንዳለው መግለጹ አስፈላጊ ይመስለኛል።
እንግዲያውስ መልከ ብዙ ሀገራዊ ችግሮቻችን የሚደበድቡን አንሶ በኃላፊዎችና በተቋማት አማካይነት በቁጥሮች ሪፖርት መቀጥቀጡ ሌላ በደልና የሞራል ጥያቄም ስለሚያስነሳ “ሠርተናል” ለማለት ብቻ በተስፋችን ላይ ጭጋግ የሚነሰንሱ ሪፖርቶች ከመቅረባቸው በፊት ችግሮቹ እንዳይከሰቱ ምን ማድረግ ነበረብኝ? ምንስ ባለማድረጌ ይሄ ሁሉ ችግር ሊከሰት ቻለ ብሎ መጠየቁ ብልህነት ብቻም ሳይሆን የአመራር ብቃትንም የሚፈትን ጥበብ ጭምር ነው።
ይልቁንስ በልማት ሪፖርቶች ላይ መጠንከሩ ይበልጥ የተሻለ ሊሆን ይችላልና ሹመኞቻችን ሆይ ልክ እንደ ስኬት ድል ቆጥራችሁ ማስተዋል በጎደለው የሪፖርት አቀራረብ እባካችሁ ልባችንን አታፍስሱ፣ ተስፋችንንም በቁጥሮች ጅራፍ እየገረፋችሁ ለምሬት አትዳርጉን፡፡ ጥበብ ይስጥልን! ሰላም ይሁንልን!
አዲስ ዘመን ጥር 22/2013