ውብሸት ሰንደቁ
የኅብረተሰቡን የፋይናንስ አገልግሎቶች ጥያቄ ለመመለስ የፋይናንስ ተቋማት ከፍተኛ ሚና አላቸው ። እነዚህ ተቋማት በቀጥታ ከሚሠሩት የብድር፣ የቁጠባ እና የፈንድ ፋይናንስ አገልግሎት ጎን ለጎን የኢንሹራንስ አገልግሎቶችንም በመስጠት ይታወቃሉ ።ከዚህ ውስጥ አንዱ ተጠቃሽ የኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ አክሲዮን ማህበር ነው ።
ተቋሙ እ.ኤ.አ ነሐሴ 4 ቀን 1997 የተቋቋመ ሲሆን በጅምሩ ጥቂት ቅርንጫፎችን በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች ከፍቶ የማይክሮ ፋይናንስ አገልግሎት በመስጠት ሥራ ጀመረ፡፡
ስለተቋሙ አጠቃላያዊ ሁኔታና እየሰጠ ስላለው አርሶ አደሩ ላይ ያተኮረ የኢንሹራንስ አገልግሎት የማህበሩን ማርኬቲንግና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኦሊ ተፈሪን አነጋግረናል ።አቶ ኦሊ ተቋሙ እንዲመሰረት አስፈላጊ ከሆነበት ምክንያት ሲነሱ የባንክ አገልግሎት በሀገሪቱ ያለው በብዛት በከተሞች ላይ በመሆኑ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርግ የፋይናንስ አገልግሎት መመስረት መሆኑን ይገልጻሉ።
በዚህም በሀገር ደረጃ የማይክሮ ፋይናንስ ፖሊሲ ተቀርፆ በባንክ አገልግሎት ያልታቀፉ አርሶ አደሮችን የቁጠባ ባህላቸውን እንዲያሳድጉ እንዲሁም ብድር በማግኘት ምርትና ምርታማነታቸውን እንዲያጎለብቱ መንገዶችን ለማመቻቸት መቃቋሙን አብራርተዋል፡፡
የኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ አክሲዮን ማህበር በዋናነት በኦሮሚያ ክልልና በሌሎች በክልሉ በሚገኙ የልማት ድርጅቶች ጋር እንዲሠራ የተቋቋመ ድርጅት ነው ።ከጊዜ ወደ ጊዜ ተቋሙ ተደራሽነቱን ለማስፋት በሠራቸው ሥራዎች በክልሉ ባሉ ወረዳዎች ጠቅላላ ሊባል በሚችል ደረጃ የደረሰ ሲሆን የቅርንጫፎቹን ቁጥርም 394 ማድረስ ችሏል ።
ሥራውን ሲጀምር የነበረው የቁጠባ መጠን አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊየን ብር ብቻ ነበር የሚሉት ዳይሬክተሩ በብድር አቅርቦት ደረጃም ከዘጠኝ ሚሊየን ብር በታች አቅርቦ በማበደር ነው የጀመረው። አሁን የብድር አቅርቦቱን ወደ 10 ቢሊየን ብር ማሳደጉን ይጠቅሳሉ ።
ዳይሬክተሩ እንደሚሉት የኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ አክሲዮን ማህበር ሲጀመር የአካባቢ አርሶአደር ማዳበሪያና ምርጥ ዘር እንዲገዛ እና ማምረት እንዲችል የብድር አገልግሎት መስጠት ላይ ያተኩር ነበር። በአሁኑ ጊዜ ግን በከተሞች የኢኮኖሚ ማነቆዎች በሆኑ ጉዳዮች ላይ እና በወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ የራሱን አሻራ እያስቀመጠ ይገኛል ።በዚህም በከተማና በገጠር የሚገኙ ሥራ አጦች ላይ በተለይም ከዩኒቨርሲቲዎች ተመርቀው ሥራ ላልተቀጠሩና መሥራት እየቻሉ በገንዘብ እጥረት መሥራት ያልቻሉትን በማደራጀትና የብድር አገልግሎት በማመቻቸት እየሠራ ነው ።
ማህበሩ የኢንሹራንስ አገልግሎቶችንም ለአርሶ አደሩ ማህበረሰብ በማቅረብ ላይ ይገኛል ብለዋል አቶ ኦሊ ።በኢንሹራንሱ ዙሪያ በተለይ ሁለት የህይወት የኢንሹራንስ
ዓይነቶች ለአርሶ አደሮች እያቀረበ ሲሆን አንደኛው ተበዳሪ በሚሞትበት ጊዜ ተቋሙ ለልማት ብሎ የሰጠው ብድር ቀሪው ቤተሰብ ላይ የዕዳ ጫና እንዳይፈጠር የሚያደርግ የኢንሹራንስ ዓይነት ነው ።ይህ የኢንሹራንስ ዓይነት አርሶ አደሩ በሚገዛው የህይወት መድህን አማካኝነት በተለያዩ አጋጣሚዎች ብድሩን ሳያጠናቅቅ ህይወቱ ካለፈ ዕዳው ከነወለዱ የሚሰረዝበት የዋስትና ዓይነት ነው ።
በተቋሙ ያለው ሁለተኛ አማራጭ የህይወት ዋስትና ደግሞ ተበዳሪ ወይም የተበዳሪ የቅርብ የሕይወት አጋር ብድሩ ሳይጠናቀቅ በሞት በሚለይበት ጊዜ ዕዳውና ወለዱ እንዲሠረዝ ለማድረግ የሚገባ የሕይወት ዋስትና ነው። አርሶ አደሮች የብድር አገልግሎት በሚጠይቁበት ጊዜ ከነዚህ ዋስትናዎች ውስጥ ከሁለት አንዱን መርጠው እንዲጠቀሙ በማድረግ ዋስትና እንዲያገኙ ይደረጋል ።
በ2012 ዓ.ም የተቋሙ ኢንሹራንስ አገልግሎት ደንበኞች አርሶ አደር ብዛት 629 ሺህ896 ሲሆኑ ከነዚህ መካከል 1ሺህ 698 ደንበኞች በሞት በመለየታቸው 14ሚሊየን 371ሺህ 331 ብር እዳቸው ተሰርዞላቸዋል። የብድር አቅርቦትን በሚመለከት በ2012 ዓ.ም 11 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ብድር ለተበዳሪዎች የተሰጠ ሲሆን 8ነጥብ 23 ቢሊዮን ብር በቁጠባ ተሰብስቧል፡፡
ገጠሩ ክፍል ላይ ሌሎች የዋስትና አገልግሎቶች ስለማይገቡ የምንሰጠውን የብድር አገልግሎት ከዚህ ጋር በማያያዝ ለአርሶ አደሩ ሕይወት ዋስትና እየሰጠን እንገኛለን ያሉት ዳይሬክተሩ የኢንሹራንስ አገልግሎቱን ለማስፋት ከዚህ እልፍ ያለ ሙከራ እንደነበርም አብራርተዋል።
ከተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት ጋር በመተባበር በአገልግሎቶች ውስጥ ተካትተው ሊሰጡ የታሰቡት የሰብል ዋስትና እና የቤት እንስሳት ዋስትና የመሳሰሉት የመድህን አገልግሎቶች ተሞክረው በተለያዩ ምክንያቶች ባለመሳካታቸው ወደሥራ አለመግባታቸውን አቶ ኦሊ ይናገራሉ፡፡
ማህበሩ የፋይናንስ ተቋም እንደመሆኑ በኢንሹራንሱ ዘርፍ የሚሠሩ ተግባራትንም አጠናክሮ ይቀጥላል። ተጨማሪ የኢንሹራንስ አገልግሎቶችን በማጥናት አገልግሎቱን እያሰፋ እንደሚሄድ ተገልጧል ።የኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ አክሲዮን ማህበር የማርኬቲንግና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኦሊ በፋይናንስ ተቋማት ላይ አደጋ ይደቅናል ያሉትን ችግርም ሳያነሱ አላለፉም ።
ስለአስተዋሏቸው ችግሮችም እንደዚህ ብለዋል፤ በተለይ በአሁኑ ጊዜ የብድር አመላለስ ላይ ችግር ይታያል ።ብድር የሚወስዱ ዜጎች ብድር ወስደው ከተጠቀሙ በኋላ በኃላፊነት መመለስ ካልቻሉ የሚቀጥለው ትውልድ ላይ ነው ጫናው የሚያርፈው ።
ብድር የወሰዱ ዜጎች ብድሩን ወስደው ከተጠቀሙ በኋላ በአግባቡ መመለስ ካልቻሉ የአበዳሪ ተቋማት ብሎም የሀገር ኢኮኖሚ ይጎዳል ።ብድር ተቀብሎ በመመለስ ረገድ በተለይ ወጣቱ ትውልድ ላይ የጎላ ችግር ይታያል ።
ይህ ደግሞ ሌሎች ወጣቶች እንዳይጠቀሙ ዕድል የሚዘጋ ስለሆነ ወጣቶች የተዘዋዋሪ ብድር ፈንድን ጨምሮ ሌሎች የሚወሰዷቸውንና የወሰዷቸውን ብድሮች በአግባቡ ተጠቅመው ሊመልሱ ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
አቶ ኦሊ በማጠቃለያቸው እንዳሉት የኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ አክሲዮን ማህበር አሁንም ቆጣቢዎች እንዲበራከቱ ይፈልጋል ።ኅብረተሰቡ ቁጠባ የሥልጣኔ መንገድ መሆኑን በመገንዘብ ሲተርፈው ብቻ ሳይሆን አቅዶ መቆጠብ አለበት ።የህዝቡ የቁጠባ ባሕል ሲያድግ የፋይናንስ ተቋማትም ጉልበት ይፈረጥምና በምላሹ ለብድርና ለኢንሹራንስ አገልግሎት ለማግኘት የማይቸገር ማህበረሰብ ይፈጠራል።
በተለይ ማህበሩ የቁጠባ ገንዘቦች በተቆጠቡበት አካባቢ እንዲያገለግሉ ስለሚያደርግ እና ተደራሽነት ስላለው እንዲሁም ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ላይ ያለ የፋይናንስ ተቋም በመሆኑ ኅብረተሰቡ ይህን ተቋም ለቁጠባ አገልግሎት ቢጠቀም የብድር አገልግሎት በማግኘትና በኢንሹራንስ አገልግሎት ተጠቃሚ ይሆናል በማለት ነው የተናገሩት።
አዲስ ዘመን ጥር 21/2013