አክበረት ታደለ (ሄዋን)
ዘወትር እሁድ ከሰዓት እዚህ ቦታ መምጣት ያስደስተኛል። እሁድ ከሰዓትን ራሴን በማዳመጥ ነው የማሳልፈው ይህን ለማድረግ የምመርጠው ደግሞ ከመኖሪያ አካባቢዬ ብዙም የማይርቀውን የብሔረ ጽጌን መናፈሻ ነው። ዛሬም እንደወትሮው የተለመደችው ቦታዬ ላይ ተቀምጫለሁ።
እዚህ በምመጣበት ጊዜ ሁሉ የማላጣት አንዲት ወጣት ልጅ አለች። እሷም እንደሁልጊዜው ቦታዋ ላይ ተሰይማለች። ከእጇ የማይጠፋውን ሲጋራዋን እንደያዘች በምታግተለትለው የሲጋራ ዋሻ ውስጥ በሃሳብ ጥፍት ብላለች። ሁል ግዜ ባየኋት ቍጥር እገረማለሁ። ደግሞ ፊቷ ላይ የመከፋት ስሜት አይነበብም። ሁሌም ፈገግ እንዳለች ሲሆን ዘወር ብላ እንኳ አካባቢዋን ስትቃኝ አይቼ አላውቅም።
እኔን በማይገባኝ ቋንቋ ከሲጋራዋ ጋር ታነበንብና ትኩር ብላ ታየዋለች ከዚያ ፈገግ ትልና ታራግፈዋለች ከዛ ትጥለውና መሬት ላይ ትደፈጥጠዋለች። በአጠገቧ ሰው አለፈ ማን መጣ ጉዳይዋ አይደለም። በቃ ሁሌም በራሷ ዓለም ውስጥ ናት። ትኩረቴን የሚስበውም ይህ ነገሯ ነው። እዚህ ቦታ ሳያት ወደ ወር ይሆነኛል።
በመጣሁ ጊዜ ሁሉ አገኛታለሁ። ዛሬን ግን በመታዘብ ብቻ ላልፋት አልፈልግኩምና ቀርቤ የተወሰነ ነገር ላወራት አሰብኩ። ሁልጊዜም ብቻዋን ነው ስለማያት ሰው የማውራት ፍላጎት ላይኖራት ይችላል የሚል ስጋት ቢኖርብኝም ለመሞከር ግን ወሰንኩ።
የተቀመጠችበት አግዳሚ ወንበር ላይ አጠገቧ ሄጄ ተቀመጥኩ። ዞር ብላም አላየችኝም። ምንም እንዳልተፈጠረ ሆና ሲጋራዋን ታቦነዋለች። ምን ብዬ መጀመር እንዳለብኝ አላውቅምና እዚህ በመጣሁ ቁጥር ሁልጊዜ አይሻለሁ ጥሩ ቦታ ነው አይደል አልኳት። ምንም አልተናገረችም ፈገግ ብቻ አለች።
ፈገግታዋ የልብ ልብ ሰጠኝ ስሜቷን የሚነካና እንድትናገር የሚገፋፋት ነገር ማውራት እንዳለብኝ ተሰማኝ። ሴት ልጅ ሲጋራ ማጨስ አያምርባትም አልኳት። ምንም ሳይደንቃት የምታጨሰው ደስ ስለሚላት ብቻ እንደሆነ ነገረችኝ። ወንዶች ላይ ሁሉም ነገር ያምራል አይደል ብላኝም ከት ብላ ሳቀች።
እንደሚጎዳሽ እያወቅሽ ይህን ማድረግ የለብሽም አልኳት። አልፎ አልፎ በትንሹ ታስላለች በመሀል አቋረጥችኝና አንቺ ስለኔ ህይወት ምን አውቀሽ ነው? በኔ ላይ መፍረድ የቀለለሽ ህመሜ እንዲገባሽ እኔን መሆን አለብሽ አለችኝ። የእሷን ያህል ባይሆን እንኳን መረዳት ግን እንደምችል የገጠማትን ለማወቅ እንደምፈልግና ብታወራኝ ለሷም ቀለል እንደሚላት ነግሬ ስለህይወቷ እንድትነግረኝ ለመንኳት። የምታወራው ሰውም የናፈቀች ትመስላለችና ልታወራኝ ብዙ አላቅማማችም።
እናትና እባቴን ካጣሁኝ ገና 10 ዓመቴ ሲሆን ተከታትለው ነበር ያረፉት። ከእነሱ ሞት በኋላ የእናቴ እህት ከሆነችው አክስቴ ጋር መኖር ጀመርኩ። አክስቴ እና ባሏ ልጅ ስላልነበራቸው በጣም ይንከባከቡኝ ነበር። ይንከባከቡኛል፤ ጥሩ ት/ቤት ያስተምሩኛል፤ በጣም ደስተኛ ነበርኩ። በተለይ የአክስቴ ባል በጣም ይንከባከበኛል፤ በትምሀርትም ያግዘኛል፤ ባለው ትርፍ ሰዓት ሁሉ ያስጠናኝ ነበር።
እኔም በጣም ነበር የምወደው። አባት ሆኖኝ ስለነበር ቆንጆ ህይወት ነበረን። ይህ አስደሳች ጊዜ ግን ለአራት ዓመት ያህል ብቻ ነው መቀጠል የቻለው። እኔም በትምህርቴ እየጎበዝኩ ሰውነቴም እያደገ መጣሁ። የ14 ዓመት ልጅ ብሆንም ሰውነቴ ከእድሜዬ በላይ ነበር የሚመስለው።
ይሄኔ ነበር የኔ መከራ ህይወት የጀመረው። እንደ አባቴ የምቆጥረው የአክስቴ ባል እኔን የሚያይበት አይኑ እየተቀየረ መጣና እንደ ሴት ያየኝ ጀመር። ብቻችንን ሆነን ሲያስጠናኝ አደግሽ እኮ ጡት እያወጣሽ ነው ይለኝና ሊነካካኝ ይሞክራል። እኔ ነገሩን ብዙም አልተረዳሁትም ነበር።
አንድ ቀን ግን በጭራሽ የማልጠብቀው ነገር ተፈጠረ ሁለቱም ጠዋት ለስራ ይወጡና ወደ ማታ ነበር የሚመለሱት። ነገር ግን የዛን ቀን የአክስቴ ባል 4፡30 ሰዓት አካባቢ ወደ ቤት መጣ። በዕለቱ ት/ቤት እረፍት ላይ ስለነበርን ቤት ነበርኩ። አሞኛል ማረፍ ፈልጌ ነው የመጣሁት አለኝና የራስ ምታት ማስታገሻና ውሃ ወደ ክፍሉ እንዳመጣለት ነገረኝ።
ይዤለት ሄድኩና ሰጠሁት። ቀለል እስኪለኝ ተቀመጪና ትንሽ አውሪኝ ስላለኝ ተቀመጥኩኝና አንዳንድ ነገሮችን ማውራት ጀመርን፡፡ ትንሽ እንደቆየን እጄን ግጥም አድርጎ ሲይዘኝ ደነገጥኩ። አሞኛል ብሎ ተኝቶ የነበረው ሰውዬ ከመቅጽበት ብድግ ብሎ ወደ ራሱ አስጠግቶ አቀፈኝ።
በጣም ደነገጥኩ ምን እየተፈጠረ እንደሆነም ሊገባኝ አልቻለም። ከእቅፉ ውስጥ ለመውጣት ታገልኩ ግን የማይታሰብ ነገር ነበርና ብድግ አድርጎ አልጋ ላይ ወረወረኝ። እሱን የምታገልበት አቅም አልነበረኝም። ልብሴን እላዬ ላይ ቀደደውና ድምጽ እንዳላወጣ አፌ ውስጥ ጨርቅ ጠቀጠቀብኝ።
እንደማይምረኝ ስላወቅኩ የመጨረሻ ዕድሌን ለመሞከር ተፍጨረጨርኩ። ይሁንና ሙከራዬ ስላልሰመረ እንደተራበ አውሬ እየተስገበገበ እላዬ ላይ ሰፈረብኝ። በደንብ ያልጠነከረ የልጅነት ገላዬ እንኳን አላሳዘነውም።
ከበታች ተጋድሜ እንባዬ ይወርዳል። ህይወት ጨለመችብኝ በምድር ላይ ከሁሉም ነገር በላይ ገዝፎ ያለነገር ቢኖር ጭካኔ ብቻ መስሎ ታየኝ። እየደጋገመ ቆሻሻውን ተፋብኝ ጣጣውን እንደጨረሰ ይሄን ጉዳይ ለማንም እንዳልናገር አለዚያ ግን በተናገርኩ ቅጽበት ፀጥ እንደሚያደርገኝ አስጠንቅቆኝ ወጣ። ሰማይ ተደፋብኝ የማደርገው ጠፋብኝ ከደማው ስጋዬ ይልቅ የቆሰለው አእምሮዬ አመመኝ።
ይልቅ ከወደቅኩበት ተነስቼ አክስቴ ከመምጣቷ በፊት በደም የተበላሸውን አልጋና እራሴን ማጽዳት እንዳለብኝ አምኜ ጊዜ የሚያጠግገው ስጋዬን እና መቼም የማይድነውን የልቤን ቁስል ይዤ ከአልጋው ተነሳሁ።
በዚህም ልጅነቴ አከተመለት። የሚታጠበውን አጣጥቤ ወደ ክፍሌ ገብቼ እድሌን እየረገምኩ ሳለቅስ ዋልኩና በዛው እንቅልፍ ወሰደኝ። የነቃሁት አክስቴ ስትቀሰቅሰኝ ነበር። ምን ሆነሽ ነው የተኛሽው አመመሽ እንዴ አለችኝ። ትንሽ እራሴን እንዳመመኝ ነገርኳትና ጉዳዩ በዛው አለፈ፤ ምንም ነገር እንዳልተፈጠረ ማለት ነው።
ከዛን ቀን ጀምሮ ግን ልጅነቴን ተቀጣሁ፤ ፈጽሞ እንደቀድሞዬ ልሆን አልቻልሁም። ሳቄን ተሰረቅኩ ደስታዬ ተደመሰሰ። ሆኖም ሌላ አማራጭ አልነበረኝምና እያስመሰልኩ መኖርን ቀጠልኩ። የዛን አውሬ ሰው ፊት እያየሁ መኖር የሞት ያህል ቢከብደኝም ሌላ የምሄድበት ዘመድና የምጠጋበት ጥግ አልነበረኝምና መኖርን ቀጠልኩ።
ነገር ግን የኔ ችግር ላያባራ ተነስቶ ነበርና የባሰ ነገር ተፈጠረ። ከተወሰነ ጌዜ በኋላ ሰውየው አክስቴ የማትኖርበትን ጌዜ እየጠበቀ ያስቸግረኝ ጀመረ። እኔ ግን ከዚያን ጊዜ በኋላ ቤት ውስጥ እሱ ካለ መጠንቀቅ ጀምሬ ነበርና ክፍሌ ውስጥ ገብቼ እቆልፋለሁ።
ነገር ግን የሱ ማስፈራሪያና በድጋሚ እኔን ለማሰቃየት መሞከሩ እየባሰ መጣ። የሆነ የተረገመ አንድ እሁድ አክስቴ ቤተክርስቲያን ሄዳ ስለነበር ሳሎን ቁጭ ብያለሁ። በዚህ ጊዜ ያ አረመኔ መጣና እጄን ይዞ ይጎትተኝ ጀመር። ወደ መኝታ ቤቱ ሊወስደኝ ሲሞክር የአቅሜን ያህል ታገልኩት። ብዙ ታገለኝ አልሸነፍ ስለው በጥፊ መታኝ።
እያለቀስኩ ሳለ አክስቴ መጣችና ምን ሆነሻል አለችኝ። ይህ ህሊና ቢስ ግን በአይን ካስፈራራኝ በኋላ የምሄድበት አለኝ ብሎ ከቤት ወጣ። አምርሬ አለቀስኩ። አክስቴ በጣም ተጨንቃ ስለነበር አጥብቃ ጠየቀችኝ። ከዚህ በላይ ዝም ማለት አልቻልኩምና ከመጀመሪያ አንስቼ የተፈጠረውን ሁሉ ነገርኳት። በጣም የሚገርመው በኔ ላይ ፈረደች።
አንቺ ነሽ ስርስሩ እያልሽ እሱማ ወንድ ነው ምን ያድርግ ልጅ መውለድ ባለመቻሌ ምክንያት በቋፍ ያለ ትዳሬን እንድታፈርሽብኝ አልፈልግም። አሁኑኑ ልብስሽን ይዘሽ ወደምትፈልጊበት ሂጂ። ከዚህ በኋላ እዚህ መቆየት ለሁላችንም ጥሩ አይደለም ብላ የልብስ ሻንጣዬን አምጥታ ፊቴ አስቀመጠችው።
ሶስት መቶ ብር አስጨበጠችኝና ምንም ማድረግ አልችልም ይሄን ነገር እንደሰማሁ አውቆ እንዳይሳቀቅብኝ ባሌ ከመመለሱ በፊት ከእዚህ መሄድ አለብሽ አለችኝ። ከእሱ አውሬነት ይልቅ የእሷ ውሳኔ ገረመኝ። ወዴት እንደምሄድ እንኳን ሳላውቅ ሻንጣዬን አንጠልጥዬ ከቤቷ ወጣሁላት።
የምሄድበትን አላውቅም፤ ከአክስቴ ውጭ የማውቀው ዘመድ የለኝም፤ ከነበርኩበት አካባቢ ራቅ ብዬ እንደሄድኩ የሆነ መንገድ ዳር ቁጭ ብዬ አለቀስኩ። ባልነግራት ይሻለኝ ነበር፤ ባልነግራት ከቤት አልወጣም ነበር፤ ባልነግራት መኖሪያ እንኳን ይኖረኝ ነበር ስልም ተፀፀትኩ። እዛው እንደተቀመጥኩ አንድ ሰውዬ ቀረበና አናገረኝ።
የገጠመኝን ነገርኩት በጣም አዘነ እንደ አጋጣሚ ሰውየው ደላላ ነው። ምንም መሄጃ እንደሌለኝ ስነግረው ስራ እስከሚያገኝልኝ ለትንሽ ቀን እሱ ጋር መቆየት እንደምችል ነገረኝ። ግን ፈራሁ እሱም ወንድ ነው። ህይወቴን ያመሰቃቀለውና ጎዳና እንድወጣ የዳረገኝ ወንድ ነበርና አሁንም ይሄ እንደማይፈጠር ምንም መተማመኛ የለኝም። ለዚያውም የማላውቀውና መንገድ ላይ ያገኘሁት ሰው።
አማራጭ ስላልነበረኝ ግን እሺ አልኩት። መንገድ ላይ ሆኜም የባሰ ነገር ነው የሚያጋጥመኝ። ስለዚህ ቢያንስ ለጊዜውም ቢሆን ማረፊያ ስላገኘሁ ደስ አለኝ። እነዛን አረመኔ አክስቴንና ባሏን ባየሁበት ዓይኔ ማንነቴን ሳያውቅ መልካም ሊያደርግልኝ የፈቀደውን ሰው ላይ በህይወት ትንሽ ተስፋ አደረግኩ። መልካምነት አሁንም አለ ማለት ነው ስልም አሰብኩኝ።
ወደ ቤቱ የወሰደኝ ሰው ብቻውን ነው የሚኖረው። አሁን ያለኝ አማራጭ ሰው ቤት መስራት እንደሆነ ነግሮኝ እሱን እስኪያገኝልኝ ግን እዚህ መቆየት እንደምችልና እንዳልጨነቅም ነገረኝ።
ከአንድ ሳምንት በኋላ አንድ ወንደላጤ ቤት የፅዳት ስራ ተመላላሽ እንዳገኘልኝ ነገረኝና ቀን እየሰራሁ እሱ ቤት ሆኜ ማታ መማር እንደምችል አስረዳኝ። አሰሪዬ በጣም መልካም ሰው ነበርና እንደልጁ ነበር የተመለከተኝ። እንደነገረኝ ክፍለ ሀገር ከኔ በ2 ዓመት የምታንስ ሴት ልጅ አለችው።
ከዛማ እኔም ተረጋጋሁና ስራዬንም ጀመርኩ፤ ትምህርቴንም ማታ መማር ጀመርኩ፡፡ ግን ለመከራ ነው የተፈጠርሽው የተባልኩ ይመስላል እፎይ ማለት ስጀምር የእኔ ስቃይ ይጀምራል።
አሁንም በአንድ በተረገመች ቀን ቤቱን የማፀዳለት ሰውዬ ቤት ሄድኩኝ። ግቢ ውስጥ ብቻውን ነው የሚኖረውና ሌላ ግዜ ቁልፍ ስላለኝ ከፍቼ ነበር የምገባው። የዛን ቀን ግን ያለወትሮው ቤት ውስጥ አገኘሁት። ሰላም ብየው ገባሁና ስራዬን ጀመርኩና መኝታ ቤቱን ላፀዳለት ወደ ክፍሉ ገባሁ።
ሳሎን ተቀምጦ የነበረው ሰው መኝታ ክፍሉ ስገባ ተከትሎኝ ገባ። አልጋውን ሳነጥፍለትም ቆሞ እያየኝ ነበር። ከዛ ሳላስበው ከኋላዬ መጥቶ ሲአቅፈኝ ደነገጥኩ እና አስለቀቅኩት ሳቀና ተወኝ። ልወጣ ስል በሩን ዘጋው እንድታገልሽና እንዳስገድድሽ አታድርጊኝ በፈቃደኝነት እናድርገው አለኝ እኔ ምንም አይነት ፍላጎት እንደሌለኝ ነገርኩት።
ነገር ግን ይሄን ሲያውቅ በግድ ለማድረግ ፈለገና ገፍትሮ አልጋው ላይ ጣለኝ። የምቋቋምበት አቅም አልነበረኝምና ወደቅኩ እሱም የሚፈልገውን እንዳደርግ፤ ማካበድ እንደሌለብኝና ቀለል አድርጌ እንዳየው ነገረኝ። በጣም ደንዝዣለሁና የሚሰማኝን ነገር እኔ እራሴ አላውቀውም። ብቻ ዕድሌ መገፋት መጣል መገለል እንደዛ መስለኝ።
ግንባሬ ላይ ድፈሯት የሚል ጸሑፍ አለብኝ እንዴ? ለምንድ ነው ወንዶች እኔ ላይ ይህን ማድረግ የሚፈልጉት? አምላክ እኔን አያየኝም ወይ? ለኔ ፍርድ የለም ወይ ብዬ አሰብኩና ስቅስቅ ብዬ አለቀስኩ። አባሽ የሌለው እንባ ሰሚ የሌለው አቤቱታ…..
ከቤቱ ልውጣ ስል እጄን ያዘና ቁጥሩን ያላወቅኩትን ገንዘብ እንቺ አለኝ። አልፈልግም አልኩት። ለማንም ትንፍሽ እንዳልል ከተናገርኩ ግን ምን እንደሚከተለኝ መሳቢያውን ከፍቶ ሽጉጥ አሳየኝና አስፈራራኝ። እንባየን ዋጥ አድርጌ ወጣሁና ወደምኖርበት ቤት ሄድኩኝ፤ ራሴን ጠላሁት በጣምም ተጠየፍኩት የወንዶች ቆሻሻ መጣያ የሆንኩ ያህልም ተሰማኝ።
በዚያች ቅጽበት ይሄ ነው የማልለው ጥላቻና በቀል በወንዶች ላይ አደረብኝ። ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ ወንዶችን ለመበቀል ወዲያው ነበር የወሰንኩት። በዛ እድሜዬ የማልችለውን መከራ እንድሸከም ያደረጉኝንና ያጎበጡኝን የአዳም ዘሮች መበቀል!
ጎረቤታችን ተከራይተው የሚኖሩ ሁለት ሴቶች አሉ ስራቸው ምን እንደሆነ አውቃለሁ። ብዙ ግዜ ብዙ ነገር ሲያወሩም ሰምቻለሁ ቀን ቀን ይተኛሉ፤ ማታ ማታ ይወጣሉ። የዛን ቀንም ስለነበሩ ቤታቸው ሄድኩኝ አውርቻቸው እነሱ የሚሰሩትን መስራት እንደምፈልግም ነገርኳቸው።
እሱ ህይወት ለኔ እንደማይሆን በዚህ እድሜዬ እዛ ህይወት ውስጥ መግባት እንደሌለብኝ ቢነግሩኝም ልሰማቸው አልፈለግኩምና በጣም ለመንኳቸው። የምትሰሩበት ብቻ ውሰዱኝ አልኳቸውና ተስማማን። ማታ ስሄዱ ይዘውኝ ሂዱ። የሆቴሉ ባለቤት ስታየኝ ገና ተደሰተች። ፍላጎቴን ስላየችና ብዙ ደንበኞች ላመጣላት እንደምችል ስላወቀችም እጅግ ተደሰተች።
ትልልቆች ወንዶች በእድሜ ትንሽ ልጅ ስለሚፈልጉ ማለት ነወ። መኖሪያ ቤት እንደሌለኝ ነገርኳትና እዛው እየሰሩ ከሚኖሩት ጋር መኖር ጀመርኩ። ገና በመጀመሪያው ቀን እዛ ቤት ውስጥ ደንበኛ የሆኑት ሃብታሞች በሙሉ ዓይናቸው እኔ ላይ ሆነና ፈላጊዬ ብዙ ሰው ሆነ። በዚህ ነገር ሌሎች ሴቶች ሳይናደዱብኝ አልቀሩም። ከዛማ ምኑን ልንገርሽ እኔን ለማግኘት ለባለቤቷ የሚሰጠው ብር ለኔ የሚመጣው ገንዘብ ወሬው ሁሉ ስለእኔ ሆነና አረፈው።
እኔ በቀል ብዬ ያሰብኩት የጠላሁትን ሰውነቴን አቅርቤ ገንዘባቸውን ማራገፍን ነው። በቀላል ገንዘብ አልወጣላቸውም። እንደሌሎቹ ሴቶችም ሆቴል ውስጥ ተቀምጬ አልቀላውጥም። ክፍሌ ውስጥ እሆናለሁ ባለቤቷ ታጫርታቸውና በእለቱ ብዙ ገንዘብ ያቀረበ ይዞኝ ይሄዳል። በቃ ህይወቴ ይሄ ሆነ።
እድሜዬን ወደ 16 የተጠጋ ቢሆንም ስታይ የምመስለው ግን ከእድሜዬ በላይ ነው። ህይወቴን እነደዚህ ቀጠልኩና ብዙ ገንዘብ ያዝኩ። ግን ምንም የማደርገው ነገር የለኝም። የማግዘው ቤተሰብም ሆነ እህትና ወንድም ስሌለኝ የሁሉንም ነገር ለመርሳት ስል እቅማለሁ፤ አጨሳለሁ ፤ እጠጣለሁ ይሄ የዕለት ዕለት ተግባሬ ነው።
ለምን እንደምኖር ለማን እንደምኖር አላውቅም ይኸው ይህን ህይወት ከጀመርኩ 9 ዓመት ሆነኝ እድሜዬ ወደ 25 እየሄደ ነው። ምንም ወደ ፊት የሚባል ነገር የለኝም፤ ዛሬን ብቻ ነው የምኖረው። በቀሌ የመጣልኝ ገንዘብ እንኳን ደስተኛ አላደረገኝም። ነገሬ ሁሉ ዝም ብዬ በሱሶቼ ውስጥ መደበቅ ብቻ ሆኗል።
የምፈልገው ትላንቴን ላለማስታወስ ይኸው ነው የኔ ህይወት። የማልጠቀመው ዕጽ የለም። ገንዘብ ስላለኝ ያለሁበት ድረስ ነው የሚያመጡልኝ እሱን ስጠቀም ሰላሜን አገኛለሁ። ትላንትም ነገንም እረሳለሁ በኔ ህይወት ውስጥ ዛሬ ብቻ ነው ያለው ይህ ነው የኔ ህይወት አለችኝ ምን መናገር እችላለሁ ምንስ አይነት ቋንቋ መጠቀም እችላለሁ ምንም መልስ አልነበረኝም ሰዓቷን አየችና አሁን መሄድ እንዳለባት ነገረችኝ። ሁልጊዜ እሁድ የምመጣ ከሆነ እንደምንገናኝ ነግራኝ እኔ እንደደነዘዝኩ እሷ ሄደች።
ይህች ሄዋን የደረሰባት ይህን መሰል ጥቃት በብዙ ሴቶች ላይ የደረሰ ስለመሆኑ ጥርጥር የለውም። ይሁንና ለመርሳት ብላ የገባችበት ህይወት አዋጭ አለመሆኑም ግልጽ ነው። ስለሆነም በቀጣይ ሳገኛት ያለፈ ህይወቷንና አሁን ያለችብትን ህይወት እርግፍ አድርጋ ረስታ አዲስና በተስፋ የተሞላ ህይወት መኖር እንድትጀምር ልመክራት ወስኜ ተነሳሁ።
አዲስ ዘመን ጥር 21/2013