አስቴር ኤልያስ
በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ያለው የድንበር ሁኔታ ላለፈው አንድ ምዕተዓመት በውዝግብ ውስጥ የቆየ ነው ።ውዝግቡ አንዴ ከረር፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ረገብ ሲል የቆየ ቢሆንም ዘላቂ መፍትሄ ሊሆን የሚችለው የጋራ ልዩ ኮሚቴ (Joint Special Committee) አዋቅሮ በሁለቱም አገራት ተቀባይነት ያለው የመፍትሔ ሃሳብ (Amicable Solution) ማምጣት ሲቻል እንደሆነ ይነገራል ።
ኢትዮጵያን ባለፉት አንድ መቶ ዓመታት ውስጥ በየጊዜው ሲያስተዳድሩ የነበሩ ነገሥታትና መሪዎቹ የዚህን የድንበር ውዝግብ ቸል ሳይሉ በተቻላቸው ሁሉ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል ።ሱዳንም ብትሆን ኢትዮጵያ በራሷ ነገር ፋታ የምታጣበትን ጊዜ እየጠበቀችና እያደባች ህጋዊ ባልሆነ መንገድ የድንበር ወረራዋን ስታካሂድ ሰንብታለች፤ በቅርቡም ያደረገችው ይህንኑ ነው ።
አዲስ ዘመን ጋዜጣም ከዚሁ ከኢትዮ-ሱዳን የድንበር ውዝግብ ጋር በተያያዘ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የድንበርና ድንበር ተሻጋሪ ሀብቶች ጉዳይ ዳይሬክተር ጄኔራል ከሆኑት አብዱራሃማን ጀማል ጋር ቃለ ምልልስ አድርጎ እንደሚከተለው አቅርቧልና መልካም ንባብ ይሁንልዎ፡፡
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያና የሱዳን የቀደመ ግንኙነት ምን ይመስላል ?
ዳይሬክተር ጄኔራል አብዱራሃማን፡- እንደሚታ ወቀው በአካባቢው ካሉ አገራት ኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ እድሜ ያስቆጠረችና ለረጅም ጊዜ በስልጣኔ የቆየች አገር ናት ።የረጅም ጊዜ የስልጣኔ ባለቤት እንደመሆኗ ከአጎራባች አገራት ጋር ያላት ግንኙነት በዚሁ የሚታይ ነው፡፡
በተለይ ከሱዳን ጋር በምንወስድበት ሰዓት ከአገሪቱ ጋር በህዝብ ለህዝብ እንዲሁም በታሪክና በኃይማኖት እንገናኛለን ።በተጨማሪም የጋራ ባህል ያለን አገራት እንደመሆናችን በእሱ በኩልም እንገናኛለን ።ይህ ግንኙነት ደግሞ ትናንት የመጣ የአጭር ጊዜ ወይም ወቅታዊ የሆነ ሳይሆን እጅግ በጣም ዘመናትን ያስቆጠረና በሁለቱ አገራት ህዝቦች መካከል የኖረና የዳበረ ግንኙነት መኖሩን አመላካች ነው ።
አዲስ ዘመን፡- አሁን በሱዳን ያለው የፖለቲካ ሁኔታ እንዴት ይታይል ?
ዳይሬክተር ጄኔራል አብዱራሃማን፡- ሱዳን እንደሚታቀው ፕሬዚዳንት አልበሽር ከስልጣን መነሳታቸውን ተከትሎ በሽግግር ላይ ያለች አገር ናት ።የፖለቲካ ሽግግሩን ተከትሎ ሊመጡ የሚችሉ ብዙ ውጣ ውረዶች ይኖራሉ ።ከዚሁ ጋር በተያያዘ የፖለቲካው ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚም ችግሮች ይኖራሉ ።
ስለዚህም ይህ የሽግግር ጊዜ እስኪያልፍ ድረስ ብዙ ፈተናዎችን ልትጋፈጥና ልታልፍ ትችላለች ።ከእነዚህ ፈተናዎች መካከል አንዱ የፖለቲካ ሁኔታው አለመረጋጋት ሲሆን፣ ወደተረጋጋ ሁኔታ እንዲመጣ የፖለቲከኞችንም አስተዋጽኦ የሚፈልግና ጊዜም የሚያሻው ነገር ነው ብዬ አስባለሁ ።
አሁን ያለው የፖለቲካ ሁኔታ ያለው በሽግግር ሂደት ላይ እንዳለ መንግሥት በዛ መልኩ ሊታይ የሚችል ነውና የተረጋጋ ነው ብሎ ለመውሰድ ወይም ደግሞ ዘለቄታዊ መስመሩን ይዟል ብሎ ለመውሰድ ትንሽ ይከብዳል ።
ምክንያቱም ይህ የሽግግር መንግሥት ወደየት መንግስት አቋቁሞ እና ተመስርቶ እስኪሄድ ድረስ ያለውን ሁኔታ ለመገመት ትንሽ አስቸጋሪ ነው ።ምክንያቱም በሽግግር ላይ ያለ መንግሥት ምንጊዜም ኢ-ተገማች የሆኑ ነገሮች ያጋጥሙታል ።
ኢ-ተገማች የሆኑ ነገሮች ሲያጋጥሙት ምን አይነት ውጤት ይዞ ሊመጣ ይችላል የሚለውንም ነገር ለማስላት አስቸጋሪ ነው ።የሽግግር መንግሥቱ በተቻለ መጠን ያለውን የፖለቲካ ሁኔታ አረጋግጦ የሕዝቡንም ጥያቄ ይመልሳል የሚል እምነት ይኖራል ።
አዲስ ዘመን፡- ይህ በሀገሪቱ ያለው ያልተረጋጋ የፖለቲካ ሁኔታው መንግሥትን ለሦስተኛ አካላት መጠቀሚያ አድርጎታል ይባላልና ይህን እንዴት ያዩታል ?
ዳይሬክተር ጄኔራል አብዱራሃማን፡– ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ምን ጊዜም አንድ የሽግግር መንግሥት በሚኖርበት ሰዓት ዘላቂ የሆነ መንግሥት ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ድጋፎችን ከውስጥም ሆነ ከውጭ የማሰባሰቡ ጉዳይ ይስተዋላል ።ፖለቲከኞችም ብዙ ጊዜ የሕዝባቸውን ድጋፍ ማግኘት ይፈልጋሉ ።
የሕዝባቸውን ድጋፍ ማግኘት ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ድጋፍም ለማግኘት ጥረት ያደርጋሉ ።በመሆኑም ለሦስተኛ ወገን ግፊትና ጣልቃ ገብነት ተጋላጭ ናቸው የሚል ታሳቢ አለ ።እንዲህ ሲባል እከሌ ወይም እከሊት ናት ባይባልም እንዲህ በሽግግር ላይ በሚኮንበት ወቅት የራሱን ክፍተቶችንም ለመሸፈንና በቀጣይነትም ስልጣን ላይ ለመቆየት በሚደረጉ ጥረቶች ሁሉም የራሱ የሆነውን ደጋፊ መሰብሰቡ ስለማይቀር በዚህ መልኩ ለሦስተኛ ወገን ተጋላጭነቱ የሰፋ ነው፡፡
ሦስተኛ ወገኖች ግን ጣልቃ የሚገቡት የራሳቸውን ፍላጎት ለማሳካት እንደሆነ መታወቅ ያለበት ጉዳይ ነው ።እነዚህ ሦስተኛ ወገኖች የራሳቸው የሆነውን ድብቅ አጀንዳ ይዘው ስለሚመጡ በሁለቱም ማለትም በራሳቸውና ጣልቃ በገቡበት ላይ የተመቻቸ መስለው ይታያሉ ።ስለዚህም ሱዳንም እንደ አንድ በሽግግር ላይ እንደምትገኝ አገር ከዚህ አይነት ተጋላጭነት ውስጥ ያለች ስትሆን ተጋላጭ አይደለችም ብሎ መደምደም አይቻልም።
አዲስ ዘመን፡- የሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት ያዋጣታል ማለት ይቻላል ?
ዳይሬክተር ጄኔራል አብዱራሃማን፡– እውነት ለመናገር አያዋጣትም፤ ምክንያቱም የሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት ዓላማው ድብቅ አጀንዳን ማሳካት ነው። ስለዚህም ድብቁ አጀንዳው ከሱዳን ጋር ምን ያህል ይዛመዳል የሚለውን ነገር ነው ማየት የሚያስፈልገው ።ስለዚህም ሱዳን በዚህ ወቅት የሚስያፈልጋት ሰላም እንዲሁም የተረጋጋ ፖለቲካና መንግሥት ነው ።
የተሻለ ኢኮኖሚና ህዝቧን ከከፋ ድህነትና ከተጫናት የኑሮ ግሽበት ማላቀቅ ነው ።እነዚህ ሦስተኛ ወገኖች በሚመጡበት ሰዓት የሱዳንን ህዝብ ጥያቄ እንመልሳለን ከሚል ተነሳሽነት ሊሆን አይችልም ።ምክንያቱም የሱዳን ህዝብ ጥያቄዎች ቀደም ሲል የጠቀስኳቸው የተረጋጋ ፖለቲካና ሰላም ሲሆን፣ በተጨማሪም የተሻለ ኢኮኖሚ እና ህዝቡን ከከፋ ድህነት የሚያላቅቁ አጀንዳዎች ይዘው ከመጡ ነው ሊረዷት የሚችሉት ።
ከዛ በተረፈ ግን የሱዳንን ጥንካሬ የማይፈልግ አካል ለሱዳን አለሁልሽ በማለት የሚረዷት በማስመሰል በተቃራኒው ግን ሱዳን ሁሌ ቀውስ ውስጥ እንድትገባ በማድረግ ጥንካሬዋ ጎልቶ እንዳይወጣ በማድረግ እነዛ ሦስተኛ ወገኖች ደግሞ በሱዳን ውድቀት ላይ የራሳቸውን ጥንካሬ እያረጋገጡ ለመሄድ ከሚያርጉት ጥረት በዘለለ የሱዳንን ፖለቲካ፣ ሰላምና ኢኮኖሚ ወደተሻለ ሁኔታ የሚወስድና ጥንካሬዋን የሚደግፍ ነው ብዬ አላምንም።
ስለዚህ እነዛ የሦስተኛ ወገን ድብቅ ፍላጎቶች አንደኛ ሱዳን ሁለተኛ ኢትዮጵያም ብትሆን ወደግጭት፣ ወዳላስፈላጊ ንትርክ ውስጥ እንድንገባ ወይም ደግሞ ልማትና ኢኮኖሚያችን እንዳያድግ የሚፈልጉ አካላት አሉ።
ይህ የሚደረገው ሁለቱንም አገራት በማጋጨት ሊሆን ይችላል፤ ወይም ደግሞ ግንኙነታቸውን በማበላሸት ሊሆን ይችላል ።ካልሆነም ደግሞ ካላቸው የወደፊት የእድገት ርዕይ ወደኋላ በማስቀረት የራሳቸውን አንድ አገር ሌላውን የሚቆጣጠርበት የጎረምሳ አይነት እንዲሆን ነው ።በዚህ አይነት መንገድ የራሳቸውን ነገር ለማጠናከር የሁለቱ አገሮች ውድቀት ወይም ደግሞ ድክመት ነው የሚያወጣ ብለው ስለሚስያቡ ያንን ውጤታማ ለማድረግ ከመሄድ በዘለለ ሱዳንን የሚጠቅም ነገር ምንም አይነት ነገር ታሳቢ ሊደረግ አይችልም፡፡
አዲስ ዘመን፡- የድንበር ውዝግቡ ሱዳን በእንግሊዝ በተገዛችበት ዘመን በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት የጀመረ ስለመሆኑ ይነገራል፤ ይህ ችግር በየዘመኑ በነበሩ መሪዎች እንዴት ተይዞ ነበር ?
ዳይሬክተር ጄኔራል አብዱራሃማን፡– አንድ መታወቅ ያለበት ነገር ይህ የድንበር ጉዳይ ከመቶ ዓመት በላይ ያስቆጠረ ውዝግብ ነው ።የድንበር ወሰኑ የተለየው እኤአ በ1902 በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ነው ።በወቅቱ አፄ ምኒልክ ከእንግሊዝ ተወካይ ጋር ድንበሩን በሚወስኑበት ወቅት የነበሩ ሁኔታዎች አሉ፡፡
ያኔ አፄ ምኒልክ ባለሙያም ስላልነበራቸው ለዛ ጉዳይ እውቀት ያለው ሰውም ስላልነበራቸው የእንግሊዙ ተወካይ እንግሊዝ ከኢትዮጵያ በተሻለ የሙያም የእውቀትም ክህሎቱና እድሉ ስለነበራቸው የተሻለ ሁኔታ ላይ የመገኘት አጋጣሚ ነበራት ።በዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ነው ስምምነት ላይ የተደረሰው ።
እኤአ በ1902 የድንበር ውሉ ከተለየ በኋላ በ1903 ላይ ሻለቃ ግዊን (Major Gwynn) የተባለ እንግሊዛዊ ቀያሽ ድንበሩን አካሏል ።እኤአ በ1902 የተፈረመውን ስምምነት መሠረት በማድረግ በ1903 የድንበር ማካለሉ ሂደት ተከናውኗል ።
ይህ የድንበር ማካለል ሂደት በሚከናወንበት ወቅት ክፍተቶች ነበሩበት ።እኤአ በ1902 ስምምነት መሠረት ድንበሩ እንዲካለል የሚወስነው ወይም ድንበሩን የሚያካልሉ የጋራ ኮሚሽን ሁለቱም ወገኖች እንደሚያቋቁሙ ይደነግጋል ።
ነገር ግን እንግሊዛዊው ሻለቃ ግዊን ብቻውን ነው ያካለለው ።ያንን ድንበር ሲያካልል ያለ ኢትዮጵያ የድንበር ኮሚሽን ነው፤ ምክንያቱም ሻለቃ ግዊን በወቅቱ ሱዳን የምትባል አገር ስላልነበረች ወይም ደግሞ ሱዳንን በቅኝ ግዛት የምታስተዳድራት ስለነበረች ሱዳንን በመወከል ብቻውን የኢትዮጵያ ተወካይ ሳይኖር አካሎታል ።የኢትዮጵያ ተወካይ ሳይኖር ማካለሉ ብቻ ሳይሆን ሁለተኛው ስህተቱ የኢትዮጵያ መንግሥት እውቅና አልሰጠውም ።
እኔ ባለሙያ የለኝም፤ ስለዚህ አንተ እኔን ወክልና ድንበሩን በስምምነቱ መሰረት ማካላል ትችላለህ የሚል እውቅና ከኢትዮጵያ በኩል አልተሰጠውም ።በመጀመሪያም ቢሆን የጋራ ኮሚሽን ባልተቋቋመበት ብቻውን ነው ያካለለው ።ለብቻውን ማካለሉ እውቅና ከተሰጠው አንዳንዴ ክፍተት ላይሆን ይችላል፡፡
ነገር ግን በኢትዮጵያ መንግሥት በአፄ ምኒልክ መንግሥት የተሰጠው እውቅና አልነበረውም ።ከዛ በኋላ እርሱ ጽፎ ያቀረበውን ሪፖርት የኢትዮጵያ መንግሥት እውቅና አልሰጠውም ።ስለዚህ በወቅቱ ሱዳን እንደ አገር ራሷን የቻለች ባለመሆኗ ታስተዳድራት የነበረችው እንግሊዝ ናት ጉዳዩን የተቀበለችው ።
ምክንያቱም ሱዳን እንደ አገር ለማለት የሚያስችል ምንም ምቹ ሁኔታ አልነበራትም ።ስለዚህ በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ድንበር የማካለል ሂደት ተቀባይነት ሳያገኝ በአፄ ምኒልክ መንግሥት መዋቅር ውስጥ የተለያዩ ውዝግቦችን ሲያስነሳ ቆይቷል፡፡
አጼ ምኒልክ የስልጣን ዘመናቸው ካበቃ በኋላ በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ውስጥ የድንበሩ ጉዳይ ለረጅም ዘመናት የክርክር መንስዔ ሆኖ ዘልቋል ።ሌላው ቀርቶ አፄ ኃይሥላሴ በራሳቸው በሚመሩት የዘውድ ምክር ቤት ውስጥ ተከታታይ የሆኑ ውይይቶች ተካሂደዋል ።
ድንበሩን በሚመለከት ያለው ችግር ምንድን ነው? እንዴትስ ሊፈታ ይገባዋል? በሚል ።አፄ ኃይለሥላሴ ለበርካታ ዓመታት ውይይት ሲያካሂዱበት ቆይተው ራሳቸው በሚመሩት በዘውድ ምክር ቤት ውይይት ካደረጉ በኋላ የድንበሩ ሁኔታ በሁለቱ አገራት ተቀባይነት ባለው መፍትሄ መፈታት ይኖርበታል የሚል አቋም ላይ ደርሰዋል ።
ከዚህ በመነሳት ሱዳን እኤአ በ1960 ነጻ ስለወጣችና አገር ስለሆነች የሁለቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ሁለቱ አገራት በሰጧቸው አቅጣጫ መሰረት ኢትዮጵያና ሱዳን የማስታወሻ ልውውጥ አድርገዋል ።በዚህ መካከል የሱዳን መንግሥት የ1902 ስምምነትን እና የ1903 የድንበር ማካላልን በመሰረቱ እንቀበለው በሚለው ሃሳብ ላይ የጋራ አቋም ቢይዙም የተቀመጠው የድንበር ወሰን ለአንዴና ለመጨረሻ መስመር ነው ወይም የድንበራችን መለያ ነው ብሎ የኢትዮጵያ መንግሥት አልተቀበለውም።
ሳይቀበለውም ሰባት አሥርት ዓመታት ቆይቷል ።ከ70 ዓመት በኋላ ግን በነበሩ ድርድሮችና ውይይቶች በመሰረቱ እንቀበለው፤ ነገር ግን ያሉትን ችግሮች ደግሞ በሁለቱ አገራት ተቀባይነት ባለው የመፍትሄ ሐሳብ (amicable solution) እንፍታ በሚል ተስማሙ፡፡
አዲስ ዘመን፡- በመሠረቱ እንቀበለው ሲባል ምን ማለት ነው?
ዳይሬክተር ጄኔራል አብዱራሃማን፡– በመሠረቱ እንቀበለው ማለት ምልክቱ አለ፤ ነገር ግን በስምምነቱም መሠረት ይሁን ሻለቃ ግዊን ድንበሩን ሲያካልል የተሳሳታቸው ስህተቶች አሉ ።የ1902 ስምምነትን ስህተት በምንወስድበት ሰዓት ድንበሩን በሁለት ከፍሎ ነው ።
በአካባቢው ደግሞ ዜጎች ይኖራሉ ።ብዙ ኢትዮጵያውያንን ወደሱዳን በኩል ቆርጦ ነው ሰውዬው ያካለለው ።ስለዚህ ኢትዮጵያውያን ያሉበትን ቦታ ወደዛ አድርጎ ማካለሉ በራሱ አንደኛው ስህተት ነው ።
ስለዚህ ሁለቱ አገራት በሚያቋቁሙት ኮሚቴ በሚመጣ መፍትሄ መሠረት የጋራ መፍትሄ ሲመጣ የድንበር ወሰኑ የዚያኔ ይስተካከላል ነው ።ስለዚህ በመሠረቱ እንቀበለው ሲባል የጋራ መፍትሄ ሲመጣ ማሻሻያ እንደሚደረግበት ታሳቢ ማድረግ እንደማለት ነው ።የዜጎቹን ሁኔታ መሠረት ያደረገ ሁለቱ አገራት በሚስማሙበት የመፍትሄ ሐሳብ ሲለይ የድንበሩ ሁኔታ ወይም የድንበር ምልክቱና የድንበር ማካለሉ እንደገና ይሰራል ማለት ነው ።
ከዳግሊሽ ተራራ በስተደቡብ በኩል አንድ አራት የሚሆኑ ተራራዎች አሉ ።እነዛን ተራራዎች ሙሉ በሙሉ ያደረገው ቆርጦ ለሱዳን ነው የሰጠውና በተራራዎቹ ግርጌ ያለው ለሱዳን እንደመሆኑ ስትራቴጂካዊ በሆነ መንገድ ለሱዳን የወገነ አከላለል ነው ማለት ይቻላል ።
ለወታደሩም ሆነ ለሌላው ነገር ስትራቴጂካዊ ቦታ ስለሆነ ጸድቆ ድንበሩ በተራራዎቹ አናት ላይ ይሂድ በሚል ማስተካከያ ይደረግበታል ።በመሰረቱ ያ እንዳለ ሆኖ ማስተካከያዎች ይደረጉበታል፡፡
በ1972ቱ ስምምነት ከዳግላሽ ተራራ በስተደቡብ ያለው አብዛኛው ክርክር የለበትም ።ክርክር የሌለበት ምክንያት ዜጎች ቀድመው ስለሚኖሩበት ነው ። በአካባቢው ድንበሩንም ለማካለል ተፈጥሯዊ የሆኑ ምልክቶች ስለተቀመጡና ወንዙንም ተራራውንም እየተከተለ ስለሄደ ብዙ ችግር የለበትም ።
ሜዳማ የሆኑ አካባቢዎች ላይ ግን እንዳለ ነው ቆርጦ ያስቀመጠው ። ያንን ለማስተካከል የጋራ የሆነ መፍትሄ መምጣት መቻል አለበት፤ የጋራ መፍትሄ ሲመጣ ግን ያው በመሠረቱ የተቀበልነውን እናጸድቃለን የሚለውን ሐሳብ ይዞ ለመሄድ ነው የታሰበው፡፡
በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ትልቅ ለውጥ የተደረገው ለብዙ ዓመታት ያህል የሱዳን መንግሥት አልቀበልም ሲል የነበረውን ሁለቱ አገራት ስምምነቱን አንጥሰውም፤ እንቀበለዋለን፤ በ1902 መሠረት ለዘመናት ሲኖሩበት የነበሩትን ኢትዮጵያውያን ይዞታቸውን በሚመለከት ሱዳንና ኢትዮጵያ በጋራ በሁለቱም አገራት ተቀባይነት ያለው መፍትሔ ሃሳብ (Amicable Solution) ሲያመጡ የሚወሰን ነው የሚለው ነው፡፡
ስለዚህ ይህ ትልቅ ለውጥ የተደረገው ነገር ምንድን ነው ቢባል ለ70 ዓመታት ያህል የአፄ ምኒልክ መንግሥትም ሲከራከር እና ይህንን አልቀበልም ሲል የነበረውን ነገር አሁን ሁለቱ አገራት ሰምምነቱን አንጥሰውም፤ በመሰረቱ እንቀበለዋለን ።
በዛ በ1902 ስምምነት መሰረት እዛ አካባቢ ለዘመናት ሲኖሩበት ያሉትን ኢትዮጵያውያን ይዞታቸውን በሚመለከት ሱዳንና ኢትዮጵያ በሁለቱም አገራት ተቀባይነት ያለው መፍትሔ ሃሳብ (Amicable Solution) ሲያመጡ የሚወሰነው ነው የሚል ነው ።
ስለዚህ ይህ በ1972ቱ የተለዋወጡት ማስታወሻ በግልጽ የሚያሳየው ከዳግልሽ ተራራ በላይ የኢትዮጵያ እና የሱዳን ድንበር አልተለየም ማለት ነው ።ስለዚህም ውዝግብ ያለበትና የግዛት ይገባኛል ጥያቄ አለበት ማለት ነው ።ይህ ማለት የ1972ቱን ስምምነት ሱዳን ተቀብላዋለች ማለት ነው ።ሱዳኖች ሰለመቀበላቸው አንደኛ ያረጋገጡት በፊርማቸው ነው ።ሁለተኛ ደግሞ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) አንቀጽ 102 መሰረት ይህንን ስምምነት ተቀብያለሁ ብላ ለተመድ አሳውቃለች፡፡
ሦስተኛው ደግሞ በወቅቱ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሊቀመንበር ለነበሩት ለሞሮኮው ንጉስ ሀሰን በኢትዮጵያና ሱዳን መካከል ለረጅም ዘመናት የቆየውን የድንበር ስምምነት አሁን በጋራ ለመፍታት ተስማምተናል፤ የተስማማንበትም ሰነድ ይህ ነው ብለው ለአፍሪካ ህብረትም አሳውቀዋል፤ ስለዚህ ሱዳኖች ዛሬ ላይ ደርሰው ያንን ስምምነት ሊጥሱ አይችሉም ።
ምክንያቱም አንደኛ መንግሥታቸው በውጭ ጉዳይ በኩል ፈርሟል ።ሁለተኛ ደግሞ በወቅቱ የነበሩት የሱዳን ፕሬዚዳንት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አሳውቀዋል ።ሦስተኛ ደግሞ በወቅቱ ለነበሩት የአፍሪካ አንድነት ድርጅትም እንዲሁ አሳውቀዋል ።
አሁን እየሆነ ያለውና ከዛ በፊት እየሆነ ያለው በደርግ ዘመነ መንግሥትም ሲስተዋል የደርግ ዘመን ያሳለፋቸው ሁኔታዎች ከበድ ያሉ ስለሆኑ ከድንበሩ ጋር በተያያዘ ሲደረግ የነበረው ጥረት እምብዛም አልነበረም ።
በኢህአዴግ ዘመንም እንደሚታየው ነው፤ እኤአ በ2002 አካባቢ በ1972 ስምምነት መሰረት ተቀባይነት ያለውን የመፍትሄ ሀሳብ (amicable solution) እንዲያመጣ ልዩ ኮሚቴ ይቋቋም ይል ነበር ።ያ ልዩ ኮሚቴ የተቋቋመው አሁን በቅርቡ እኤአ በ2002 ነው ።የተወሰነ እንቅስቃሴ የተደረገው እኤአ ከ2002 እስከ 2008 አካባቢ ነው ።
በዚህ ጊዜ ልዩ ኮሚቴው የተለያዩ ስምንት ስብሰባዎችን አድርጎ ቃለ ጉባኤዎችን ይዟል ።ነገር ግን የሁለቱ አገራት የጋራ ኮሚቴው ተቀባይነት ያለውን የመፍትሄ ሀሳብ (amicable solution) የተባለውንና የመጨረሻውን ሪፖርት አላቀረበም ።
ይህ ሐሳብ ቢቀርብ በቦታው ያለውን ችግር ይፈታል የሚል የመፍትሄ ሐሳብ ባለመቅረቡ ነገሮች በእንጥልጥል ቀርተዋል ።በመሆኑም በመሃል ተቋርጦ ነው ያለው ።በጥቅሉ በዘመናት ከፋፍለን ስናየው ይህን ይመስላል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በዚህ ዘመን ሁሉ የመንግሥታቱ አቋም እንዴት ይገለጻል? የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፉት ጊዜያት በድንበር ጉዳዩ ጥሩ ነገር ነው ይዞ የመጣው ማለት ይቻል ይሆን?
ዳይሬክተር ጄኔራል አብዱራሃማን፡- አዎ ጥሩ ነገር ነው ይዞ የመጣው ማለት ይቻላል ።አንድ ነገር ብቻ ቀድሜ ለማስታወስ እፈልጋለሁ ።ሱዳን ነጻ ከወጣች በኋላ የድንበሩን ጉዳይ የያዘችበት አግባብ በትንሹ ለማንሳት ያህል እኤአ በ1972 ቀደም ብዬ ያልኩሽ ስምምነት ከተደረገ በኋላ በዛ ስምምነት መሰረት የድንበሩ ጉዳይ መፍትሄ ለማግኘት እንቅስቃሴዎች ተደርገው ነበር ።
እንደሚታወቀው አፄ ኃይለሥላሴ ከስልጣን የወረዱት እኤአ በ1974 ነው፤ ስለዚህ እንቅስቃሴ እንደተጀመረ ወደትግበራ ሊገባ የድንበር ኮሚሽንም ተቋቁሞ የተወሰኑ የፋይናንስ ድጋፎችንም ለማስገኘት በተለይ በዳግላሽ ተራራዎች በስተደቡብ በኩል ያለው ብዙ ጭቅጭቅ ስለሌለው እሱን እያካለልን የላይኛውን ደግሞ በሁለቱ አገሮች ተቀባይነት ባለው የመፍትሄ ሀሳብ (amicable solution) እስክንፈታ የሚል ጥሩ እንቅስቃሴዎች ተጀምረው ነበር ።ነገር ግን በአገራችን የመንግሥት ለውጥ በመምጣቱ እንቅስቃሴው ተደናቀፈ።
የሱዳን መንግሥት የተለየ ባህሪ ደግሞ የሚጀምረው ከዛ አካባቢ ነው ።ስለዚህ የኢትዮጵያ መንግሥት ለውጥ በሚደረግበት ሰዓት ኢትዮጵያ ተዳክማለች የሚል ታሳቢ በመውሰድ ኢትዮጵያን ለመውረር ሙከራ አድርገዋል ።እንደሚታወሰው ደርግም ከሱዳን መንግሥት ጋር ቁርሾ የነበረው አንድም በዚህ የድንበር ምክንያት ነው ።
ቀጥሎም ደርግ ትኩረትም ሳይሰጠው ያደረገው ነገር ቢኖር በምሁራን ጥናት ማስጠናት ነው ።ከዚህ ባለፈ ግን በአገር ውስጥ ፖለቲካ ያለፈበት ሁኔታ ነበር ያለው፡፡
ሁለተኛ የሱዳን መንግሥት ባህሪ የሚገለጸው የደርግ መንግሥት ሊወድቅ በደረሰበት እኤአ በ1989 እስከ 1991 አካባቢ መሬቱን ወረረው ።ወረረው ስልሽ በውዝግብ ላይ ያለውንና በጋራ እስክንፈታው ብለን ያለውን መሬት ነው ።እንዲህም ሲባል የእከሌ ወይም የእከሊት መሬት ነው ያልተባለውን መሬት ነው የወረሩት ለማለት ነው ።
የመውረሩ ምክንያት ደግሞ ኢትዮጵያ ተዳክማለች፤ የውስጥ ችግርም አለባት በሚል ነው ።ይህ እንግዲህ የሱዳን መንግሥት ለሁለተኛ ጊዜ ያደረገው ትንኮሳ መሆኑ ነው ።ከዚህ ጋር ተያይዞ መሬቱ ለ25 ለ35 ዓመት ተያዘብን በሚልም የተለያዩ ፕሮፓጋንዳዎችንም የመንዛት ነገርም አለ፡፡
እኤአ በ1989 እስከ 1991 ድረስ የወረሩትን መሬት የግብጹ ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ አዲስ አበባ ላይ ሊገደሉ ሲሉ እኤአ በ1995 በተደረገው የሰርጎ ገቦች እንቅስቃሴ ሰርጎ ገቦቹ በዛ በድንበሩ በኩል ስለመጡ የኢትዮጵያ መንግሥትም ያ እኤአ በ1989 እስከ 1991 የተያዘውን መሬት ነው ማስመለስ የቻለው ።
ይህም ማለት የሱዳን ጦር ከ25 ዓመታት በኋላ የተወሰደብንን መሬት አስመለስን የሚለው ስሞታን በተመለከተ የሱዳን ጦር እ.ኤ.አ ከ1989 እስከ 1991 ኢትዮጵያን በመውረራቸው እ.ኤ.አ በ1995 በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ወደነበረበት እንዲመለስ ተደረገ እንጂ በኢትዮጵያ የተያዘ መሬት የለም። እንደሚታወቀው የሃይለሥላሴ መንግሥት በሚለወጥበት ጊዜ ተመሳሳይ የመውረር እንቅስቃሴዎችን ማድረጋቸው ይታወሳል።
ይህ ማለት እኤአ በ1972ቱ የጋራ የሆነ መፍትሄ እስኪመጣ ድረስ በመሬት ላይ ያለው ነባራዊ ሁኔታ (Status quo) ተከብሮ ይቆያል ነው ።ያንን ነባራዊ ሁኔታ ስለጣሱት እኤአ በ1995 የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲከበር አደረገ እንጂ አልፎ ሄዶ የሱዳን ግዛት ውስጥ የገባበት ሁኔታ የለም ።ነገር ግን ትክክለኛው አስተዳደር እንዲጸና በመሬት ላይ ያለው ነባራዊ ሁኔታ (Status quo) አስከብሮ ነው የቆየው ።
ከዛም በኋላ ግጭቶች ሲስተዋሉ ቆይተዋል ።በተለይ ከእርሻ ጋር በተያያዘ ክረምት ሲመጣ የተወሰኑ ግጭቶች አሉ ።እንዲህም ሲባል ትልቅ የማይባሉና አርሶ አደሩ እስር በእርስ የሚደያርጓቸው ግጭቶች ይስተዋሉ ነበር ።ነገር ግን በአገራችን አሁንም ተጨማሪ ሌላ ለውጥ ሲመጣ ካለፈው ሰኔ በፊት ግንቦት አካባቢ በወታደር የተደገፈ እንቅስቃሴ ማድረግ ጀመሩ ።
ይህ በወታደር የተገደፈ እንቅስቃሴ የተደረገበትም ምክንያት የመንግሥት ለውጥ መጥቷል፤ ኢትዮጵያ ሽግግር ላይ ናት ያለችውና የውስጥም ፖለቲካዋም ትክክል አይደለም፤ ስለሆነም ይህን ጉዳይ እንደ እድል ወስደን ጉዳዩን እናስተካክላለን የሚል የተሳሳተ ስሌት ይዘው ነው ።
ግንቦት መጨረሻ ሰኔ አካባቢ ላይ ያንን አደረጉ፤ እሱ ግን መሆን እንደማይገባው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ያለ የፖለቲካ ኮሚቴ ተቋቁሞ ግንቦት ወር ውስጥ አዲስ አበባ ስብሰባ ተካሄደ ።በዚህም ከአካባቢው እንዲገደቡ ተነገራቸው ።ያ ነገር በተወሰነ ደረጃ ጊዜያዊ መፍትሄ ማግኘት ቻለ ።
አሁንም በእሱ አይነት አስተሳሰብ ችግሩ ስላተቀረፈ አገራችን በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የህግ ማስከበር ሂደት ውስጥ በምትገባበት ጊዜ በአካባቢው የነበሩ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አካባቢውን ተቆጣጥሮ እያስተዳደረ ያለው የመከላከያ ሠራዊት ወደትግራይ ክልል ሲያቀና ተከትለው መጥተው ያንን ቦታ ይዘዋል ።ሱዳኖች አሁን እየፎከሩ ያሉት የተያዘብንን መሬት አስመለስን በማለት ነው ።ሱዳኖቹ ጦሩ በሌለበት በጦርነት እንዳሸነፉ ነው እያሰቡ ያለው ።
እና ፉከራውም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ።ሁለተኛው ደግሞ የያዟቸውን ቦታዎች ሰርገው እንደገቡ ከአንድ ወር በፊት የተሰራው ካርታ ላይ የሚያሳይ ነው ።ካርታው ለመረጃ ያህል የሚያገለግል ነው ።በጥቅሉ ሱዳኖቹ ጠባቂ በሌለበት ብዙ ጉዳት አድርሰዋል ።ብዙ ዜጎቻችንን አፈናቅለዋል ።ለሞትም ዳርገዋል ።ንብረታቸውን ዘርፈዋል ።ሀብታቸውን አቃጥለውባቸዋል ።ሴቶችንም እስከመድፈር ደርሰዋልና እዛ አካባቢ በሱዳን ወታደር እየተደረገ ያለው ሁኔታ ተገቢ አይደለም ።
የሱዳን ወታደር ያበላሸው ሁለት ነገር ነው ።እኤአ የ1972 ስምምነትን ሙሉ በሙሉ ነው የጣሰው ።የ1972 ስምምነት ኢትዮጵያ ሳትሆን ሱዳኖች ናቸው ዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ዓለም አቀፍ ሰነድ ነው ብለው ያሳወቁት ።
ለዓለምአቀፍ ያሳወቁትን ሰነድ በዓለም አቀፍ ህግ ጥሰዋል ።ሁለተኛው ስህተት ደግሞ በዜጎቻችን ላይ ጉዳት አድርሰዋል ።በተጨማሪም ደግሞ የወንድማማችነት ወይም የጉርብትና መንፈስ ያልታከለበት ግንኙነት ለመፍጠር ጥረት እያደረጉ ነው ።ነባራዊ ሁኔታውን እየቀየሩ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የሱዳን መንግሥት ችግሩን ለመፍታት የሄደበት መንገድ እንዴት ይገለጻል?
ዳይሬክተር ጄኔራል አብዱራሃማን፡– የሱዳን መንግሥት የድንበሩን ጉዳይ ለመፍታት የሚሄድበት ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ በጉልበት ነው ።በኃይለሥላሴ ውድቀት፣ በደርግ ውድቀትም ሆነ የዛሬ ሁለት ዓመትና አሁን በቅርቡም በተደረገው የህግ ማስከበር ዘመቻ ጊዜ የነበራቸው አካሄድ የጉልበት ነው ።
በዚህ አካሄዳቸው የሚሳካላቸው ይመስላቸዋል ።ምክንያቱም እንደሚታወቀው በመርህ ደረጃ ድንበር ማለት በሁለት አገራት መካከል በዘለቄታነት በወዳጅነት እንድትቆዪ፤ ካልሆነም ደግሞ በዘለቄታዊነት በጠላትነት እንድትቆዪ ከሚወስኑ ጉዳዮች አንዱ ነው ።
ስለዚህ ድንበር ደግሞ በዘላቂነት አብሮ ለመኖር የሚለይ ነገር ስለሆነ ጥንቃቄ ይፈልጋል ።ድንበር በተናጠልም ሊወሰን አይችልም፤ በጋራ በመስማማት እንጂ ።ይህ ድንበሬ ነው በማለት ለብቻ ለመወሰን ዓለም አቀፍ መርሁም አይፈቅድም ።ስለዚህ ሁለት አገራት ወይም ከሁለት አገራት በላይ አንድን ድንበር የሚያዋስኑ ከሆነ እነዛ ተዋሳኝ አገራት በጋራ ድንበራችን ነው ሊሉ ይገባል ።
እሱ የሚሆነው ደግሞ አንደኛ በስምምነት ሲለዩ ነው ።በስምምነት ከለዩት በኋላ ደግሞ የለዩትን ቦታ ምልክት ሲያርጉበት ነው ።ምልክት ካደረጉት በኋላ ደግሞ በጋራ ሲያስተዳድሩት ነው ።በምልክቱ ላይ ደግሞ ቁጥጥር ይደረግበታል ።የወደቀ የድንበር ምልክት ካለ ደግሞ ይጠገናል፡፡
አንድ ሉዓላዊ አገር የግዛት ድንበሩ መወሰን ስላለበት ያ ሲወሰን ከሚጋራው አገር ጋር የግዴታ የጋራ የሆነ ስምምነት መኖር አለበት ።ለዚያም ነው እኤአ በ1902 የተፈረመውን ስምምነት ዳግም በመሠረታዊነት ተቀብለን ያሉብንን ችግሮች ደግሞ በጋራ በሁለቱም አገራት ተቀባይነት ባለው መፍትሔ ሃሳብ (Amicable Solution) እንዲፈታ ለማድረግ የተስማማነው።ያንን ስምምነት ነው ሱዳኖቹ ጥሰው በጉልበት ጉዳዩን ለመፍታት እየተንቀሳቀሱ ያሉት፡፡
በኢትዮጵያ በኩል በምናይበት ሰዓት እንደሚታወቀው ከድንበር ውዝግቡ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ ትዕግስት እስከመቶ ዓመት አኑሮናል ።ምክያቱም በአፄ ምኒልክ መንግሥትም ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድና በድርድር ለመፍታት ብዙ ጥረት አድርገዋል ።በአፄ ኃይለስላሴ ዘመንም በጣም ጥልቅ የሆኑ ውይይቶች ተካሂደዋል ።
ጉዳዩን ለመፍታትም በሁለቱም አገራት ተቀባይነት ባለው መፍትሔ ሃሳብ (Amicable Solution) ብቻ ነው መፈታት ያለበት የሚል ድርድር ላይ ተደርሶ፤ ያንን ነገርም የሱዳንን መንግሥት አሳምኖ እኤአ በ1972 የተደረሰበትን ስምምነት ወይም ደግሞ የማስታወሻ ልውውጡን ካሳመነ ውጤታማ ሆኗል ማለት ነው፡፡
ስለዚህ ይህ የኢትዮጵያን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ።አንደኛ ጉዳዩን በጉልበት ለመፍታት አልሄደበትም ።በድርድር፣በውይይት እንዲሁም በባለሙያዎች እንዲፈታ በአፄ ምኒልክም ሆነ በአፄ ኃይለሥላሴ እንዲሁም ደርግም የራሱ የሆነ ክፍተት የነበረበት በመሆኑ በጥልቀት ባይሄድበትም ከደርግ ውደቀት በኋላ በነበረው ጊዜ እኤአ ከ2002 እስከ 2008 አካባቢ ባሉት ጊዜያትም የጋራ ድንበር ኮሚሽን ተቋቁሞ የጋራ ልዩ ኮሚቴ ተቋቁሞ የጋራ ድንበር ኮሚቴ ልዩ የቴክኒክ ኮሚቴ ተቋቁሞ ስራቸውን ሲሰሩ ቆይተዋል ።ሁሉም የየራሳቸውን ተግባር በየፊናቸው ሲያከናውኑ ቆይቷል፡፡
ነገር ግን የጋራ ልዩ ኮሚቴው በሁለቱም አገራት ተቀባይነት ያለው መፍትሔ ሃሳብ (Amicable Solution) ባለማምጣቱ የጋራ ድንበር ኮሚቴው ያንን የድንበር ማካለሉን ተግባር መሬት ላይ ማውረድ አልቻለም ።
ወደ ድንበር ማካለሉ ሊገባ የሚችለው እንደቅድመ ሁኔታ የሚወሰደው የልዩ ኮሚቴው ከዳግልሽ ተራራ በስተ ሰሜን የእነዛ ኢትዮጵያውያን እጣ ፈንታ ሲለይ እና የኢትዮጵያና የሱዳን የድንበር ወሰን እዚህ ዘንድ ነው ተብሎ ሲወሰን ይህ ያልኩሽ የድንበር ኮሚሽን ይመጣና የዛን ውሳኔ ምልክት ያደርጋል ።ከዛ በኋላ ነው ወደ ድንበር ማስተዳደሩ ሥራ መገባት የሚቻለው፡፡
ስለሆነም ኢትዮጵያ ለዘመናት ያደረገቻቸው ጥረቶች በዲፕሎማሲ፣ በባለሙያዎች እንዲሁም በቴክኒክ ጉዳይ እንዲፈታ ነው ።ምክንያቱም የድንበር ጉዳይ ለረጅም ጊዜ በሰላም እንድትኖሪ የሚወስን ነውና በሰላም ለመኖር ደግሞ በጋራ እኩል በሆነ መንገድ መፍትሄ ማስቀመጥ ሲቻል ነው ።
ስለዚህ ዛሬ ድንበሬ እዚህ ድረስ ነው በማለት የያዙትን መሬት በጉልበት ማጽናት አይችሉም ።ምክንያቱም ዜጎቻችንን ያሉት እዛ ነው፤ በተጨማሪም የድንበር ወሰናችን ደግሞ እኛ ፈቅደን የለየነው ባለመሆኑ ኢትዮጵያ አልተቀበለችውም ።
አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ ይህ የሱዳን አካሄድ ከዓለም አቀፍ ሕግ አንጻር ሲታይም ተቀባይነት የሌለው ነው ማለት ነው ?
ዳይሬክተር ጄኔራል አብዱራሃማን፡- አካሄዷ ሙሉ ለሙሉ ዓለም አቀፍ ህግን የጣሰ ነው። ሱዳን ራሷ የተቀበለችውን፣ ወደተባበሩት መንግሥታት ያቀረበችውንና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ያስተዋወቀችውን ስምምነት ነው የጣሰችው ።ስለዚህም ራሳቸውን ያስተዋወቁትን ሰነድ በጭራሽ ሊጥሱት አይገባም ።
አካሄዳቸው ግን ህግን እየጣሱ ስለመሆናቸው የሚያሳይ ነው ።ምክንያቱም በሁለቱም አገራት ተቀባይነት ያለው የመፍትሔ ሃሳብ (Amicable Solution) እናምጣ ማለት ከጉልበት መፍትሄ ጋር ሊስተካከል የሚችል ነገር እንዳልሆነ ግልጽ ነው ።
በቀጣይ እኤአ የ1972ቱን ስምምነት ማክበርና ወደትግበራ መግባት ነው የሚበጀው ።ወደትግበራ ለመግባት ደግሞ በሱዳን በኩል ያለው የፖለቲካ ቁርጠኝነት ወሳኝ ነው ።የፖለቲካ ቁርጠኝነት ሲባል ደግሞ ዝም ብሎ በባዶ ሜዳ መፎከር አይደለም ።ምክንያቱም ድንበር በፉከራ አይረጋገጥም።
ዛሬ በጉልበት የያዙትን ድንበር ማጽናት በፍጹም አይችሉም ።እሱ አማራጭ ደግሞ ማንም እጅ ላይ ሊኖር ቢችልም ዘለቄታዊ መፍትሄ ሊያመጣ ስለማይቻል ማንም አይቀበለውም ።
እኛ ኢትዮጵያውያንም እሱን መንገድ አንመርጠውም ።ኢትዮጵያ በጉልበት ብታደርገው ኖሮ ቀድማ ታደርገው ነበር ።ምክንያቱም መቶ ዓመት ያህል ስንቆይ ያንን አማራጭ የመጠቀም እድሉ ነበረን ። በእርግጥ ለወደፊቱም ዝግ ላይሆን ይችላል፡፡
ዋናው ነገር የድንበር ጉዳይ የሚፈታው በሰላም ነው ።ዓለም አቀፍ መርሁንና ህጉን ተከትሎ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ነው ሊፈታ የሚችለው እንጂ ህግን በጣሰ መንገድ ሊሆን አይችልም ።ያኔ የሁለቱ አገራትን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ ይቻላል ።የሁለቱ አገራት ህዝቦችን ርዕይ እውን ያደርገዋል ።
እንደዛ ካልሆነ ለሦስተኛ ወገኖች አላስፈላጊ የሆነ እድል እንደመስጠት ይሆናል ።እኛ እርስ በእርስ እየተተናኮስንና እየተባላን በምንሄድበት ወቅት ትኩረታችን በዚህ ጉዳይ ላይ ከመሆኑም በተጨማሪ ራዕያችን እየከሸፈ ይመጣል ።
በአካባቢው ላይ ለመንገስ የሚፈልግ አካል ካለ ደግሞ ለብቻው እየጎላ ይወጣል ።በአካባቢው ላይ ያለውን የተፈጥሮ ሀብት በግል ለመጠቅለል የሚፈልገው አካል እድል ይሰጠዋል ።ከዚህ ሌላ ለሱዳን ህዝብ ምንም ትርፍ የለውም፤ ለመንግሥቱም አይጠቅምም ።ይህንን ደግሞ የሱዳን ህዝብ በውል ይገነዘበዋል ።መንግሥቱ ግን ጊዜያዊ የሆነ የፖለቲካ ጥቅም ለማግኘት ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ሱዳን ሁልጊዜ ኢትዮጵያ በሆነ ጉዳይ ተይዛለች ብላ በምታስብበት በዚያ ወቅት ለወረራ የመነሳሳቷ ነገር ምክንያቱ ምንድን ነው ?
ዳይሬክተር ጄኔራል አብዱራሃማን፡- እውነቱን ለመናገር የጦር ኃይሎቹም ስለጦርነት ሳይንስ በውል ያውቁታል ።ሳያውቁት የጦር መሪ ሊሆኑ አይችሉም ።ጦርነት ምን ያህል አዋጭ ይሁን አይሁን ይረዱታል ።ማንኛውም አይነት ጦርነት ትርፉ ኪሳራ እንጂ ውጤት የለውም ።ስለሆነም የእነርሱ ስሌት በአግባቡ የህዝባቸውን እሴቶች ወይም ደግሞ የመልካም ጉርብትናን እሴቶች ካልሆነ ደግሞ የኢትዮጵያን ህዝብ እና መንግሥት አቋምና አመለካከት በውል አለመገንዘብ ነው ።
ምንም ጊዜ የትኛውም አገር የቱንም ያህል ቢደክም ወራሪን ከራሱ ላይ ለመመከት አያንስም ።ስለዚህም የሱዳን ስሌት ተገቢ አይደለም ።ምክንቱም የጦርነትን ሳይንስ የሚያውቅ አካል በጦርነት መፍትሄ አመጣለሁ ማለቱ ትክክል አይደለም ።ጦርነት ደግሞ ምናልባት የመጨረሻው መፍትሄ የሚባለው አይነት ነገር ነው ።
እንዲያም ቢሆን ተገዶ የሚገባበት እንጂ በአማራጭነት የሚያዝ አይደለም ።ስለሆነም ወደጦርነት መሄድ ተገቢም አግባብነት ያለውም ስሌት አይደለም ። ጦርነት የኢትዮጵያን እና የሱዳንን መንግሥትን እሴት የማይመጥን ነው ።የቱንም ያህል ደግሞ ኢትዮጵያ ደካማ ብትሆን ጠላቶቿን ከላይዋ ለመመከት አቅም ያንሳታል የሚል እምነት የለኝም ።
አዲስ ዘመን፡- ሱዳኖቹ ኢትዮጵያ በሌላ ነገር ስትጠመድ አድፍጠው የመምጣታቸው ነገር ኢትዮጵያን ከመፍራት የመነጨ ነው ማለት ያስችል ይሆን ?
ዳይሬክተር ጄኔራል አብዱራሃማን፡– እውነት ለመናገር እንደሱ ለመገመት ይከብደኛል ።አንዳንድ ጊዜ ፈሪም እኮ ይተናኮሳል ።ለምን ቢባል ሆነ ብሎ ተንኳሽ አድርጎሽ ከዛ በኋላ ተነካሁ ማለትም ይመጣል ።
ነገር ግን የግሌን ሐሳብ ስነግረሽ እንዲህ ስንዳከም ተጋላጭ ሊያደርጉን አንደኛ በውስጥም ችግር አለ፤ ከውጭም የሆነ ምክንያት ስንከፍትባቸው በአካባቢው ላይ የኢትዮጵያን ገጽታ በመጥፎ ለመገንባት ከሚደረግ ጥረት ባለፈ ትርጉም የለውም ።
ቀላል ምሳሌ ላነሳልሽ የምችለው፤ በአገር ውስጥ የህግ ማስከበር መካሄዱ ይታወቃል ።መልሰው መላልሰው መሳሪያም ተኮሱ፤ የተወሰኑ መሬቶችንም ያዙ ።ኢትዮጵያ ወደዛ ብትገባ ደግሞ አገር ውስጥም አላስፈላጊ የሆኑ እንቅስቃሴዎች ቀጣናው ላይ አላስፈላጊ የማሸማቀቅ ጫናዎች ከማምጣት በዘለለ ምንም ትርጉም የለውም ።
ለዚህም የኢትዮጵያ መንግሥት የሚሄድበት አግባብ እጅግ ብልህነት የተሞላበት ነው ።ይህን የኢትዮጵያ መንግሥት ብልህነት የተሞላበት አካሄድ የሱዳንም መንግሥት ያልጠበቀው ነው ።እንዲያውም የሱዳንን መንግሥት ከመጠን በላይ ያበሸቀውም በተጨማሪም ሦስተኛ ወገኖች የተባሉትንም አካላት ምኞትና ዓላማ ያላሳካ፤ ነገር ግን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ያላስደፈረ እንቅስቃሴ በማድረግ ያለ ጥሩ አካሄድ ነው ።
አዲስ ዘመን፡- ሱዳን ራሷ በውስጧ ያልፈታችው ችግር አለና ጊዜው በራሱ የሱዳንን ወቅታዊ ሁኔታ ያገናዘበ ነው ተብሎ ይታሰባል ?
ዳይሬክተር ጄኔራል አብዱራሃማን፡– ያገናዘበ አይደለም ።ምክንያቱም የድንበርን ጉዳይ ለመፍታት ቢያንስ ጉዳዩን እፈታዋለሁ ብሎ የሚንቀሳቀሰው አካል ከሽግግር መውጣት መቻል አለበት ።በሽግግር መንግሥት ውስጥ ሆኖ የሁለቱን አገራት ዘለቄታዊ እጣ ፈንታ የሚወስን ነገር ላይ ተወያይቶ መፍትሄ ለመስጠት አሁን ወቅቱ አይደለም ።
ምክንያቱም ከሽግግር መንግሥት ወጥተው ትክክለኛ መንግሥት ሲያቋቁሙ ነው ያ መንግሥት ተደራድሮ ጉዳዩን ሊፈታ የሚችለው ።ለዚህ ነገር ዘለቄታዊ መፍትሄ ለማምጣት በትክክል መንግሥት ተመስርቶ እንጂ በሽግግር መንግሥት በዚህ አይነት ሁኔታ የሚሆን አይደለም ።እውነት ለመናገር አጀንዳም መሆን አይችልም ።
አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ ይህ አካሄድ የሱዳንን ዘላቂ ጥቅም አደጋ ውስጥ ሊጨምረው ይችላል ማለት እንችላለን ?
ዳይሬክተር ጄኔራል አብዱራሃማን፡– በሚገባ እንጂ፤ አንደኛ ጥቅም ብለን የምንለው ፖለቲካዊ መረጋጋቱን ነው ።በተጨማሪ ደግሞ ኢኮኖሚውም ማንሰራራት መቻል አለበት ።ህዝቡ ከድህነቱና ከዋጋ ግሽበቱ መውጣት መቻል ይኖርበታል ።
ይህ ነገር እስከቀጠል ድረስ ቀውሱም አብሮ የሚቀጥል ነው የሚሆነው ።ስለዚህ ይህ አካሄዱ የሱዳንን ህዝብ ጥቅም አላስጠበቀም ማለት ነው ።የሱዳን ህዝብ ዛሬ ዳቦ፣ መድኃኒት፣ ነዳጅ እያለ እየጠየቀ ባለበት ሁኔታ ያቀረበው ጥያቄ ሰሚ አግኝቶ ካልተፈታለት ምኑን ጥቅም አገኘ ይባላል ።
አዲስ ዘመን፡- ችግሩ ለዘለቄታው ለመፍታት ያለው አማራጭ ምንድን ነው ይላሉ ?
ዳይሬክተር ጄኔራል አብዱራሃማን፡– ቀደም ሲል እንደጠቀስኩልሽ ሁለቱ አገራት እኤአ በ1972 ተስማሙ ባልኩሽ የማስታወሻ ልውውጥ በግልጽ ምን ምን መደረግ እንዳለባቸው አስቀምጧል ።ለምሳሌ ኮሚቴዎች ተቋቁመዋል ።የጋራ የሆነ ልዩ ኮሚቴ ተቋቁሟል፤ ሱዳኖች ይህንን አይፈልጉትም ።
የልዩ ኮሚቴው ስም እንዲነሳ አይፈለጉም ።ኢትዮጵያና ሱዳን እንዳልኩሽ ስምንት ስብሰባዎችን በጋራ አድርገናል ። ስለዚህ ሱዳኖቹ ያንን ስብሰባ አስቀጥለው በሁለቱም አገራት ተቀባይነት ያለው የመፍትሔ ሃሳብ (Amicable Solution) ማክበርና ማምጣት ይጠበቅባቸዋል ።ይህም ማለት ከዳግልሽ ተራራ በስተሰሜን ያለው ቦታ ላይ፡፡
ከዳግልሽ ተራራ በስተደቡብ ያለውን ቦታ በማንኛውም ሰዓት ማድረግ ይቻላል ።በዛ በኩል ያሉት ችግሮች በጣም ዝቅተኛ ናቸው ።አንደኛ የ1972ቱ ስምምነት በራሱ በተራራዎቹ አናት እንዲያልፍ ፈቅዶላቸዋል ።ሁለተኛ ደግሞ የተወሰነ ችግር እንኳ ቢኖር ሊፈታ የሚችል ነው ።
ምክንያቱም አብዛኛዎቹ የድንበር ወሰኖቹ በተራራ ወይ በወንዝ ወሰን የተደረገላቸው ሲሆኑ የጎላ ችግር የለባቸውም ።ከዳግልሽ ተራራ በስተሰሜን ያለው ግን በርካታ ህዝብ ያለበት ነው ።ብዙ ኢትዮጵያውያን ከአንድ ምዕተዓመት በላይ ያሉበት አካባቢ ነው ።
አንድ መታወቅ ያለበት ነገር ቢኖር በሁለቱም አገራት ተቀባይነት ያለው የመፍትሔ ሃሳብ (Amicable Solution) እስኪመጣና ድንበሩ እስኪለይ ድረስ ቦታው የሱዳን ግዛት ውስጥ ወይም የኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ነው ማለት አይቻልም ።
ማለት የሚቻለው ውዝግብ ያለበት ድንበር ነው ።ነገር ግን በህግ የተደገፈና እውቅና ያለው ውዝግብ ያለበት ድንበር ነው ማለት ይቻላል ።እውቅና የሰጠው ደግሞ እኤአ የ1972ቱ ስምምነት ነው፡፡
ለምሳሌ በሌሎች አገራት መካከል ያለውን የድንበር ውዝግብ ማንሳት እንችላለን ።ኢትዮጵያንና የሱዳንን ያህል በህግ የተደገፈ አይደለም ።በትንሹ ግብጽ ከሱዳን የወሰደችውን ወደ ሃያ ሺህ የሚጠጋ ካሬ ኪሎ ሜትር መሬት የኛ ወደ ሦስት ሺህ ካሬ ኪሎ ሜትር አካባቢ ብትሆን ነው፤ ወይም ደግሞ ሦስት ሺህ ስኩዌር ኪሎ ሜትር ነው ።
ስለዚህ በግብጽ በኩል ያለውን ግብጽ ወስዳ ሚሊታሪውን አስፍራበት የምርጫ ክልል አቋቁማ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ፣ የፓርላማ ምርጫም ስታደርግ የቆየችው ።የእኛ ግን ቦታው ውዝግብ ያለበት ድንበር ሲሆን የኢትዮጵያ ቦታ ስለሆነ የሚገባ ነው ።የኢትዮጵያ ዜጎች ከመቶ ዓመት በላይ ኖረውበታል፤ የኖሩበት ደግሞ የኢትዮጵያ መሬት ነው ።
ይህንን ለማምመጣት በጋራ የተቋቋሙት ኮሚቴዎች በጋራ ተቀምጠው ይወያያሉ፤ ዜጎቹንም በሚመለከት የመፍትሄ ሐሳብ ያቀርባሉ ።የመፍትሄ ሐሳቡ ደግሞ ለመሪዎች ይቀርብና መሪዎቹ ያጸድቁታል ።የጋራ የድንበር ኮሚሽኖቹ ደግሞ በስምምነቱ መሠረት ምልክት ያስቀምጣሉ ።
ስለዚህ ዘለቄታዊ መፍትሄ የሚሆነው ቦታውን በጉልበት ለመያዝ ጥረት ከማድረግ ይልቅ እነዚህ ኮሚቴዎችን ወደሥራ ማስገባትና ስራቸውን እንዲያጠናቅቁ ማበረታታት ነው።
ከዚህ ሁሉ በፊት ግን ሊሆን የሚችለው የሱዳን መንግሥት በተለይ ከህዳር ስድስት በኋላ የያዟቸውን ቦታዎች ለቆ መውጣት ግድ ይለዋል ።እኤአ የ1972ቱን ስምምነት ራሱ ለማክበር የ1972ቱን ስምምነት የደነገገውን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ መግባት መቻል አለበት ።አሁን ሱዳን የያዝኩትን ይዤ እንደራደር ብትል አይሠራም ።
ተቀባይነት የለውም ።ለምን ቢባል የ1972ቱን ስምምነት ላይ በመመስረት ነው እንጂ ስራው የሚሰራው ህጉን በመጣስና አዲስ ነባራዊ ሁኔታ በማምጣት አይደለም ።ይህ በፍጹም ተቀባይነት የለውም ።እሱ ደግሞ ዘላቂ መፍትሄም ማምጣት አይችልም ።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡኝ ሰፊ ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
ዳይሬክተር ጄኔራል አብዱራሃማን፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ ።
አዲስ ዘመን ጥር 21/2013