ወንድወሰን መኮንን
የሀገር ሰላም የሕዝብ ሰላም ነው፡፡ሕዝብ ሰላም የሚሆነው ሀገር ሰላም ውላ ሰላም ስታድር ነው ። የሕዝብና የሀገርን ሰላም ለማናጋት ሆን ብለው ሽብር የሚነዙ፤ ፈጥረው የሚያወሩ በዚህም የነቀዘ የፖለቲካ ፍላጎታቸውን የሚያሳኩ የሚመስላቸው ከንቱዎች ሞልተው ተርፈዋል፡፡የወሬና የአሉባልታ ጦረኞች!! ሀገር በደም መስዋዕትነት የጸናች እንደመሆኗ መጠን በወሬና በአሉባልታ አትፈርስም።
የሽብር ወሬ የሚነዙት ግለሰቦች ለብቻቸው ፈጥረው የሚያወሩት ሳይሆን ከጀርባቸው ያለ ይሄንኑ የሀሰት ወሬ እያደራጀ እየፈበረከ የሚሰጥና የሚለቅ እኩይ አላማን የሰነቀ ኃይል አለ ።ትርፋቸው ሀገርና ሕዝብን ማመስና ማተራመስ ነው ።ምን ተፈጠረ ፤ምን መጣ፤ ምን ሊመጣ ይሆን በሚል የሕዝብን ሰላም ማናጋትና ማስጨነቅ አንዱ ግባቸው ነው ።
በዚሁ እንቶ ፈንቶ የሽብር ወሬያቸው ሕዝቡን ከሥራና ከምርት ወጣቱንም ከትምህርቱ እንዲዘናጋ ተጨንቆ ውሎ እንዲያር ያደርጉታል ።ይሄም አንዱ ሌላው ግባቸው ነው ።በዚህም ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ ትርምስ ሁከት ብጥብጥ ውስጥ እንዲገባ ሰላም እንዲደፈርስ መረጋጋት እንዳይኖር ለማድረግ አቅማቸው የቻለውን ሁሉ ያደርጋሉ ።ያልተጨበጠና የፈጠራ ወሬ ከፍተኛ የመዋጋት አቅምና ችሎታ ያለውን ሠራዊትም ይፈታል። ለዚህ ነው ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው የሚባለው።
በተቃራኒው ጎራ በጠላትነት ያለው ክፍል ሆን ብሎ በተጠናና በታቀደ መንገድ የሚነዛው በአግባቡ የሚጠቀምበትም ራሱን ያቻለ የስነልቦና ጦርነት አይነተኛ መሳሪያ ነው ።ከጦርነት አውደ ውጊያ በመለስ ያለ አሸባሪነት መሆኑ ነው ።ከዋና ግዳጁ ከዋና ስራው እንዲዘናጋ ሆን ተብሎ በተጠና መንገድ በተቃራኒው ክፍል የሞራል ጥንካሬውን ለማላላት የሚጠቀምበት ስልት ነው።
ባልተጨበጡ ወሬዎችና ፕሮፓጋንዳዎች በይሆ ናልና በሆኗል ምናልባታዊ ግምት ሲታመስ ውሎ ሲጨነቅ የሚውለው ሕዝብ ወይንም ሠራዊት በዚሁ ታቅዶ በሚለቀቀው የሀሰት ወሬ የተነሳ ወሳኝ አቅሙ ይሳሳል ።ወሬ በሚገባ የታጠቀን የተደራጀን ሠራዊትም አቅም ይፈታተናል ።የፈረንሳዩ መሪና ጦረኛው ጀነራል ናፖሊዮን ቦናፓርት የጠላቱን ኃይል ለመምታት በሚያደርገው ጠንቃቃ ዝግጅት አስቀድሞ በወኪሎቹ አማካኝነት በጠላቶቹ ላይ አርበድባጅ ሽብር እንዲለቀቅባቸው ያደርግ ነበር ።
አስቀድሞ ጠላቶቹ በስነልቦና ደረጃ እንዲታወኩ እንዲታመሱ አብዝተው እንዲጨነቁ የሚገጥማቸው ሀይል እጅግ የገዘፈ እንደሆነ እንደሚደመስሳቸው አውቀው በፍርሀት እንዲርዱ ያደርግ ነበር ።ጦርሜዳ ፊት ለፊት ገጥመው ተፋልመው ከሚሸነፉት የበለጠ አስቀድሞ በሚነዛው ወሬ የመዋጋት አቅማቸው የሚሰለበውና በወሬ የሚፈቱት ይበልጡም ነበር ።ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው የሚባለውም ለዚሁ ነው ።
ይህ የስነልቦና ጦርነት ራሱን የቻለ ሰፊ መስክና ሙያ ነው ።ሳይኮሎጂካል ዋር ፌር ይሉታል ። ሀገራት ተቃራኒያቸውን ለማንበርከክ በሰፊውና በተለያየ ዘዴ ይጠቀሙበታል፡፡ይህን ተከትሎ መጨበጥ ወይንም ማግኘት የሚፈልጉት ግብ አለ ።ወደ እኛም ሀገር እውነት ስንመለስ ዋናዎቹ የወሬ ሴራው ባለቤቶች ድብቅ ፖለቲካዊ አላማና ግባቸው ያላቸው መሆኑን እንረዳለን ።
ከጀርባ በመሆን እያሴሩ ምንም በሌለበት አቧራ የሚያስነሱ፤ ሕዝብን የሚያሸብሩ ድንጋጤ ውስጥ የሚከቱ፤ ሰላምና መረጋጋትን የሚያደፈርሱ፤ ቁጣን ሊያስነሱ ሊቀሰቅሱ የሚችሉ የፈጠራ ወሬዎችን እየነዙ ሀገር እንዲታመስ የሚያደርጉ እልፍ ሴረኞች እኛም ዘንድ ሞልተዋል ።
አደናቀፈው ሲባል ተሰበረ፤ ተሰበረ ሲባል ተሰነጠረ፤ ከማለት የማይመለሱ አዳራቸው ወሬና አሉባልታ ብቻ የሆኑ ወሬ ፈታዮችና ሸማኔዎች በመዲናችንም ሆነ በየክልሉ ሞልተው ተርፈዋል ።ራሳቸው ወሬ ፈጥረው እንደገናም ጨምረው አባዝተው፤ አስፋፍተው፤ ቅመም ጨምረው አጣፍጠው ሕዝቡን የሚያሸብሩ በእንባ የሚያራጩ ጉድ ጉድ የሚያሰኙ ጉዶች እንደ አሸን የፈሉበት ዘመን ነው ።
እነዚህ አውርቶ አደሮች በላባቸው ሰርተው ለፍተው አይኖሩም ።ምላሳቸው ጤፍ ይቆላል ።ግብርና ታክስ የለባቸውም ።ወሬ ወዳዱ ሁሉ ይገብርላቸዋል ።
ታዋቂ የሀገር መሪዎችን የጦር ጀነራሎችን፤ የፖለቲካ መሪዎችን አርቲስቶችን ወ.ዘ.ተ በል ያላቸውን ተነስተው ሞቷል፤ ቆስሏል፤ ተከቧል፤ ታስሯል ወዘተ በማለት በተደጋጋሚ ግዜያት የሀሰት ወሬዎችን በመንዛት ፈጥኖም ሕዝብ ጆሮ እንዲደርስ በማድረግ በህዝቡ ውስጥ ሽብር ሁከት መደናገጥና ግርግር ፈጥረዋል።
እየፈጠሩም ነው። ተጠያቂነት ሊኖር ግድ ይላል። አለበለዚያ ማንም ፌስቡክና ዩቲዩብ የከፈተ ሁሉ እየተነሳ አስሩን ውሸት ሲወሻክት ሲቀደድ ውሎ ሊያድር ነው ።ሀገርና ሕዝብ ጭብጥ በሌለው ወሬ ሊሸበር ነው ማለት ነው፡ እነሱ ስራቸውን እየሰሩ ተልዕኳቸውን እየተወጡ ነው።
በእኛ ባሕል ውስጥ ገዝፎ የሚታየው አንደ ወሬ ሲሰሙ በስሜታዊነት መሞላት ፤ በእርጋታ አለማመዛዘን፤ ጭራሽም ምንጩን ሳያረጋግጡ በስማ በለው ማስተጋባት፤ ከድምጽ ፍጥነት ወሬውን ጨልፎ ወይንም ነጥቆ በመውሰድ መንዛት የተለመደ ነው ። አንድ ወሬ ምንም ይሁን ምን ከመቅጽፈት ድፍን ሀገርን አካሎ አፍሪካን አዳርሶ ቀይባሕርን አትላንቲክና ሕንድ ውቅያኖስን አቋርጦ አውሮፓና አሜሪካ ይደርሳል።
ይሄን ሁሉ ሀገርና አህጉርን አቆራርጦ ወሬው ለመድረስ በዚህ ዘመን ደቂቃዎች ብቻ ነው የሚፈጀው። ስለዚህ መጀመሪያ ሰክኖ መስማትና እውነት ነው አይደለም የሚለው ማረጋገጥን እያዳበርን መሄድ አለብን። እንደወረደ እንደሰማነው ተቀብሎ ወሬውን መንዛቱና ሀገር ማዳረሱ በስማ በለው መቀባበሉ ይጎዳን እንደሁ እንጂ አይጠቅeንም ።
ይሄ የጠላቶቻችንን ፍላጎትና አላማ ማሳካት ማለት ነው፡፡ እነሱ የሚፈልጉትም ይሄን ስለሆነ። ይሄንን የክፋት ወጥመድና ስራቸውን በቴክኒዮሎጂ በመታገዝ ዘመናዊ ሆኖ በተሰራው የሰውን ድምጽ እንዳለ አድርጎ ከሰውየው መልክ ጋር አቀናብሮ በሚያቀርበው የኮምፒዩተር አፕ በመጠቀም ሰርተው ያሰራጩታል ።
ለምሳሌም ታዋቂውን የቴሌቪዥን ዜና አንባቢ የተመስገን ገብረህይወትን ምስልና ንግግር በራሱ ድምጽ አቀናብረው በዜና ሰዓት ንባቡን እንደሚያቀርብ አስመስለው በመጠቀም ሰበር ዜና ብሎ እንዲጀምር አድርገው እከሌ የሚባለው ሰው ተገደለ፤ ለቤተሰቡ መጽናናትን እንመኛለን ምናምን እያለ ለሕዝቡ በዩቲዩብ ያስተላልፉሉ ።ይሄኔ ሀገር ያለቅሳል ።ያረግዳል ። ባሕላችን በጭካኔ የተሞላ አይደለም ።
ሰፊ ርህራሄና አዛኝነት አለ፡፡ የእኛን ሰው ቅንነት፤ ሰው ወዳድነት፤ ገራገርና ርህሩህነት ፤አልቃሻነት፤ ከዚህ ከሚነዛው የአሸባሪዎች ወሬ ጋር ውስደው ።ድፍን ከተማው መንደሩና ሰፈሩ አሮጊትና ሽማግሌው ወጣቱ በለው ሕጻናቱ ቄሱ በለው ሼሁ በየቤቱ በየመንደሩ በየመሸታ ቤቱ፤ በየቢሮው፤ በእድርና ለቅሶው በየሰርጉ፤በየገጠሩና በየከተማው ወሬው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን በተመለከተ ብቻ ነው። ይሄን ያህል የጠለቀ የሕዘብ ፍቅር ማግኘትም ትልቅ ጸጋና መታደል ነው ።
የሚያለቅሰው የሚያነባው በዛ። የተነዛው ወሬ የውሸት ነው ቢባልም ሕዝቡ አላመነም። ታዲያ ውሸት ከሆነ ለምን ብቅ ብለው አናያቸውም የሚለው እልፍ ጥያቄ አፋጣጭና ሞጋች ነው። አንተስ ክፉ አይንካህ፤ ስንት አዛባ የቤተሰብና የሀገር ሸክም ሞልቶ ተርፎ የለም ወይ ? አሉዋ እማማ ምንትዋብ የሰሙትን ሰምተው።
ለሁሉም ለወሬ የለው ፍሬ ፤ ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው ብለን እናልፈዋለን። በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የተነዛው የሀሰት ወሬ ሆን ተብሎ ሕዝብን ለማሸበር ግጭት ሁከትና ትርምስ ለመፍጠር ተብሎ በጸረ ሰላም ኃይሎች የተቀነባበረ ስልት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። የተፈጠረም የሚፈጠርም ነገር የለም።
አዲስ ዘመን ጥር 21/2013