ወርቁ ማሩ
በአገራችን ለውጡን ተከትሎ በርካታ አወንታዊ ለውጦች የተገኙ ቢሆንም በአንጻሩ በርካታ ፈተናዎችም አጋጥመዋል:: ከነዚህ ፈተናዎችም ውስጥ ዋነኛው ከሰላምና ፀጥታ ጋር የተያያዘው ችግር ነው::
ከዚህ አንጻር ከለውጡ ወዲህ ብቻ 113 ግጭቶች መከሰታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በህዳር ወር በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት መግለፃቸው ይታወሳል:: ከነዚህ ግጭቶችም ውስጥ አንዱ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ያጋጠመው ተጠቃሽ ነው::
ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህም በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በተለይ በመተከል ዞን ተደጋጋሚ ግጭቶች ሲከሰቱ እንደነበር ይታወሳል:: በዚህም የተነሳ መንግስት በአካባቢው ከአንድም ሶስት ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ በማድረግ ችግሩን ከመሰረቱ ለመፍታት ጥረት አድርጓል::
ከዚህም ባሻገር ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ከፍተኛ የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ችግሩን ለመፍታት ያደረጉት ጥረት ሊሳካ አልቻለም:: ይባስ ብሎም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአካባቢው ተገኝተው ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት ባደረጉ ማግስት በርካታ ዜጎች መገደላቸው ይታወሳል::
ይህንንም ተከትሎ መንግስት ችግሩ በተደጋጋሚ የሚከሰትበት የመተከል ዞን የፌዴራል መንግስት ባቋቋመው ጊዜያዊ ኮሚቴ እንዲመራ ተደርጓል:: ሆኖም ኮሚቴው ዞኑን እየመራ ባለበት ሁኔታም ቢሆን ችግሩ ሙሉ ለሙሉ ሊፈታ አልቻለም::
የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚጠቅሱት ችግሩ ውስብስብ የሆነበት ምክንያት ከችግሩ ጀርባ በርካታ የውስጥና የውጭ ሃይሎች በመኖራቸው እንደሆነ ያነሳሉ:: ከዚህም ባሻገር የክልሉ መንግስት ችግሩን ለመፍታት ቁርጠኝነት ይጎድለዋል የሚል አቤቱታ በተደጋጋሚ ይቀርብበታል::
እኛም ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት በክልሉ በተለይ በመተከል ዞን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ምን ይመስላል? የክልሉ መንግስት ችግሩን ለመፍታት ያልቻለበት ምክንያት ምንድነው? በአሁኑ ወቅትስ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ምን ይመስላል ስንል የክልሉን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታደለ ተረፈን አነጋግረናል፤ እንደሚከተለው አቅርበነዋል ::
አዲስ ዘመን፡- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቤኒሻጉል ጉምዝ ክልል በተለይ በመተከል ዞን ከፍተኛ የፀጥታ ችግሮች ይስተዋላሉ፤ ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የክልሉ ምክር ቤት ምን ሲሰራ ነበር፤ አሁንስ ምን እየሰራ ነው?
አቶ ታደለ፡– የክልሉ ምክር ቤት በተሰጠው ህገ መንግስታዊ ስልጣን መሰረት ባሉት አደረጃጀቶች ተቋማትን የመከታተልና የመቆጣጠር ስራዎችን እየሰራ ነው:: በዚህ መሰረት አጠቃላይ በክልሉ ባሉ የሰላም፤ የፀጥታ እና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮችን በተመለከተ በቋሚ ኮሚቴዎች አማካኝነት የክትትልና የቁጥጥር ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል፤ አሁንም እነዚህን በመስራት ላይ ይገኛል::
አዲስ ዘመን፡- በተለይ በምክር ቤቱ እንዲህ አይነት ጉዳዮችን የመከታተል ስልጣን የተሰጠው የክልሉ የህግ እና የዴሞክራታይዜሽን ቋሚ ኮሚቴስ በአካባቢው ያለውን የፀጥታ ሁኔታ በተመለከተ ምን ያህል ክትትል ያደርጋል፤ ሪፖርቶችንስ እንዴት እያቀረበ ነው?
አቶ ታደለ፡- እንደሚታወቀው ቋሚ ኮሚቴው እንዲህ አይነት ሪፖርቶችን ሲያቀርብ በተግባር ቦታው ላይ ተገኝቶ ያሉ ነባራዊ ሁኔታዎችን በማየት፣ ተንትኖ ነው መሆን ያለበት:: አሁን ባለው ሁኔታ ግን ቋሚ ኮሚቴው በየቦታው ተንቀሳቅሶ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ አልቻለም:: ባለፉት ስድስት ወራትም ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት በየቦታው በነፃነት ተንቀሳቅሶ ሪፖርት ለማድረግ የሚያስችል ነባራዊ ሁኔታ አልነበረም::
አዲስ ዘመን፡- የአካባቢው ችግር ግን ያለፉት ስድስት ወራት ብቻ አይደለም?
አቶ ታደለ፡- አዎ፣ እንደተባለው ችግሩ ከስድስት ወራት ያለፈ ነው:: ከመጋቢት 2011 ጀምሮ በዚያ አካባቢ የፀጥታ ችግሮች ነበሩ:: ይህም ችግር በተደጋጋሚ በምክር ቤቱ ውይይት ተደርጎበታል፤ አስተያየትም ተሰጥቶበታል፤ አቅጣጫም ተቀምጦለታል:: ነገር ግን በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት መሄድ ያልተቻለበት ሁኔታ ነበር የነበረው::
አዲስ ዘመን፡- ለምንድነው በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት መሄድ ያልተቻለው?
አቶ ታደለ፡– በዚያ አካባቢ ያለው ችግሩ ዘርፈ ብዙ ነው:: ችግሩ የአስፈጻሚ አካላትና ሌሎች ከጉዳዩ ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያላቸው አካላት እጅም ያለበት ነው:: በዚህም የተነሳ የተለያዩ እርምጃዎች ተወስደዋል:: ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ችግር ያለባቸው የምክር ቤት አባላት እና የምክር ቤት አባል ያልሆኑ አመራሮችም ጭምር ከኃላፊነታቸው ተነስተው ለህግ እንዲቀርቡ የተደረገበት ሁኔታ ነው ያለው::
በዚህ መሰረት ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ በርካታ አመራሮች ላይ እርምጃ የተወሰደበት ሁኔታ ነው ያለው:: ያም ሆኖ ግን ችግሩ አሁንም ሙሉ ለሙሉ አልተፈታም:: ይህ በመሆኑም የፌዴራል መንግስት በክልሉ ውስጥ ገብቶ ችግሩን ለመፍታት ከአንድም ሶስት ጊዜ ኮማንድ ፖስት አቋቁሞ ሲሰራ ነበር፤ አሁንም የመተከል ዞን በልዩ ሁኔታ በፌዴራል መንግስት በተቋቋመው ጊዜያዊ ኮሚቴ እንዲመራ ተደርጓል::
አዲስ ዘመን፡- በዚያ አካባቢ ያለው ችግር ዋነኛ መንስኤ ምንድነው ይላሉ?
አቶ ታደለ፡- በዚህ አካባቢ የተለያየ ፍላጎት ያላቸው አካላት አሉ:: በአንድ በኩል አካባቢው ከሱዳን ጋር ሰፊ ድንበር ይጋራል፤ ከዚህም በተጨማሪ ከክልሎች ጋር ይዋሰናል:: ከዚህም ባሻገር ክልሉ የተለያዩ የተፈጥሮ ሃብቶች ያለበት ነው:: ሰፊ መሬት እና የተለያዩ ማእድናት ጭምር በስፋት ያለበት ክልል ነው:: ይህንን ለግል ፍላጎታቸው ማሳኪያነት ለመጠቀም የሚፈልጉ ሃይሎች አሉ::
ከዚህም ባሻገር አካባቢው የታላቁ ህዳሴ ግድብ መገኛ ቦታ እንደመሆኑም የውጭ ሃይሎች በዚህ አካባቢ የራሳቸው ፍላጎት አላቸው:: በዚህ የተነሳ ከውስጥም ሆነ ከውጭ ሃይሎች የተለያዩ ፍላጎቶች ይንፀባረቃሉ::
እነዚህ የራሳቸው ድብቅ አጀንዳ ያላቸው የውስጥም ሆኑ የውጭ ሃይሎች ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም አካባቢውን ለማተራመስ የሚጥሩበት ሁኔታ አለ:: ስለዚህ የጥፋት ሃይሎችን አደራጅተው ለእኩይ ዓላማ የሚያውሉበት ሁኔታ ነው በአካባቢው ያለው:: ስለዚህ ይህንን የሚሰሩ ሃይሎች ህዝቡን ባልተገባ መንገድ ለችግር የዳረጉበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው:: እነዚህ ናቸው ዋና ዋና መንስኤዎች::
አዲስ ዘመን፡- በተለይ በአካባቢው ከነባር ብሄረሰቦች በተጨማሪ ሌሎች በርካታ ብሄረሰቦችም ይኖራሉ፤ የክልሉ መንግስት ደግ የነዚህን ዜጎች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ማስጠበቅ ይኖርበታል:: ሆኖም የክልሉ መንግስት ይህን ማድረግ አልቻለም፤ ለዚህ ደግሞ የክልሉ ህገመንግስት ጭምር ከክልሉ ነባር ብሄረሰቦች ውጭ ያሉ ዜጎችን መብት የማያስጠብቅ መሆኑ ለችግሩ መባባስ ምክንያት ነው የሚሉ አሉ:: ለአብነትም ከመሬት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ መሬትንና የተፈጥሮ ሃብትን መጠቀም ያለበት የክልሉ ነባር ህዝብ ብቻ ነው የሚል አንቀጽ መኖሩን ይጠቅሳሉ:: በዚህ ላይ የእርስዎ ሃሳብ ምንድ ነው?
አቶ ታደለ፡- ይህ በተለያየ ጊዜ ይነሳል፤ ከክልሉ ውጭ ያሉ ብሄረሰቦች መብት እየተከበረ አይደለም የሚሉ አሉ:: የክልሉ ህገ መንግስት አግላይ ነው የሚሉ አሉ:: ነገር ግን የችግሩ ምንጭ ይህ አይደለም:: አሁን ለተፈጠረው የሰላም መደፍረስ ተጠቂ እየሆኑ ያሉት ከሌሎች ክልሎች የመጡ ብሄረሰቦች ብቻ አይደሉም:: የአካባቢው ነባር ብሄረሰቦች ጭምር ተጎጂ የሆኑበት ሁኔታ ነው ያለው::
ከዚህም በላይ ግን እየተጎዱ ያሉት ኢትዮጵያውያን ናቸው:: ስለዚህ ይህ ሃሳብ ሚዛን የሚደፋ አይደለም:: በአካባቢው ላይ ያሉ ነባር የሚባሉ ብሄረሰቦችም በእጅጉ እየተጎዱ ያሉበት ሁኔታ ነው ያለው:: ዋነኛ ችግሩ በቆዳ ቀለም ላይ ተመስርቶ ነው እየተፈጠረ ያለው እንጂ በዘር ላይ የተመሰረተ አይደለም:: በተለይ በመተከል ሰዎች ጉዳት እየደረሰባቸው ያለው በቆዳ ቀለማቸው ተለይተው ነው::
አዲስ ዘመን፡- በተለይ በአማራ ብሄረሰብ ላይ ነው ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ያለው የሚል መረጃ በተደጋጋሚ ይወጣል፤ ይህ ትክክል አይደለም?
አቶ ታደለ፡- ትክክል ነው:: እዚያ አካባቢ የአማራ ብሄረሰብ ተጎጂ ነው:: ነገር ግን የሺናሻ እና የኦሮሞ ብሄረሰቦችም በእጅጉ ተጎጂ ናቸው:: በተለይ እነዚህ ሶስቱ ብሄረሰቦች በቆዳ ቀለማቸው ተመሳሳይ በመሆናቸው የደረሰባቸው ጉዳትም ተመሳሳይ ነው:: ስለዚህ ዋነኛ ችግሩ ከህገመንግስት ወይም ከሌላ ጋር ተያይዞ ሳይሆን ከቆዳ ቀለም ጋር ተያይዞ ነው ጥቃት እየደረሰ ያለው:: ከዚያም አልፎ የፀረ ሰላም ሃይሉን ድርጊት የሚቃወሙ የጉምዝ ብሄረሰብ አባላትም የዚህ ጥቃት ሰለባ የሆኑበት ሁኔታ አለ ::
ችግሩን ለመፍታት የተለያዩ አደረጃጀቶች ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል:: ለምሳሌ የሃገር ሽማግሌዎች እና ሴቶች ችግሩን ለመፍታት ተደራጅተው የተንቀሳቀሱበት ሁኔታ ነበር:: ነገር ግን በነሱም ላይ ጭምር ጉዳት ሲደርስ የነበረበት ሁኔታ ነበር የነበረው:: ስለዚህ ጉዳዩ የፀረ ሰላም አላማን በሚደግፉና በማይደግፉ መካከል ያለ ነው ማለት ይቻላል:: ችግሩ እየተፈጠረ ያለው በዚህ መንገድ በመሆኑ አጠቃላይ ሁኔታውም በዚህ መልኩ ቢወሰድ የተሻለ ነው የሚል እምነት አለኝ:: እኔ በግሌ የዚያ አካባቢ ተወላጅ እንደመሆኔና ችግሩንም በቅርበት እየተከታተልኩ እንደመሆኑ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በአግባቡ እገነዘባለሁ::
አዲስ ዘመን፡- አሁን ብዙ ሰዎች ሲናገሩ በዚህ ችግር ውስጥ አብዛኛው የክልሉ አመራርና የክልሉ የፀጥታ መዋቅር እጅ አለበት ይላሉ:: ችግሩም መፍታት ያልተቻለው በየደረጃው ያለው አመራር ስለተሳተፈበት ነው ይላሉ:: እርስዎ ምን ይላሉ?
አቶ ታደለ፡– ችግሩ እንዳይፈታ የሚፈልጉ ሃይሎች ስለመኖራቸው ከላይ ገልጫለሁ፤
አዲስ ዘመን፡- ስፋቱ ምን ያህል ነው የሚለውን እንዲመልሱልኝ ነው፤
አቶ ታደለ፡– ጉዳዩ በየደረጃው ያለው አመራር የተሳተፈበት ነው:: ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ክልል ድረስ ያሉ ከፍተኛ አመራሮች በጉዳዩ ላይ እጃቸው አለበት:: የቀበሌ፣ የወረዳ እና የዞን አመራሮች ጭምር በጉዳዩ ላይ በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ የተሳተፉበት ሁኔታ ነው ያለው:: ከዚህም አልፎ በጉዳዩ ላይ የተሳተፉ የክልል ምክር ቤት አባላት አሉ:: ለዚህም ነው ችግሩን ከስር ከመሰረቱ ለመፍታት ያልተቻለው:: ምክንያቱም በተለይ የወረዳና የቀበሌ አመራር በህዝብ ውስጥ ያለ በመሆኑ በቀላሉ ለመለየትና እርምጃ ለመውሰድ አስቸጋሪ ነው::
በዚህ ውስጥ የሚሳተፉ የታችኛው መዋቅር ውስጥ ያሉ አመራሮችን ሁኔታ ስንመለከት አንዳንዱ ሆን ብሎ የሃሳቡ ደጋፊና ተጋሪ ሆኖ ሲሆን ከፊሉ ደግሞ ተገዶ በጫና የነዚያ የፀረ ሰላም ሃይሎችን እቅድ የሚያስፈጽም ነው:: ወደ ከፍተኛ አመራሩ ሲመጣ ደግሞ በአብዛኛው የአስተሳሰቡ ተሸካሚ ሆኖ ነው:: ይህ ደግሞ ከግል ጉዳይ ወይም ከስልጣን ጥማት ጋር ተያይዞ ሊሆን ይችላል:: በዚህ የተነሳ የሃሳቡ ተጋሪ የሚሆንበት ሁኔታ አለ:: በአጠቃላይ ግን በታችኛው መዋቅር ውስጥ ችግሩ በጣም ሰፊ ነው::
አዲስ ዘመን፡- እስካሁን በሄዳችሁበት ሂደት ምን ያህል ሰዎች ናቸው ተጠርጥረው በህግ ጥላ ስር የዋሉትና ከሃላፊነታቸው የተነሱት?
አቶ ታደለ፡– ችግሩ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ሰዎች በህግ ተጠያቂ ሆነዋል:: ለምሳሌ የቀድሞው የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርን ጨምሮ የቢሮ ሃላፊዎች፣ የፀጥታ ዘርፍ አመራሮች፣ ዳይሬክተሮች፣ የዞን እና የወረዳ አስተዳዳሪዎች እንዲሁም የቀበሌ ሊቃነመናብርት ጭምር ተጠያቂ የሆኑበት ሁኔታ አለ:: ከዚህም ባሻገር አራት የምክር ቤት አባላት ያለመከሰስ መብታቸው ተነስቶ በህግ ጥላ ስር የዋሉበት ሁኔታ አለ:: ስለዚህ በርካታ አመራሮች ናቸው በዚህ ጉዳይ ተጠያቂ የሆኑት::
አዲስ ዘመን፡- በቁጥር ምን ያህል ሰዎች ናቸው ተጠያቂ የተደረጉት?
አቶ ታደለ፡– ከምክር ቤት አባላቱ ውጭ አሁን ይህንን ያህል ናቸው ለማለት አልችልም:: ምክንያቱም በርካታ ሰዎች ናቸው በቁጥጥር ስር የዋሉት::
አዲስ ዘመን፡- ምክር ቤቱ ራሱ ይህንን ችግር በቁርጠኝነት ለመፍታት ምን ያህል ዝግጁ ነው?
አቶ ታደለ፡- እንግዲህ እንደሚታወቀው ይህ ስራ በዋናነት የአስፈጻሚው አካል ስራ ነው:: የምክር ቤቶች ስራ በዋናነት ህግ የማውጣት እና የወጡ ህጎችን የመከታተል ነው:: ነገር ግን ችግሩ የአስፈጻሚው ብቻ ነው ብለን አልተውንም::
እኔ ከራሴ ጀምሮ ችግሩ እንዲፈታ ከክልል ጀምሮ በጣም በርካታ ሰዎች ደፋ ቀና እያልን ነው:: ከዚህም አልፎ የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው:: ለምሳሌ በክልሉ ሶስት ጊዜ የኮማንድ ፖስት ተቋቁሞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል ነገር ግን ሰላማዊ ዜጎችና ፀረ ሰላም ሃይሎችን ለመለየት ስላልተቻለ ችግሩን በቀላሉ መፍታት አልተቻለም:: ስለዚህ ይህንን ጉዳይ ለምክር ቤት ወይም ለአስፈጻሚ አካል ብቻ የምንተወው ሳይሆን የሁሉንም ርብርብ የሚጠይቅ ነው::
ከፌዴራል ጀምሮ የፌዴራል ፀጥታ አካላት፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፌዴራል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ ወዘተ እየተረባረቡ ነው:: ስለዚህ ይህ ስራ የምክር ቤት ነው፤ ይህ የአስፈፃሚ አካል ነው፤ ወዘተ ተብሎ ተለይቶ ሳይሆን ሁሉም እየተረባረበበት ያለበት ሁኔታ ነው ያለው:: በዚያ መንገድ ነው እየተሰራ ያለው::
አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ የተቋቋመው ጊዜያዊ ኮሚቴ በመተከል ዞን ለብዙ ጊዜ ወደፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ጭምር ታስረው የነበሩ ዜጎች መኖራቸውን ይፋ አድርጓል፤ ከዚህ አንጻር ክልሉ በአጠቃላይ ከመልካም አስተዳደር አንጻር እንዴት እየሰራ ነው?
አቶ ታደለ፤– በቅርቡ ኮማንድ ፖስቱ ጉዳያቸው በአግባቡ ወደህግ ያልቀረበ 644 ሰዎች መኖራቸውን አረጋግጧል:: ይህ ትክክል ነው:: ችግሩ አለ:: የችግሩ መንስኤ ግን የክልሉና የፌዴራል መንግስት ቅንጅት ማነስ ውጤት ነው:: እንደሚታወቀው በአካባቢው ያለው ችግር ከመጋቢት 2011 ዓ.ም ጀምሮ ነው:: በዚያ ችግር ውስጥ በርካታ ሰዎች ተይዘው ማረሚያ ቤት የገቡበት ሁኔታ ነበር::
በወቅቱም ችግሩ የብሄር መልክ ስለነበረው ይህንን ጉዳይ የፌዴራል መንግስት ማየት አለበት ከሚል መንፈስ የተከሰተ ነው:: በዚህ የተነሳ ይህንን ጉዳይ የፌዴራል መርማሪዎች እና የፌዴራል ተዘዋዋሪ ችሎት ማየት አለበት በሚል ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የፌዴራል መንግስት አካላት ጋር በነበሩ መጓተቶች የተከሰተ ችግር ነው::
በዚህ መካከል እነዚህ ዜጎች ወደፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በርካታ ጊዜ በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ ተደርጓል:: በዚህ የተነሳ አንዳንዱ ጉዳይ እስከ ሁለት ዓመት ድረስ፤ አንዳንዱ ደግሞ ከዚያ በታች የቆየ ነው:: በአጠቃላይ ግን ይህንን ጉዳይ የክልሉ መንግስት ብቻውን ሊፈታው የሚችለው አልነበረም:: ለዚህ ነው ችግሩ ሳይፈታ ረጅም ጊዜ የቆየው:: ነገር ግን አሁን ችግሩ እየተፈታ ነው::
አዲስ ዘመን፡- አሁን ባለው ሁኔታ ክልሉ ችግሮችን ለመፍታት ከአጎራባች ክልሎችም ሆነ አዲስ ከተቋቋመው የፌዴራል መንግስት ጊዜአዊ አስተዳደር ጋር ምን ያህል ተናቦ ይሰራል?
አቶ ታደለ፡– አሁን ባለው ሁኔታ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባቋቋሙት ኮማንድ ፖስት አማካኝነት ችግሩን ሙሉ ለሙሉ ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው:: ኮሚቴው የአማራና የኦሮሚያ ክልሎች ተወካዮችንም ያካተተ ሲሆን ችግሩ እስከተከሰተበት ቀበሌና ወረዳ ድረስ ወርዶ ተንቀሳቅሶ እየሰራ ነው:: አሁን ኮሚቴው ከአንድ ወር በላይ ሆኖታል:: በአሁኑ ወቅትም በተጨባጭ ለውጦች እየመጡ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው::
አሁን ሰላም የሚፈልጉና በችግሩ የተነሳ ጫካ የገቡ ዜጎች ወደቦታቸው እየተመለሱ ነው:: ከዚህ ውጭ ሰላማዊ ሁኔታ የማይፈልጉ ሃይሎች ደግሞ በፀጥታ ሃይሎች እርምጃ እየተወሰደባቸው ይገኛል:: በዚህ የተነሳ በተለይ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ችግሮች እየተቃለሉ መጥተዋል::
አዲስ ዘመን፡- ምክር ቤቱስ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ምን እያደረገ ነው?
አቶ ታደለ፡– ምክር ቤቱ ብቻውን ሳይሆን ከታችኛው መዋቅር ጀምሮ እስከ ላይ ድረስ በፌዴራል መንግስት ከተቋቋመው ጊዜያዊ ኮሚቴ ጋር በጋራ እየተንቀሳቀሰ ነው እየሰራ ያለው:: ስለዚህ በአሁኑ ወቅት የምክር ቤት ስራ፣ የአስፈፃሚ ስራ የሚባል የለም ማለት ነው:: ስራው በቅንጅት ነው እየተሰራ ያለው::
አዲስ ዘመን፡- ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የህብረተሰቡ ተሳትፎ ምን መሆን አለበት፤ ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላትስ ምን ማድረግ አለባቸው?
አቶ ታደለ፡- አሁን ባለው ሁኔታ የማህበረሰቡ እና አጠቃላይ የምላተ ህዝቡ ተሳትፎ ወሳኝ ነው:: ከዚህ በፊት ህዝቡ ራሱ በአንድ በኩል የዚህ አስተሳሰብ ተሸካሚ የነበረበት ሁኔታ ነበር:: በዚህ የተነሳም ጭምር ነው ችግሩን መፍታት ያልተቻለው::
አሁን ግን ይህ ጉዳይ የማይጠቅምና አጥፊ፣ አውዳሚ ስለሆነ ሁሉም ህዝብ በያለበት ይህንን ድርጊት እያወገዘ ነው:: ሰላም ሚኒስቴርም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የድርሻውን ሚና እየተጫወተ ነው:: በዚህ የተነሳ አሁን ከፍተኛ ለውጥ እየመጣ ነው:: ይህንኑ አጠናክሮ ማስቀጠል ያስፈልጋል::
ቀደም ሲል በተከሰተው ችግር በርካታ የጉምዝ እናቶችና የሃገር ሽማግሌዎችም ጫካ የገቡበት ሁኔታ ነበር፤ እናቶች ጫካ ውስጥ የሚወልዱበት ሁኔታም ነበር:: እናቶች ታመው እንኳን በአግባቡ የማይታከሙበት ሁኔታ ነበር:: ስለዚህ ራሳቸው ከምንም በላይ ተጎጂ በመሆናቸው ይህንን በተግባር ከማውገዝ አልፈው እስከመፋለም የሄዱበት ሁኔታ ስላለ አሁን ጥሩ ሁኔታ እየተፈጠረ ነው::
ለውጡም እየመጣ ያለው በዚህ የተነሳ ነው:: ቀበሌያቸውን ለቀው ወደ ጫካ የገቡ የማህበረሰብ ክፍሎችም አሁን ሙሉ ለሙሉ ወደቀዬአቸው እየተመለሱ ነው:: ስለዚህ በቀጣይ ችግሩን ከመሰረቱ ለመፍታት ሁላችንም በትብብር ልንሰራ ይገባል::
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡኝ ማብራሪያ አመሰግናለሁ፤
አቶ ታደለ፡- እኔም አመሰግናለሁ::
አዲስ ዘመን ጥር 20/2013