ውብሸት ሰንደቁ
በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች እንደ የአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ የሚያማልሉ የተፈጥሮ ፀጋዎች ቢኖሩም ከሀገር ውስጥ ባለሀብቶችም ሆነ ከውጭ ባለሀብቶች መነሻውን ያደረገ ኢንቨስትመንት ሊሳብ የሚችለው ሰላምና ፀጥታ ሲረጋገጥ ነው።
ባለሀብቶች በአንድ ዘርፍ ሀብታቸውን ለማፍሰስ በመጀመሪያ ከሚያስቀምጡት ቅድመ ሁኔታ ውስጥም አንዱ ይሄው ነው ።ይህን ተከትሎም ፀጋ የታደሉ አካባቢዎች ሰላምና መረጋጋት ሳይኖርባቸው ሲቀር የኢንቨስትመንት ርሀቡም በዚያው ልክ ይፀናባቸዋል።
ኢንቨስትመንት የሚፈለገው ኢንቨስትመንት በመሆኑ ብቻ አይደለም፤ እሱን ተከትለው የሚመጡ በርካታ ጥቅሞች ስላሉት እንጂ ። አሁን ያለው ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ ኢንቨስትመንትን ያኮሰመነ መሆኑ ባይካድም ችግሮችን ተቋቁሞ መሻገር ግድ ነውና ሌሎች የዘርፉን አማራጮች መማተር የሚደርሱ ጉዳቶችን ለመቀነስ ያግዛል ።
አንዳንድ ክልሎች እና በሥራቸው የሚገኙ ዞኖች የኢንቨስትመንቱ ፍሰት በሚጠበቀው ልክ ባለመሆኑ ይህንኑ ተከትሎ ከሚመጣው ጫና ለማምለጥ የራሳቸውን መላ እየዘየዱ ነው ።የተንጠባጠቡ የውጭ ኢንቨስተሮችን መቀበሉ እንደቀጠለ ሆኖ በሀገር ውስጥ ኢንቨስት ማድረግ የሚችሉ ባለሀብቶችን ለማፍራት የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ከሚካሄድባቸው ክልሎች አንዱ ኦሮሚያ ክልል ነው፡፡
ኦሮሚያ ክልል ለኢንቨስትመንት ምቹ ፀጋዎችን ከአይለኬ ምጣኔ ጋር በውስጡ ያቀፈ ክልል ነው። ሆኖም ከለውጡ በፊት ይሠሩ የነበሩ ግፎችን በአደባባይ በመቃወሙ ሂደት በሚነሱ ግርግሮች ብዙ ኢንቨስትመንቶች አደጋ ውስጥ መግባታቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው ።ከለውጡ በኋላ ትንሽ ጋብ ያለ የመሰለው ተቃውሞ እና የተፈጠረው ሰላም በተወሰኑ ቦታዎች በተለያዩ ምክንያቶች እዚህም እዚያም አለመረጋጋቶች እና የሰላም መደፍረሶች ተስተውለዋል።
በወለጋ በተለይም በምሥራቅ ወለጋ ዞን የነበረው ሁኔታም ከዚህ የተለየ አልነበረም ።ሆኖም የመንግሥት ተቋማት ሥራቸውን እየሠሩ በመሆኑ ሰላምን ከማረጋገጡ ሥራ ጎን ለጎን የኢንቨስትመንት ሥራው እንዴት ይሆን ስል ጠይቄያለሁ ።
በዞኑ የውጭም ሆነ የሀገር ውስጥ ኢንቨስ ትመንትን ለመሳብ በርካታ አማራጮች አሉ። በእርሻ፣ በማዕድን፣ በማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎችና ሌሎች በርካታ ዘርፎችም አካባቢው ፀጋዎች እንዳሉት ይወሳል። በዞን ደረጃ ያሉ አመራሮች የውጭ ኢንቨስተሮችን እንዲሳቡ የሚያደርግ በአካባቢው ያሉ የኢንቨስትመንት መልካም ዕድሎችን ከማስተዋወቅ በዘለለ በቀጥታ የሚሳፉበት ብዙም ዕድል የለም።
በመሆኑም በምሥራቅ ወለጋ ዞን ያሉ አመራሮች ትኩረታቸውን ያደረጉት የአካባቢውን አርሶ አደሮች እና በጥቃቅንና አነስተኛ የተደራጁ የአካባቢውን ዜጎች ወደ ኢንቨስተር ደረጃ ደግፎ ማሳደግ ላይ ነው ።የኮቪድ 19 ወረርሽኝ እና አካባቢው ሰላምና መረጋጋት እያጣ ቢያደናቅፋቸውም ይህን ተቋቁመው ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ የሄዱት ርቀት ምን ያህል እንደሆነ አቶ አዲሱ ጥላሁን አስረድተውኛል ።
አቶ አዲሱ ጥላሁን በምሥራቅ ወለጋ ዞን ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት የኢንቨስትመንት ውጤታማነት ዘርፍ ቡድን መሪ እና የጽህፈት ቤቱ ተወካይ ናቸው ።አቶ አዲሱ እንደሚሉት በአጠቃላይ ባለፉት ስድስት ወራት ጽህፈት ቤቱ ሁለት ዋና ዋና ተግባራት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ሲሆን የኢንቨስትመንት ማስፋፋት ላይ እና የኢንቨስትመንት ውጤታማነትን እያረጋገጡ መሄድ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው።
በምሥራቅ ወለጋ ዞን ባለፉት ስድስት ወራት በክልሉም ይሁን በዞን ደረጃ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራበት ያለው በጥቃቅንና አነስተኛ የተደራጁወጣቶችን እና አርሶ አደሮችን አቅም ወደ ኢንቨስተር ደረጃ ማሳደግ ላይ በመሆኑ በግማሽ ዓመቱ ከ50 በላይ አርሶ አደሮች ወደ ኢንቨስተር ደረጃ ማደግ ችለዋል። በተጨማሪም ሦስት በጥቃቅንና አነስኛ የተደራጁ ማህበራት ወደ ኢንቨስትመንት ደረጃ አድገዋል ።
አቶ አዲሱ ባለፈው ዓመት ወደ 76 የሚሆኑ በጥቃቅንና አነስተኛ የተደራጁ ማህበራት እና አርሶ አደሮች ወደ ኢንቨስተር ደረጃ አድገው የነበረ መሆኑን አስታውሰው ጉዳዩ በኦሮሚያ ኢንቨስትመንት ቦርድ ሳይወሰን በመቆየቱና አሁን ቦርዱ መረጃዎችን አይቶ ውሳኔውን በማስተላለፉ በድምሩ በዚህ ዓመት ወደ ኢንቨስትመንት ደረጃ ያደጉ የአካባቢው አርሶ አደሮችና በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ የተሰማሩ ቁጥር ከፍ ሊል ችሏል ብለዋል፡፡
የውጭ ባለሀብቶች ወደ አካባቢው እንዲሳቡ ለማድረግ ኃላፊነቱን ለፌዴራል መንግሥት እና ለክልል ከፍተኛ ባለሥልጣናት ብቻ ትቶ መቀመጥ ስለማይቻል ባለሀብቱን ለመሳብ የአካባቢውን ፀጋ የሚያሳዩ ሥራዎችን ሠርተው ለኢንቨስትመንት ኮሚሽን ማስተላለፋቸውንም አቶ አዲሱ ገልፀዋል ።
በምሥራቅ ወለጋ ዞን አብዛኞቹ ባለሀብቶች በአብዛኛው የሚሰማሩት የእርሻ ኢንቨስትመንት ላይ ነው። የእርሻው ኢንቨስትመንት አዋጭ ሆኖ ስለተገኘ ይመስላል ከጥቂቶቹ በስተቀር በአካባቢው ያሉት የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች የማንጎ፣ የሩዝና የመሳሰሉትን በማምረትና በማቀነባበር ዙሪያ በመሥራት ላይ ናቸው ።ሆኖም ፈቃድ የወሰዱ ኢንቨስተሮች ሁሉ ቦታውን ለአስፈላጊው ተግባር ማዋላቸውና በሥራ ላይ ስለመሆናቸው ክትትልና ቁጥጥር ይደረጋል ።
በዚህ ረገድ በኢንቨስትመንት ውጤታማነት ዙሪያ ባለፉት ስድስት ወራት ተደጋጋሚ ፍተሻዎች መደረግ ችለዋል ።በዚህም አዲስ ፈቃድ ያላቸው ዘጠኝ ኢንቨስተሮችን ጨምሮ ከዚህ ቀደም ወደሥራ የገቡት ላይ በተደረገ የውጤታማነት ክትትል 148 ከሚሆኑ አጠቃላይ በእርሻው ዘርፍ የተሰማሩ ኢንቨስተሮች 113 ያህል የሚሆኑት በሥራ ላይ መሆናቸው ተረጋግጧል።
ከቀሪዎቹ 35 ኢንቨስትመንቶች ውስጥ በሙሉ አቅማቸው ባይሆንም የሚንቀሳቀሱ እንዳሉ በተወሰደ ግንዛቤ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ባላሳዩ 15 ያህሉ ላይ ውል እንዲቋረጥ ተደርጓል ።ይህ እርምጃም ኢንቨስትመንቱን ለማነቃቃት አወንታዊ ሚና እንደሚጫወት የታመነበት ሲሆን በተወሰደ ፈቃድ ሰበብ ሳይለሙ የሚቀመጡ የኢንቨስትመንት ፀጋዎችንም በአግባቡ ለመጠቀም ያስችላል ።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የኮቪድ 19 ወረርሽን አላራምድ ባለው ኢንቨስትመንት ሁኔታ እና ባለው አለመረጋጋት ውስጥም ሆኖ በያዝነው ዓመት ስድስት ወር ውስጥ ከውጭ መጥተው በምሥራቅ ወለጋ የተሰማሩ ሦስት ኢንቨስትመንቶች አሉ ።
የተሰማሩበት ዘርፍ በማንጎ ተክል፣ በስኳር ፕሮጀክት እና በሩዝ ማቀነባበር እንዲሁም ከአካባቢው ባለሀብት ጋር በጥምረት በሚሰሩ ዘርፎች ላይ ተሰማርተው እየሠሩ ይገኛሉ ። እነዚህ ኢንቨስትመንቶች ቢያንስ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ አፍስሰዋል ።
በእርሻው ዘርፍ ከተሰማሩ ባለሀብቶች በተጨማሪ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ያሉት ኢንቨስትመንቶች ላይም ክትትልና ቁጥጥር ተደርጓል ።በዚህም በኢንዱስትሪው ዘርፍ ወደ 13 የሚሆኑ ፕሮጀክቶች ፈቃድ ወስደው የነበረ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ አራቱ ሥራ ላይ፤ ቀሪዎቹ አራቱ በግንባታ ላይ ያሉ ሲሆኑ አምስቶቹ ገና ወደ ሥራ ያልገቡ መሆናቸው ተደርሶበታል ።
በምሥራቅ ወለጋ ዞን በቱሪዝም ዘርፍ የተሠማሩ ሦስት ፕሮጀክቶች የነበሩ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ በዚህ ስድስት ወር በተደረገ ክትትል አንዱ ሥራ ላይ እንዳለ፤ ሌላኛው በግንባታ ላይ እደሆነ እና ሦስተኛው በቱሪዝም አገልግሎት ዘርፍ ተመዝግቦ የነበረ ኢንቨስትመንት ፈቃድ እንደተቋረጠ አቶ አዲሱ ተናግረዋል፡፡
አቶ አዲሱ እንደሚሉት የሚደረገው ክትትል በእርሻ ኢንቨስትመንት ላይ፣ በኢንዱስትሪና በቱሪዝም ላይ በተሰማሩ ኢንቨስተመንቶች ላይ ተደርጎ አላበቃም ።በአገልግሎት ዘርፉ ተመዝግበው አገልግሎት እየሰጡ በሚገኙ ላይም ክትትል ተደርጓል። በዞኑ በዚህ ዘርፍ የተሰማሩ ወደ 22 ፕሮጀክቶች ያሉ ሲሆን እነዚህ ፕሮጀክቶች በከተሞች በተለያዩ ዘርፎች አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ማረጋገጥ መቻሉም የጽህፈት ቤቱ ተወካይ አስረድተዋል ።
ከዚህ ጋር ተያይዞ በዞኑ የሥራ ዕድል ፈጠራን በተመለከተም በዘንድሮው ዓመት የመጀመሪያ መንፈቅ ላይ 350 ቋሚ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ የነበረ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ለ135 ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል ።ከዚህ ሌላ በጊዜያዊነት ሰባት ሺህ የሚሆኑ ዜጎች ሥራ ዕድል ይፈጠራል ተብሎ ታቅዶ ይህ ዕቅድ ከታቀደው በላይ መሳካት ተችሏል ብለዋል አቶ አዲሱ።
የጽህፈት ቤቱ ተወካይ እንደሚሉት ከአርሶ አደርነትና ከጥቃቅንና አነስተኛ ማህበርነት ወጥተው የኢንቨስትመንት ዘርፉን ለተቀላቀሉ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷቸው መሰራት ይኖርበታል ።በተለይ በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩት የብድር አገልግሎትና የሜካናይዜሽን ቁሶች አቅርቦት ይፈልጋሉ ።ሆኖም በዚህ ረገድ ያለው አቅርቦት አነስተኛ መሆኑ በተፈለገው መጠን የታለመላቸውን ዓላማ ማሳካት እንዳይችሉ አድርጓል።
ከአርሶ አደርነት ወደ ኢንቨስትመንት የሚቀላቀሉ አርሶ አደሮች የግድ እያንዳንዳቸው ከ350 ሺህ ብር በላይ ማስመዝገብ እና የተዘጋጀ መሬት ሊኖራቸው ይገባል ።እንደዚህ መሆን የቻሉ አርሶ አደሮችን ለማበረታታት በተለይ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት መሬቱን ከግብር ነፃ ከመስጠት ጀምሮ ልዩ ልዩ ማበረታቻዎችን ያደርጋል። በተጨማሪም የብድር አቅርቦት እንዲመቻችላቸው በማድረግ ዘመናዊ የእርሻ መሣሪያዎችን እዲያገኙ ይደረጋል፡፡
አቶ አዲሱ እንደሚሉት በምሥራቅ ወለጋ ዞን አልፎ አልፎ የፀጥታ ችግር ይስተዋል ነበረ ።በዚህም ምክንያት ኢንቨስተሮች በዞኑ ሀብታቸውን አፍሰው ሥራ ለመጀመር ትልቅ ጥርጣሬ ነበራቸው ።በዚህም የተለያዩ ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ እንዳይገቡ ሆነው ቆይተዋል ።ይህን አጋጣሚ አልፎ አልፎም ቢሆን ተጠቅመው ስርቆትና ዘረፋ ይስተዋልባቸው የነበሩ አካባቢዎችም አሉ ።ይህ በመንፈቅ ዓመቱ ከተፈጠሩ ተግዳሮቶች አንዱ ነው፡፡
በተጨማሪም አምራች ዘርፉን ወደ ሥራ ለማስገባት መሰናክል ከፈጠሩ ጉዳዮች አንዱ የብድር አለመቻቸት ነበር ።በተጨማሪም የኃይል አቅርቦት አናሳነት፤ ከውጭ ዕቃዎችን ለማስገባት የምንዛሬ እጥረት የመሳሰሉ ችግሮችም ፈታኝ ሁኔታዎችን ፈጥረዋል፡፡
በምሥራቅ ወለጋ ዞን ያለው የሰላም ሁኔታ በመሻሻል ላይ ነው ።ችግሮችን በቦታው በመሄድ የማረጋጋት ሥራ እየተሠራ ስለሆነ ብዙም ለስጋት የሚያጋልጥ ችግር አለ ብዬ አላስብም ።አልፎ አልፎ ከሚከሰቱ ችግሮች ውጪ ይህ ነው የሚባል ሥጋት አለ ብዬ ማንሳት አልችልም ብለዋል አቶ አዲሱ ።
አቶ አዲሱ በጥቅሉ በዞኑ በአራት ዘርፎች ላይ ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ላይ ይገኛል። ዞኑ ለኢንቨስትመንት ምቹ ነው ።ከዚህ የበለጠ የሰላሙ ሁኔታ እየተረጋገጠ ሲመጣ ማንኛውም ባለሀብት መጥቶ ኢንቨስት ቢያደርግ ዞኑ በሩ ክፍት መሆኑን ማሳወቅ እወዳለሁ ያሉ ሲሆን አክለውም ምንም እንኳን በምሥራቅ ወለጋ ዞን የነበረው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በኮቪድና በፀጥታ ችግር ምክንያት አጣብቂኝ ውስጥ የነበረ ቢሆንም በዞኑ በሥራ ዕድል ፈጠራና በኢንቨስትመንት ደረጃ የተሠሩ ሥራዎች ውጤታማ ነበሩ ።ሆኖም የተሠሩት ሥራዎች ሊያዘናጉን የሚችሉ መሆን የላባቸውም። በሚቀጥሉት ስድስት ወራት የተሻለ እንደምንሠራ እምነት አለን በማለት አጠቃለዋል ።
አዲስ ዘመን ጥር 19/2013