ታምራት ተስፋዬ
በቴክኖሎጂው የ21 ክፍለ ዘመን የሰው ልጅ በእለት ተእለት ህይወት ለሚገጥሙት ውስንነቶች መፍትሄ ከማበጀት አልፎ ቀጣዩን ገምቶ እየሰራ ነው። ለዚህ ደግሞ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ወይንም ሰው ሰራሽ አስተውሎት ዋነኛ መፍትሄው አድርጓል።
አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ወይንም ሰው ሰራሽ አስተውሎት የኮምፒውተር ፕሮግራሚንግ ሳይንስን በመጠቀም የሰዎችን አስተሳስብና ድርጊት ኮምፒውተሩ እንዲፈጽመውና እንዲተገብረው ማስቻል ማለት ነው።
ኮምፒውተሩ ይህን ማድረግ የሚችለው ዳታዎችን በመጠቀምና አካባቢውን በማንበብ ሲሆን ለችግር መፍትሄ መፈለግ ፤ ራሱን ከነገሮች ጋር በማላመድና በማስተማር ማንኛውንም አይነት ተግባር ለመፈጸም ሲዘጋጅ ማለት ነው።
አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በጤናው ዘርፍ፤ በወታደራዊ ሳይንስ፤ በትምህርት እንዲሁም በሌሎች በማንኛውም ዘርፎች በመደበኛ የሰው ልጅ ህይወት ውስጥ ያሉ እንቅስቃሴዎችን ኮምፒውተሮች ሰዎችን አግዘው እንዲሰሩ ማድረግ ያስችላል።
ከዚህም ባሻገር ሰዎች በማያስፈልጉባቸው ወይንም ደግሞ በግማሽ መታገዝ በሚያስፈልጋቸው ቦታዎች ላይ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ማሽኖች ስራ እንዲሰሩ ማድረግ ይቻላል።
ለአብነት በጤናው ዘርፍ ትላልቅ የፋይል መጠን ያላቸውን የኤክስሬይ ዳታዎች፤ የኤም አር አይና ሲቲ ስካን ዳታዎችን በቀላሉ ለማንበብ፣ በፋይናንስ ዘርፍ ደግሞ ለማጭበርበር የሚደረጉ ሙከራዎችን ለማወቅና ለመከላከል እያገዘ ይገኛል። በጦር ሃይሉ ዘርፍም የስጋት ትንተና የጠላት ቀጠናን ለመለየት፣ ለስለላ፣ የመከላከያ መረጃዎችን ሚስጢራዊነት ለመጠበቅና ሌሎችም ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶች ለሃያላኑ አገራት እየሰጠ ይገኛል።
በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃም የተለያዩ አገራት ለአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ወይንም ሰው ሰራሽ አስተውሎት ልዩ ትኩረት ሰጥተዋል። የተለያዩ ምሁራንና የስልተ ቀመር ሳይንሱ ላይ ሰፊ ምርምሮችን ከማድረግ ባለፈ ቴክኖሎጂውን በመጠቀም የሰው ልጆችን ድካም እያቀለሉለት ስራውንም እያቀላጠፉ ይገኛል።
ሳራ መንክር ትባላለች። ትውልድና እድገቷም ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። በማሳቹሴት ማውንት ሆሊዮክ ኮሌጅ እንዲሁም በእንግሊዝ ለንደን ኢኮኖሚን አጥንታለች። ከኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲም በቢዝነስ አስተዳደር ሁለተኛ ዲግሪዋን አግኝታለች።
ሳራ ከዚህ በኋላም በግብርና ኢንቨስትመንት ላይ ትኩረቷን ያደረገች ሲሆን የዓለም የምግብ እጥረት ቀውስም ዋነኛ ስጋታ ነበር። በተለይ የአፍሪካ ምግብ ዋስትና እኤአ በ2030 እጅጉን የከፋ አደጋ እንደሚገጥመው ግምቷን አስቀምጣለች። እ.ኤ.አ በ2014 በምስራቅ አፍሪካዊቷ አገር ኬንያ ‹‹ግሮ ኢንተለጀንስ›› የተሰኘ ድርጅት አቋቋመች።
ተቋሙም በዓለም ላይ የሚታየውን የግብርናና ምግብ ነክ መረጃዎች ክፍተት ለመሙላት የተመሰረተ ነው። ተቋሙ በዋነኝነት የሰው ሰራሽ አስተውሎት ስልተ-ቀመሮችን በመጠቀም የዓለምን የግብርና መረጃዎች በማሰባሰብ፣ በማዋቀር፣ በመተንተንና ትርጉም ባለው መልኩ በማደራጀት ለደንበኞች የማቅረብ ስራ ይሰራል።
ባለፉት ዓመታት የምግብ ምርት ላይ ተፅእኖ ሊፈጥሩ የሚችሉ ነገሮችን ከእህል ዘር እስከ አፈር ጥራትና አየር ንብረት ለውጥ ድረስ የምግብ ምርት ላይ ተፅእኖ ሊፈጥሩ የሚችሉ በርካታ መረጃዎችን አሰባስቧል።
የተዋቀሩና ያልተዋቀሩ ለሕዝብ ተደራሽ የሆኑ መረጃዎችን (ለምሳሌ፡- ከናሳ የሚገኙ የሳተላይት ምስሎችን፣ የሀገራት የጉሙሩክ መረጃዎችን፣ የሀገራት የፍላጎትና አቅርቦት ሪፖርቶችና የመሳሰሉትን) በመሰብሰብ የትንበያ ሞዴሎችን በማዘጋጀት ለባለድርሻ አካላት አቅርቧል።
ይህ ትንበያ በግብርናው ምህዳር ውስጥ ያለውን ለውጥ በመገንዘብ ባለድርሻ አካላት ውሳኔዎችን ማድረግ እንዲችሉ ትልቅ አቅም እየፈጠረ ይገኛል። ይህም ከዓለም ዙሪያ ትሪሊዮን ከሚደርሱ የዳታ ነጥቦች የሚሰበሰቡ መረጃዎችን በመተንተን፤ የግብርና ምርቶችን ፍላጎትና አቅርቦት እንዲሁም ዋጋ የመተንበይ አቅምን የፈጠረ ተቋም እንዲሆን አስችሎታል።
የሳራ መንክር ግሮ ኢንተለጀንስ በአሁኑ ወቅት በግብርናና በከባቢ አየር ስጋት ዙሪያ በዓለማችን በግንባር ቀደምትነት ከተቀመጡ መረጃ ተንታኝ ተቋማት መካከል አንዱ ነው። የእሷ እቅድ ግን ከዚህም አልፎ ድርጅቱ አገራትና ምግብ አምራች ድርጅቶች የምግብ ሰንሰለታቸውን እንዲያስተካክሉ የሚያስችል ዘዴን መፍጠርና የአየር ለውጥ ፈተናን ለመቅረፍ እርዳታ ማድረግ ነው።
ሀገራት እና ምግብ አምራች ኩባንያዎችም የምርት እና አቅርቦት ሥርዓታቸውን ለማቀድ እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የሚጠቀሙበት እንዲሆን ትፈልጋለች።
የትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ግሮ ኢንተለጀንስ በአሁኑ በወቅት የፖሊሲ አውጪዎች፣ የኢንሹራንስ ካምፓኒዎች ትላልቅ ኢንቨስተሮችን ትኩረት በመሳብ ላይ ይገኛል። ከቀናት በፊትም በኢንቴል ካፒታል የሚመሩ በርካታ የአሜሪካ ድርጅቶች እቅዷን እውን ለማድረግ እንድትችል የ85 ሚሊዮን ዶላር ካፒታል ፈሰስ ሊያደርጉላት ተስማምተዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 18/2013