ለምለም መንግሥቱ
ግንባታ (ኮንስትራክሽን) የማያቋርጥ ዕድገት ውስጥ ያለ በባህል ጀምሮ በሳይንሳዊ መንገድ የዳበረና እየዳበረ የሚገኝ የሰው ልጅ ጥበብ ውጤት ነው። የመጀመሪያው ግንባታ የሚባለውም በጥንታዊ የጋርዮሽ ሥርዓተ ማህበር የሰው ልጅ ለመጠለያነት የተጠቀማቸው ጎጆዎች እንደሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በዓለም ታሪክ ደግሞ የባቢሎን ግንብ፣ ታላቁ የቻይና ግንብ እና ፒራሚዶች በዋናነት ይጠቀሳሉ። በኢትዮጵያም ግንባታ ረጅም ዕድሜ አስቆጥሯል። የአክሱም ሀውልት፣ የላልይበላ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት፣ የፋሲለደስ ግንብ እና ሌሎችም ለአብነት ይጠቀሳሉ።
አሁን ባለንበት ዘመን የህንፃና የመንገድ ግንባታ ሥራ የአንድ ሀገር የዕድገት መለኪያና የኢኮኖሚ ማሳለጫ መንገድ ሆኖ ተገኝቷል። በሀገሮች መካከል የመወዳደሪያ መስክም ነው። ጥሩ መንገድ ያለው ሀገር የንግድ ለውውጥ ያካሂዳል፤ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ግንኙነቱን የበለጠ ለማጠናከር ይጠቀምበታል።
በቂ የመኖሪያ ቤት መገንባት የቻለች ሀገር የዜጎቿን መሠረታዊ የቤት ፍላጎት ከማሟላት ባለፈ በተለያየ ምክንያት ወደ ሀገሯ ለሚመጡና ኑሯቸውንም በሀገሪቷ ለማድረግ ለሚፈልጉ ሁሉ ማሟላት ትችላለች። ይህ ሲሆን ደግሞ ተመራጭና ተፈላጊ ሀገር እንድትሆን ይረዳታል። ይህ ለሰዎች መሠረታዊ የሆነው የግንባታ ዘርፍ ከፍላጎት ባለፈም ጥራትን ያሟላ እና ሳቢ እንዲሆን ይጠበቃል።
በኢትዮጵያ የግንባታ ዘርፉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ፣ የሥነ ህንጻውም ጥበብ እያደገ፣ ሰዎች ለህንጻና መንገድ ግንባታ ያላቸው ፍላጎት እየጨመረ እና ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ ባለሙያ በማሳተፍ የሥራ ዕድል በመፍጠር ዛሬ ላይ ደርሷል። እንደሀገር የሕንፃና የመንገድ ግንባታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋና በመንግሥትም ትኩረት እያገኘ የመጣ ዘርፍ ነው። በመሆኑም ከሀገሪቷ በጀት ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው የግንባታው ዘርፍ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የግንባታው ዘርፍ ብዙ ተዋናዮች የሚሳተፉበትና ከፍተኛ በጀት ተመድቦለት የሚከናወን በመሆኑ ልዩ ትኩረትና ጥንቃቄ ይፈልጋል። በመሆኑም በብዙ ችግሮች ውስጥ አልፎ ነው ለውጤት የሚበቃው። በአሁኑ ጊዜም በሀገሪቱ ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ (ሜጋ ፕሮጀክቶች) ሰፊ የግንባታ አቅም መፍጠር ተችሏል።
ሥራዎቹም በሀገር ውስጥና በውጭ ተቋራጭ ኩባንያዎች በመከናወን ላይ ይገኛል። ይሁን እንጂ በዘርፉ የግንባታ መጓተት፤ የጥራት መጓደል፤ የባለሙያ ብቃት ማነስ፤ የግብዓት አቅርቦት ማነቆ መሆን፤ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፤ ዘርፉ የሚመራበት በተለይም በህንፃ ግንባታ ሥርዓት ወይም ህግ ላይ ክፍተት መኖር እንዲሁም በዘርፉ ውስጥ የሚስተዋለው ሙስና ከሚነሱ ተግዳሮቶች መካከል ይጠቀሳሉ። ይህ ደግሞ በግንባታው ላይ ከፍተኛ ጫና እየፈጠረ ዘርፉን እያዳከመው እንደሆነ በሰፊው የሚነሳ ርዕሰ ጉዳይ ሆኗል።
ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት ተቋቁሞ ወደ ሥራ የገባውና በዘርፉ ለውጥ ለማምጣት በእንቅስቃሴ ላይ የሚገኘው የኮንስትራክሽን ሥራዎች ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን የነበሩትን የዘርፉን ማነቆዎች በመለየትና የመፍትሄ አቅጣጫም በማስቀመጥ እንዲሁም የንቅናቄ መድረኮች በማዘጋጀት ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር እየሠራ መሆኑን አስታውቋል።
የኮንስትራክሽን ሥራዎች ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሥፍን ነገዎ ዘርፉ ተቀዛቅዟል እየተባለ የሚሰጠውን አስተያየት ይጋራሉ ‹‹እንደሀገር የግንባታ ዘርፉ እየተስፋፋ የመጣ ቢሆንም በሕግ ማዕቀፍ ከመመራት ጀምሮ በብዙ ችግሮች ውስጥ ለማለፍ ተገዷል። ውስብስብ በሆነ ማነቆ ውስጥ መቆየቱ ታሞ ነበር ለማለት ያስደፍራል። ነገር ግን ዘርፉ በባህሪው ውስብስብ እንደሆነም መዘንጋት የለበትም። ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ የሚንቀሳቀስበትና በርካታ ተዋናይ የያዘ ዘርፍ ነው›› ሲሉ ያስረዳሉ።
እንደርሳቸው ማብራሪያ ባለፉት ዓመታት በብዙ ችግሮች ውስጥ ሆኖ ነው ሲከናወን የነበረው። ችግሩ ከጨረታ አወጣጥና ከንድፍ (ዲዛይን) ሥራ ይጀምራል። በጨረታ ሂደት የነበረው የተቋራጭ (የኮትራክተር) መረጣው አቅምንና ብቃትን ያገናዘበ አልነበረም።
ይልቁንም አንድን አካል ለመጥቀም ተብሎ እርሱን ሊመጥንና ሊያሸንፍ የሚችልበትን መሥፈርት መሰረት ያደረገና አሸናፊው ተለይቶ የሚገባበት ዓይነት የኮንስትራክሽን ኢንደስትሪ ዘርፍ እንደነበር ደፍሮ መናገር ይቻላል።
በትክክለኛ የመወዳደሪያ መሥፈርት ሳያልፍ የመወዳደሪያ ዋጋም ሳይኖረው ወደ ሥራው የገባው ተቋራጭ የወሰደውን ሥራ ከመወጣት ይልቅ በአቋራጭ የሚከብርበትን ጥቅም በማሳደድ ላይ የተጠመደ ነበር። እንዲህ ያለው አቅምን ማዕከል ያላደረገ አካሄድ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች በጊዜና በተመደበላቸው በጀት እንዳይጠናቀቁ፤ ይልቁንም በናረ ገንዘብ እንዲያልቁና ለሁለት ዓመት ጊዜ የተያዘው ግንባታ አሥር ዓመት ድረስ መጓተት ዘርፉ የታመመ እንዲሆን ከሚጠቀሱ ምክንያቶቹ ውስጥ ናቸው።
የዋና ዳይሬክተሩን ሀሳብ የሚጋሩት የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ማተቤ አዲስ ‹‹የመንገድ ሥራ ግንባታው በኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን እንደሚመራው የህንፃ ፕሮጀክት በባለቤት እየተመራ አይደለም።
ህንፃን የሚያስተዳድር አካል የለም። በርካታ መስተካከል ያለባቸው ደካማ ጎኖች ያሉበት ዘርፍ ነው›› ይላሉ። እንደርሳቸው ማብራሪያ ከገበያ ልንወጣ ነው የሚለው የተቋራጮች ቅሬት ትክክል ነው። አብዛኞቹ ተገቢውን የውድድር መስፈርት አሟልተው የገቡ ባለመሆናቸው ከመፈጸምና ከገንዘብ አቅም ጋር ተደራራቢ የሆኑ ችግሮች ይገጥሟቸዋል።
ፕሮጀክቶች ሲጓተቱ ጫናው የሚያርፈው ሥራ ተቋራጩ ላይ በመሆኑ ከገበያ የመውጣቱን ስጋት ይፈጠራል። እንደሀገር ከነበረው የፖለቲካ ጉዞ ጋር ተዳምሮ የዘርፉ ችግሮች ገዝፈው እንዲታዩ ሆኗል።
እንደ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ ከሀገሪቷ በጀት 60 በመቶ የገንዘብ ድርሻ ያለው ብዙ ኃይሎችን የያዘና በርካታ ዓይኖች የሚያርፍበት ነው። በአጠቃላይ የግንባታ ኢንደስትሪው ከሕግ የወጣ አሰራርን የተከተለ መሆኑ ዘርፉን ጎድቶታል። በዘርፉ የሚስተዋሉት ችግሮች የሚቀጥሉ አይደሉም።
ጨረታዎች ግልጽና ፍትሐዊ ሆነው ሁሉንም የሚያሳትፉ መሆን አለባቸው። ከአሁን በኋላ ዘርፉ ካንቀላፋበት ወጥቶ መነቃቃት ውስጥ ይገባል የሚል አቅጣጫ ተይዞ ስራ በመስራት ላይ ይገኛል።
ይሁን እንጂ በነዚህ ሁሉ ተግዳሮቶች ውስጥ ተቋራጩ እና መሀንዲሱ እየሰራ ነበር። መንግሥትም በተወሰነ መልኩ ድጋፍ እያደረገ ነበር። በአጠቃላይ ዘርፉ በተስፋና በተግዳሮት ውስጥ ሆኖ ቢያልፍም አንዳንድ ፕሮጀክቶች ወደፊት ሄደዋል። ሀገሪቱ በለውጥ ሂደት ባጋጠማት ያለመረጋጋት የውስጥ ችግሮችና የኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት ተደማምሮ የዘርፉን ችግሮች የበለጠ አጉልቶታል።
ያም ሆኖ ግን ሥራዎች አልተቋረጡም። በተለይ እንደታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶችና በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ተነሳሽነት የተጀመሩት ለመዝናኛና ለተለያዩ አገልግሎት የሚውሉ የገቢ ማስገኛ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ በመከናወን ላይ ይገኛሉ። በተለይም በወረርሽኙ ምክንያት የግንባታ ዘርፉ አልተስተጓጎለም እየተከላከሉ መሥራት የሚለውን መርህ የሚተገብር ነው።
በግንባታ ኢንደስትሪው በተለያዩ አካላት ከሚነገረው በላይ ባለሥልጣኑ በተለይ በመንግሥት ፕሮጀክቶች ላይ ባደረገው ቁጥጥር ብዙ ክፍተቶች መኖራቸውን አረጋግጧል ያሉት በባለሥልጣኑ የቁጥጥር ሥራዎች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ እንዳለው ተመስገን እንዳስረዱት፤ በህንፃና በመንገድ ዘርፍ የሚከናወኑት ግንባታዎች ፍጹም የተለያዩ ናቸው።
በህንፃ ግንባታ መጓተት ብቻ ሳይሆን ያልተጀመሩም ሥራዎች ይገኙባቸዋል። መንገድ በማዕከል እየተመራ የሚከናወንና መረጃም የሚገኝበት መሆኑ የተሻለ ሆኖ እንዲገኝ ያስቻለው ቢሆንም ክፍቶች አሉበት። ባለሥልጣኑ በሁለት ዓመት የሥራ ቆይታው በ35 የመንገድ ፕሮጀክቶች ላይ ቁጥጥር አድርጓል።
ባለሥልጣኑ ችግሮችን መለየት ብቻ ሳይሆን የግንባታ ኢንዱስትሪው ካለበት ተግዳሮት ተላቅቆ የተሻለ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ጎን ለጎን የሚያሠሩትንና የማያሠሩትን የሕግ ማዕቀፎች ለይቶ በማስተካከል ላይ ይገኛል። በከፊልም የተስተካከለውን መተግበር ጀምሯል።
በተለይም ከግብዓት አቅርቦት፣ ከዋጋ ጀምሮ ያለው መረጃ የተበታተነ መሆኑ የመረጃ አሰባሰቡ ሂደትም በአንድ ማዕከል ተደራጅቶ ከከተማ ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ጋር በጋራ የሚከናወንበት የአሠራር ሥርዓት ተዘርግቷል። ይህንን ደግሞ ግንዛቤ በመፍጠር ኢንዱስትሪው እንደባህል ይዞት መልሶ እንዲጠቀመው ይደረጋል። ከዚህ ሁሉ በኋላ መመሪያና ሕጉን ወደ ማስፈጸምና እርምጃ መውሰድ ይገባል። በዚህ መልኩ ዘርፉ እንዲሻሻል ያደርጋል።
ባለሥልጣኑ ከያዝነው ጥር ወር ጀምሮ እስከ የካቲት መጀመሪያ ‹‹ውጤታማ የኮንስትራክሽን ኢንደስትሪ ለኢትዮጵያ ብልጽግና›› በሚል መሪ ቃል በሐዋሳ፣ በጅማ፣ በደብረ ብርሃን፣ በጂግጂጋ፣ በአዳማና በአዲስ አበባ ከተሞች ሀገር አቀፍ ይዘት ያላቸው የንቅናቄ መድረኮች ያካሂዳል።
ዘርፈ ብዙ ተልዕኮዎችን በያዘው በዚህ የንቅናቄ መድረክ በግንባታ ዘርፉ የሚስተዋሉ ማነቆዎች፣ ባለሥልጣኑ ባለፉት ሁለት ዓመታት ያከናወናቸው የክትትልና የቁጥጥር ግኝቶች እንዲሁም ከጊዜው ጋር እንደሚመጥን ተደርጎ በተሻሻለው የባለሙያና የኩባንያ ምዝገባ መመሪያና ሌሎችም የሕግ ማዕቀፎች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ይወያያል።
የግንባታ ዘርፉን አገልግሎት ሀገራዊ ፍላጎት ለማሟላት የባለድርሻ አካላት ሚና እንዲኖራቸውና የዓለም አቀፍ ተሞክሮውም ተቀምሮ የሚቀርብ ሲሆን በሚቀረቡት ላይ ሰፊ ውይይት በማካሄድ የጋራ ግንዛቤና መግባባት ይዞ ዘርፉን የላቀ ደረጃ ላይ ለመድረስ እንደሆነ ከባለሥልጣኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የንቅናቄ መድረኩ ባለሥልጣኑ የግንባታ ኢንደስትሪውን የቁጥጥር ሥርዓት ለማዘመንና የዘርፉን ሀገራዊ ፋይዳ ይበልጥ ለማሳለጥ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ለሚያደርገው እንቅስቃሴ ጥሩ ግብዓት እንደሚፈጥርለትም ይጠበቃል። ባለሥልጣኑ የአምስት ዓመት የሥራ ዕቅዱን ያስተዋውቃል። ለቀናት ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚካሄደው የምክክር መድረክ የዘርፉን የወደፊት አቅጣጫ የተሻለ እንደሚያደርገውም ይጠበቃል።
የኮንስትራክሽን ሥራዎች ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን በአዋጅ ቁጥር 1097/2011 ዓ.ም በአንቀጽ 32 በንዑስ አንቀጽ 18 የተቋቋመ መንግሥታዊ ተቋም ሲሆን አራት ዓላማዎችን ከግብ የማድረስ ኃላፊነቶች ተሰጥተውታል።
የመጀመሪያው የግንባታ ዘርፍ አፈጻፀሙ በብቃት፣ በምክንያታዊ ወጪ፣ በታሰበበት ጊዜ፣ በሚፈለገው የጥራት ደረጃ መተግበሩን እንዲሁም ሀገራዊ ፍላጎትን ማሟላት የሚያስችለውን አስተዋጽኦ በብቃት እየፈጸመ መሆኑን የማረጋገጥ ኃላፊነትን መወጣት ነው። ሁለተኛው ደግሞ በግንባታ ኢንደስትሪው ውስጥ የሚሰማሩ ባለሙያዎች፣ የሥራ ተቋራጮችን፣ አማካሪዎችን እና በዘርፉ የሚሳተፉ ድርጅቶችን የሥራ አፈጻጸም በመቆጣጠር ከሀገራዊ ፍላጎት ጋር የሚጣጣም መሆኑን ማረጋገጥ ነው።
በሦስተኛ ደረጃ የዘርፉን ባለሙያዎች፣ ተቋራጮች፣ አማካሪዎችና ሌሎችም በዘርፉ ዙሪያ የሚገኙ ባለድርሻ አካላት አፈጻጸማቸው ሀገሪቱ በምትፈልገው መሰረት በግንባታ ኢንደስትሪው አስተዋጽኦ የማድረግ ብቃታቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነት ሲሆን የግንባታ ኢንዱስትሪው የዜጎችን፣ የአካባቢ ደህንነትና ጤና ያረጋገጠ እንዲሆን ማድረግ እና የግንባታ ግብዓቶችንና ውጤቶችን ጥራት እንዲሁም ደረጃ ቁጥጥር ማረጋገጥ አራተኛ ተልዕኮዎቹ ናቸው።
ባለሥልጣኑ በኃላፊነት እንዲተገብራቸው የተቀመጡ ግቦች ሥራ ላይ ከዋሉ ወደ ሥራ ከገባ ወዲህ የጀመራቸው እንቅስቃሴዎችና ሊተገብራቸው የያዛቸው ዕቅዶች በአግባቡ ከተገበራቸው ባለድርሻ አካላትም በዘርፉ ጣልቃ በመግባት የግል ጥቅማቸውን የሚያሳድዱ አካላትን በጋራ በመዋጋት ማስወገድ ከቻሉ ዘርፉን ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ የተያዘውን ዕቅድ ማሳካት ይቻላል መልዕክታችን ነው።
አዲስ ዘመን ጥር 18/2013