ውብሸት ሰንደቁ
በኢትዮጵያዊ ተቀምሮ የተቀመመ ኬሚካል አልባ የፅዳት ምርትን የሚያመርት እንዲሁም ለመጸዳጃ ቤቶች መጥፎ ሽታ ማጥፊያ አምርቶ የሚያቀርብ ሀገር በቀል ኢንተርፕራይዝ ጋር በቀጭኑ ሽቦ ተገኝተናል።አማራ ክልል፤ ባህር ዳር ዙሪያ አዴት 03 ቀበሌ ውስጥ ነዋሪ ናቸው።ናሳ በሚል ስያሜ የሚጠራው አምች ኢንተርፕራይዝ ለንፅህና መጠበቂያና ለፅዳት አገልግሎት የሚውሉ ግብዓቶችን በማምረት የማቅረብ ሥራ ውስጥ የገባው በ2011 ዓ.ም ነው።
የግብአቶቹ የፈጠራ ባለቤት አቶ አህመድ አልሴ ይባላሉ።ለፈጠራ ሥራቸው ከኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት በ2010 ዓ.ም ላይ የብቃት ማረጋገጫ የምሥክር ወረቀት (ፓተንት) አግኝተዋል።
ከባለቤታቸው ኑራ ጌቴ እና ከሦስት ልጆቻቸው ጋር በሚኖሩበት ግቢ ውስጥ አቶ አህመድ በሰሩት የማምረቻ ማሽን(መሳሪያ) በመጠቀም የንጽህና መጠበቂያ ግብአቶችን በመቀመም ለገበያ ያቀርባሉ።በትምህርት ከስምንተኛ ክፍል በላይ ያልዘለቁት አቶ አህመድ አዳዲስ ነገሮችን የመፍጠር ብሩህ አዕምሮ ያላቸው ጎልማሳ ናቸው።
አቶ አህመድ እንዳጫወቱኝ ወደዚህ ሥራው ውስጥ የገቡት ከራሳቸው ችግር በመነሳት ነው።በመኖሪያ ግቢው ውስጥ ለኪራይ አገልግሎት የገነባቸው መኖሪያ ቤቶች ብዙ ነዋሪዎች ስላሉ በመፀዳጃ ቤት ሽታ ይቸገር ነበር።ከዕፅዋት ውጤት በመቀመም የሚያስቸግረውን የመፀዳጃ ቤት መጥፎ ሽታ ለማስወገድ ችሏል።
ችግሩ የብዙዎች መሆኑን በመገንዘብም የፈጠራ ሥራውን አጠናከሩ።በዚህ የጀመረው ፈጠራ እያደገ ዛሬ በሀገር አቀፍ ደረጃ እውቅና አስገኝቶላቸው እስከማከፋፈል ደረጃ ደርሰዋል።
በአሁኑ ጊዜም ቅርንጫፎችን ከፍተው ምርታቸውን በማከፋፈል ላይ በየቢሮው እና በተለያዩ ቦታዎች ሲንቀሳቀስ ይህ ችግር የእርሱ ብቻ ሳይሆን የሌሎችም ችግር እንደሆነ በመገንዘቡ መፍትሄ እንደሚያስፈልገው ማሰብ የጀመረውና ወደ ተግባር የገባው ያኔ ነው።
በ2010 ዓ.ም ለምርቱ ፓተንት ካገኙ በኋላ በ2011 ዓ.ም በ100 ሺህ ብር ካፒታል ሥራውን ጀመሩ። በአሁኑ ጊዜ ከባለቤታቸው እና ከስድስት ሠራተኞቻቸው ጋር በትጋት በመሥራት በተለያዩ የቅርንጫፍ ማከፋፈያዎቻቸው በማከፋፈል የካፒታል መጠናቸውን ወደ 500 ሺህ ብር ማድረስ ችለዋል።
አቶ አህመድ በኢትዮጵያ ከኬሚካል ነፃ የሆነ በፈሳሽና በዱቄት ብቸኛ የሽንት ቤት ሽታ ማጥፊያና የፅዳት ዕቃዎች በማምረት የገቢ ምንጭ ፈጥረው ለህብረተሰቡ ችግር ፈቺ የሆነ ምርት በማቅረብ ላይ ይገኛሉ::
አቶ አህመድ በልበ ሙሉነት እንደሚናገሩት ምርቱ በዋጋው ተመጣጣኝ መሆኑና ተጓዳኝ ጉዳት የሌለው መሆኑ ልዩ ያደርገዋል። እስካሁንም ምርቱን ከሚጠቀሙ ደንበኞቹ ምሥጋና እንጂ ቅሬታ አለመሰማቱ የበለጠ ለመስራት አቅም ፈጥሮላቸዋል።
ምርቱን በሀገር ውስጥ በማምረት ብዙዎችን ተጠቃሚ ከማድረግ አለፍ ብሎም ለውጪ ገበያ ለመላክ አልመው በመሥራት ላይ ናቸው።
ብዙ የፈጠራ ውጤቶች አሉኝ የሚሉት አቶ አህመድ፤ገና ለፈጠራቸው ዕውቅና ለማግኘት በሂደት ላይ በመሆናቸው ስለምርቶቻቸው ከወዲሁ ለማሳወቅ እንደሚቸገሩ ይገልጻሉ።ይህን ይበሉ እንጂ በሚስጥር ከያዟቸው ውስጥ ጥቂቶቹን ለአብነት ገልጸውልናል።
በዓይነቱ ልዩ የሆነ የገላ ሳሙና እና የእግር ሽታ ማጥፊያ ሳሙና ይገኙበታል።እነዚህ ምርቶች አዲስና የጎንዮሽ ጉዳት የሌላቸው ወደ ለውጪ ሀገር ገበያም መቅረብ የሚችሉ እንደሆኑ ያስረዳሉ።መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ድጋፉን ባይነፍገኝ ደሥ ይለኛል ብለዋል።
ይህ ምርት የሕዝብን ችግር ለመፍታት የተፈጠረ ነው የሚሉት አቶ አሕመድ እንደሚገልጹት በከተሞች ላይ የሚታየው የሕዝብ ብዛት ቆሻሻዎች እንዲበዙ ያደርጋል። ቆሻሻዎችን ሁሉ ከመኖሪያ ቦታ ሩቅ ማድረግ ስለማይቻል በፈጠራ የሰሯቸው የጽዳት መጠበቂያዎች፣የመጥፎ ጠረን ማጥፊያዎችና ሌሎችም ከኬሚካል የጸዱ መድኃኒቶች በሽታ በማጥፋትና በአካባቢው ያሉ ነፍሳት ወደ ቆሻሻ ቦታው ወይም ወደ ሽንት ቤት እንዳይመጡ በማድረግ ብዙ ዓይነት በሽታዎችን መከላከል ይቻላል። ይህን የመሰለ ለሀገር የውጭ ምንዛሪን ለማስገኘት የሚያግዝና ከውጪ ምንም ዓይነት ግብዓት የማያስገባ አንጡራ የሀገር ሀብት መጠቀም ግድ ይላል ብለው ያምናሉ።
አንድ ሽንት ቤት በዚህ ምርት ሲፀዳ ዝንብ ወይም ትንኝ በአካባቢው ዝር እንደማይል እና ከዚህ በፊት ከአፍሪካ ሀገራት ጋር በፅዳት ዕቃዎች ውድድር ከአራት ሀገራት ተመራጭ መሆን ችሎ የነበረ መሆኑን እንዲሁም የመድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ምርቱን ካጤነ በኋላ በሀገር ውስጥ ሲሸጥ እንዲቆይና የመሥሪያ ቦታዎችና አንዳንድ ነገሮች ሲስተካከሉ ወደ ውጪ የመላክ ደረጃውን ስለማሟላቱ ዕውቅና እንደሚሰጣቸው ጠይቀዋል።
በክልልና በዞን ደረጃ በኢንቨስትመንት መልክ የማምረቻ ቦታ እንዲሰጣቸው ከክልልና ዞኑ ፈቃድ ማግኘታቸውንና ከወረዳው በኢንቨስትመንት ሥም ቦታ ለመቀበል በመጠባበቅ ላይ እንደሆኑ ተናግረዋል።
ሀገር የምትበለፅገው በዜጎቿ ብርታት ነው። በፈጠራ ደረጃም ሆነ በምርት ጥቃቅን የሚመስሉ ነገሮች ከውጭ የሚገቡ ሆነው ሲገኙ በአስተውሎት ውስጥ አይግቡ እንጂ በርካታ የውጭ ምንዛሪ ያስገኛሉ።
እንደ አቶ አህመድ ዓይነት ዜጎችን ማበረታታት የውጭ ምንዛሪን መታደግ፤ ሀገርን ከኬሚካል ሸቀጦች ማራገፊያነት ማዳን፤ የዜጎችን የፈጠራ ክህሎት ማነቃቃት እና የሀገሪቱ ሕዝቦች በሀገራቸው ምርት የመጠቀም ዝንባሌያቸውን ማሳደግ ስለሚሆን መንግሥት እንዲህ ዓይነት ዜጎች ሲገኙ በቸልታ ማለፍም ሆነ በዝምታ መሸበብ አይኖርበትም።
አዲስ ዘመን ጥር 17/2013