አንተነህ ቸሬ
ማክሰኞ፣ ጥር 11 ቀን 2013 ዓ.ም … የበዓለ ጥምቀት ዕለት … ፀበል ለመጠመቅና በበዓለ ጥምቀቱ ላይ ለመታደም ታቦታት ወዳደሩበትና ሺዎች (ምናልባትም ሚሊዮኖች) ወደተሰባሰቡበት ጃንሜዳ አቀናሁ፡፡ ወደ ፀበል ቦታው ለመግባት ለፍተሻ ተሰልፈናል፡፡ የፀጥታ ኃይሎች እየተዘዋወሩ ሰልፈኛውን ይቃኛሉ፤ትዕዛዝ ይሰጣሉ፡፡ [አብዛኞቹ የፀጥታ ኃይሎቹ በመልካም ሁኔታ ሕዝቡን ሲያስተናግዱ ተመልክቻለሁ] … ከትዕዛዞቻቸው አንዱና ዋነኛው የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል (ማስክ) ማድረግን የሚመለከት ነው፡፡
ከሞላ ጎደል ሁሉም ሰው ጭምብል አድርጓል:: ማስክ ያላደረጉት ጥቂቶችም እዚያው በሰልፉ መሐል ማስኮችን እያዞሩ ከሚሸጡ ወጣቶች ላይ እየገዙ እያደረጉ ነው:: በግምት ከእኔ ፊት አምስተኛ ላይ የተሰለፈው ወጣት ማስክ አላደረገም፡፡ አንድ ፖሊስ ወደ ወጣቱ ቀረብ ብሎ ማስክ እንዲያደርግ ነገረው፡፡ የወጣቱ ምላሽ ግን እጆቹን የሱሪው ኪሶች ውስጥ በመክተት የታጀበ ዝምታ ነበር:: ‹‹ምናልባት አልሰማኝም ይሆናል›› ብሎ የተጠራጠረው ፖሊስ ወጣቱ ማስክ እንዲያደርግ በድጋሚ ነገረው፡፡
የወጣቱ ምላሽ ግን አሁንም ዝምታ ሆነ፡፡ በሌላኛው ረድፍ ከጎኑ የተሰለፉት እንዲሁም ከፊትና ከኋላው ያለነው ሁሉ ተገረምን፡፡ ወጣቱ በእጁ ይዞት ያየነው ማስክ እንደእኔ ‹‹ማስክ የለው ይሆን እንዴ?›› ብለን ላሰብን ሰዎች ምላሽ ሆኖናል፡፡ በወጣቱ ሁኔታ የተገረመው ፖሊስም ለምን ማስክ እንደማያደርግ በድጋሚ ጠየቀው፤ማስክ ካላደረገ መሰለፍም ሆነ ወደ ውስጥ መግባት እንደማይችልም አስጠነቀቀው፡፡ ወጣቱ ግን ይባስ ብሎ ‹‹አላደርግም›› ብሎ አግራሞታችንን ወደ ድንጋጤና ንዴት ለወጠው፡፡
በዚህ ጊዜ ነው ለእምቢተኛው ወጣት ተደጋጋሚ ምክርና ማስጠንቀቂያ የሰጠው ፖሊስ ብቻ ሳይሆን የእኛም ትዕግሥት ያለቀው፡፡ ፖሊሱም ‹‹ … ማስክ ለማድረግ ፈቃደኛ ካልሆንክ’ማ ወደ ውስጥ መግባት አትችልም … ›› በማለት ወጣቱን ከሰልፉ ውስጥ አስወጣው፡፡ ብዙ ሰው ወጣቱን ጥፋተኛ አደረገው፡፡ ‹‹ … አንዳንድ ሰው አውቆ ለመረበሽ ይመጣል … ‹ማስክ አላደርግም› የሚባል እብሪት ከምን የመጣ ነው? … ›› የሚሉ ድምፆችን ሰማሁ፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ ከተነገረበት ቀን ጀምሮ እስካሁን ድረስ በአገሪቱ ውስጥ ከ132ሺ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል፤ከሁለት ሺ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በእርግጥ ቫይረሱ በአውሮፓ፣ በአሜሪካና በእስያ ያደረሰውን ጉዳት ያህል ባያደርስብንም ‹‹ምንም አላደረገንም›› ማለት ግን አይደለም፡፡ ቀላል የማይባሉ ማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ፖለቲካዊ ጫናዎችን አሳርፎብናል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እስከማወጅ የደረሱ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የሚያስችሉ እርምጃዎች ተወስደው ውጤት ተመዝግቦባቸዋል፡፡ በሌሎች አገራት የተመዘገበው አስደንጋጭ የሟቾች ቁጥር በኢትዮጵያ አለመመዝገቡ በእርምጃዎቹ ትግበራ ብቻ ሳይሆን በፈጣሪ እርዳታ ጭምር የተገኘ እድል እንደሆነ እኔን ጨምሮ የሚሊዮኖች እምነት ነው፡፡
በአገሪቱ በተለይም ሕዝብ በሚበዛባቸው እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች የቫይረሱን ስርጭት ያባብሳሉ ተብለው ከተገመቱ ቦታዎች መካከል አንዱ የመጓጓዣ አገልግሎት ነው፡፡ ለስድስት ወራት ያህል ታውጆና እየተተገበረ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እድሜው ማለቁን ተከትሎ ቀድሞ ከነበረው ብዙም ሳይለወጥ የቀጠለው የመጓጓዣ አገልግሎት ‹‹ኮሮና የሚባል ነገር የለም›› የተባለ እስከሚመስል ድረስ ችላ ተብሏል፡፡
አገልግሎቱን ለማግኘት የሚስተዋሉት መጋፋቶችና የሚታዩት የተጨናነቁ/አካላዊ ርቀትን ያልጠበቁ/ ሰልፎች ያስፈራሉ፡፡ በተሸከርካሪዎች ውስጥ ማስክ አለማድረግና አካላዊ ርቀትን አለመጠበቅ፣ ብርና ሳንቲም ከተለዋወጡ
በኋላ የእጅ ማፅጃ (ሳኒታይዘር) አለመጠቀም እንዲሁም ሳልና ማስነጠስን በተገቢው መንገድ አለማስተናገድ, ‹‹ማስክ አላደርግም›› እንዳለው የጃንሜዳው ወጣት ድርጊት ያስደነግጣሉ፤ያስፈራሉ፡፡
ለወትሮው ትርፍ በመጫን የሚታሙት የታክሲ አሽከርካሪዎችና ረዳቶች አሁን ግን በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የተቀመጡ ደንቦችን መሰረት በማድረግ መጫን ሲጀምሩ ‹‹እቸኩላለሁ፤እንደድሮው ጠጋ ጠጋ ብለን እንቀመጣለን … ችግር የለውም፤ኮሮና የሚባል ነገር የለም … ›› እያሉ ደንቦቹን ለመጣስ የሚጥሩ ብዙ ተሳፋሪዎች አሉ፡፡
‹‹የመዝናኛ›› ስፍራዎችም እንደመጓጓዣ አገልግሎቶች ሁሉ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን የሚያባብሱ ቦታዎች ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት በእነዚህ ስፍራዎች የሚስተዋለው ከልክ ያለፈ ግዴለሽነት ‹‹ቫይረሱ ተሰባስበን የመብላት፣ የመጠጣትና የመዝናናት አገራዊ ልማዳችንን ጎድቶብን ቆይቷል …›› የሚል የ‹‹በቀል›› ስሜት ያዘለ ይመስላል:: እኛ ‹‹በቀል›› ያስመሰልነውን መዘናጋት ቫይረሱ እጥፍ አድርጎ እንዳይመልስልን መጠንቀቅ ያሻል!
ቫይረሱ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ በታወቀበት ሰሞን ይደረግ የነበረው ጥንቃቄ አሁን የለም፡፡ ውሃ ተሞልተው በየቦታው ተቀምጠው የነበሩት የእጅ መታጠቢያዎች ዛሬ የውሃ ሽታ ሆነዋል፡፡ አካላዊ መራራቅ ለመተቃቀፍና ለመሰባሰብ ቦታውን አስረክቧል፡፡ መጨባበጥ እንደወትሮው ቀጥሏል፡፡
ታዲያ እነዚህ ሁሉ መዘናጋቶች የፅኑ ህሙማን ቁጥር በእጅጉ እንዲያሻቅብና የሟቾችም ቁጥር እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል፡፡ ቀድሞውንም ቢሆን ቁጥራቸው ጥቂት የነበሩት አጋዥ የመተንፈሻ መሳሪያ (ቬንትሌተር) የተገጠመላቸው የጽኑ ህሙማን መታከሚያ ክፍሎች በሙሉ በታካሚዎች ተይዘው በክፍሎቹ ለመስተናገድ የሚጠብቁ ህሙማን እንዳሉ ተገልጿል፡፡ ወረርሽኙ
ደግሞ ለጽኑ ታማሚነት ደረጃ ላይ ካደረሰ ፋታ የሚሰጥ አይደለም፡፡ የሕክምና ባለሙያዎች በተደጋጋሚ እንደገለፁት ወደ ጽኑ ሕሙማን ክፍል የገቡ የበሽታው ተጠቂዎች ከሌሎች ታካሚዎች ጋር ሲነፃፀር የመዳን (የመትረፍ) እድላቸው ዝቅተኛ ነው፡፡ የጽኑ ሕሙማን መታከሚያ ክፍሎች እጥረትና የሕክምና ባለሙያዎቹን ገለፃ በአገራችን ከሚስተዋለው መዘናጋት ጋር ስንደምረው የምናገኘው ውጤት ‹‹የሟቾች ቁጥር በእጅጉ መጨመር እና የጤናውን ጨምሮ የሌሎች ዘርፎች መናጋት›› የሚል ይሆናል፡፡
በቅርቡ የተጀመረው ‹‹እንድናገለግልዎ ማስክዎን ያድርጉ›› አገራዊ ንቅናቄ ቀደም ሲል ይደረጉ ከነበሩት ጥንቃቄዎች መካከል ጥቂቶቹን በድጋሚ በማጠንከር የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ጉልህ ፋይዳ ይኖረዋል ተብሎ ይታመናል፡፡
የሕክምና ባለሙያዎች ጥንቃቄ እንድናደርግ ያለመታከት ሲናገሩ ከርመዋል፤አሁንም እየተናገሩ ነው:: እንደ እኛ ጥንቃቄና ዝግጅት ቢሆን’ማ በጤና ዘርፍ አገልግሎታቸው እጅግ በላቁት በአሜሪካና በአውሮፓ ከተመዘገበው የታማሚዎችና የሟቾች ቁጥር የበለጠ ባስመዘገብን ነበር፡፡ እንደሚፈለገው ባይሆንም መጠነኛ ሊባሉ በሚችሉ የጥንቃቄ እርምጃዎችና በፈጣሪ እርዳታ እስካሁን የአሜሪካና የአውሮፓ እጣ ፈንታ አልደረሰንም::
በዓለም ዙሪያ ከ98 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በቫይረሱ ተይዞና ከሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን የሚበልጠው ደግሞ በዚሁ ወረርሽኝ ምክንያት ለሞት ተዳርጎ ሳለ ‹‹ኮሮና የሚባል ነገር የለም›› እያሉ ማውራት ፈጣሪንም ሆነ ሰውንም ማስቸገር ነው፡፡ ስለሆነም በሕክምና ባለሙያዎች የሚመከሩትን የመከላከያ ዘዴዎች (በተለይም የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማድረግን) በመተግበር የአስከፊውን ቫይረስ ስርጭት መቆጣጠር ይገባል!
አዲስ ዘመን ጥር 17/2013