አስመረት ብስራት
ስለ ዝሆኔ በሽታ ምን ያህል ያውቃሉ? የዝሆኔ በሽታ ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀስ ሲሆን በባዶ እግር በመሄድ የተነሳ የሚከሰት የእግር እብጠት በሽታ ነው፡፡ በበሽታው ከተያዙ በኋላም ቀላል የሕክምና አማራጮችን በመከታተል መዳን የሚችል እንዲሁም በሽታውም በቀዳሚነት የሚከሰትባቸው አካባቢዎች ቀይ ሸክላማ አፈር ያለባቸው ከባህር ጠለል በላይ 1000 ሜትር የሚገኙ ደጋና ወይናደጋ ቦታዎች ላይ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።
ለምሳሌ ሊምፋቲክ ፍላሪያሲስ ተብሎ የሚታወቀው ዝሆኔ መነሻው በጥገኛ ትላትሎች የፍላሪዮ አይደያ በሆነው ዝርያ ሲሆን በበርካታ ክስተቶች ህመም ይታያል። የዝሆኔ በሽታን ለመከላከል በሽታው ይገኝበታል በሚባልበት አካባቢ የሚኖረውን የኅብረተሰብ ክፍል ግንዛቤ መስጠት ተገቢ እንደሆነ የሕክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ።
በተጨማሪም በሽታውን ለመከላከል ዘወትር ጫማ ማድረግ፤ አፈር ወለል በሚገኝባቸው ቤቶች ውስጥ ምንጣፍ ማንጠፍ እና የእግር ንጽህናን መጠበቅ ሁነኛ መፍትሔዎች እንደሆኑ ያስረዳሉ፡፡
የበሽታው የመጀመሪያ ደረጃ ምልክቶች አብዛኛውን ጊዜ የእግርን የላይኛውን ቆዳ ማሳከክ እና የታችኛውን መርገጫዎች የማቃጠል ስሜት የሚፈጥሩ ናቸው። በዚህም በእግር የላይኛው ቆዳ ላይ የተሰራጩ እብጠቶችን መፍጠር፤ ከተሰነጠቀ ቆዳ የሚወጣ ፈሳሽ መኖር እና መጥፎ ጠረን ማሳየቱ የበሽታው ቀጣይ ምልክቶች ናቸው፡፡
ዝሆኔ መሰል የእግር እብጠት በሽታ ፖድኮኒዮሲስ ማለት የዘር ተጋላጭነት ኖሯቸው ለረዥም ጊዜ በባዶ እግራቸው የሚሄዱ ሰዎች ቀይ አፈር ውስጥ ከሚገኙ አብረቅራቂ ቅንጣቶች ጋር በሚኖር ንክኪ ምክንያት በሂደት የሚያጋጥማቸው የእግር እብጠት በሽታ ነው።
ሌላው ደግሞ የእከክ በሽታ (ስኬቢስ ማለት ደግሞ ቆዳን ሰርስረው በሚገቡ ጥቃቅን ነፍሳት አማካኝነት የሚከሰትና ከባድ ማሳከክ የሚያስከትል የተለመደ ተላላፊ የቆዳ በሽታ ነው፡፡ ማይሴቶማ ማለት በዝግታ የሚያድግ የቆዳ እና የመሠረታዊ ጡንቻዎች መታጠፊያ ቁስለት በሽታ ነው።
ፖዶኮኒዮሲስ ተላላፊ ያልሆነ የዝሆኔ ዓይነት ሲሆን ከሰው ወደ ሰው የማይተላለፍና እግርንና ሌሎች የሰውነት ክፍሎችን የሚያሳብጥ በሽታ ሲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ የበሽታው ስርጭት በትክክል የተለየ ባይሆንም በሽታው በአፍሪካና ደቡብ ምዕራብ እሲያ የሚገኝ ሲሆን በሽታው ከሚገኝባቸው 10 የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ኢትዮጵያ፣ ካሜሮን፣ ኡጋንዳና ሩዋንዳ በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡
በሽታው አፈር ውስጥ ባለው አሉሚንየም ሲልኬት በተባለ ንጥረ ነገር በሰውነት ውስጥ ከገባ በኋላ ሰውነታችን የውሃ ማስተላለፊያ እንዳይኖረው በማድረግ ለከፍተኛ የእግርና የሰውነት ማበጥ ችግሮችን በማስከተል ለከፋ አካላዊና ማህበራዊ ቀውስ ይዳርጋል፡፡
በሐሩራማ አካባቢ በብዛት የሚገኙ እና ትኩረት የተነፈጋቸው የቆዳ በሽታዎች (NTDs) ላይ ዓላማ አድርጎ የሚሠራው 5S ፋውንዴሽን የተሰኘ ፕሮጀክት 3.5 ሚሊዮን የእንግሊዝ ፓውንድ ተመድቦለት ተግባራዊ ማድረግ ጀምሯል::
ፕሮጀክቱ የብራይተን እና በሰሴክስ ሜዲካል ትምህርት ቤት (BSMS) መቀመጫውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ካደረገው የምሥራቅ እና የደቡባዊ አፍሪካ የማህበራዊ ሳይንስ ምርምር ድርጅት (OSSREA)፣ ከሱዳን ማይሴቶማ ምርምር ማዕከል (MRC)፣ ከሩዋንዳ ዩኒቨርሲቲ እና ከእንግሊዝ የልማት ጥናት ኢንስቲትዩት (IDS) ጋር በመተባበር እየተተገበረ የሚገኝ የምርምር ፕሮጀክት ነው:: ፋውንዳሽኑ በእንግሊዝ መንግሥት ከብሔራዊ የጤና ምርምር ተቋም (NIHR) በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የሚተገብር መሆኑን በኢትዮጵያ የ5S ፋውንዴሽን ፕሮጀክት ተጠሪ እና የጥናቱ ዋና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ጌትነት ታደለ ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ በአፍሪካ ውስጥ በስፋት በሚገኙ ሦስት ዓይነት የቆዳ በሽታዎች ማለትም ዝሆኔ መሰል የእግር እብጠት (ፖድኮኒዮሲስ)፣ እከክ (ስኬቢስ) እና ማይሴቶማ ላይ ትኩረት በማድረግ ይሠራል፡፡ እነዚህ ህመሞች ፕሮጀክቱ እየተተገበረባቸው ባሉ ሦስት ሀገሮች በኢትዮጵያ፣ በሱዳን እና በሩዋንዳ ከፍተኛ የኅብረተሰብ ጤና ችግሮች ናቸው፡፡
ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት በሚገኙ ሁለት ዓይነት የቆዳ በሽታዎች ማለትም ዝሆኔ መሰል የእግር እብጠት (ፖድኮኒዮሲስ እና እከክ (ስኬቢስ) ላይ ትኩረት በማድረግ ሥራ ይሠራል፡፡
የፕሮጀክቱ ጥናት በማህበራዊ ሳይንስ እይታዎች ላይ በመመርኮዝ በበሽታዎቹ የተጠቁ የማህበረሰብ ክፍሎችን የጤንነት ሁኔታ ቀጣይነት ባለው መልኩ መለወጥ የሚችሉ የትግበራ ስልቶችን በግለሰብ/ በነዋሪዎች ደረጃ፣ በማህበረሰቡ ደረጃ እንዲሁም ደግሞ በፖሊሲ ደረጃ ይለያል፡፡
ከበሽታዎቹ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ ማህበራዊ ችግሮች አስመልክተው የሚከተለውን ሁኔታ ፕሮፌሰር ጌትነት ሲገልፁ:- «በኢትዮጵያ ውስጥ በሐሩራማ አካባቢ በብዛት የሚገኙ ትኩረት የሚሹ የቆዳ በሽታዎችን በመከላከል ረገድ ከሚጠቀሱ ተግዳሮቶች መካከል ዋነኛው በታማሚዎች ላይ የሚደርስ መገለል ነው::»
በተጨማሪም ፕሮፌሰሩ ስለሁኔታው ሲያብራሩ፡- «ጉዳዩን የበለጠ የከፋ የሚያደርገው ደግሞ አንድ ጊዜ ተጎጂዎቹ በበሽታው እንደተያዙ ከታወቀ፣ የምንጊዜም መለያቸው እንዲሆን እና ከማህበረሰቡ የተለዩ ተደርገው መታየታቸው ነው:: ይህ ደግሞ በበሽታዎቹ የተጠቁ ግለሰቦችን ማንነት፣ ያላቸውን አቅም እና ችሎታ ሳይታወቅ ተደብቆ እንዲቀር ይሆናል፡፡»
«በበሽታው አማካኝነት የሚከሰተው ህመምና አካላዊ የቅርጽ ለውጥ በሚሰጡ ህክምናዎች ሊድኑና ሊሻሻሉ ይችሉ ይሆናል ሆኖም ግን አብሮ የሚዘልቀው ተጓዳኙ ማህበራዊ መገለልና መድሎ ግን በቀላሉ ሊጠፋ አይችልም:: እንዲያውም በተጎጂዎቹ ማንነት ላይ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ መጥፎ ጥላ ማጥላቱን ይቀጥላል::
እንደ አለመታደል ሆኖ እስካሁን ድረስ ከበሽታዎቹ ጋር በተያያዘ በተጎጂዎች ላይ የሚስተዋል መገለልን ለማስወገድ የተደረገው ሙከራ ውጤቱ ሙሉ በሙሉ አጥጋቢ አልሆነም::»
በመጨረሻም ፕሮፌሰር ጌትነት የገለፁት «ፕሮጀክቱ በማህበረሰቡ ውስጥ የሚከሰት መገለልን በመግታት ረገድ፣ የማህበረሰቡን አመለካከት በመለወጥ ዙሪያ፣ እንዲሁም ደግሞ አሰራሮችንና ፖሊሲዎችን ለማሳደግ እና ለመለወጥ አስተዋፅዖ ይኖረዋል፡፡» ሲሉ ነው።
በአጠቃላይ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለበሽታው ተጠቂዎች ህክምና ከመስጠት ባለፈ በኅብረተሰቡ ውስጥ በተሳሳተ አመለካከት ህመምተኞችን የማግለል እሳቤ እንዳይኖር ማስረዳት ተገቢ ሲሆን፤ ይህ በመደረጉ ከአካላዊ ተፅዕኖው በተጨማሪ ሥነልቦናዊ ህክምና ይሰጣልና መንግሥትም በጉዳዩ ላይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል እንላለን።
አዲስ ዘመን ጥር 17/2013