ዳንኤል ዘነበ
ትምህርት ለሰው ልጆች ንቃተ ህሊና እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው። የትምህርት ዓላማ የሕዝቡን የአስተሳሰብ፣ ሞራልና ማኅበራዊ መስተጋብሩን ማጠናከር፤ ግቡም ተማሪዎች ኃላፊነት እንዲሰማቸው፣ ዕውቀትና ጥበብን ለመመርመር ተነሳሽ እንዲሆኑ ማድረግ ነው። የትምህርት አላማ በትክክል ግቡን እንዲመታ ለግብረ ገብ ትምህርት ዋጋ መስጠት እንደሚያስፈልግ በብዙዎች ይታመናል።
እ.ኤ.አ. በ1933 የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት የነበሩት ማይክል ሲቨርን በትምህርት ማህበራዊ ለውጥ ማምጣት የሚቻለው ለግብረ ገብ ትምህርት ትኩረት መስጠት ሲቻል እንደሆነ ተናግረዋል ነበር።
በእውቀትና በሥነ ምግባር የታነፀ ምክንያታዊ ማህበረሰብ ለመፍጠር የግብረ ገብ ወይም ሥነ ምግባር ትምህርት ትልቅ ቦታ ሲሰጠው እንደሆነ ፕሮፌሰሩ በንግግራቸው ያመላከቱት፤ «ግብረ ገብነትና ሥነ-ምግባር ሰላማዊ የሆነ ማህበረሰብ ይኖረን ዘንድ የግድ የሚያስፈልጉን ተገቢና ጠቃሚ የመልካም ተግባር መርሆችን ናቸው።
ስለዚህ ግብረ ገባዊነት የኅብረተሰብና የአገር መሠረት ከመሆኑ አንፃር ከታች ጀምሮ የግብረ ገብ ትምህርት መሰጠት አለበት» ነበር ያሉት። በርካታ ሀገራት የትምህርት ፖሊሲያቸውን ሲያዘጋጁ ለግብረ ገብ ትምህርት ትልቅ ቦታ በመስጠት ስኬትን መጨበጥ ችለዋል።
በዚህ ረገድ በዓለም ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ እና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑትን የእነ ጃፓን፣ ቻይና፣ ኮሪያ ዋነኛ ተጠቃሽ ሀገራት ናቸው። የትምህርት ተቋማቶቻቸውን የእውቀት መሰረት እንዲሆኑ ከመገንባት ባሻገር፣ ሀገሩን የሚወድ፣ በሥነ ምግባር የታነጸ ጨዋ ትውልድ የመፍጠር አቅምን የተላበሱ ማድረጋቸው ነበር።
የሀገራቱ ትምህርት ሥርዓት ለሀገር በቀል የግብረገብ ትምህርት ትኩረት ከመስጠት ባሻገርም፤ ሥርዓተ ትምህርታቸውን የቀረጹት የማህበረሰቡን ታሪክ፣ ባህል፣ እሴት፣ ሥነ ልቦናን መሰረት በማድረግ ነው።
የተጠቀሱትና ሌሎች ሀገራት ተሞክሮ በትምህርት የሕዝብን አስተሳሰብ፣ ሞራልና ማኅበራዊ መስተጋብርን በማጠናከር ረገድ በጎ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻለው ሁሉ፤ የግብረ ገብ ትምህርት በጎደለው ሥርዓት ከተመሩ ውጤቱ አስከፊ መሆኑ አይቀሬ ነው። ይህም በትምህርት ሀገር ገንቢም ትውልድ መፍጠር እንደሚቻል ሁሉ፤ ሀገር አፍራሽ ትውልድ መፍጠር የሚቻል መሆኑን ያሳየናል።
ለዚህ ደግሞ የሀገራችን ተሞክሮ ይሄንኑ ያረጋግጥልናል። የትምህርት ተቋማቶቻችን ዜጎችን በእውቀት በጥበብ በሥነ ምግባር ለማነጽ እየተጉ ቢሆንም፤ በሥነ ምግባሩ የተመሰገነ ትውልድ እያፈሩ አለመሆኑን ብዙዎች ሲናገሩ ይደመጣሉ።
የወጣቶችን ሥነምግባርና የባህሎቻችንን መጣስ በዋቢነት በመጥቀስ «የዘመኑ ትምህርት ግብረ ገብነትን ከማስረጽ አንፃር ፈዛዛ ነው» የሚሉ ትችቶች ይሰነዘራሉ። ከእነዚህ ትችቶች ጀርባ፤ የትምህርት አላማ ግቡን እንዳይመታ ለግብረ ገብ ትምህርት ዋጋ አለመሰጠቱን ያረጋግጥልናል።
የኢፌዴሪ የፖሊሲ ጥናት እና ምርምር ማዕከል በ2009 ዓ.ም ይፋ ያደረገው የጥናት ውጤት ይሄንኑ ያረጋግጥልናል። የምርምር ማዕከሉ «በትምህርት ተቋማት የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ግንባታና ዴሞክራሲያዊነት፣ ተግዳሮቶችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች» በሚል ርዕሰ ጉዳይ ለንባብ አብቅቶት በነበረው የጥናት ውጤት፤ በኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት «የሥነ ምግባርና ሥነ ዜጋ ትምህርት» በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ ተካቶ እየተሰጠ ይገኛል።
ይሁን እንጂ የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ትምህርት ተማሪዎችን በሥነ ምግባር በማነፅ ረገድ ውጤታማ አለመሆኑን ማረጋገጥ መቻሉን አስታውቋል። በማዕከሉም በተደረገው ጥናት እንደተረጋገጠው መንግሥትም በተጨባጭ እንዳመነው በትምህርት ሥርዓቱ ላይ ዋጋ ያልተሰጠው የግብረ ገብ ትምህርት ሀገሪቱን ዋጋ እያስከፈላት እንደሆነ መታዘብ ይቻላል።
በሀገራችን እየተስተዋለ ለሚገኘው የማኅበራዊ ቀውስ፤ ታሪክን ማንቋሸሽ፤ ሀገር ክብርና ፍቅር አልባ መሆን፤ ገንዘብ እስካገኘ ድረስ ለዜጋው ለወገኑ ደንታ ቢስ ትውልድ ለመፈጠሩ የትምህርት ሥርዓቱ ጎዶሎነት ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ ብዙዎች ይስማሙበታል። የኢፌዴሪ የፖሊሲ ጥናት እና ምርምር ማዕከል በጥናቱ ለጠቀሳቸው ችግሮች ያቀረባቸውን መፍትሄዎች ስንመለከት ይሄንኑ ይነግሩናል።
«የአንድ አገር ትምህርት ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ትምህርት ጎን ለጎን ዜጎች የማህበረሰባቸውን እና የዴሞክራሲ እሴቶችን እንዲረዱ፣ በማህበረሰባቸው ውስጥ ስለሚኖራቸው ሚናና ሚናቸውን በአግባቡ መወጣት የሚያስችላቸው ክህሎት እንዲያገኙ እና አገር ወዳድ እንዲሆኑ የሚያስችል መሆን እንዳለበት» በመፍትሄነት ጠቁሟል::
በመንግሥት በኩልም ተመሳሳይ አቋም የተወሰደ ስለመሆኑ፤ ነሐሴ 14 ቀን 2010 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ይፋ በተደረገው የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ፤ ከሥርዓተ-ትምህርቱ ችግሮች መካከል የግብረ-ገብ ትምህርትን በሚፈለገው ልክ አካቶ አለመያዙ መሠረታዊ ችግር እንደሆነ ተገልጿል። አሁን የተዘጋጀው የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ ለሀገር በቀል የግብረ ገብ ትምህርት ትልቅ ዋጋ እንዲሰጥ ተደርጎ መሆኑ ተስፋን አጭሯል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶክተር ዳኛቸው አሰፋም ሀገር በቀል የግብረ ገብ ትምህርትን በፍኖተ ካርታው ዳግም መካተቱ የጎበጠውን ለማቃናት እንደሚያግዝ አስተያየታቸውን መስጠታቸው ይሄንኑ ያመላክታል።
«የግብረ ገብ ትምህርት ድሮ ልጅ እያለን ከሁለተኛ ክፍል ወይም ከሦስተኛ ክፍል ጀምሮ እንማር ነበር» ሲሉ ያስታወሱት ዶክተር ዳኛቸው፤ የግብረ ገብ ትምህርት በትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታው ተካቶ ተመልሶ እንዲሰጥ መደረጉ ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል።
አንድ ሀገርና ማህበረሰብ ያለ ግብረ ገብና ሞራል እሴት ሊኖር እንደማይችል በመገንዘብ፤ በትምህርት ፍኖተ ካርታው ትኩረት የተሰጠውን የግብረ ገብና ሥነ ዜጋ ትምህርትን ወደ ተግባር ለመቀየር የሚደረገው ጥረት እንደቀጠለ ለማወቅ ተችሏል።
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ትምህርት ሚኒስቴር ሀገር በቀል የግብረ-ገብ፣ የዜግነትና የሰላም ዕሴቶችን ያካተተ ሥርዓተ-ትምህርት ለማዘጋጀት እየሰራ መሆኑን ይፋ ማድረጉ ይሄንኑ ያመላክታል፡፡ በታኅሣሥ 27 ቀን 2013 ዓ.ም ሚኒስቴሩ በሥርዓተ ትምህርቱ ውስጥ የሀገር በቀል የግብረ-ገብ፣ ዜግነትና የሰላም ዕሴቶች ላይ ግብዓት መሰብሰብ ዓላማ አድርጎ ባዘጋጀው አውደ ጥናት ይሄንኑ አስታውቋል። በአዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ዋጋ የተሰጠው የግብረ ገብና የዜግነት ትምህርት ከ1ኛ-6ኛ ክፍል የግብረ-ገብ ትምህርት እንዲሁም ከ7ኛ ክፍል ጀምሮ ደግሞ የዜግነት ትምህርት ተብሎ እንደሚዘጋጅ ይጠበቃል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 17/2013