አስናቀ ፀጋዬ
ከኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት የተገኙ መረጃዎች እንደሚያሳዩት እስከ 7 ሺ የሚደርሱ ትላልቅ የእፅዋት ዝርያዎች የሚገኙ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 12 ከመቶ ወይም 840 የሚሆኑት በኢትዮጵያ ብቻ ይገኛሉ:: የተፈጥሮ ደኖች ከማህበራዊ ፣ኢኮኖሚያዊና አካባቢያዊ ጠቀሜታ በተጨማሪ በውስጥ ላሉ የተለያዩ የዱር እንስሳት መኖሪያና የምግብ ምንጭ ሆነው የሚያገለግሉ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች በየጊዜው ጥፋት ሲደርስባቸው ይታያል፡፡
በተለይ በከፍተኛ ቦታዎች በሚገኙና 42 ሚሊዮን ሄክታር ይደርስ ከነበረው ወይም ከጠቅላላ የሃገሪቱ የቆዳ ስፋት 35 በመቶ ይሸፍን የነበረው የተፈጥሮ ደን በአደገኛ ሁኔታ በመጎዳት ላይ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት መረጃ ያረጋግጣል፡፡ የብዝሃ ህይወቶች ክምችት በተፈጥሮ ደን ውስጥ የሚገኙ ቢሆንም አሁንም የተፈጥሮ ደኖችን ለመጠበቅና ለመንከባከብ የሚደረገው ጥረት አርኪ አለመሆኑም ይገልፃል፡፡
የተፈጥሮ ደኖች በስፋት ከሚገኝባቸው የሀገሪቱ ክልሎች ውስጥ አንዱ የኦሮሚያ ክልል ሲሆን በክልሉ በተለይም በአራቱም የወለጋ ዞኖች ስፋት ያለው የተፈጥሮና በሰው የተተከለ ደን ሃብት እንዳለ ከክልሉ ደንና ዱር እንስሳት ድርጅት የተገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ሆኖም ይህ ብዛት ያለው የተፈጥሮና በሰው የተተከለ የደን ሃብት እንክብካቤ አግኝቶና ተጠብቆ በዘላቂነት እንዲቆይ ከማድረግ አንፃር አሁንም ልዩ ልዩ ችግሮች እየፈተኑት እንደሆነ ይነገራል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ደንና ዱር እንስሳት ድርጅት የወለጋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደጀኔ ከበደ እንደሚናገሩት በወለጋ አራቱም ዞኖች 583 ሺ 318 ሄክታር ስፋት ያለው ደን ይገኛል፡፡ ከዚህ ውስጥ 576 ሺ ያህሉ የተፈጥሮ ደን ሲሆን 7 ሺ 318 ያህሉ ደግሞ በሰውየተተከለ ደን ነው፡፡
የተፈጥሮ ደኖቹም በአብዛኛው በቄለም ወለጋ ዞን ገርጌዳ ስቴት ፎረስት፣ በምዕራብ ወለጋ ጆርጎ ዋቶ ፎረስት፣ በምስራቅ ወለጋ ጫፎ ዘንጊ ደንገም ፎረስት እንዲሁም በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ቱሉ ላፍቶ አካባቢዎች ላይ ይገኛሉ:: በሰው የተተከሉ ደኖች ደግሞ በአብዛኛው በነቀምትና ጊምቢ ከተሞች እንዲሁም በሻምቡ ከተማ ዙሪያ በብዛት አሉ፡፡
ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ በሁለት መልኩ የደን ጥበቃና እንክብካቤ ስራዎችን እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን አንደኛው የአካባቢውን ህብረተሰብ በማሳተፍና በተለይም የተፈጥሮ ደን ሃብቶችን ለህብረተሰቡ በማስተላለፍ የሚደረግ ጥበቃና እንክብካቤ ሲሆን ይህን ስራ ለማከናወን ማህበረሰቡ እንዲደራጅ ተደርጓል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በሰው የተተከሉ ደኖችን ፅህፈት ቤቱ የራሱን ጥበቃዎች በመመደብና በማሰማራት ጥበቃና እንክብካቤ እያደረገ ይገኛል፡፡ ሌሎችም መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከጽሕፈት ቤቱ ጋር በመሆን የደን ጥበቃና እንክብካቤ ስራውን በተለያየ መልኩ ያግዛሉ፡፡ ህብረተሰቡም በደን ጥበቃና እንክብካቤ ዙሪያ ከእነዚሁ መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በፅህፈት ቤቱ በኩል ስልጠናዎችን ያገኛል፡፡
ኃላፊው እንደሚሉት በደኑ ዙሪያ ያለው የአካባቢ ማህበረሰብ ከደን ሃብቱ በተዘዋዋሪ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆን በሰው ከተተከለው ደን ሽያጭ 5 ከመቶ ያህሉን ገቢ እንዲያገኝ ይደረጋል፡፡ ከተፈጥሮ ደን ደግሞ በተለይ ከቀርከሃ ምርት ሽያጭ 50 ከመቶ ያህል ገቢው ለህብረተሰቡ እንዲሆን ይደረጋል፡፡
የተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የአካባቢውን ህብረተሰብ ህይወት ለማሻሻል ከሚያከናውኗቸው ፕሮጀክቶችም ህብረተሰቡ 50 ከመቶ ገቢ የሚያገኘው ከተፈጥሮ ደኖች ነው። በንብ ማነብና በከብት እርባታ ስራዎች ላይ በመሳተፍ ህይወታቸውን እንዲያሻሽሉም ድጋፍ ይደረግላቸዋል፡፡
በዞኑ ከሚገኙ የተፈጥሮና በሰው የተተከሉ የደን ሀብቶች ጋር በተያያዘ በተለይ በከተማ አካባቢዎች ደኖችን ተደራጅቶ የመዝረፍና ደኖቹ ባሉባቸው አካባቢዎች በመግባት መሬቱን ለግንባታ የመጠቀም ችግሮች በስፋት ይታያሉ፡፡
በተመሳሳይ በገጠር አካባቢዎች ላይም በኢንቨስትመንት ስም ወደ ደኖቹ ውስጥ የመግባትና ቡናዎችን በደን ውስጥ በመትከል የእርሻ መሬቶችን የማስፋፋት ችግሮችም ይታያሉ፡፡ በመንግስት በኩልም የደን ሃብቱ ያለበት መሬት ለሌላ ጥቅም እንዲውል ተደጋጋሚ ፍላጎቶች ይታያሉ፡፡
ከደን ሃብቱ ጋር በተያያዘ በተለይ በከተማ አካባቢ የሚታየውን ችግር ለመቅረፍ ከከተማ አስተዳደሮችና ከባለድርሻ አካላት ጋር ተደጋጋሚ ውይይት ተደርጓል:: ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቱ ሳያውቅ በደኑ አካባቢ ምንም አይነት የግንባታ ስራ እንዳይከናወንም በተከታታይ ለመንግስት ሪፖርት ቀርቧል፡፡ በዚህም ችግሮቹን በመጠኑም ቢሆን ለመፍታት ተችሏል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት የተውጣጣ ግብረኃይል በማቋቋም በደኑ አካባቢ የሚገነቡ ህገወጥ የቤት ግንባታዎችንና አጥሮችን እንዲፈርሱ እየተደረገ ነው፡፡ እነዚህም ስራዎች በተለይ በነቀምት ከተማ አካባቢ በስፋት ተሰርተዋል፡፡ በዚህ ተግባር የተሳተፉ ሰዎችም ለህግ እንዲቀርቡ መደረጉን የዞኑ ኃላፊ ይናገራሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት በዞኑ ያለው የፀጥታ ሁኔታ አስተማማኝ ባይሆንም ቀደም ሲል በገጠር አካባቢ በደኖች ውስጥ በህገወጥ መልኩ የተተከሉ ቡናዎች ህዝቡ ወጥቶ እንዲነቅልም በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 17/2013