አሸብር ኃይሉ
ለአንድ ሃገር ሉዓላዊነት መከበር ከሁሉም በፊት በሕዝቦች መካከል መከባበር እና አንድነት መኖር አለበት:: ከዚያም ቀጥሎ በፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በተለያዩ አደረጃጀቶች መካከል የአመለካከት አንድነት ወይም የመርህ አንድነት ባይኖርም እንኳን የሃገርን ሉዓላዊነትን አሳልፎ እስከሚሰጥ ድረስ መከፋፈል እና መነካከስ ፣ መወቃቀስ ሊኖር አይገባም ።
ከዚህ በላይ ግን ለአንድ ሃገር የመኖር እና ያለመኖር ህልውና ስጋት በመሆን የሚያስፈራው በአንድ የፖለቲካ ፓርቲ በተለይም በገዢው ፓርቲ ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ውይይት ከሌለ እና በፓርቲው አመራሮች መካከል እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ የሚል እሩጫ እና ፍትጊያ ካለ የውስጠ ፓርቲን አንድነት የሚያናጋ ስለሚሆን ለአንድ ሃገር መፍረስ ትልቅ ምክንያት ይሆናል ፡፡ ለከፋ እና ልንወጣው ወደማይቻል የእርስ በእርስ ጦርነትም ይዳርጋል፡፡
ይህን ስል ዝም ብየ አይደለም፤ ይልቁንም ከአለማችን የታሪክ ተሞክሮዎች በመነሳት እንጂ:: ለምሳሌ የላይቤሪያ የእርስ በእርስ ጦርነት እንዴት ተነሳ ፣ የኮርያ የእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያቱ ምንድን ነው? ፣የቻይናውያን እና የቬትናማውያን የእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያቱስ ምን ነበር ? በአለም ላይ የተካሄዱ አብዛኛዎቹ የዕርስ በእርስ ጦርነቶች እንደ ዋናው ምክንያት የሚጠቀሰው የተለያዩ መርህን ባነገቡ ፤ የግል ጥቅማቸውን ከሃገር ጥቅም ባስቀደሙ የንዋይ ሴሰኞች እና እውነተኛ ለሃገራቸው ህልውና በቆሙ ኃይላት መካከል በተፈጠረ ግጭት መሆኑ መረሳት የለበትም::
በዚህም የእርስ በእርስ ጦርነት ሃገራት የራሳቸውን ችግር በራሳቸው መፍታት ይሳናቸው እና የውጭ ሃገራትን እርዳታ ይሻሉ፡፡ ይህ ደግሞ ለጉልበታም ሃገራት ችግር በተፈጠረበት አካባቢ ሊኖር የሚችለውን ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ በማሰብ እንኳንስ ተጠርተው ይቅር እና ሳይጠሩ እንደ እርጎ ዝንብ ጥልቅ የሚሉ መሆናቸው የሚያጠራጠር አይደለም ፡፡
በዚህም በትንሽ ውሃ ይጠፋ እና ይበርድ የነበረው የመለያየት እና የመጠፋፋት እሳት ችግሩን እናጠፋለን በሚሉ ጣልቃ ገብ ሃገራት ችግሩን ለማጥፋት ውሃ እየጨመረን ነው በሚል ምክንያት አንድ ጉንጭ ውሃ ወደ እሳቱ ሲጨምሩ በአደባባይ ያሳዩን እና ብዙ ቦቴ ቤንዚል በስውር እሳቱ ላይ ጨምረው እሳቱን መብረጃ ያሳጡታል ፡፡ ነዳጅ የተጨመረበትም እሳት ከማንም ቁጥጥር ውጭ ይሆናል ፡፡
እሳት ደግሞ በብሄር ፣ በሃይማኖት ወዘተ መርጦ ስለማያቃጥል የተበጣበጡት ዜጎች በግፍ ያልቃሉ፡፡ በዚህ ግርግር ደግሞ ጣልቃ ገብ ሃገራት ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ግብ ግብ ሲገቡ ለችግሩ መባባስ ጣልቃ የገቡት ሀገራት መሆናቸው ለማንም በግልፅ ፈጦ ይታያል፡፡
ይሁን እንጂ ቤቱ በመቃጠል ላይ ስለሆነ እነዚህን ጣልቃ ገብ ሃገራት ማንም ሳይነካቸው ለጥቅማቸው መፋጨታቸውን ይቀጥሉበታል ፡፡ በዚህም ችግር የተፈጠረባት ሃገር ለማይበርድ ጦርነት እና ትርምስ ትዳረጋለች ፡፡
ለምሳሌ የቬትናምን የዕርስ በእርስ ጦርነት ብንመለከት ፤ ቬትናም የዕርስ በእርስ ጦርነት እንዳይበርድ ካደረጉት ዋና ምክንያት አንዱ የካፒታሊስቶች እና የሶሻሊስቶች” የተቆለፈበት መርዛማ ኢኮኖሚያዊ ምስጢር” ቁርቁስ ነበር ፡፡ የኮሪያም የእርስ በእርስ ጦርነትም በተመሳሳይ የካፒታሊስቶች እና የሶሻሊስቶች ኢኮኖሚያዊ ቁርቁስ ዋናው ምክንያት ነበር ፡፡ በዚህም ኮሪያም ሆነች ቬትናም የደረሰባቸውን ችግር ለማሰብ ሁሉ ይዘገንናል፡፡
ከላይ ያሉት ነገሮች ለማንም ይሰወራሉ ብየ አይደለም የፃፍኳቸው፤ ግን ለማስታወስ እና አሁን በእኛ ሀገር ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ለሚፈጠሩ ችግሮች አንድ “ የተቆለፈበት መርዛማ ሚስጥር” እንዳለ በማሳሰብ ሁሉም ኢትዮጵያዊ “ የተቆለፈበት መርዛማ ሚስጥር” ለመንቀል ቆም ብሎ በሰከነ መንፈስ ግራ ቀኙን እንዲያይ ለማሳሰብ ነው::
ምክንያቱም ኢትዮጵያን ለማጥፋት ያለመ አንድ የተቆለፈበት መርዛማ ሚስጥር እንዳለ በግልፅ ማየት ይቻላል ፡፡ ይህን ስል ዝም ብየ በግብዝነት እንዳልሆነ በአመክንዮ አንመልከት፡፡ ለምሳሌ በሶማሊያ እና በኦሮሚያ ፣ በጉጂ እና በቡርጂ ፣ በኮንሶ ሕዝቦች መካከል ፣ በአማራ እና በቅማንት ፣ በአማራ እና በጉምዝ ሕዝቦች ወዘተ መካከል የሚደረገውን ከተራ ግጭት ያለፈ ብጥብጥ መመልከት በቂ ነው ፡፡ ይህ ሁሉ ውጥንቅጥ ዝም ብሎ የመጣ አይደለም ፡፡ ይልቁንም አንድ ኢትዮጵያን ለማጥፋት ያለመ የተቆለፈበት መርዛማ ምስጢር ስላለ እንጂ፡፡
ከሁሉም ይባስ ብሎ አሁን ላይ ደግሞ ሱዳን የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ጥሳ ገባች ፡፡ አሁን የተቆለፈበት መርዛማ ምስጢር ሊከፈት ይመስላል:: ሱዳን በችግር በታመሰችበት ጊዜ ከማንም በላይ የሱዳንን ችግር ለመቅረፍ እና አሁን ወደ አለችበት አንፃራዊ ሰላም የመለሰቻት ኢትዮጵያ ነበረች ፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ ችግር በገጠማት ጊዜ ሱዳን የሰራችውን ስራ ተመልከቱ::
ይህ ማለት ምን እንደሆነ መረዳት ይቻላል ፡፡ ህወሓት ሲደራጅ ህወሓትን ያደራጀው ለዚያውም ቢሮ ካርቱም ላይ ከፍታ ያደራጀችው ሱዳን ነች ፡፡ እኔ እንደሚመስለኝ ህወሓትን በዘር ተኮር ፖለቲካ እንዲደራጅ እና የኢትዮጵያን አንድነት እንዲፈታተን ህወሓት እንኳን ሊረዳው በማይችለው ረቂቅ ስልት ኢትዮጵያን መርዛማ መርህ የጋተቸው ሱዳን እና ከሱዳን ጀርባ ያሉ ሃገራት መሆናቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ይህ መርዛማ መርህ ህወሓትን በሀገር መከላከያ ላይ ግድያ እስኪፈፅም ድረስ ያደነዘዘው መሆኑንን ልብ ሊባል ይገባል፡፡
ይህ የተቆለፈበት መርዛማ ምስጢር አንዳንድ ገዢው ፓርቲን ብልፅግናን አባላት ሲፈትን በአደባባይ እያየን ነው፡፡ ገዢው የብልፅግና ፓርቲ እንደነዚህ ያሉ ሃገር መርዝ የበሉ ባለስልጣኖቹን ከቻለ የውስጠ ፓርቲ ዲሞክራሲን በማጎልበት ከህመማቸው ሊያክማቸው ካልቻለ እንደ ጁንታው ህጋዊ እርምጃ ይውሰድባቸው:: አለበለዚያ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ያዘጋጁልንን የተቆለፈበት መርዝ መጠጣታችን አይቀሬ ነው ፡፡
እነኝህ የተቆለፈበት መርዛማ ሚስጥር ያዘሉ ሃገራት የሚስጥራዊ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ኤርትራን እንዴት ከእናት ሃገሯ እንደገነጠሏት እና ኢትዮጵያንም እንዴት ያለባህር በር እንዳስቀሯት እና ኤርትራ ያሉ እህት ወንድሞቻችንን ደማችን በደም ስራቸው እየተዘዋወረ እያወቅን ደማቸው ደማችን እንደሆነ እየተረዳን ሳንወድ በግድ ለያይተውናል:: አሁን ደግሞ ከዚያ የባሰ ሁኔታ የችግር ጋሬጣ ተደቅኖብን ምንድን ነው ችግራችን ከመባባል ይልቅ ልዩነታችንን እየሰበክን በግብዝነት እንድንቆም ልባችንን ያደነደነው ? ኧረ ጎበዝ ይህ ነገር አያዋጣንም!!
በመጨረሻም እኛ ኢትዮጵያውያን በአንድ ላይ እጅ ለእጅ በመያያዝ ከአልማዝ ማዕድን በበለጠ አንድነታችንን አጠናክረን የምንቆምበት ሰዓት አሁን ነው፡፡ ምክንያቱም የተቆለፈበት መርዝ ፈንድቶ ሀገራችንን ከማጥፋቱ በፊት ሁላችንም የዜግነት ግዴታችንን እንድንወጣ አደራ እላለሁ፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 17/2013