ኃይለማርያም ወንድሙ
አቶ ዮሐንስ ተገኔ አንስቴቲስት (የሰመመን ህክምና ሰጪ)ናቸው።አዲስ አበባ በሚገኘው ሃሌሉያ አጠቃላይ ሆስፒታል ይሠራሉ።በትርፍ ሰዓታቸው ደግሞ በድራማና በፊልም ተዋናይነት ይሳተፋሉ።
አቶ ዮሐንስ በልጅነታቸው ከሠፈር ጓደኞቻቸው ጋራ ድራማ እያሉ ይሠሩ ነበር ፡፡በቀድሞው ባሌ ክፍለ ሀገር ጊኒር ከተማ መኩሪያ ተሰማ ት/ቤት እና በከተማው ውስጥ በነበረ አንድ የክብር ዘበኛ 16ኛ ሻለቃ ውስጥም ልምምድ ያደርጉ እንደነበር ያስታውሳሉ።
ከክፍል ጓደኞቻቸው ጋር በር ላይ ሆነው ሌሎች ልምምድ ሲያደርጉ ይመለከቱ እንደ ነበር ያስታውሳሉ።በወቅቱ ከልጆች መሀል ተጠርተው ለድራማው በልጅ ገፀባህሪነት ሠርተዋል፡፡ ይህ ሁሉ በልጅነታቸው አዕምሮ ውስጥ ተሳለ፡፡ አቶ ዮሐንስ በትምህርት ቤትም ከሚለማመዱት በተጨማሪ ባደግ የሚባለው የሻለቃው አባል ሰዎችን በቲያትር በሚያሰለጥንበትና በሚያለማምድበት ጊዜ በልጅነቴ እመለከት ነበር፤ይህም ትልቅ ትምህርት ሆኖኛል ይላሉ።
ሰባተኛ ክፍል እያሉ ”እኔ ላንቺ ክፉ” የሚል ቲያትር እንዲሠሩ ተመርጠው አቶ ከበረ በሚል በዋና ገፀባህሪ ተጫወተዋል፤ ‹‹በጣም አሳዛኝ (ትራጀዲክ) ቲያትር ነበር፤በጥሩ ሁኔታ ተወጣሁት›› ሲሉ ያስታውሳሉ።
”ፍቅር ከሞት ያድናል” የሚል የክቡር ዶ/ር ከበደ ሚካኤል ትርጉም ቲያትር ዋናውን ገፀባህሪ እንድተወኑም ያስታውሳሉ። ”ቲያትሩ በትምህርት ቤት ዝና ካተረፉባቸው ቲያትሮች አንዱ ነበር፡፡ ‹‹በአካባቢው ከተሞች እየዞርን ከስካውት አባላት ጓደኞቼ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ቲያትር ታይቶ በማይታወቅባቸው ቦታዎች ጭምር እየዞርን አሳይተነዋል፡፡በዚህም ከፍተኛ አድናቆትን አግኝቼበታለሁ፡፡”ሲሉ ያብራራሉ፡፡
ጎባ እያሉ ችሎታቸውንና ተሰጥኦዋቸውን የሚያውቁ ሰዎች በሎሬት ፀጋዬ ገብረመድን የተተረጎመውን ሀምሌት የተሰኘውን የሼክስፒር ትያትር ውስጥ አንዲተውኑ ጠየቋቸው፡፡ለመጀመሪያ ጊዜ ዳሞንን ሆነው ተውነዋል፤ በቀጣዩ ዓመትም ዋናውን ገፀባህሪ ሀምሌትን ሆነው ሰርተዋል። ኦቴሎንም ጨምሮ፡፡ በዚህም ከፍተኛ አድናቆት አግኝበታለሁ የሚሉት አቶ ዮሐንስ፣ ውስጠ ወይራና አስመሳይ ምሁር በሚሉት አጫጭር ቲያትሮችም በወቅቱ መጫወታቸውን ያስታውሳሉ።
አሁን ደግሞ በሌላ ሙያ ውስጥ ቢገኙም በትርፍ ሰአታቸው በተዋናይነት ይሰራሉ፡፡እኔ የሠራሁባቸው ድራማዎች እያዝናኑ ቁምነገር የሚያስጨብጡ ናቸው የሚሉት አቶ ዮሐንስ፣ሣልሳዊን ካስት እንደተደረጉና ድርሰቱን እንዳዩት ፊልሙን የመሥራት ፍላጎት ያድርባቸዋል። ይህ ብቻም ሳይሆን የሚያስተላልፋቸው ቁም ነገሮች በተለይ ሀገራዊ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑ ፊልሙን በደስታ እንዲቀበሉት ያረጋቸዋል፡፡
አቶ ዮሐንስ፤ የፊልሙ ሁሉም ገፀባህሪዎች አስተማሪ ነበሩ፡፡ ሀገራችን ታሪካዊ ጠላቶች አሏት፤ እነዚህ ጠላቶቻችን እስከ ዛሬ ድረስ አልተኙልንም ይላሉ፡፡ ቲያትሩ ሀገራችን የተፈጥሮ ሀብቷን እንዳትጠቀም የሚደረገውን ደባ ያሳያል፡፡ለዚህም ደግሞ ዛቢያ ሆነው የሚያገለግሉት የኛው ዜጎች ናቸው።ይሄንን ለማስገንዘብ ነው የተሠራው ሲሉም ያብራራሉ።
ይህ ቲያትር ከአስር ዓመት በፊት መታየቱን፣ነገርግን ትምህርት እንዳልተወሰደበት ይገልጻሉ።በየሲኒማ ቤቶቹ እንዳይታይ ሲደረግ ቆይቷል፡፡እንደዚያም ሆኖ ግን ይህ በገባቸው ሰዎች ሁለት ጊዜ ተመርቋል፤በተለይ አረንጓዴ ኢትዮጵያ በሚል ድርጅት መጀመሪያ በማዘጋጃ ቤት ተመርቋል፤ ቀጥሎ በብሔራዊ ቲያትር እንዲመረቅ በዚሁ ድርጅት በአዲስ አበባ የሚገኙ አርቲስቶች ጭምር በተጋበዙበት እንዲታይ ተደርጎ ለሁለተኛ ጊዜ ተመርቋል።
በከተማችን በተለይ በመንግሥት ደረጃ ሆን ተብሎ በተዘዋዋሪ መንገድ እንዳይታይ ተደርጓል፤ያሳዝናል፡፡ሊበረታታ ይገባ ነበር፤ ለመንግሥትም መስታወት፣ለህዝብም ትምህርት ይሆን ነበር፡፡ እያዝናና የሚስተምር በቁም ነገር የታጨቀ ነበር፡፡ በዚህም ዋናውን ገፀ ባህሪ ሆኜ ተጫውቻለሁ፤መልዕክቱም በትክክል ደርሷል።የተሰጠኝን ገፀ ባህሪ ወክዬ ተጫወቻለሁ ብዬ የማምንበት ነው ሲሉ አቶ ዮሐንስ ያብራራሉ፡፡
በእሳት ቀለበት ፊልም ተመልምዬ ከጋዜጠኛ መስታወት አራጋው ጋር ሠርቻለሁ ይላሉ።ላባጆንም እንዲሁ በዋና ገፀባህሪ መጫወታቸውን ይጠቅሳሉ።ለባጆ ታላቅ ቁም ነገር ያጨቀ፣ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል የሚያስተምር ነው።ከሣልሳዊ በስተቀር ሁሉም በዩቲብ ላይ ይታያሉ፡፡
ወደ ላባጆ ከመሄዳቸው በፊት በእሳት ቀለበት መስራታቸውንም ይገልጻሉ፡፡ ይህም በትዳር መካከል የሚፈጠሩ ሳንካዎች ምን ያህል ዋጋ እንደሚያስከፍሉ የሚያስገነዝብ ነው፤ ችግሮቹ በወቅቱ ካልታረሙ ዋጋ እንደሚያስከፍሉ ጠቅሰው፣ የሰው ልጅን የጭካኔ ጥግ የሚያሳይ ነው ይላሉ።
ከቴሌቪዥን ድራማዎቹ በመጀመሪያ የተጫወቱት አየር ባየር ተከታታይ ድራማ መሆኑን ይገልጻሉ።በዚህም አስራደ በሚለው ዋና ገፀባህሪ ተጫውተዋል፡፡ሰዎች ለጥቅማቸው በአልጠግብ ባይነታቸው ምን ያህል በሰው ላይ ግፍና ተንኮል እንደሚሠሩ የሚያሳይ ነው ይላሉ።ድራማው በተከታታይ በዋልታ ቴሌቪዝን መተላለፉን ይጠቅሳሉ።
አቶ ዮሐንስ አየር ባየር ሁለተኛ ክፍል ለረጅም ጊዜያት በተከታታይ ለማስተላለፍ ተቀርጾ በዝግጅት ላይ መሆኑን በመጥቀስ፣ይህም ህዝቡን በማዝናናት ያስተምራል፤ ለተመልካችም ጥሩ የጊዜ ማሳለፊያ ይሆናል ይላሉ፡፡
የታጠቡ ኪሶች በሚል ድራማ ላይም ዋና ገፀ ባህሪውን ሆነው ተጫውተዋል። በዚህ ድራማ የሰዎችን ክፋት የሚያሳይ ገጸባህሪ ሆነው ነው የተጫወቱት።ድራማው በእህቶቻችን ላይ የሚደርሱትን አንዳንድ ጥቃቶችንም ሆነ የተለያዩ ችግሮችን በአጠቃላይ ኅብረተሰብን ቤተሰብን የሚመለከት ነው፡፡በጣም ደስ ብሎኝ የሠራሁት ነው፡፡በቃና ቴሌቪዥን በተከታታይ ለህዝብ ቀርቦ ታይቷል ሲሉ ያብራራሉ፡፡
ያለፈውን ዘመንና ያሁኑን እንዴት ይመለከቱታል በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም ሁለቱን ማወዳደር ይከብዳል ሲሉ ነው ምላሻቸውን የጀመሩት፡፡ በርግጥ በአልባሳት እና በመድረክ ዝግጅት አሁን በጣም ዕድገት አለ፡፡ በቀደመው ትያትር በባዶ መድረክ ለተመልካቾች አሳምነው አሳዝነው፣ አስደስተውም አስቀውም፣ አዝናንተውም ይለያዩ ነበር፡፡የዘመናችን የመድረክ ዝግጅቶችና መብራቱ የሚሰጡት ትልቅ ግብዓትና አስተዋፅዖ አለ፡፡በቴክኒኩም ዕድገት አለ፤ አሁንም የተለያየ አቅምና ችሎታ ያላቸው ወጣቶችም ሆነ ጎልማሶችም እንደየደረጃቸው አሉ ይላሉ፡፡
በስነምግባርም ወጣቱን የሚያንፁትን እንደ ስካውት እና ቲያትር ክበብ የመሳሰሉትን ብናጠናክር መልካም ነው ሲሉ ይመክራሉ።በስካውት ክበብ የሀይኪንግ ጉዞ የሚባል እንዳለ ጠቅሰው፣ እኛ ከጊነር ተነስተን ጎሮ፣ ሮቤ፣ ጎባ፣ ጋሰራ፣ ዶሎሰሮና ወለልቻጃራ ሁሉ እየሄድን ድራማ እናሳይ ነበር ሲሉ ያስታውሳሉ፡፡
አሁን የቲያትርና የስካውት ክበባት በየት/ቤቶቹ ቢጠናከሩ በተለይ ለገጠሩ የኢትዮጵያ ክፍል ጠንካራ የሆኑ ክበባት እየዞሩ ትምህርታዊ ድራማዎችን ቢያሳዩ የማዝናናት አቅም አላቸው፤ኅብረተሰቡን አልባሌ ቦታ እንዳይውል ማድረግም ያስችላል፡፡እየተዝናና ዕውቀትን ይገበይባቸዋል። በመንግሥት ደረጃ በተለይ ትምህርት ሚኒስቴር በዚህ በኩል ክበባቱ በተደራጀ መልኩ እንዲጠናከሩ እንዲቋቋሙ ግፊት ማድረግ ይኖርበታል። ፖሊሲም ሊይዘው የሚገባ ጉዳይ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
በአጠቃላይ መንግሥት ት/ቤቶች ለወጣቶች ትኩረት ሰጥተው በጥበብ ታንፀው እንዲያድጉ ሰመልካም ስነምግባር እንዲኖራቸው የሚተላለፉ መልዕክቶች ተሰሚነት እንዲኖራቸው በክልል ከተሞች ጭምር ወጣቶችን በቲያትር በሙዚቃ በስነጥበብ ማነፅ ክበባት የሚጠናከሩበት መንገድ ማመቻቸት ይገባዋል ባይ ናቸው።
ጥበቡ የማይነካው የማይዳስሰው የኅብረተሰብ ክፍል የለም የሚሉት አቶ ዮሐንስ፣ በተለይ ጥበቡ ተደራሽነቱ ሠፊ ስለሆነ ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ ይሰጣሉ ባልዋቸው የጥበብ ሥራዎች ለመሥራት ካላቸው ፍላጎት አንፃር እንደሚሳተፋ ይናገራሉ፡፡ ”ጥበቡ ተደራሽነቱ ሰፊና እያዝናና የሚያስተምር ስለሆነ ቢስፋፋ ጥሩ ነው። ወጣቱም ሆነ ኅብረተሰቡ ለሞራል ያለው ግንዛቤ የወረደ ነው፡፡ ወጣቱን በሞራል ለመገንባት አንዱ መንገድ በተለይ በትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚደረጉ የድራማና መሰል ነገሮች እጅግ ጠቀሜታ አላቸው” ይላሉ፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 16/2013 ዓ.ም