ለምለም መንግሥቱ
የጥምቀት በዓል ድባብ ከበዓል አክባሪና ታዳሚ ሥሜት ውስጥ ገና አልወጣም። በሀገር ባህል አልባሣት የተዋቡ ሰዎችን በየመንገዱ እያየን ነው።ለቀናት በጥምቀተ ባህር ያደሩ ታቦታትን ወደ ማደሪያቸው በመሸኘት ላይ ናቸው።ቃና ዘገሊላ የበዓሉ ማሣረጊያ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች ዘንድ ልዩ ቦታ የሚሰጠው ጥር 21 ቀን የአሥተርዮ ማርያም ክብረ በዓል ከፊታችን ይጠብቀናል። በዓሉ በአንዳንድ የእምነቱ ተከታዮች ዘንድ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የበለጠ ይደምቃል። ሴቶች በሥፋት አምረውና ደምቀው የሚታደሙበት በዓልም ነው፡፡
ድምጻዊው ይሁኔ በላይ ‘ዘገሊላ‘ በሚለው የሙዚቃ ሥራው
‘የዘገሊላ ለት የዘገሊላ ለት
ነይልኝ በእኔ ሞት፤
ያስተርዮ ማርያም ያስተርዮ ማርያም
እመጣለሁ እኔም፤
ባልነው ባልነው ባልነው ዓለም ባልነው
ባልነው ባልነው እንገናኝ ምነው – ዓለም ባል ነው።” እያለ በማቀንቀን በዓሉን ያደምቃል። የዘፈኑ መልዕክት በጥምቀት በዓል ላይ በዓይንም በልብም ለተፈላለጉ ተቃራኒ ጾታዎች ልዩ ሥሜት የሚሰጥ በመሆኑ ሙዚቃውን በባህላዊ ጭፈራ ይዝናኑበታል። በዓሉ ከኃይማኖታዊ ሥርዓቱ በተጨማሪ ባህላዊ ይዘት እንዳለው አንዱ ማሣያ ነው። ጥምቀትን ለማክበር ወደ ጎንደርና የተለያዩ አካባቢዎች የሄዱ ታዳሚዎች እስከ ጥር 21 ያስተርዮ ክብረ በዓል ድረስ የሚቆዩም እንዳሉ መረጃዎች ያመለክታሉ። ተራርቆ የቆየ ቤተሰብም በዚህ አጋጣሚ የሚገናኝ በመሆኑ ከሩቅም ከቅርብም ያለው ይሰባሰባል። በተለይ ከሀገር ውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው ለመምጣት መልካም አጋጣሚ በመሆኑ ወቅቱን በጉጉት የሚጠብቁ ጥቂት አይደሉም፡፡
የሆቴሎች፣ አሥጎብኝ ድርጅቶችና በተለያየ አገልግሎት ላይ የተሠማሩ አካላትም ከውጭና ከሀገር ውስጥ በዓሉን ለመታደም ወደ አካባቢያቸው የሚሄዱ እንግዶችን በማስተናገድ ገቢ የሚያገኙበት ወቅትም በመሆኑ የገቢ ጥቅሙ ከፍ የሚልበት ጊዜ ነው። በተለይ በዚህ ወቅት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የውጭ ሀገር ቱሪስቶች የሚመጡበት ጊዜ በመሆኑ የጥምቀት በዓልን ከታደሙ በኋላ ወደተለያዩ የቱሪስት መዳረሻዎች ስለሚሄዱ እንደሀገር ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የጎላ ይሆናል፡፡
የሀገር ገጽታ ግንባታ የሚሰራበትም ወቅት ነው። ቱሪስቶቹ በሚደረግላቸው መስተንግዶና በሚጎበኟቸው የቱሪስት መዳረሻዎች እርካታ ያገኙ ከሆነ ወደመጡበት ሲመለሱ በጎ ተጽዕኖ ይፈጥራሉ።
በአሁኑ የጥምቀት በዓል የዓለም ሥጋት የሆነው ኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ ባስከተለው የጤና ቀውስ የሚጠበቀውን ያህል ቱሪስት ባይሆንም ጥቂቶች በዓሉን ታድመዋል። ጥቂቶቹም በጋራና በተናጠል በኢትዮጵያዊ የሀገር ባህል ልብስ ደምቀው ነበር በዓሉን የታደሙት።ሌላው ሥጋት የነበረው ኢትዮጵያ የገጠማትን የውስጥ ፈተና ለመቅረፍ ሕግ የማስከበር ሂደት ላይ ባለችበት ወቅት መሆኑ በዓሉ ይደበዝዛል የሚል ጥርጣሬም ተፈጥሮ ነበር። እንደተፈራው ሣይሆን በተቃራኒው በድምቀት ተከብሮ መጠናቀቁ በዓሉን በማስተባበርና እንግዶችን በማስተናገድ ኃላፊነታቸውን ሲወጡ የነበሩ ይገልጻሉ። ታዳሚዎችም ደስ ብሏቸው በዓሉን እንዳሳለፉ በተለያየ የመገናኛ ብዙሃን ሲገልጹ ሰምተናል፡፡
የበዓል እንግዶቻቸውን አስተናግደው በመሸኘት ላይ ካሉት አካባቢዎች ጎንደር ከተማ ተጠቃሽ በመሆኑ ወደ አማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃሎ ብያለሁ። በመላ ሀገሪቱ የተከበረው የጥምቀት በዓል ፍጹም ሠላማዊና ደማቅ እንደነበርም የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ገልጿል። የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሙሉቀን አዳነ እንደነገሩኝ በላልይበላ ቀድሞ የተከበረው የእየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል፣ በጥምቀተ ባህር የሚያድሩ ታቦታት በሥፋት በሚገኙበት በጎንደርና በሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ሸኮራ ወረዳ ኢራጉዲ በሚባል አካባቢ የከተራ፣ የጥምቀትና የቃና ዘገሊላ ኃይማኖታዊ በዓል በክልሉ እጅግ ሠላማዊ በሆነ ሥነ ሥርዓት ተከብሯል። በላልይበላ የገና በዓል ወደ አንድ ሚሊየን 314 ሺህ ሰው በጎንደር ደግሞ የከተራና የጥምቀት በዓል የበለጠ ሰፊ
ቁጥር ያለው ሰው ታድሟል። ኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽን በሽታ ሣይበግራቸው የውጭና የሀገር ውስጥ ታዳሚዎች መሣተፋቸው በዓሉ የቀድሞ ታዳሚውን ሣያጣ መከበሩ ብዙዎችን አስደስቷል። የቱሪስቶች ቁጥር እንደቀድሞ ባይሆንም አይገኙም ተብሎ እንደተፈራው ሣይሆን በብዛት ተገኝተዋል። ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ትውልደ ኢትዮጵያዊና ኢትዮጵያውያን ግን በሥፋት ታድመዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት የበዓሉን ታዳሚ በማስተናገድ በተለይም ኮቪድን ለመከላከል የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ) በማሰራጨት ጭምር ጠንካራ የሆነ ተግባር ለማከናወን ችሏል። ብዙዎቹም በራሳቸው በመከላከል ተባብረዋል። በአጋጣሚውም የአካባቢው ወጣትና ከእምነት ተቋማት የተውጣጡ አስተባባሪዎች ያበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጽኦ በዓሉ በሠላም እንዲጠናቀቅ አስችሏል፡፡
ጥምቀት ያለው ሁለንተናዊ ጠቀሜታ ታይቶ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሣይንሥና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ከዓመት በፊት መመዝገቡን ያስታወሱት ዶክተር ሙሉቀን ከምዝገባ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑን ጨምሮ እንደ ክልል መልካም የሆነው ገጽታውን ሣይለቅ በዓሉ በድምቀት መከበሩ ልዩ ሥሜት ፈጥሯል ብለዋል፡፡
እንዲህ ሰፊ ቁጥር በተስተናገደበት ጎንደር ከተማ የሚገኙ የባህል አልባሣት፣ ጌጣጌጦች፣ የተለያዩ ገፀ በረከቶች ለገበያ የሚያቀርቡ እንዲሁም አገልግሎት ሰጭ ሆቴሎች እና አስጎብኝ ድርጅቶች ገቢ የሚያገኙበት ወቅት ነው። በተለይም ገቢያቸውን ቱሪስት ላይ መሠረት ያደረጉት ደረጃ ያላቸው ሆቴል ቤቶችና አስጎብኝ ድርጅቶች እንዴት አሣለፉ የሚለውንም ለማጣራት ሞክሪያለሁ።
የጎንደር ከተማ የሆቴሎች ማህበር ፕሬዚዳንትና የጎሀ ሆቴል ሥራ አስኪያጅ አቶ አማረ አጥናፉ እንደገለጹት ኮቪድ ከመከሰቱ በፊት በነበረው ተሞክሮ በዚህ ወቅት ከተለያዩ ሀገራት ለመምጣት የሚያስቡ ቱሪስቶች ከዓመትና ከስድስት ወራት በፊት ነበር በበይነ መረብ ወይም የኦንላይን አገልግሎት በመጠቀም የሚመዘገቡት፤ (ቡክ) የሚያደርጉትና ክፍያ የሚፈጽሙት። ሆቴል ቤቶችም ቀድመው ስለሚያውቁ ዝግጅት ያደርጋሉ። የ2012 ዓ.ም በዓል እየተከበረ ለ2013 ዓ.ም ምዝገባ ይካሄድ ነበር። እርሳቸው የሚያስተዳድሩት ጎሀ ሆቴል ካለው ክፍል 80 ያህሉ በውጭ ሀገር ዜጎች ወይንም ቱሪስቶች ነበር የሚያዘው። በአሁኑ በዓል ግን ይህ ሁኔታ ባለመኖሩ እርግጠኛ ሆኖ እንግዶችን ለመቀበል አስቸጋሪ ነበር። የሚያስተዳድሩት ሆቴል በዓሉ አምሥት ቀን እስኪቀረው ድረስ በጣም ጥቂት ክፍሎች ነበር የተያዙት። የሆቴል አገልግሎቶቹ በወረርሽኙ ተዳክመው ስለቆዩ ተሥፋ እንዳይኖራቸው አድርጎ ነበር። በበዓሉ ዋዜማ ግን የውጭ ሀገር ዜጎች በብዛት ባይኖሩም ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያን እንዲሁም ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በመጡ እንግዶች ሆቴል ቤቶቹ ተጠቃሚ ሆነዋል። ክፍሎቻቸው በሙሉ ተይዘው ነበር። ከመኝታ አገልግሎት በተጨማሪ ባህላዊና ዘመናዊ የምሽት ሙዚቃና የተለያዩ ዝግጅቶችን በማድረግ ደንበኞች በዓሉን በመዝናናት አሣልፈዋል፡፡
ምንም እንኳን የውጭ ሀገር ዜጎች በብዛት ባይገኙም የሆቴል አገልግሎት ሰጭው ሥራ በመከናወኑና መነቃቃት በመፈጠሩ ደስተኛ ሆኗል። በከተማዋ ሪዞርቶችን ጨምሮ 12 የሚሆኑ ኮከብ ያላቸው ሆቴል ቤቶች ይገኛሉ። ከዚህ ቀደም በነበረው ተሞክሮ በጥር ወር ብቻ በኮከብ ደረጃ የሚገኙ ሆቴል ቤቶች ከአራት እስከ አምስት ሚሊዮን ብር ገቢ ያገኛሉ።
የሆቴል አገልግሎቱ በኮቪድ ምክንያት በጣም ተጎድቶ እንደነበርና ችግሩን ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ በመንግሥት በአነስተኛ የወለድ መጠን ብድር ቢመቻችም ዘርፉን ከነበረበት ጉዳት መመለስ እንዳልተቻለ አቶ አማረ ይናገራሉ። የሆቴል ሠራተኛው ከሚሰጠው አገልግሎት በሚገኘው ገቢ ይጠቀም የነበረው መቅረቱና በደመወዝ ብቻ መተዳደሩ ተጎጂ እንዳደረገውም ገልፀዋል፡፡
እንደርሳቸው ማብራሪያ እንደሌሎች ከተሞች ቱሪዝም ኮንፈረንስ በከተማዋ ቢለመድ የገቢ ማካካሻ መሆን ይችል ነበር።በዚህ በኩል ያለውን ክፍተት የከተማ አስተዳደሩ እንዲፈታ በመጠየቅ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ። አሁንም ኮቪድ በመቀጠሉ እንደማህበር በዘላቂነት የታሰበውን አቶ አማረ ላቀረብኩላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ስብሰባዎች ወደ ከተማዋ እንዲመጡ ግፊት ከማድረግ ጎን ለጎን የሆቴል ኢንዱስትሪውም የራሱን ፈጠራ በመጠቀም በአካባቢው ላይ ገቢ ማመንጨት የሚችልበት አሠራር በማመቻቸት ጥረት እንዲያደርግ ማህበሩ የሚችለውን ሁሉ ጥረት ያደርጋል። ዘርፉ ከፍተኛ የመንግሥት እገዛ እንደሚያስፈልገው ግን ጠቁመዋል።
ሆቴል ቤቶቹ ለማረፊያነት ብቻ ሣይሆን በሥነ ሕንፃ ጥበባቸውም ቱሪስቱን የሚስቡ መሆናቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል የሚል እሳቤ አለ። ከዚህ አንጻር በጎንደር የሚገኙ የሆቴል ባለቤቶች ምን ያህል ትኩረት ሰጥተዋል ለሚለው ጥያቄም አቶ አማረ በሰጡት ምላሽ እርሣቸው የሚያስተዳድሩት ከ40 ዓመት በፊት የተገነባውና በመንግሥት ይዞታ ሥር ይተዳደር የነበረው ጎሀ ሆቴል ያሉት የቀደሙት ባህላዊና አካባቢያዊ ገጽታን የሚያንፀባርቅ ጥበብ ያረፈበት ነው።በጎንደር ጎሀ፣ በአክሱም፣ በላልይበላ ሮሃ፣ በባህርዳር ጣና በሚል ሥያሜ የሚታወቁ ሲሆን፤ በወቅቱም ሆቴል ቤቶቹ የቱሪስት መዳረሻ ቦታ ተብሎ በተመረጡ አካባቢዎች ነው የተገነቡት። በአሜሪካ ኒውዮርክ ከተማ በሚገኝ የሥነ ሕንጻ ባለሙያዎች ዲዛይን ተደርጎ በበርታ ኮንስትራክሽን ተቋራጭነት ነው የተገነቡት። ሆቴል ቤቶቹ ሥነ ሕንፃ ጥበባቸው ብቻ ሣይሆን የውስጥና የውጭ ቁሳቁሳቸውም ጭምር የቱሪስት መስህብ ናቸው። ሆቴሎቹ በአሁኑ ጊዜ በግል ይዞታ ሥር ሆነው ይዞታቸውን እንደጠበቁ ይገኛሉ። አዳዲስ የሚገነቡት ግን አብዛኞቹ ዘመናዊ መሆናቸውን ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡
የጎንደር አካባቢ የግል አስጎብኚዎች ማህበር ሊቀመንበር አቶ ማሥረሻ ፋንታሁን ማህበራቸው 74 አባላት ያሉት ቢሆንም በአሁኑ የጥምቀት በዓል በማስጎብኘት ሥራ ላይ የተሠማሩት ከግማሽ በታች የሚሆኑት የማህበሩ አባላት ናቸው። ቀደም ሲል በነበረው ተሞክሮ ከማህበሩ አባላት ተርፎ ከአዲስ አበባ ከተማ ቱሪስት ይዘው ወደሥፍራው ለሚሄዱ አስጎብኚዎችና በከተማው ረዳት ተብለው የሚጠሩ አስጎብኚዎች ጭምር ሥራው ይተርፍ ነበር።በአሁኑ ጥምቀት የውጭ ሀገር ቱሪስት ቁጥር በእጅጉ ማነሱ ይገኝ የነበረው ገቢም ሆነ ሥራ ቀንሷል። የማህበሩ አባላትም ቱሪስቶችን መሠረት አድርገው ነው ማህበር እስከማቋቋም የደረሱትና የግል ኑሯቸውንም የመሠረቱት። የቱሪስት ፍሰቱ በነበረበት ወቅት እያንዳንዱ አስጎብኚም በወር እስከ ስምንት ሺህ ብር የሚያገኝበት ዕድል ነበረው፡፡
ከከተራው ጀምሮ በጎንደር የተገኘው ቱሪስት ጎንደርን፣ ሰሜን ተራሮች ፓርክን ላልይበላንና አክሱምን ጎብኝቶ ስለሚመለስ ለአስጎብኚው መልካም አጋጣሚ ነው።በጎንደር ከተማ በውስጡ ስድስት ትላልቅ ቤተ መንግሥት የያዘውን አጼ ፋሲለ ደስ ቤተመንግሥት፣ በከተማው በሌላኛው አቅጣጫ የሚገኘውንና ከከተማው ሁለት ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የአጼ ፋሲለ ደስ የመዋኛ ሥፍራ የነበረውና የጥምቀት በዓል በየዓመቱ የሚከበርበትን፣ የደብረብርሃን ሥላሴ፣ ቁስቋም ቤተክርስቲያን አስጎብኚዎች ከሚያስጎበኟቸው መካከል ይጠቀሣሉ፡፡
አስጎብኚው ኮቪድ ተወግዶ ወደቀድሞ ሥራው እስኪመለስ ያለበትን ችግር በማህበሩ አማካይነት ለከተማ አስተዳደሩ በመሣወቅ በሌሎች የገቢ ማስገኛ ዘርፎች ተሠማርቶ ኑሮውን ለመምራት እንዲያስችለው ጥረት በማድረግ ላይ እንደሆነ የማህበሩ ሊቀመንበር ተናግረዋል።
‹‹እንደ ሀገር ኮቪድን ለመከላከል የተላለፈው መልዕክት በሚገባ ተተግብሯል። በእምነት ተቋማትና በተለያየ መንገድ ተደራጅተው ሲያስተባብሩ የነበሩትም በሚገባ ተልዕኳቸውን መወጣታቸውና የፀጥታና የተለያዩ አካላት የጋራ ቅንጅት የበዓል አከባበር ሥርዓቱን ውጤታማ አድርጎታል›› በማለት የገለጹት በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ከሣሁን አያሌው ከቱሪስት ቁጥር አንጻር አጠቃላይ ቁጥሩን ገና መረጃ የማጠናከር ሥራ በመከናወን ላይ በመሆኑ ትክክለኛውን መረጃ መግለጽ ባይቻልም ከኮቪድ ጋር ተያይዞ ከነበረው ሥጋት አንጻር የተሻለ እንደነበር ተናግረዋል።እንደ እርሳቸው ማብራሪያ በቀጣይ ከቱሪዝም ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ ለማካካስና ሥራውም እንዳይቀዛቀዝ በሚኒስቴሩ የሀገር ውስጥ ማበልፀጊያ ዳይሬክቶሬት ተቋቁሞ ሥራ ተጀምሯል። ኃይማኖታዊ ጉዞ የሚያደርጉ ምዕመናን እግረ መንገዳቸውን የቱሪስት መዳረሻዎችን የሚጎበኙበትን መንገድ በማመቻቸት ክፍተቶችን ለመሙላት ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 16/2013 ዓ.ም