ማህሌት አብዱ
ኢትዮጵያ የመንገድ፣ የባቡር፣ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ የአየር ትራንስፖርት፣ የሀይል ማመንጫና አገልግሎት እንዲሁም የቴሌኮም መሠረተ ልማቶችን በማከናወን ላይ ትገኛለች።ይሁንና እነዚህ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች በቅንጅት የማይካሄዱ በመሆናቸው ለጥራት መጓደል፣ ለአገልግሎት መጓተትና ለሕዝብና መንግሥት ሀብት ብክነት ምክንያት ሆኖ ቆይቷል።በተመሣሣይ በመሠረተ ልማት ግንባታዎች ምክንያት ለሚደርስ የይዞታ መፈናቀልና የንብረት ጉዳት ተገቢ ካሣ የሚከፈልበት ወጥ የአገማመት ቀመር ያለመኖሩ በመሠረተ ልማቶች አፈጻፀም ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እየፈጠረ ይገኛል።ይህም በአገራዊ የመሠረተ ልማት አቅርቦትና አገልግሎት አሠጣጥ ረገድ የመልካም አስተዳደር ምንጭ ሆኖ ይገኛል።
በመሆኑም በፌዴራል መንግሥት የሚገነቡ ትላልቅ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን የሚያስፈፅሙ ተቋማት የሚቀናጁበት ሥርዓት በመዘርጋት፤ በማስተባበርና በመቆጣጠር ችግሮችን ለማስወገድ በሚል የተቀናጀ መሠረተ ልማቶች ማስተባበሪያ ኤጀንሲ በአዋጅ አቋቁማል።ኤጀንሲው በ2006 ዓ.ም ቢመሠረትም በተጨባጭ ወደ ሥራ የገባው በ2009 ዓ.ም ነው።ከዚያ ወዲህም ቢሆን ኤጀንሲው ከተቋቋመበት ዓላማ አንፃር የሚፈለገውን ውጤት በተጨባጭ ማምጣት አልቻለም።ለዚህና ኤጀንሲው እያከናወናቸው በሚገኙ ሥራዎች ዙሪያ የፌዴራል የተቀናጀ መሠረተ ልማት ማስተባበሪያ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሠዓዳ ከድርን አነጋግረናቸዋል እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአገሪቱ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ቅንጅት ያለመኖሩ እያስከተለ ያለውን ችግር ያስረዱንና ውይይታችንን ብንጀምር?
ወይዘሮ ሠዓዳ፡- መሠረተ ልማት የአንድ ሀገር የዕድገት መለኪያ መሆኑ እሙን ነው።መንግሥት ለመሠረተ ልማት መሥፋፋት ልዩ ትኩረት እና ከፍተኛ በጀት፣ ተቋማትን ማደራጀትና ማጠናከር፣ ድጋፍና ክትትል በማድረግ፣ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ባለመቀናጀታቸው ምክንያት ከፍተኛ የሐብትና የጊዜ ብክነት እያስከተለ ይገኛል። እንዲሁም የመሠረተ ልማት ቅንጅት ማስተር ፕላንና ስታንዳርድ አለመኖር፣ የመሠረተ ልማት መረጃዎች በበቂ ሁኔታ አለመደራጀት፣ ተቋማዊ ባህሉ በሚናበብና በተቀናጀ ሁኔታ ለመሥራት የማያስችል፣ የአሠራር ሥርዓትና ተጠያቂነት በበቂ ሁኔታ ያልተሟላ መሆን አገሪቱን ለከፍተኛ ኪሣራ እየዳረጋት ይገኛል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞም ዜጎች ከዘርፉ ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም አለማግኘት፣ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች መጓተት፣ የአገልግሎት መቆራረጥ እና ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ችግር፣ ከፍተኛ የሐብት ብክነት ማስከተል ይታያል።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ አኳያ የኤጀንሲው መቋቋም እነዚህን ችግሮችን ምን ያህል ይፈታል ተብሎ ይታመናል?
ወይዘሮ ሠዓዳ፡- እንደሚታወቀው የፌዴራል የተቀናጀ መሠረተ ልማቶች ማስተባበሪያ ኤጀንሲ በ2006 ዓ.ም በአዋጅ ቁጥር 857/2006 ነው የተቋቋመው። ይሁንና በተለያዩ ምክንያቶች የሰው ኃይል ሣይመደብለት፣ በጀትና አስፈላጊ ግብዓቶች ሣይሟሉለት ቆይቶ ከህዳር 2009 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሥራ ገብቷል። ወደ ሥራ በገባበት ወቅትም ከግዥ ሥርዓቱና ከሰው ኃይል ቅጥሩ ጋር ተያይዞ ችግር የነበረበት በመሆኑ ፈጥኖ ወደ ዋናው ሥራ አልገባም፡፡
በዚህ መሠረተ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የቅንጅት ማስተር ፕላንና ለካሣ ተከፋዮች የንብረት ካሣ ቀመር ማዘጋጀት ዋና ተልዕኮው አድርጎ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። በተጨማሪም የመሠረተ ልማት መረጃዎችን ማደራጀት፣ መተንተን፣ ማሠራጨት፣ የተለያዩ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን ማከናወን፣ የቅንጅት ስታንዳርዶችን ማዘጋጀት፣ ለሚመለከታቸው አካላት የቅንጅት ፈቃድ መስጠት፣ የድጋፍና ክትትል ሥራዎችን ማከናወን ከተሰጡት ተግባራት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
በዚህ አግባብም ባለፉት ዓመታት በመንገዶች ማስተር ፕላን ላይ የተመሠረቱ የተቀናጁ የመሠረተ ልማት ሥራዎች እንዲካሄዱ ማስተባበር፣ ማቀናጀትና መቆጣጠር፣ በመሠረተ ልማት ሥራዎች ምክንያት ለሚነሱ ንብረቶችና ለሚለቀቁ ይዞታዎች የካሣ ግምት ቀመር ማዘጋጀት፣ የመሠረተ-ልማት ሥራዎች ሲካሄዱ አንዱ በሌላው ላይ በሚያደርሰው ጉዳት ምክንያት የሚያስከትለው የአገልግሎቶች መቋረጥና የአካባቢ ብክለት በተቋማት እና በመንግሥት ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ ውስብስብ ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ችግሮችን የመከላከል ሥራዎችን ዋነኛ ዓላማው አድርጎ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኤጀንሲው በዋናነት የትኞቹን ተቋማት ነው እያስተባበረ ያለው? የግንኙነት አግባቡስ ምን ይመሥላል?
ወይዘሮ ሠዓዳ፡- ኤጀንሲው እንዲያስተባብራቸው በማቋቋሚያ አዋጁ የተጠቀሱት ተቋማት፤ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ ኢትዮቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን፣ የኤርፖርቶች ድርጅት፣ የኢንደስትሪ ፓርኮች ሲሆኑ፤ በየክልሉ የሚገኙ የውኃ ተቋማትንም ያስተባብራል። ከተቋማቱ ጋር ያለው የግንኙነት አግባብ በተመለከተ ለኤጀንሲው ከተሰጡት ተልዕኮዎች የመነጨ ሲሆን፤ ዋና ዋናዎቹ ተቋማት ዓመታዊ የቅንጅት ዕቅዳቸውን በጋራ እንዲያቅዱ እና አፈጻፃሙን በየሩብ ዓመቱ በጋራ እንዲገመግሙ የማስተባበርና ግብረ መልስ የመስጠት፣ የመሠረተ ልማት የቅንጅት ሥራዎች ጋር በተያያዘ ለሚቀርብ የፈቃድ ጥያቄ መልስ የመስጠት ሥራዎችን ያከናውናል።
በተጨማሪም ኤጀንሲው በሚያዘጋጃቸው የአሠራር ሥርዓት ሠነዶች ለምሣሌ በማስተር ፕላንና በስታንዳርዶች ዝግጅት እንዲሁም በፍሬም ወርኮች፣ ሥልጠናዎች እና በመመሪያዎች ዝግጅት ወቅት የተቋማቱን ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሣተፉ ያደርጋል። ከዚህም ባሻገር መሠረታዊ የሆኑ የመሠረተ ልማት መረጃዎች ከተቋማቱ ጋር የሚለዋወጥ ሲሆን፤ በጋራ የቅንጅት ዕቅዱ መሠረተ ፕሮጀክቶችን በጋራ ድጋፍ፣ ክትትልና ግምገማ ያደርጋል።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ አኳያ ምን ዓይነት ተጨባጭ ውጤቶች ተገኝተዋል ማለት ይቻላል?
ወይዘሮ ሠዓዳ፡- ኤጀንሲው ምንም እንኳን ከተሰጠው ተልዕኮ አንፃር በርካታ ሥራዎችን ማከናወን ቢጠበቅበትም አስቀድሜ በነገርኩሽ ምክንያቶች ቶሎ ወደ ሥራ አልገባም ነበር።ሆኖም ባለው አቅም ሁሉ ተንቀሳቅሶ ያስገኛቸው ውጤቶች የሚናቁ አይደሉም። ከእነዚህም መካከል የተለያዩ የአሠራር ሠነዶች፣ የቅንጅት ችግሩን በተወሰነ ደረጃ ሊቀርፉ የሚችሉ የአሠራር ማዕቀፍ ሠነዶች፤ ሀገራዊ የመሠረተ ልማት ኮሪደር ስታንዳርድ ማዘጋጀት መቻሉ ተጠቃሽ ነው።በተጨማሪም የመንገድ ቆረጣና ጥገና ስታንዳርድ፤ ሀገራዊ የመሠረተ ልማቶች የዕቅድ ዝግጅትና ትግበራ ፍሬም ወርክ፣ ለሀገራዊ የቅንጅት የማስተር ፕላን ዝግጅት ፕሮጀክት ፕሮፖዛል ዝግጅት ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡
በሌላ በኩልም የጥናትና ምርምር ሥራዎች፣ በመሠረተ ልማት ግንባታዎች ወቅት ከይዞታቸው ለሚነሱ ባለይዞታዎች በሚከፈል የካሣ ክፍያ ላይ ያሉ የነጠላ ዋጋ ልዩነቶችን ለማጥበብ የሚያስችል፣ በፕሮጀክቶች መጓተት ምክንያት የሚከሰተውን የመንግሥት ሀብት ብክነት የሚያሣይ እንዲሁም በካሣ አከፋፈል ሂደትየሚፈጠሩ ቅሬታዎችንና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የሚያመላክቱና የመፍትሄ አቅጣጫ የሚጠቁሙ ጥናቶች እየተካሄዱ ይገኛሉ፡፡
የሕግ ማዕቀፎችን በማዘጋጀት ረገድም የኤጀንሲውን የመፈፀም አቅም ሊያሣድጉ የሚችሉ አንዳንድ የሕግ ማዕቀፎችን የማዘጋጀት ሥራ ተከናውኗል።በተጨማሪም የአቅም ግንባታ ሥራዎች በክልሎችና ከዚያ በታች ለሚገኙ አመራሮች እንዲሁም ለተመረጡ ለንብረት ካሣ ገማች ኮሚቴዎች የአቅም ግንባታ ሥልጠና እየተሰጠ ይገኛል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኤጀንሲው ከተሰጡት ተልዕኮች መካከል ሀገሪቱ እያከናወነቻቸው ባለቻቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች ሥኬት የመሠረተ ልማት ዝርጋታን ማሣላጥ አንዱ እንደመሆኑ በዚህ ረገድ ምን ምን ሥራዎች ተከናውነዋል?
ወይዘሮ ሠዓዳ፡- እንዳልሽው ኤጀንሲያችን ከተሠጠው ተልዕኮ አንዱ በግዙፍ ላይ ፕሮጀክቶች ክትትልና ድጋፍ ሥራዎችን ማከናወን ተጠቃሽ ነው። በዚህም መሠረት በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች በ2012 ዓ.ም 69 ፕሮጀክቶች በ2013 ዓ.ም ባለፉት አምስት ወራት በሰሜን ሪጅን 9፣ በደቡብ ሪጅን 7፣ በምዕራብ ሪጅን 6፣ በምሥራቅ ሪጅን 7፣ በማዕከላዊ ሪጅን 8 እና በፍጥነት መንገድ አንድ በድምሩ 38 ፕሮጀክቶች ክትትል ተደርጎባቸው ችግሮቻቸው ተለይቶ ለሚመለከታቸው አካላት ግብረ-መልስ እየተሰጠ ነው።
ከዚህም ጋር ተያይዞ የመረጃ ማሰባሰብና የማደራጀት ሥራ እየተሠራ ይገኛል።ለአብነት ያህልም ለሀገራዊ የቅንጅት ማስተር ፕላኑ ዝግጅት የሚሆኑ መረጃዎች ከክልሎችና ከሚመለከታቸው የፌዴራል ተቋማት እየተሰበሰቡና እየተደራጁ የሚገኙ የሚጠቀሱ ሲሆን፤ እንደ አስፈላጊነቱ አጠቃቀም ላይ ይውላል።
አዲስ ዘመን፡- ኤጀንሲው እነዚህን ሥራዎች በሚያከናውንበት ጊዜ ያጋጠሙት ተግዳሮቶች ካሉ ቢጠቅሱልን?
ወይዘሮ ሠዓዳ፡- ተቋማት ለቅንጅት ሥራው ትኩረት አለመስጠትና ችግሮች ሲፈጠሩ በጋራ ለመፍታት ያላቸው ተነሣሽነት ዝቅተኛ መሆን፣ በቁጥራቸው እጅግ ብዙ ቦታ የመቀየር ሥራ /የሪሎኬሽን/ ጥያቄዎች ለመብራት አገልግሎትና ለኢትዮ ቴሌኮም በመቅረባቸው ምክንያት ለካሣ ክፍያ ብዙ ሀብት መባከን እና የተገልጋዮች የአገልግሎት መቆራረጥ ካጋጠሙ ችግሮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።በተጨማሪም በመሠረተ ልማት ሥራዎች ምክንያት ለሚነሱ ንብረቶች በአንድ አካባቢ ለተመሣሣይ ንብረት የተለያየ የካሣ ክፍያ መፈፀም፣ ለመንገድ ሥራ ዲዛይን በወጣላቸው ሣይቶች ሕገ ወጥ ግንባታዎች እንዲሁም ቋሚ ተክሎችን በመትከል ተገቢ ያልሆነ የካሣ ክፍያ በመጠየቅ በሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት ላይ ከፍተኛ ጫና አሣድራል፡፡
ከዚህም ባሻገር አንዱ ተቋም መሠረተ ልማት ሲገነባ በሌሎች ቀድመው በተገነቡ መሠረተ ልማቶች ላይ ጉዳት ማስከተል፣ የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት ለንብረቶቻቸው የካሣ ግምት ከተከፈለ በኋላ በወቅቱ ንብረቶቻቸውን ያለማንሣት በየአካባቢው ከሚታዩ ችግሮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
በሌላ በኩልም በተቋሙ የአደረጃጀት ችግር ምክንያት የተቋሙን ሥራ የሚመጥን ባለሙያ ማግኘት ያለመቻሉም በቀላሉ የሚታይ ተግዳሮት አይደለም። በአጠቃላይ የመሠረተ ልማት ቅንጅት ሥራው በሚጠበቀው ልክ ውጤታማ ያለመሆን የሀገሪቱን ዕድገት ወደኋላ አስቀርቶታል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የእነዚህ ችግሮች ድምር ውጤት ምን ያስከትላል ተብሎ ይታመናል?
ወይዘሮ ሠዓዳ፡- የችግሮቹ ድምር ውጤት አስቀድሜ እንደገለፅኩልሽ በአጠቃላይ የሀገሪቱን የምጣኔ ሀብት ዕድገት ወደፊት እንዳይራመድ ሣንካ ሆኖ ቆይቷል። እንደ አጠቃላይ ግን የፕሮጀክቶች ከተጠበቀው በላይ መዘግየት በበርካታ አካቢዎች ላይ የተከሰተ ሲሆን፤ ለአብነት እንኳን ብጠቅስልሽ አልበረክቲ – ገለምሶ፣ ገለምሶ – መቻራ፣ መልካሳ – ሶደሬ መተማ – አብርሃ ጅራ ይገኙበታል። ድሬዳዋ – መልካ ጀብዱ – ኢንደስትሪ ፓርክ ደግሞ የቆመ ፕሮጀክት ነው። ተጨማሪ የሀብት ብክነት፣ የመሠረተ ልማቶች ሀገራዊ የቅንጅት ማስተር ፕላን ያለመኖር፣ ሀገራዊ የቅንጅት ስታንዳርድ ያለመኖር ሁኔታዎች በሥፋት ተከስተዋል።ይህም የቅሬታ ምንጭ ወይም የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ ነው የቆየው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በእርስዎ እምነት የችግሮቹ መንሥዔዎች ምንድን ናቸው?
ወይዘሮ ሠዓዳ፡- የመሠረተ ልማት ፈፃሚ ተቋማት የተሟላና የተደራጀ መረጃ ያለመኖር፣ መረጃዎች ቢኖሩም ያለመናበብ፣ በየክልሎች የሚሠራው የአቅም ግንባታና የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ አጥጋቢ ያለመሆን፣ ኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የመሠረተ ልማት አገልግሎት ተቋማትን በዲዛይን ደረጃ እንዲሣተፉና አስተያየት እንዲሰጡ ያለማድረግ፣ ከካሣ ክፍያ ጋር ተያይዞ የወጥነት መጉደልና መዘግየት እንደ መንሥዔ ሊነሱ የሚችሉ ጉዳዮች ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በኤጀንሲው ችግሮቹን ለመፍታት የተደረጉ ጥረቶች ምንድን ናቸው? የተገኙ ውጤቶችስ?
ወይዘሮ ሠዓዳ፡- ኤጀንሲው የአደረጃጀት ችግር ያለበት መሆን ሀገራዊ የቅንጅት ማስተር ፕላን በሚቀጥሉት ዓመታት ለማዘጋጀት የሚረዱ የፕሮጀክት ፕሮፖዛል፣ መረጃዎችን የማሰባሰብና የማደራጀት ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛል። የቅንጅት ችግሩን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ሊፈቱ የሚችሉ ሁለት ሀገራዊ ስታንዳርዶች ተዘጋጅተው መጽደቅ ብቻ ይቀራቸዋል።ተመሣሣይ የካሣ ክፍያ ሥርዓት እንዲኖር የካሣ ቀመር ተዘጋጅቶ ተግባራዊ እየሆነ ይገኛል።
በተጨማሪም በመላው ሀገሪቱ የግንዛቤ ፈጠራውና የአቅም ግንባታ ሥራው ክፍተቶች እየተለዩ ለሚመለከታቸው የክልል፣ የዞን፣ የወረዳ እና የከተማ አስተዳደር አመራሮችና ለንብረት ገማች ኮሚቴ አባላት እየተሰጠ ነው።የሁሉም ተቋማት ባለሙያዎች የተሣተፉበት ዓመታዊ የጋራ የቅንጅት ዕቅድ በማዘጋጀት እየተተገበረ ይገኛል፤ ግብረ -መልስም ይሰጣል፤ ፕሮጀክቶች ሲገነቡ በወሠን ማስከበር፣ በዲዛይን፣ በካሣ ክፍያና በሌሎች ምክንያቶች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ለመፍታት እየተሞከረ ይገኛል።ኤጀንሲው ባለው አደረጃጀትና ሠራተኞች ሥራዎችን ለመከወን መሞከር እንደመፍትሄ ተወስዷል፡፡
የተገኙ ውጤቶችን በሚመለከትም አንዳንድ ከፍተኛ ችግር የነበረባቸውና ለመቆም ጫፍ ላይ ደርሰው የነበሩ ፕሮጀክቶች ሥራቸው እንዲቀጥል ተደርጓል።ለአብነትም አዳማ ውኃ ፕሮጀክት ከፍጥነት መንገድ ጋር የነበረ ችግር፣ ቡራዩ ሣንሱሲ ፕሮጀክት እንዲሁም ጎንደር – አዘዞ ፕሮጀክት የሚጠቀስ ነው፡፡
በየክልሎችና ከዚያ በታች ባሉ የአስተዳደር እርከኖች ያሉ አመራሮችና በመሠረተ ልማት ግንባታዎችና በካሣ አከፋፈል ዙሪያ ያላቸው ግንዛቤ በመሻሻል ላይ ይገኛል።የንብረቶች የካሣ ክፍያ በሁሉም አካባቢዎች በተመሣሣይ ቀመር በመሠራቱ ተያያዥ ቅሬታዎች እየቀነሱ መጥተዋል፡፡
በወሠን ማስከበርና በካሣ ክፍያ ምክንያት ችግር ውስጥ የነበሩ ፕሮጀክቶች በተወሰነ ደረጃ ችግሮቻቸውን ለመፍታት እየተደረገ ባለው ጥረጥ ውጤት እየተገኘ ነው። እንደ አጠቃላይ ግን ኤጀንሲው በተሰጠው ሥልጣን ልክ በቅንጅት ችግር ምክንያት የሚከሰቱ መጠነ ሰፊ ችግሮችን ለመቅረፍ እየሰራ ቢሆንም ችግሩን መቅረፍ አልተቻለም።ስለሆነም በቅንጅት ጉድለት የሚከሰት ብክነትን ማስቀረት ወይም መቀነስ በእጅጉ አስፈላጊ በመሆኑ የሁሉንም አካላት ትኩረትና ተሣትፎ ለማሳሰብ እወዳለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- በዚህ ረገድ የሚዲያ አካላት ሚና ምን ሊሆን ይገባል ይላሉ?
ወይዘሮ ሠዓዳ፡- እንደ እኔ እምነት ከምንም በፊት የተቀናጀ መሠረተ ልማት ሥራዎች ዓላማና ተግባራትን በአግባቡ መረዳት ይገባቸዋል ባይ ነኝ።በተመሣሣይ በተቀናጀ መሠረተ ልማት እጦት ምክንያት በሀገር ደረጃ እየተፈጠሩ ያሉ ጉዳቶችን መገንዘብ ይገባቸዋል። እያስከተለ ያለውን አላስፈላጊ የሀብትና የጊዜ ብክነት፣ በሕዝቡ ውስጥ እየፈጠረ ያለውን ቅሬታና የመልካም አስተዳደር ችግርም መገንዘብም ይጠበቅባቸዋል። በአጠቃላይ ችግሩ ሀገራዊና ከበርካታ ተቋማት ጋር የሚያያዝ መሆኑን፣ ቀጥሎ ይህን የመሠረተ ልማት ቅንጀት ችግር ለመቅረፍ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የሚዲያ አካላት ሚና ወሣኝና አስፈላጊ መሆኑን ተረድተው የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል፡፡
በዚሁ መሠረተ ሚዲያው ለመሠረተ ልማት ቅንጅት ዘርፍ ልዩ ትኩረት መስጠት ይገባቸዋል።በተለይም የመሠረተ ልማት ተቋማት የተቀናጀ የጋራ ዕቅድ አፈጻፀምን፤ ሀገራዊ የተቀናጀ የመሠረተ ልማት ማስተር ፕላን ዝግጅት ሂደት፣ የመሠረተ ልማት ቅንጅት ስታንዳርዶች ዝግጅት ሂደት እና የካሣ ቀመር አተገባበርና የነጠላ ዋጋ ዝግጅቶችን አስመልክቶ ከኤጀንሲው ጋር በመተባበር ቋሚ ወርሀዊ ፕሮግራም በመቅረጽና የአየር ሰዓት በመመደብ መረጃዎችን ማሠራጨት የሚቻልበት ሁኔታ መፍጠር ይገባቸዋል። ለምሣሌ በዜና፣ በቃለ መጠይቅ፣ በዶክመንተሪና በፊልም በሥፋት በመዘገብ ሀላፊነታቸውን መወጣት ይገባል። በተለይም በመሠረተ ልማት ቅንጅት ትግበራና በካሣ ክፍያ ዙሪያ ህብረተሰቡ ኃላፊነቱን በአግባቡ ለመወጣት የሚያስችል ግንዛቤ እንዲኖረው ሚዲያው ተከታታይ ዘገባዎችን መሥራት ይኖርበታል።
ከዚህም ባሻገር ከኤጀንሲው ለሚቀርቡ የአየር ሰዓት ወይም የዜና ሽፋን ጥያቄዎች አዎንታዊ ምላሽ መስጠቱን አጠናክሮ ማስቀጠል፣ በመሠረተ ልማት ቅንጅት ሥራ ውስጥ የመሠረተ ልማት አስፈጻሚ ተቋማት ሀላፊነታቸውን እየተወጡ ስለመሆኑ እና ስላለመሆኑ እየተከታተሉ መዘገብና ማጋለጥ ላይም ትኩረት ሊያደርጉ ይገባል።
እንዲሁም የመስክ ጉብኝት በማድረግ ፕሮጀክቶች የሚተገበሩባቸውን የአካባቢው አመራር፣ ህብረተሰቡን፣ ኮንትራክተሮችን፣ አማካሪዎችንና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላትን ያካተቱ ፕሮግራሞችን በመሥራትና በማሠራጨት የቅንጅት ሥራውን ሕዝቡና የሚመለከታቸው አካላት እንዲያውቁት ማድረግም ለቁጥጥሩ መጠናከር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል የሚል እምነት ነው ያለኝ።
አዲስ ዘመን፡- እንደአጠቃላይ መነሣት ይገባዋል የሚሉት ሐሳብ ካለዎት ዕድሉን ልስጥዎት?
ወይዘሮ ሠዓዳ፡- መንግሥት ለመሠረተ ልማት ግንባታ ልዩ ትኩረት ሰጥቷል፤ ውጤትም ተመዝግቧል።ነገር ግን ግንባታው ተቀናጅቶ የማይታቀድና የማይተገበር በመሆኑ አንዱ ተቋም ሲገነባ ሌላው ተቋም ያፈርሣል።አላስፈላጊ የሐብትና የጊዜ ብክነትን እያስከተለ ይገኛል። የቅሬታና የመልካም አስተዳደር ችግር መንሥዔ እየሆነ ይገኛል።በአጠቃላይ ሕዝቡ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባውን ጥቅም እንዳያገኝ አድርጎታል።በመሆኑም ኤጀንሲው ተጠቃሚውን ሕዝብና የሚመለከታቸው የባለ ድርሻ አካላትን በማሣተፍ ችግሩን ለመቅረፍ እየሠራ ይገኛል፡፡
በዚሁ መሠረተ የሕዝቡና የአስፈጻሚ ተቋማትን ግንዛቤ በማሣደግ ተሣትፏቸውንና ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ የሚዲያ አካላትና የመሠረተ ልማት ተቋማት የሥዝብ ግንኙነት አካላት ሚና ከፍተኛ ነው።የመሠረተ ልማት ተቋማት የሕዝብ ግንኙነት አካላት ተቋሞቻቸው ለቅንጅት ሥራው ትኩረት እንዲሰጡ ማድረግ መቻል አለባቸው።የሚዲያ አካላት የሕዝቡን ግንዛቤ ማሣደግ፣ የቅንጅት ሂደቱን ተከታትሎ መዘገብና የመሠረተ ልማት ተቋማት ኃላፊነታቸውን ሣይወጡ ሲቀሩ ማጋለጥና ማስተካከል ይገባል። በአጠቃላይ ሚዲያው የመሠረተ ልማት ቅንጅት ሥራ ትልቅ ሀገራዊ ጉዳይ መሆኑን አውቀው ልዩ ትኩረት መስጠትና የበኩሉን ሚና እንዲጫወት ነው ጥሪዬን ማስተላለፍ የምፈልገው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ሥም ከልብ አመሠግናለሁ፡፡
ወይዘሮ ሰዓዳ፡- እኔም አመሠግናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 16/2013 ዓ.ም