እየሩስ አበራ
የጁንታውን ፍጻሜ አይተን ለማመን የተቸገርን ስንቶቻችን እንሆን? እነስብሀት ነጋ እጃቸው በካቴና የፊጥኝ ታሰሮ በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ሲሉ የደነገጥነው አደነጋገጥማ የተለየ ነበር። እነዚያ የሰማይ ስባሪ ያህል ገዝፈው ራሳቸውን ከምድር ከፍ አድርገው አይነኬ ሆነው ሲያስፈራሩን የኖሩ አምባገነን መሪዎች ስለመሆናቸው የተጠራጠርን ተቆጥረን የምናልቅ አይመስለኝም፡፡
ማንም የሚደፍራቸው የሌለ አድራጊ ፈጣሪ የነበሩ ሁሉ በእጃቸው፤ ሁሉ በደጃቸው የነበሩ አምባገነኖች በግፍና በጭካኔ ድርጊታቸው የታወቁ ነበሩ። እንኳን እጃቸው በካቴና ሊታሰር ቀርቶ ደፍሮ ለአያቸው አፀፋውን በአሰቃቂ ጭካኔ የሚመልሱ ነበሩ።
ከወራት በፊት ‹‹ጦርነት አዋቂዎቹ እኛ ነን›› በሚል፤ ሊያጠፉ እንጂ ሊጠፉ የማይችሉ መሆናቸውን ነግረውን ነበር። ታዲያ ያ ሁሉ ትዕቢትና ድንፋታ በአንድ ጊዜ ተንፍሶ ፤ ወዘናቸው ጠፍቶ ቆሌያቸው ተገፎ እፍኝ የማይሞሉ ሆነው ማየት እውን ለማመን ይቸግራል፤ ግርምትንም ይፈጥራል።
የግፈኞቹ የጁንታ አባላት ገጽታቸው ሲታይ ከሞት የተነሱ እንጂ በበረሃ ሲንከራተቱ የቆዩ አይመስልም።ቆመው ሲራመዱ የቅዥት ዓለም ውስጥ ያሉ ይመስላሉ።በሰመመን ውስጥ ያሉ እንጂ ፤ የነቃ ገጽታ አልነበራቸውም። ከሞት አፋፍ የተረፉ ስለመሆናቸው ነጋሪ ሳያሻ ገጽታቸው ይመሰክራል።
ከሁለት ወራት በፊት መከላከያ ሠራዊት ላይ የሠሩት ደባ ሳይበቃቸው በቀሰቀሱት ጦርነት በሽርፍራፊ ደቂቃዎች ድል በድል ተንበሻብሸው ያሰቡትን የሚያሳኩ መስሏቸው የጀመሩት ጦርነት ሩቅ አላሚዎቹ ቅርብ አዳሪዎች ሆነው ከንቱነታቸውን አሳይቶናል፡፡
ለ45 ዓመታት በአገርና በህዝብ ላይ የሠሩትን ግፍና በደል በይቅርታ በማለፍ ሁለት ዓመት ተኩል እንዳሻቸው እንዲፈነጩ ተፈቅዶላቸው ነበር። የአህያ ስጋ አልጋ ሲሉት አመድ ያላል እንዲሉ፤ በምቾት ሰክረው የሚያደርጉት መላው ጠፍቶባቸው ሀገርና ህዝብ ሰላም እንዳይኖረው ለማተራመስ የሚያስችላቸውን ስልት ሲቀይሱ ቆይተዋል።
የስልጣን ምኞታቸው ስር የሰደደ ነውና እስከ ዕለተ ሞታቸው ነግሰው ለመኖር አልመው ስላልተሳካላቸው በየቦታው መርዛቸውን እየረጩ ሲያውኩ ኖረዋል። ጭንቅላታቸው ማሰብ የተሳነው በትዕቢትና በክፋት የተሞላ ነውና እራሳቸውን እንጂ ሌላውን ለማዳመጥ ጊዜ አልነበራቸው። ድርጊታቸው ‹‹ ያላነበበ ጭንቅላትና ጨጓራ አንድ ናቸው ሁለቱም ባዶ ሲሆኑ አሲድ ያመነጫሉ›› ያሉትን መጋቢ ሃዲስ እሸቱ አለማየሁ ንግግር አስታወሰኝ። ባዶነታቸው ማሰብ ተስኖቸው በቀሰቀሱት ጦርነት ሀገርና ህዝብ ላይ የማይሽር ጠባሳ ጥለዋል።
ከአራት አስርት ዓመታት በላይ በንጹሀን ዜጎች ላይ የፈጸሙት ግፍ ኑሯቸውን በሰላም መግፋት አላስቻላቸውም። በመከላከያ ሠራዊት ላይ በገሃድ ጦርነት አወጁ፤ መብረቃዊ ጥቃት መፈፀማቸውን ብቻ ሳይሆን ተአምራዊ ድል ማስመዝገባቸውን ለሁሉም ደሰኮሩ።በስልጣን ላይ ሆነው ያልበጁትን ህዝብ፤ መሸሸጊያ በማድረግ የድሃውን ህዝብ ልጅ በጦርነት ማገዱት። ድርጊታቸው የአውሬ እንጂ የሰው አይደለምና ከሰው ተለይተው ወደ በረሃ ፈረጠጡ።
በወገናቸው ላይ የፈጸሙት አስነዋሪ ድርጊት የህሊና ሰላም አይሰጣቸውምና፤ ከከተሙበት በረሃ እንደቃኤል በየገደላገደሉ ከእዚያ ወደ እዚያ ሲቅበዘበዙ ገደል የገቡ ፤የተደመሰሱና በመከላከያ ሠራዊት ብርታት ከሞት የተረፉትን ለማየት በቃን። በሀገሪቱ ላይ የፈጸሙት ድርጊት የማይሽር ጠባሳን ጥሎ ቢያልፍ የኋላኋላ በተጠየፉት ህዝብ ፊት በፍርድ አደባባይ መቆማቸው የግድ ሆኗል።
እነዚህ ከንቱዎች ሀያልነታቸውና ገናናነታቸውን ሲደሰኩሩ የኖሩ ለትግራይ ህዝብ ወገንተኛ መስለው ህዝቡን አስፈጅተዋል።እራሳቸውን ለማትረፍ ደግሞ እስከመጨረሻም ጥግ ድረስ የሄዱ እራስ ወዳዶች ናቸው። ከመጀመሪያቸው እስከ መጨረሻቸው ጦሳቸውን በዚሁ ህዝብ ላይ አራግፈው የማይቀረው ግብዓተ መሬታቸው እየተፈጸመ እንኳን የትግራይ ህዝብ ላይ መከራ አብዝተውበታል።ለህዝቡ አሳቢ ቢሆኑማ እራሳቸውን ከህዝቡ በፊት ባስቀደሙ ነበር፤ ንጽሃንን ለእልቂት ባልዳረጉ ነበር፡፡
‹‹ካልጠገቡ አይዘሉ ካልዘለሉ አይሰበሩ ››ማለት እንግዲህ እንደዚህ ነው። ህዝቡን ይቅርታ መጠየቃቸው ቢቀር እንኳን ለዳግም ጥፋት ከመነሳሳት አርፈው እንዲቀመጡ ቢጠየቁም ትዕቢት ልባቸውን ደፍኖት እንደአሻቸው ሲረግጡት የኖሩት ህዝብ ዳግም ለመርገጥ በምኞት ናላቸው የዞረ ስለነበር አልሞቃቸውም፤ አለመሞቅ ብቻ አይደለም አልበረዳቸውም ነበር። ይልቅ ሌላ ስልት ቀይሰው ለሁለት ወራት ጊዜ ቢሆንም አልሞት ባይ ተጋዳይነታቸውን ለማሳየት ተፍጨርጭረዋል። ቆሜለታለሁ ከኔ በቀር ለትግራይ ህዝብ የሚበጅ ላሳር እያሉ የነበረው፤ የትግራይን ህዝብ ለጦርነት በመማገድ ሊያሳዩን ቋምጠው ነበር።
ለተንኮል ተኝተው አያድሩምና የለመዱትን ተግባራቸውን ለመፈጸም የሚያስችላቸውን ስልት ጉምን በእጅ እንደመዝገን ሆኖባቸው ባሰቡት ልክ አልተሳካላቸውም። የኢትዮጵያውያንን አንድነት ማየት ስላመማቸው ህዝቡ ለአንድነት መነሳቱ የእግር እሳት ሆኖ ለበለባቸው፤ እልህ ተናንቋቸው ለበቀል አበረታቸው። ጅምራቸው ሆነ መጨረሻቸው በክፋት የተሞላው የጁንታ አባላት ከእራሳቸው በላይ ማንንም የማይወዱ ናቸው። ለዚህም ነጋሪ የማይሻው ተግባራቸው ምስክር ነው።
ሀገርን እንደ ራስ እናት ሳይሆን እንደ ጠላት እያዩ ሌት ተቀን ለማፈራረስና ለማጥፋት ሲሰሩ ቆይተዋል። ትናንት የፈጸሙትን ግፍ ዛሬ ላይ ላለመድገም የሚያግዳቸው የሌለ መሰላቸው። ማመዛዘን ተሳናቸው በእርጅና የዛገው አእምሮአቸው ወደ ልጅነት የዕቃ ዕቃ ጨዋታ መልሷቸው ይህንን አይነት የልጅ ጨዋታ እንዲጫወቱ አድርጓቸዋል።
ይህ ሁሉ ሲሆን ታዲያ የጁንታው የተከታይ ርዝራዦች ግብዓተ መሬታቸው እየተፈጸመ መሆኑን ማመን የተሳናቸው ይመስላል። እነዚህ ከራሳቸው ውጪ ለማንም የማይበጁ ከንቱዎች የዲስኩር መንፈስ እያመኑ ፈጻሜያቸውን ላለማመን የሚዳዳቸው አሉ።
በረጀሙ የቅዠት ጉዟቸው አብረዋቸው ሲጓዙ የነበሩት ርዝራዦችን በትናንት ማንነት እያሰቡ መስሚያቸው ጥጥ ሆኗል። ጆሮ ያልተበጀላቸው ይመስል፤ እየሰሙና እያዩ ያለውን ማመን ያቃታቸው ርዝራዦች እስከዛሬ በዲስኩራቸው ተታለው አመኑ ቢባል እንኳን አርቀው የቀበሯት እውነት ፍንትው ብላ ስትወጣና መጨረሻው ሲታይ አለማመን ግን ውስጣዊ ማንነታቸው መገለጫ ነው።
ክፉዎች የሚጎነጩት ጽዋ አንድ ነው የሚባለው ለዚህ ነው። ሆነም ቀረ የእነሱ ማመንና አለማመን እውነታውን ባይቀይረውም ሌላ አጀንዳዎች እየፈበረኩ የእነሱን ተግባር ለመድገም እያሰቡ መሆናቸው ግን ዝም ሊባል አይገባም። የትናንት በደላቸውን ማውገዝ አቅቷቸው፤ በዝምታ እንዳልተመለከቱ ሁሉ የግፈኞቹን ሴራ በመድገም ሌላ የፖለቲካ አጀንዳ እየቀረጹ አቅጣጫ ለማስቀየር እየሞከሩ መሆናቸው እጅግ ያማል።
ከእንግዲህ እውነት መጋረጃውን እየገለጠች ስትታይ እስካሁን ያልተሰሙ፤ ገና የሚሰሙ ነገሮችን በደንብ ስናስተውል እውነታን ሳንወድ በግድ እንጋታለን፤ ጉድና ጅራት ከወደኋላ ነው እንደሚባለው ገና ብዙ ይሰማል።
አይሆኑት ሆኖ አይሞቱ ሞትን በገዛ እጃቸው እየተጎነጩ መጨረሻቸውን በዚህ የደመደሙ ጁንታዎችን ማሰብ፤ ለኛ ወደ ኋላ መመለስ ነው። ይህ የሆነው ዳግም ላይመለሱ ነውና ትንሳኤያቸውን የምትሹ ግን የእነሱ ጽዋ ከመጎንጨቻችሁ በፊት ወደ ራሳችሁ ትመለሱ ዘንድ ሰፊ ጊዜ አላችሁ።
እናም ‹‹የአበራሽን ጠባሳ ያየ በእሳት አይጫወትም›› እንደሚባለው ሁሉ የጁንታውን ቡድን መስመር አስማሪዎች እና ስትራቴጂ ቀያሾችን ጠባሳ ያየ በእሳት አይጫወትም እና ተጠንቀቁ እንላለን።
በሰፈሩት ቁና መሰፈር አይቀርም የሚለው አባባል ለእነሱ ባይመጥንም እንግዲህ ጁንታዎች እንድትፈርስ በፈለጓት ሀገር ላይ የግፍ አለንጋ ገፈት ቀማሽ በሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ፊት ቆመው በፍርድ አደባባይ ሊዳኙ ጊዜው አሁን ሆኗል።
ይህ ጊዜ ከሁሉ በላይ አንድነት የሚያስፈልግበት እና እነዚህን መሰል የጥፋት ኃይሎች ወደ ህግ እንዲቀርብ ለማድረግ መተባበር የሚያስፈልግበት ጊዜ ነው። ምክንያቱም እንድትፈርስ በታቀደላት አገር ውስጥ የምንኖር ሁሉ፤ አገር አፍራሾችን ተባብረን ህግ ፊት ማቅረብ ይኖርብናል። ሰላም!
አዲስ ዘመን ጥር 16/2013